የብዙኃኑ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርብህ ተጠንቀቅ
የብዙኃኑ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርብህ ተጠንቀቅ
ተገቢ ስለሆነውና ስላልሆነው እንዲሁም ተቀባይነት ስላለውና ነውር ስለሆነው ነገር ሰዎች ያላቸው አመለካከት ከቦታ ቦታ ይለያያል። በተጨማሪም እነዚህ ነገሮች በጊዜ ሂደት ይለወጣሉ። በመሆኑም በጥንት ዘመን ስለተከናወኑ ሁኔታዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በምናነብበት ጊዜ ሁኔታውን አሁን ካለው አመለካከት አንጻር ከማየት ይልቅ በወቅቱ ሰዎች የነበራቸውን አመለካከት እንዲሁም ትልቅ ቦታ የሚሰጧቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ከግምት ማስገባት ይኖርብናል።
በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ሁለት ነገሮችን ይኸውም ክብርን እና ኀፍረትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ክብር ስለሚያስገኙና ለኀፍረት ወይም ለውርደት ሊዳርጉ ስለሚችሉ ነገሮች የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በተሻለ መንገድ መረዳት እንድንችል በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ለእነዚህ ነገሮች የሚሰጧቸውን ቦታ ማጤን ይኖርብናል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ትልቅ ቦታ ይሰጣቸው የነበሩ ነገሮች
“በግሪኮችም ሆነ በሮማውያን እንዲሁም በአይሁዶች ባሕል ውስጥ ለክብር ከፍተኛ ግምት ይሰጥ የነበረ ሲሆን ለኀፍረት የሚዳርጉ ነገሮች ደግሞ እንደ ትልቅ ነገር ይታዩ ነበር” በማለት አንድ ምሑር ይናገራሉ። “ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ክብር፣ መልካም ስም፣ ታዋቂነት፣ ውዳሴና አክብሮት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን እንኳ ይሰጡ ነበር።” እነዚህን ነገሮች ለማግኘት በጣም ስለሚፈልጉ የሌሎች አመለካከት በቀላሉ ተጽዕኖ ያደርግባቸው ነበር።
ለደረጃ ትልቅ ግምት በሚሰጥ ማኅበረሰብ ውስጥ ማዕረግ፣ ሥልጣንና ክብር ከምንም በላይ ከፍ ተደርገው ይታዩ ነበር፤ ሰዎች ከመኳንንት እስከ ባሪያ የተለያየ ደረጃ ነበራቸው። አንድን ሰው የተከበረ የሚያሰኘው ግለሰቡ ለራሱ የሚሰጠው ግምት ብቻ ሳይሆን ሌሎች እሱን የሚያዩበት መንገድም ጭምር ነው። ደረጃ ያለው አንድ ሰው ከእሱ የሚጠበቀውን በማድረጉ ሰዎች በሕዝብ ፊት እውቅና ከሰጡት ይህን ሰው አክብረውታል ሊባል ይችላል። በተጨማሪም አንድን ሰው ማክበር ሲባል ግለሰቡ ባለው ሀብት፣ ሥልጣን ወይም ደረጃ እንደሚከበር ማሳየትና ተገቢውን ትኩረት መስጠት ማለት ነበር። ከዚህም በላይ በጎ ነገር በማድረግ ወይም ከሌሎች በልጦ በመገኘት የሰዎችን አክብሮት ማትረፍ ይቻል ነበር። በተቃራኒው አንድ ሰው ተዋረደ ወይም ክብሩን አጣ የሚባለው ሕዝቡ ግለሰቡን ዝቅ አድርጎ የሚመለከተው ወይም የሚንቀው ከሆነ ነው። የግለሰቡ ስሜትና ሕሊና እንዳለ ሆኖ ይበልጥ ለኀፍረት እንዲዳረግ የሚያደርገው ከማኅበረሰቡ የሚደርስበት ነቀፌታ ነበር።
ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ አንድ ሰው ግብዣ በሚጠራበት ጊዜ “የክብር ቦታ” ማግኘቱ ወይም “በዝቅተኛው ስፍራ” ላይ እንዲቀመጥ መደረጉ በዘመኑ በነበረው ባሕል መሠረት መከበሩን ወይም ለውርደት መዳረጉን የሚያሳይ ነበር። (ሉቃስ 14:8-10) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘ከመካከላቸው ታላቅ ሊሆን የሚችለው ማን እንደሆነ’ ከአንዴም ሁለቴ ተከራክረው ነበር። (ሉቃስ 9:46፤ 22:24) ይህም የሚኖሩበት ማኅበረሰብ ለደረጃ ያለው አመለካከት ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው የሚያሳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኩሩ የሆኑትና የፉክክር መንፈስ የተጠናወታቸው የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ ኢየሱስ መስበኩ ክብራቸውንና ሥልጣናቸውን ዝቅ እንደሚያደርግባቸው ተሰምቷቸው ነበር። ከኢየሱስ ጋር ክርክር ገጥመው በሕዝብ ፊት በመርታት ከእሱ የሚሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት ሙከራ ቢያደርጉም አንድም ጊዜ አልተሳካላቸውም።—ሉቃስ 13:11-17
በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት አይሁዳውያን፣ ግሪካውያንና ሮማውያን ዘንድ ተስፋፍቶ የነበረው ሌላው አመለካከት ደግሞ አንድ ሰው “መጥፎ ድርጊት ፈጽሟል በሚል ተይዞ በሕዝብ ፊት መከሰሱ” እንደ አሳፋሪ ነገር ተደርጎ መታየቱ ነበር። አንድ ሰው መታሰሩ ወይም ወኅኒ መውረዱ እንደ ውርደት ይቆጠር ነበር። ግለሰቡ ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋገጠም አልተረጋገጠ ተይዞ መታሰሩ ብቻ በወዳጆቹ፣
በቤተሰቡና በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ ክብሩን እንዲያጣ ያደርገው ነበር። በዚህ መንገድ ስሙ መጉደፉ ለራሱ አክብሮት እንዲያጣና ከሌሎች ጋር ያለው ግንኙነት እንዲበላሽ ያደርጋል። ከመታሰር ይበልጥ አሳፋሪ የነበረው ደግሞ ልብሱን መገፈፉ ወይም መገረፉ ነበር። እንዲህ ያለው ቅጣት የግለሰቡን ክብር በማዋረድ ሰዎች እንዲንቁትና እንዲያፌዙበት ያደርግ ነበር።በመከራ እንጨት ላይ መሰቀል ከሁሉ የከፋ ውርደት ነበር። ማርቲን ሄንግል የተባሉት ምሑር እንዲህ ያለው ፍርድ “በባሪያዎች ላይ የሚበየን ቅጣት” እንደሆነ ይገልጻሉ። “በመሆኑም እንዲህ ያለው ቅጣት ከባድ ውርደትን፣ ኀፍረትንና ሥቃይን ያመለክት ነበር።” በዚህ መንገድ እንዲዋረድ የተደረገውን ግለሰብ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ እንዲክዱት ማኅበረሰቡ ጫና ያሳድርባቸው ነበር። ክርስቶስ የሞተው በዚህ መንገድ በመሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ለመሆን የሚፈልጉ ሁሉ በሕዝቡ ዘንድ የሚደርስባቸውን ነቀፌታ መቋቋም ነበረባቸው። ተሰቅሎ የተገደለ ግለሰብ ተከታይ መሆንን በይፋ ማሳወቅ በብዙዎች ዘንድ እንደ እብደት ይታይ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁዳውያን መሰናክል ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 1:23) ታዲያ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህንን ፈተና እንዴት ተቋቋሙት?
ከብዙኃኑ የተለየ አመለካከት
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ሕግን ያከብሩ የነበረ ሲሆን መጥፎ ድርጊት መፈጸም የሚያስከትለው ውርደት በእነሱ ላይ እንዳይደርስ ይጠነቀቁ ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ከእናንተ መካከል ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ ወይም በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባ በመሆን መከራ አይቀበል” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥ. 4:15) ይሁንና ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ስለ ስሙ መከራ እንደሚደርስባቸው አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ዮሐ. 15:20) ጴጥሮስ፣ አንድ ሰው “ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ምንም ኀፍረት አይሰማው፤ ይልቁንም በዚህ ስም አምላክን ማክበሩን ይቀጥል” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥ. 4:16) አንድ ሰው የክርስቶስ ተከታይ በመሆኑ መከራ ሲደርስበት በኀፍረት ስሜት አለመዋጡ የብዙኃኑን አመለካከት እንደማይቀበል የሚያሳይ ነበር።
ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎች ያወጧቸው መሥፈርቶች በአኗኗራቸው ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ አይፈቅዱም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ማኅበረሰብ ውስጥ ተሰቅሎ የሞተን ሰው እንደ መሲሕ አድርጎ መቁጠር እንደ ሞኝነት ይታይ ነበር። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ክርስቲያኖች ብዙኃኑ የሚከተለውን አመለካከት እንዲቀበሉ ጫና ሊያሳድርባቸው ይችል ነበር። ሆኖም ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ እምነት ካላቸው ቢፌዝባቸውም እሱን መከተል ነበረባቸው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ አመንዝራና ኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ሲመጣ ያፍርበታል።”—ማር. 8:38
በዛሬው ጊዜም እኛን ከክርስትና ጎዳና ለማስወጣት ሰዎች ጫና ያሳድሩብን ይሆናል። እንዲህ ያለው ጫና የሚመጣው የሥነ ምግባር ብልግና፣ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ወይም ሌሎች አጠያያቂ ተግባሮችን እንድንፈጽም ሊገፋፉን ከሚሞክሩ አብረውን የሚማሩ ልጆች፣ ጎረቤቶቻችን ወይም የሥራ ባልደረቦቻችን ሊሆን ይችላል። እነዚህ ግለሰቦች ትክክለኛ የሆኑ መሥፈርቶችን ለመከተል በወሰድነው አቋም የኀፍረት ስሜት እንዲሰማን ሊያደርጉን ይሞክሩ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ውርደትን ከምንም ያልቆጠሩ ሰዎችን ምሳሌ ተከተል
ኢየሱስ ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት ለመጠበቅ ሲል ከሁሉ የከፋ ውርደት ደርሶበት ተገድሏል። “የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት ላይ እስከመሞት ድረስ ጸንቷል።” (ዕብ. 12:2) የኢየሱስ ጠላቶች በጥፊ መተውታል፣ ተፍተውበታል፣ ልብሱን ገፈውታል፣ ገርፈውታል፣ ሰቅለውታል እንዲሁም ሰድበውታል። (ማር. 14:65፤ 15:29-32) ጠላቶቹ በኀፍረት እንዲዋጥ ለማድረግ ቢጥሩም ኢየሱስ የሚደርስበትን ውርደት ከምንም አልቆጠረውም። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? እንዲህ ያለ እንግልት ቢያደርሱበትም ከአቋሙ ዝንፍ አላለም። ኢየሱስ በይሖዋ ዘንድ ያለውን ክብር እንዳላጣ ያውቅ ነበር፤ ከሰው የሚገኘውን ክብር ደግሞ እንዳልፈለገ ምንም ጥርጥር የለውም። ምንም እንኳ ኢየሱስ እንደ ባሪያ ተቆጥሮ ቢሞትም ይሖዋ እሱን ከሞት በማስነሳት እንዲሁም ከጎኑ እንዲሆን በማድረግ ከሁሉ የላቀውን ቦታ በመስጠት አክብሮታል። ፊልጵስዩስ 2:8-11 እንዲህ ይላል፦ “[ክርስቶስ ኢየሱስ] ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል። በዚህም ምክንያት አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ያሉ ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው፤ ምላስም ሁሉ አባት ለሆነው አምላክ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በይፋ እውቅና እንዲሰጥ ነው።”
ኢየሱስ ተሰቅሎ ከመገደሉ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ውርደት አልተሰማውም ማለት አይደለም። አምላክን እንደተሳደበ በመግለጽ የቀረበበት ክስ የአባቱን ክብር ሊነካ የሚችል መሆኑ በጣም አስጨንቆት ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ያለው ውርደት የሚያስከትል ሁኔታ እንዳይደርስበት ይሖዋን ጠይቆ ነበር። “ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ” በማለት ጸለየ። ይሁንና ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን አቅርቦ ነበር። (ማር. 14:36) ኢየሱስ የደረሰበትን ተጽዕኖ የተቋቋመ ሲሆን ውርደትን ከምንም አልቆጠረም። በደረሰበት ሁኔታ ኀፍረት ሊሰማው የሚችለው፣ በዘመኑ በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት በነበረው አመለካከት ሙሉ በሙሉ የሚመራ ቢሆን ኖሮ ነበር። ኢየሱስ ግን እንዲህ እንዳላደረገ ግልጽ ነው።
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ቢሆኑ ታስረዋል እንዲሁም ተገርፈዋል። እንዲህ ያለው ድርጊት በእነሱ ላይ መፈጸሙ በብዙዎች ዘንድ ክብራቸውን እንዲያጡ አድርጓቸው ነበር። በሌሎች ዘንድ ዝቅ ተደርገው ይታዩ ብሎም ይናቁ ነበር። ያም ሆኖ ሁኔታው ወደኋላ እንዲሉ አላደረጋቸውም። እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የብዙኃኑ አመለካከት ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው አልፈቀዱም፤ እንዲሁም ውርደትን ከምንም ነገር አልቆጠሩም። (ማቴ. 10:17፤ ሥራ 5:40፤ 2 ቆሮ. 11:23-25) ‘የራሳቸውን የመከራ እንጨት መሸከምና ያለማቋረጥ ኢየሱስን መከተል’ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር።—ሉቃስ 9:23, 26
በዛሬው ጊዜ ስላለነው ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? ዓለም እንደ ሞኝነት፣ ደካማነትና ውርደት አድርጎ የሚቆጥራቸው ነገሮች በአምላክ ፊት እንደ ጥበብ፣ ኃያልነትና ክብር ተደርገው ይታያሉ። (1 ቆሮ. 1:25-28) ታዲያ በብዙኃኑ አመለካከት ሙሉ በሙሉ መመራት ሞኝነትና አርቆ ማስተዋል የጎደለው አካሄድ አይሆንም?
በሰው ዘንድ ክብር ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ዓለም ለእነሱ ያለው አመለካከት ሊያሳስባቸው ይገባል። እኛ ግን ልክ እንደ ኢየሱስና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ተከታዮቹ የይሖዋ ወዳጅ መሆን እንፈልጋለን። በመሆኑም በእሱ ዘንድ ክቡር የሆነውን እናከብራለን፤ እንደ ውርደት የሚያየውን ነገር ደግሞ እንደ አሳፋሪ ነገር እንቆጥረዋለን።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ፣ ዓለም ውርደት ስለሚያስከትሉ ነገሮች ያለው አመለካከት ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት አልፈቀደም