የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛ መሆኑ ተረጋገጠ!
የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛ መሆኑ ተረጋገጠ!
‘ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ ይገዛል።’—ዳን. 4:17
1, 2. ሰብዓዊ አገዛዝ እንዳይሳካ ያደረጉት አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
ሰብዓዊ አገዛዝ ስኬታማ መሆን አልቻለም! ይህ ምንም ጥያቄ የለውም። ሰብዓዊ አገዛዝ ስኬታማ ያልሆነበት ዋነኛው ምክንያት ሰዎች በተሳካ መንገድ ለመግዛት የሚያስችላቸው ጥበብ የሌላቸው መሆኑ ነው። በርካታ ገዥዎች ‘ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ በኩራት የተወጠሩ’ በሆኑበት በዛሬው ጊዜ ሰብዓዊ አገዛዝ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተረጋግጧል።—2 ጢሞ. 3:2-4
2 ከበርካታ ዘመናት በፊት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል እምቢተኞች ሆነው ነበር። እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ያደረጉት ከየትኛውም አገዛዝ ነፃ እንደሚሆኑ አስበው ሊሆን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በሰይጣን አገዛዝ ሥር ለመሆን መምረጣቸው ነበር። “የዚህ ዓለም ገዥ” በሆነው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ለስድስት ሺህ ዓመታት የቆየው ብልሹ የሆነ ሰብዓዊ አስተዳደር በታሪክ ዘመናት ከታዩት ሁሉ አስከፊ ለሆነው አሁን ላለንበት ሁኔታ ዳርጎናል። (ዮሐ. 12:31) ዚ ኦክስፎርድ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ትዌንቲይዝ ሴንቸሪ የተባለው መጽሐፍ የሰው ዘር በአሁኑ ጊዜ ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት “ፍጹም የሆነ ዓለም ለማምጣት መጣር” ከንቱ እንደሆነ ገልጿል። መጽሐፉ አክሎም “እንዲህ ዓይነት ዓለም ማምጣት የማይቻል ነገር ከመሆኑም ባሻገር ይህን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ጥፋት፣ አምባገነንነት ሲከፋ ደግሞ ጦርነት ያስከትላል” ብሏል። ሰብዓዊ አገዛዝ ሊሳካ እንደማይችል በግልጽ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም አባባል ነው!
3. አዳምና ሔዋን ኃጢአት ባይሠሩ ኖሮ የአምላክ አገዛዝ ምን ሊመስል ይችል ነበር?
3 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ስኬታማ መሆን የሚችለውን ብቸኛ አስተዳደር ማለትም የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል እምቢተኞች መሆናቸው እንዴት የሚያሳዝን ነው! እርግጥ ነው፣ አዳምና ሔዋን ለአምላክ ታማኞች ሆነው ቢቀጥሉ ኖሮ ይሖዋ ምድርን በምን መልኩ ያስተዳድር እንደነበር በትክክል ማወቅ አንችልም። ይሁንና የሰው ዘር በሙሉ መለኮታዊውን አገዛዝ ቢቀበለው ፍቅር በሰፈነበትና መድሎ በሌለበት መስተዳድር ሥር እንደሚኖር እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሥራ 10:34፤ 1 ዮሐ. 4:8) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ በጥበቡ ተወዳዳሪ ስለሌለው የሰው ዘር በይሖዋ አገዛዝ ሥር ለመሆን ቢመርጥ ኖሮ ሰብዓዊውን አገዛዝ የሚደግፉ ሰዎች የፈጸሟቸው ስህተቶች በሙሉ አይኖሩም ነበር ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። ቲኦክራሲ ማለትም አምላካዊ አገዛዝ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት ባረካ’ ነበር። (መዝ. 145:16) በአጭር አነጋገር ፍጹም አገዛዝ ይኖር ነበር። (ዘዳ. 32:4) የሰው ልጆች እንዲህ ያለውን አገዛዝ አለመቀበላቸው ምንኛ የሚያሳዝን ነው!
4. ሰይጣን እንዲገዛ የተፈቀደለት እስከ ምን ድረስ ነው?
4 ያም ቢሆን የሚከተለውን ሐቅ ማስታወሳችን ተገቢ ነው፦ ይሖዋ የሰው ልጆች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ቢፈቅድላቸውም መቼም ቢሆን በፍጥረታቱ ላይ የመግዛት መብቱን አሳልፎ አልሰጠም። ኃያል የሆነው የባቢሎን ንጉሥም እንኳ በመጨረሻ ‘በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ የሚገዛው ልዑሉ እንደሆነ’ አምኖ ለመቀበል ተገድዶ ነበር። (ዳን. 4:17) ወደፊት የአምላክ መንግሥት የይሖዋ ፈቃድ እንዲፈጸም ያደርጋል። (ማቴ. 6:10) እርግጥ ነው፣ ሰይጣን ላስነሳቸው ወሳኝ ጉዳዮች የማያሻማ መልስ ማግኘት እንዲቻል ይህ ተቃዋሚ ለጊዜው “የዚህ ሥርዓት አምላክ” እንዲሆን ይሖዋ ፈቅዶለታል። (2 ቆሮ. 4:4፤ 1 ዮሐ. 5:19) ይሁንና ሰይጣን ይሖዋ ከፈቀደለት አንዲት ስንዝር እንኳ አልፎ መሄድ የቻለበት ጊዜ የለም። (2 ዜና 20:6፤ ከኢዮብ 1:11, 12፤ 2:3-6 ጋር አወዳድር።) ደግሞም በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው በአምላክ ቀንደኛ ጠላት በሚተዳደር ዓለም ውስጥ እየኖሩም እንኳ ራሳቸውን ለአምላክ ለማስገዛት የመረጡ ሰዎች ጠፍተው አያውቁም።
አምላክ እስራኤላውያንን ሲገዛ የነበረው ሁኔታ
5. እስራኤላውያን ለአምላክ ምን ቃል ገቡ?
5 ከአቤል ዘመን ጀምሮ የእስራኤል ብሔር እስከተቋቋመበት ጊዜ ድረስ በርካታ ታማኝ ግለሰቦች ይሖዋን ያመልኩ እንዲሁም ትእዛዛቱን ይከተሉ ነበር። (ዕብ. 11:4-22) በሙሴ ዘመን ይሖዋ ከያዕቆብ ዝርያዎች ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ የእስራኤል ብሔር ተቋቋመ። በ1513 ዓ.ዓ. እስራኤላውያን ‘ይሖዋ ያለውን ሁሉ እናደርጋለን’ በማለት እነሱም ሆኑ ዘሮቻቸው ይሖዋን እንደ ገዥያቸው አድርገው ለመቀበል ቃል ገቡ።—ዘፀ. 19:8
6, 7. አምላክ እስራኤላውያንን የገዛው በምን መንገድ ነበር?
6 ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን ሕዝቡ እንዲሆኑ የመረጠው በዓላማ ነበር። (ዘዳግም 7:7, 8ን አንብብ።) የመረጣቸው ለእነሱ ደኅንነት በማሰብ ብቻ አልነበረም። ይሖዋ ይህንን ያደረገበት ምክንያት ከስሙና ከሉዓላዊነቱ ጋር የተያያዘ ሲሆን እነዚህ ነገሮች ደግሞ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው። የአምላክ ዓላማ እስራኤላውያን ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ይሖዋ መሆኑን እንዲመሠክሩ ነበር። (ኢሳ. 43:10፤ 44:6-8) በዚህም ምክንያት ይሖዋ ይህንን ብሔር እንዲህ ብሎት ነበር፦ “አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ ለራሱ የተለየ ሕዝብ እንድትሆንለት እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ አንተን መርጦሃል።”—ዘዳ. 14:2
7 አምላክ እስራኤላውያንን የገዛበት መንገድ ፍጽምና የጎደላቸው መሆናቸውን ከግምት ያስገባ ነበር። እንደዚያም ቢሆን ሕግጋቱ ፍጹምና የእሱን ባሕርያት የሚያንጸባርቁ ነበሩ። ይሖዋ በሙሴ በኩል የሰጣቸው ትእዛዛት አምላክ ቅዱስ፣ ፍትሕን የሚወድ፣ ታጋሽ እንዲሁም ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑን በግልጽ የሚያሳዩ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ኢያሱና በእሱ ዘመን የነበረው ሕዝብ በሕይወት በኖሩበት ወቅት ብሔሩ የይሖዋን ሕግጋት ይታዘዝ ስለነበር ሰላምና መንፈሳዊ በረከት አግኝቶ ይኖር ነበር። (ኢያሱ 24:21, 22, 31) በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ ያ ዘመን የይሖዋ አገዛዝ ስኬታማ እንደሆነ የታየበት ነበር።
ሰብዓዊ አገዛዝን መምረጥ ዋጋ ያስከፍላል
8, 9. እስራኤላውያን ምን ጥበብ የጎደለው ጥያቄ አቀረቡ? ይህስ ምን አስከተለባቸው?
8 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜያት ለአምላክ አገዛዝ ጀርባቸውን ይሰጡ ጀመር፤ በዚህም የተነሳ ይሖዋ የሚያደርግላቸውን ጥበቃ ያጡ ስለነበር ብዙ ጊዜ መከራ ደርሶባቸዋል። ውሎ አድሮ እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ እንደሚፈልጉ በነቢዩ ሳሙኤል በኩል ጥያቄ አቀረቡ። ይሖዋም ጥያቄያቸውን እንዲፈጽምላቸው ለሳሙኤል ነገረው። ይሁን እንጂ ይሖዋ አክሎ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለም” ብሎት ነበር። (1 ሳሙ. 8:7) ይሖዋ የሚታይ ንጉሥ እንዲኖራቸው ለእስራኤላውያን ቢፈቅድላቸውም ሰብዓዊ አገዛዝን መምረጥ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው አስጠንቅቋቸው ነበር።—1 ሳሙኤል 8:9-18ን አንብብ።
9 ይሖዋ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ትክክል መሆኑን ታሪክ አሳይቷል። እስራኤላውያን በሰብዓዊ ንጉሥ በተለይ ደግሞ ለይሖዋ ታማኝ ባልሆነ ንጉሥ መገዛታቸው ከባድ ችግሮች አስከትሎባቸዋል። ከእስራኤላውያን ታሪክ አንጻር ይሖዋን በማያውቁ ሰዎች የሚመሩ መንግሥታት በታሪክ ዘመናት ሁሉ ዘላቂ የሆነ ጥቅም ማስገኘት አለመቻላቸው ምንም አያስገርምም። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ፖለቲከኞች አምላክ ሰላምና ደኅንነት ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲባርክላቸው ይጸልያሉ፤ ይሁን እንጂ አምላክ የእሱን አገዛዝ የማይቀበሉ ሰዎችን እንዴት ሊባርክ ይችላል?—መዝ. 2:10-12
በአምላክ አገዛዝ ሥር ያለ አዲስ ብሔር
10. የአምላክ ምርጥ ብሔር የነበሩት እስራኤላውያን በሌላ ብሔር የተተኩት ለምን ነበር?
10 የእስራኤል ብሔር ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን አምላክ የሾመውን መሲሕ ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ይሖዋ ተዋቸው፤ ከዚያም የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በመምረጥ እነሱን የሚተካ አዲስ ብሔር ለማቋቋም ወሰነ። በዚህም የተነሳ በ33 ዓ.ም. በመንፈስ የተቀቡ የይሖዋ አምላኪዎችን ያቀፈ የክርስቲያን ጉባኤ ተወለደ። ይህ ጉባኤ በይሖዋ አገዛዝ ሥር ያለ አዲስ ብሔር ነበር ማለት ይቻላል። ጳውሎስ ይህንን ብሔር ‘የአምላክ እስራኤል’ በማለት ጠርቶታል።—ገላ. 6:16
11, 12. የእስራኤል ብሔርና ‘የአምላክ እስራኤል’ በአመራር ረገድ የሚመሳሰሉባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
11 የመጀመሪያው የእስራኤል ብሔርና አዲሱ ‘የአምላክ እስራኤል’ የሚለያዩባቸውና የሚመሳሰሉባቸው ነገሮች አሉ። ከጥንቱ የእስራኤል ብሔር በተለየ መልኩ የክርስቲያን ጉባኤ ሰብዓዊ ንጉሥ የለውም፤ እንዲሁም ለኃጢአት ማስተሰረያ የሚሆን የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም። የእስራኤል ብሔርንና የክርስቲያን ጉባኤን ከሚያመሳስሏቸው ነገሮች አንዱ የሽማግሌዎች ዝግጅት መኖሩ ነው። (ዘፀ. 19:3-8 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መንጋውን የሚገዙ አይደሉም። ከዚህ በተቃራኒ ለጉባኤው እረኞች ሆነው ያገለግላሉ፤ እንዲሁም መንጋውን ግንባር ቀደም ሆነው በመምራት በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ይካፈላሉ። እያንዳንዱን የጉባኤ አባል በፍቅርና በአክብሮት ይይዙታል።—2 ቆሮ. 1:24፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3
12 ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት እና አጋሮቻቸው የሆኑት “ሌሎች በጎች” ይሖዋ እስራኤላውያንን በያዘበት መንገድ ላይ በማሰላሰል ለእሱም ሆነ ለአገዛዙ ያላቸውን አድናቆት ማሳደግ ይችላሉ። (ዮሐ. 10:16) ለአብነት ያህል፣ የእስራኤል ሰብዓዊ ገዥዎች በበጎም ሆነ በመጥፎ በሕዝቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ ከታሪክ ማየት ይቻላል። ይህ እውነታ፣ በዛሬው ጊዜ በክርስቲያኖች መካከል አመራር የሚሰጡት ወንድሞችም እንደ ጥንቶቹ ነገሥታት ገዥዎች ባይሆኑም እንኳ ምንጊዜም በእምነታቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን እንዳለባቸው ያስገነዝባቸዋል።—ዕብ. 13:7
ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚገዛው እንዴት ነው?
13. በ1914 አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ምን ወሳኝ ነገር ተከናወነ?
13 በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ሰው ሰውን መግዛቱ በቅርቡ እንደሚያበቃ ለመላው ዓለም እየሰበኩ ነው። በ1914 ይሖዋ፣ በመረጠው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚተዳደረውን መንግሥቱን በሰማይ አቋቁሟል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ ‘ድል እያደረገ እንዲወጣና ድሉን ለማጠናቀቅ ወደፊት እንዲገሠግሥ’ ይሖዋ ሥልጣን ሰጥቶታል። (ራእይ 6:2) አዲስ የተሾመው ንጉሥ ‘በጠላቶችህ መካከል ሆነህ ግዛ’ ተብሎ ነበር። (መዝ. 110:2) የሚያሳዝነው ብሔራት ለይሖዋ አገዛዝ ራሳቸውን ለማስገዛት አሻፈረን ማለታቸውን ቀጥለዋል። የሚያደርጉት ነገር “እግዚአብሔር የለም” ብለው የሚናገሩ ያህል ነው።—መዝ. 14:1
14, 15. (ሀ) በዘመናችን የአምላክ መንግሥት እየገዛን ያለው እንዴት ነው? ከዚህ አንጻር የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል? (ለ) የአምላክ አገዛዝ ከሁሉ የላቀ መሆኑ በዛሬው ጊዜም እንኳ የሚታየው እንዴት ነው?
14 ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት የሆኑ ጥቂት የተቀቡ ክርስቲያኖች አሁንም በምድር ላይ አሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ወንድሞች እንደመሆናቸው መጠን ‘ክርስቶስን ተክተው የሚሠሩ አምባሳደሮች’ በመሆን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። (2 ቆሮ. 5:20) እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ቅቡዓንን እንዲሁም ቁጥራቸው እያደገ የመጣውን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን እንዲንከባከቧቸውና በመንፈሳዊ እንዲመግቧቸው ታማኝና ልባም ባሪያ ሆነው ተሹመዋል። (ማቴ. 24:45-47፤ ራእይ 7:9-15) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ያገኙት መንፈሳዊ ብልጽግና ይሖዋ ይህንን ዝግጅት እንደባረከው የሚያሳይ ነው።
15 እያንዳንዳችን እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ልሸከመው የሚገባኝን ኃላፊነት በሚገባ ተገንዝቤያለሁ? ዕብራውያን 13:17ን አንብብ።) በፈቃደኝነት መገዛታችን በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ዓለም አቀፋዊ አንድነት እንዲኖረን አስችሏል። ከዚህም በተጨማሪ ሰላምና ጽድቅ እንዲሰፍን አድርጓል እንዲሁም ለይሖዋ ክብር አምጥቷል፤ ይህም የይሖዋ አገዛዝ ከሁሉ የላቀ መሆኑን ያረጋግጣል።
የይሖዋን አገዛዝ በተገቢው መንገድ እየደገፍኩ ነው? በመግዛት ላይ ያለው የይሖዋ መንግሥት ተገዢ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል? አቅሜ እስከ ፈቀደ ድረስ ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት መናገሬን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ?’ በቡድን ደረጃ ሲታይ የበላይ አካሉ ለሚሰጠው መመሪያ በፈቃደኝነት እንገዛለን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ከተሾሙት ሽማግሌዎች ጋር እንተባበራለን። እንዲህ በማድረግ የአምላክን አገዛዝ እንደምንቀበል እናሳያለን። (የይሖዋ አገዛዝ
16. በዛሬው ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ምን ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅበታል?
16 በኤደን የተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙበት ጊዜ በጣም እየቀረበ ነው። በመሆኑም ሰዎች ውሳኔ የሚያደርጉበት ጊዜ አሁን ነው። እያንዳንዱ ሰው የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል አሊያም ሰብዓዊ አገዛዝን መደገፉን ለመቀጠል መምረጥ አለበት። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ የመርዳት መብት ተሰጥቶናል። በቅርቡ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያሉት ሰብዓዊ መንግሥታት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በይሖዋ አገዛዝ ይተካሉ። (ዳን. 2:44፤ ራእይ 16:16) ሰብዓዊ አገዛዝ ያበቃለታል፤ የአምላክ መንግሥትም መላውን ምድር ያስተዳድራል። የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛ መሆኑ ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል።—ራእይ 21:3-5ን አንብብ።
17. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከአገዛዝ ጋር በተያያዘ ጥሩ ምርጫ እንዲያደርጉ የሚረዷቸው የትኞቹ ነጥቦች ናቸው?
17 እስካሁን ድረስ ከይሖዋ ጎን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ ያላደረጉ ሁሉ የአምላክ አገዛዝ ለሰው ልጆች የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በጸሎት ሊያስቡባቸው ይገባል። ሰብዓዊ አገዛዝ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ወንጀል ማስወገድ አልቻለም። የአምላክ አገዛዝ ክፉዎችን በሙሉ ከምድረ ገጽ ያጠፋቸዋል። (መዝ. 37:1, 2, 9) ሰብዓዊ አገዛዝ መቋጫ የሌለው ጦርነት አስከትሏል፤ የአምላክ አገዛዝ ግን “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል።” (መዝ. 46:9) ሌላው ቀርቶ በሰው ልጆችና በእንስሳት መካከል እንኳ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል! (ኢሳ. 11:6-9) በሰብዓዊ አገዛዝ ሥር የሰው ልጆች ከድህነትና ከረሃብ ተላቅቀው አያውቁም። የአምላክ አገዛዝ ግን እነዚህን ችግሮች ያስቀራቸዋል። (ኢሳ. 65:21) በቅን ልቦና ተነሳስተው የሚሠሩ ሰብዓዊ ገዥዎችም እንኳ በሽታንና ሞትን ማስወገድ አልቻሉም፤ የአምላክ አገዛዝ ግን አረጋውያንና የታመሙ ሰዎች የወጣትነት ብርታት እንዲያገኙ ያደርጋል። (ኢዮብ 33:25፤ ኢሳ. 35:5, 6) ምድር ወደ ገነትነት የምትለወጥ ሲሆን ሙታንም እንኳ ይነሳሉ።—ሉቃስ 23:43፤ ሥራ 24:15
18. የይሖዋ አገዛዝ ከሁሉ የላቀ መሆኑን እንደምናምን እንዴት ማሳየት እንችላለን?
18 አዎን፣ ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ከፈጣሪያቸው እንዲያፈነግጡ በማድረግ ያደረሰውን ጉዳት በሙሉ የአምላክ አገዛዝ ያስተካክለዋል። እስቲ አስበው፣ ሰይጣን ለ6,000 ዓመታት ያህል ያደረሰውን ጥፋት አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በ1,000 ዓመት ውስጥ ያስተካክለዋል! የአምላክ አገዛዝ የላቀ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንዴት ያለ ድንቅ ማስረጃ ነው! የአምላካችን ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ገዥያችን አድርገን እንቀበለዋለን። እንግዲያው በሕይወታችን ውስጥ እያንዳንዱን ቀን እንዲያውም እያንዳንዱን ሰዓት የይሖዋ አምላኪዎችና የመንግሥቱ ተገዥዎች እንደሆንን ብሎም የእሱ ምሥክሮች በመሆናችን እንደምንኮራ በሚያሳይ መንገድ እንኑር። እንዲሁም የይሖዋ አገዛዝ ከሁሉ የላቀ መሆኑን ለሚሰሙን ሰዎች በሙሉ ለመናገር ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እንጠቀም።
የሚከተሉትን ጥቅሶች በማንበባችን ስለ አምላክ አገዛዝ ምን ትምህርት አግኝተናል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ መቼም ቢሆን የመግዛት መብቱን አሳልፎ አልሰጠም
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለይሖዋ አገዛዝ በፈቃደኝነት መገዛት ዓለም አቀፋዊ አንድነት ያስገኛል