በቡልጋሪያ የተደረገው ልዩ ዘመቻ ውጤት አስገኘ
በቡልጋሪያ የተደረገው ልዩ ዘመቻ ውጤት አስገኘ
“አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ጌታ ወደ መከር ሥራው ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” —ማቴ. 9:37, 38
ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ፣ ከባልካን አገሮች አንዷ በሆነችውና በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ በምትገኘው ውብ አገር በቡልጋሪያ ያለውን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። ከሰባት ሚሊዮን ለሚበልጡ ለዚህች አገር ነዋሪዎች ምሥራቹን ለማዳረስ ተጨማሪ ሠራተኞች በጣም ያስፈልጋሉ። በቡልጋሪያ ወደ 1,700 ገደማ የሚሆኑ አስፋፊዎች ቢኖሩም ክልሉን ሙሉ በሙሉ መሸፈን አልቻሉም። በመሆኑም የበላይ አካሉ በሰጠው ፈቃድ መሠረት በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሚኖሩ የቡልጋሪያ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቡልጋሪያ መጥተው በ2009 በሚደረገው ልዩ ዘመቻ እንዲካፈሉ ጥሪ ቀረበላቸው። ዘመቻው በበጋ ወቅት ለሰባት ሳምንታት እንዲካሄድና በሶፊያ ከተማ ከነሐሴ 14-16, 2009 በሚደረገው “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ!” የተባለው የአውራጃ ስብሰባ በሚካሄድበት ሳምንት ላይ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደረገ።
እጅግ የሚያስደንቅ ምላሽ
በሶፊያ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የሚሠሩ ወንድሞች ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከግሪክ፣ ከጣሊያን፣ ከፖላንድና ከስፔን ይህን ጥሪ ተቀብለው ምን ያህል ወንድሞችና እህቶች እንደሚመጡ ለማወቅ ጓጉተው ነበር። ምክንያቱም ወደ ቡልጋሪያ የሚመጡ ወንድሞች የትራንስፓርት ወጪያቸውን ራሳቸው መሸፈን ብሎም የዓመት እረፍታቸውን ለስብከቱ ሥራ ማዋል እንደሚጠይቅባቸው ያውቁ ነበር። ሆኖም በየሳምንቱ የአመልካቾቹ ቁጥር እየጨመረ ሄዶ 292 መድረሱ በጣም የሚያስደስት ነበር! ምላሽ የሰጡት ወንድሞችና እህቶች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ እነዚህን ፈቃደኛ ሠራተኞች ካዛንላክ፣ ሳንዳንስኪ እና ሲሊስትራ ወደ ተባሉ ሦስት የቡልጋሪያ ከተሞች መመደብ ተችሏል። በቡልጋሪያ የሚገኙ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ በአገሪቱ ለሚኖሩ አቅኚዎችና አስፋፊዎች በዘመቻው እንዲካፈሉ ግብዣ አቅርበውላቸው ነበር። በመጨረሻም 382 የሚሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ምሥራቹ እምብዛም ወዳልተዳረሰባቸው ክልሎች ሄደው በቅንዓት ሰብከዋል።
ምሥራቹ በሚሰበክባቸው ክልሎች አቅራቢያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች ማረፊያ ቦታ እንዲያዘጋጁ አስቀድመው ተላኩ። ወንድሞች አፓርታማዎችን የተከራዩ ከመሆኑም ሌላ ውድ ባልሆኑ ሆቴሎች ውስጥ ክፍል ያዙ። እነዚህ ወንድሞች ከውጭ አገር የሚመጡት ፈቃደኛ ሠራተኞች ማረፊያ ቦታ እንዲያገኙና የሚያስፈልጋቸው ነገር እንዲሟላላቸው ለማድረግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሠርተዋል። በሦስቱም ከተሞች ወንድሞች ለመሰብሰቢያ የሚሆን ቦታ ተከራይተው ነበር። ከውጪ አገር የመጡት ወንድሞች የጉባኤ ስብሰባዎችን እንዲመሩ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። አንድም የይሖዋ ምሥክር በሌለበት ቦታ 50 የሚሆኑ አስፋፊዎች ይሖዋን ለማወደስ ተሰብስበው እንደነበር ማወቅ በጣም ያስደስታል።
በዘመቻው ለመካፈል ከሌሎች አገሮች የመጡት ወንድሞች የነበራቸው ቅንዓት የሚገርም ነው። በቡልጋሪያ በበጋ ወራት የሙቀቱ መጠን ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ሊሆን ይችላል። ሆኖም እነዚህን ቀናተኛ ወንድሞችና እህቶች ምንም ነገር አልበገራቸውም። ዳንዩብ በተባለው ወንዝ አቅራቢያ በምትገኘውና ከ50,000 በላይ የሕዝብ ብዛት ባላት በሲሊስትራ ከተማ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ሳምንታት ውስጥ የተሟላ ምሥክርነት መስጠት ተችሏል። ወንድሞች በዚያ ብቻ ሳይወሰኑ በአቅራቢያው ወዳሉት መንደሮች ሌላው ቀርቶ ከሲሊስትራ በስተ ምዕራብ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እስከምትገኘው እስከ ቱትራካን ድረስ ሄደው ምሥራቹን ሰብከዋል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ወንድሞች አገልግሎት የሚጀምሩት ከጠዋቱ 3:30 ላይ ነበር።
የምሳ እረፍት ካዳረጉ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ እስከ ምሽቱ 1:00 ሰዓት ድረስ ያገለግሉ ነበር። በተመሳሳይም በካዛንላክና በሳንዳንስኪ እንዲያገለግሉ የተመደቡት ፈቃደኛ ሠራተኞች አስገራሚ ቅንዓት አሳይተው ስለነበር ዘመቻው በእነዚህ ከተሞች አቅራቢያ በሚገኙ መንደሮችና ትንንሽ ከተሞች ውስጥም እንኳ ተካሂዷል።ምን ውጤት ተገኘ?
በእነዚህ ሰባት ሳምንታት ውስጥ ግሩም የሆነ ምሥክርነት መስጠት ተችሏል። በሐዋርያት ዘመን እንደተባለው ሁሉ የእነዚህ ከተሞች ነዋሪዎችም ‘ከተማችንን በትምህርታችሁ ሞልታችኋታል’ ብለው መናገር ይችላሉ። (ሥራ 5:28) በዘመቻው የተካፈሉ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ 50,000 የሚጠጉ መጽሔቶችን ያበረከቱ ከመሆኑም በላይ 482 ሰዎችን ጥናት አስጀምረዋል። ደስ የሚለው ነገር ከመስከረም 1, 2009 ጀምሮ በሲሊስትራ ከተማ አንድ ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን በካዛንላክና በሳንዳንስኪ ደግሞ ቡድኖች ተመሥርተዋል። በዚህ ዘመቻ ወቅት ምሥራቹን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙ ሰዎች ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እያደረጉ መሆኑን መመልከት እጅግ የሚያስደስት ነው።
ዘመቻው በተጀመረበት ሳምንት፣ ከስፔን የመጣች የቡልጋሪያ ቋንቋ የምትናገር አቅኚ እህት በሲሊስትራ ለምትኖርና መንገድ ላይ ጋዜጣ ለምትሸጥ ካሪና የተባለች ሴት መሠከረችላት። ካሪና ፍላጎት ያሳየች ከመሆኑም በላይ በስብሰባ ላይ ተገኘች። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድትጀምር የቀረበላትን ግብዣም ሳታቅማማ ተቀበለች። ባለቤቷ በአምላክ መኖር የማያምን ሰው በመሆኑ ጥናቱ በመናፈሻ ውስጥ እንዲደረግላት ጠየቀች። ሁለት ሴት ልጆቿም አብረው ማጥናት ጀመሩ። በተለይ ዳንየላ የተባለችው ትልቋ ልጇ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለየት ያለ አድናቆት ነበራት። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በሳምንት ውስጥ ያነበበች ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን እንደሚከለክል ስታውቅ ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደች። ከዚያም የተማረችውን እውነት ለጓደኞቿ መናገር ጀመረች። በጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኘች ከሦስት ሳምንት በኋላ ለምታስጠናት እህት “እንደ እናንተ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ታዲያ እኔም መስበክ እንድጀምር ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” አለቻት። ዳንየላ፣ እናቷና ታናሽ እህቷ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ላይ ናቸው።
በካዛንላክ በተደረገው ዘመቻ የተካፈለው ከጣሊያን የመጣ ኦርሊን የተባለ አንድ ቡልጋሪያዊ ወንድም አገልግሎት ጨርሶ ወደ ማረፊያው በእግሩ እየሄደ ነበር። ኦርሊን በመንገዱ ላይ በአንድ መናፈሻ ውስጥ ተቀምጠው ለነበሩ ሁለት ወጣቶች መሠከረላቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ያበረከተላቸው ከመሆኑም ሌላ በሚቀጥለው ቀን ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ዝግጅት አደረገ። በቀጠሮው ቀን ኦርሊን ስቬቶሚር ከተባለው ወጣት ጋር ጥናት የጀመረ ሲሆን በማግስቱም ጥናታቸውን ቀጠሉ። ኦርሊን ስቬቶሚርን በዘጠኝ ቀን ውስጥ ስምንት ጊዜ አስጠንቶታል። ስቬቶሚር እንዲህ ብሏል፦ “አንተን ከማግኘቴ ከሁለት ቀን በፊት አምላክ እሱን እንዳውቀው እንዲረዳኝ ጸልዬ ነበር። እሱን እንዳውቀው የሚረዳኝ ከሆነ ሕይወቴን ለእሱ እንደምወስን ቃል ገብቼ ነበር።” ኦርሊን
ወደ ጣሊያን ከተመለሰ በኋላ ስቬቶሚር በአካባቢው ከሚገኙ ወንድሞች ጋር ጥናቱን የቀጠለ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እውነትን የራሱ ለማድረግ እየጣረ ነው።መሥዋዕትነት የከፈሉ ወንድሞች ያገኙት የተትረፈረፈ በረከት
ምሥራቹን ለመስበክ ሲሉ በደግነት የእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው በራሳቸው ወጪ ወደ ሌላ አገር የሄዱ ወንድሞች ምን ተሰማቸው? በስፔን የሚያገለግል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ዘመቻው በስፔን የሚኖሩ የቡልጋሪያ ቋንቋ በሚሰበክበት ክልል የሚያገለግሉ ወንድሞችንና እህቶችን ይበልጥ አቀራርቧቸዋል። በዘመቻው በተካፈሉ ወንድሞች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።” ከጣሊያን የመጡ አንድ ባልና ሚስት “ይህ ወር በሕይወታችን ውስጥ እጅግ የተደሰትንበት ወቅት ነበር” በማለት ጽፈዋል። አክለውም “ዘመቻው ሕይወታችንን ለውጦታል! አሁን ሌላ ሰው ሆነናል” ብለዋል። እነዚህ ባልና ሚስት በቋሚነት ወደ ቡልጋሪያ በመምጣት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል በቁም ነገር ማሰብ ጀምረዋል። ከስፔን የመጣችው ካሪና የተባለች ነጠላ እህት የዘወትር አቅኚ ስትሆን በሲሊስትራ በተደረገው ዘመቻ ተካፍላ ነበር። ከዘመቻው በኋላ በዚያ ከተማ የተቋቋመውን ጉባኤ ለመርዳት ስትል በስፔን የነበራትን ሰብዓዊ ሥራ ትታ ወደ ቡልጋሪያ ተመልሳለች። ቡልጋሪያ ውስጥ ለአንድ ዓመት ለመኖር የሚያስችላትን በቂ ገንዘብ አጠራቅማለች። ካሪና ያደረገችውን ውሳኔ በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እዚህ ቡልጋሪያ እንዳገለግል ስላስቻለኝ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በቡልጋሪያ ረጅም ጊዜ መቆየት እንደምችል ተስፋ አደርጋለሁ። ገና ከአሁኑ አምስት ጥናቶች ያሉኝ ሲሆን ሦስቱ በስብሰባ ላይ መገኘት ጀምረዋል።”
አንዲት ጣሊያናዊ እህት በዘመቻው መካፈል ብትፈልግም አዲስ ሥራ የጀመረችው በቅርብ በመሆኑ ምንም የእረፍት ቀን አልነበራትም። ሆኖም ይህ ወደኋላ እንድትል አላደረጋትም። ለአንድ ወር ያለ ክፍያ እረፍት እንዲሰጣት የጠየቀች ሲሆን ፈቃድ ካልተሰጣት ሥራዋን ለመልቀቅ ተዘጋጅታ ነበር። በጣም የሚገርመው አሠሪዋ “እሺ፤ እረፍት የምሰጥሽ ግን አንድ ነገር የምታደርጊልኝ ከሆነ ነው። ከቡልጋሪያ ፓስት ካርድ ልትልኪልኝ ይገባል” አላት። እህት ይሖዋ ለጸሎቷ ምላሽ እንደሰጣት ተሰምቷታል።
በቡልጋሪያ ቫርና በተባለው ከተማ የምትኖር ስታኒስላቫ የተባለች አንዲት ወጣት እህት በሲሊስትራ ከተማ በተደረገው ዘመቻ ለመካፈል ስትል ከሥራዋ እረፍት ወሰደች፤ ይህች እህት ሙሉ ቀን ትሠራ የነበረ ከመሆኑም በላይ ዳጎስ ያለ ደሞዝ ታገኝ ነበር። በአገሯ ምሥራቹን ለመስበክ ሲሉ ከሩቅ ቦታዎች የመጡ በርካታ አቅኚዎች ያላቸውን ደስታ ስትመለከት እንባዋን መቆጣጠር አልቻለችም። በሰብዓዊ ሥራ የተጠመደች በመሆኗ የወደፊት ሕይወቷን እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል ቆም ብላ ማሰብ ጀመረች። ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደቤቷ ስትመለስ ሥራዋን አቁማ የዘወትር አቅኚ ሆነች። ይህች እህት በወጣትነት ዕድሜዋ ፈጣሪዋን እያሰበች በመሆኗ አሁን በጣም ደስተኛ ናት።—መክ. 12:1
በይሖዋ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዴት ያለ በረከት ነው! ጊዜህንና ጉልበትህን አስፈላጊ በሆነው በዚህ የማስተማርና ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ላይ ከማዋል የተሻለ ልታደርገው የምትችለው ምንም ነገር የለም። አንተስ ሕይወት አድን በሆነው በዚህ አገልግሎት ያለህን ድርሻ ከፍ ማድረግ የምትችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? በምትኖርበት አገር የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ የሚያስፈልጉበት ቦታ ሊኖር ይችላል። በዚህ አካባቢ ሄደህ መኖር ትችል ይሆን? አሊያም በምትኖርበት አገር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተጠሙ ሰዎችን ለመርዳት ሌላ ቋንቋ ስለ መማር ልታስብ ትችላለህ። በአገልግሎቱ ያለህን ተሳትፎ ለመጨመር ስትል የምታደርገው ማስተካከያ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ አትረፍርፎ እንደሚባርክህ እርግጠኛ ሁን።—ምሳሌ 10:22
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የማይረሳ ቀን
በቡልጋሪያ የተካሄደውን ልዩ የአገልግሎት ዘመቻ ለመደገፍ ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች የመጡ ወንድሞችና እህቶች በሶፊያ በተደረገው “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ!” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር። በአገሪቱ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከተለያዩ አገሮች የመጡትን በርካታ ወንድሞችና እህቶች ማየታቸው በጣም አበረታቷቸዋል። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ሙሉው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቡልጋሪያ ቋንቋ መውጣቱን ባበሰረበት ጊዜ 2,039 የሚሆኑት ተሰብሳቢዎች እጅግ ተደስተዋል! ዓርብ ዕለት በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኙት በሙሉ የተሰማቸውን ደስታና አድናቆት በከፍተኛ ጭብጨባ ገልጸዋል። እንዲያውም ብዙዎች የደስታ እንባ አንብተዋል። ትክክለኛና ለመረዳት ቀላል የሆነው ይህ ትርጉም ቅን ልብ ያላቸው ቡልጋሪያውያን ይሖዋን እንዲያውቁ ለመርዳት ያስችላል።
[በገጽ 30 እና 31 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቡልጋሪያ
ሶፊያ
ሳንዳንስኪ
ሲሊስትራ
ካዛንላክ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በእነዚያ ሰባት ሳምንታት ከፍተኛ የሆነ ምሥክርነት ተሰጥቷል