አስደናቂ እድገት በተከናወነበት ወቅት ማገልገል
አስደናቂ እድገት በተከናወነበት ወቅት ማገልገል
ሃርሊ ሃሪስ እንደተናገሩት
ጊዜው መስከረም 2, 1950 ሲሆን ቦታው ደግሞ ኬነት፣ ሚዙሪ፣ ዩ ኤስ ኤ ነበር። የወረዳ ስብሰባ እያደረግን እያለ ረብሻ ለማስነሳት የፈለጉ በርካታ ሰዎች ከበቡን። ከንቲባው፣ ረብሸኞቹ ጥቃት እንዳይሰነዝሩብን ለመከላከል ወታደሮች ይዘው መጡ። ወታደሮቹም ጠመንጃቸውንና ሳንጃቸውን በመደገን ሰልፍ ይዘው ቆሙ። ረብሸኞቹ የስድብ ናዳ እያወረዱብን መኪናችን ውስጥ ገብተን ቀሪውን የስብሰባ ፕሮግራም ለማከናወን ወደ ኬፕ ጀራርዶ፣ ሚዙሪ ሄድን። የተጠመቅሁት በዚያ በተደረገው ስብሰባ ላይ ሲሆን በወቅቱ 14 ዓመቴ ነበር። እስቲ በመጀመሪያ እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ወቅት ይሖዋን ለማገልገል የመረጥኩት እንዴት እንደሆነ ላጫውታችሁ።
በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ አያቶቼና ስምንት ልጆቻቸው የወንድም ራዘርፎርድን አንዳንድ የተቀዱ ንግግሮች በማዳመጣቸው እውነትን እንዳገኙ እርግጠኞች ሆነው ነበር። ወላጆቼ ቤይ እና ሚልድረድ ሃሪስ በ1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠመቁ። ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ማንነት የተገለጸው በዚያ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሲሆን ወላጆቼ ከዚህ ሕዝብ መካከል በመሆናቸው በጣም ተደስተው ነበር!—ራእይ 7:9, 14
በቀጣዩ ዓመት እኔ ተወለድኩ። ከዓመት በኋላ ወላጆቼ ሚሲሲፒ ውስጥ ወንድሞች በሌሉበት አካባቢ መኖር ጀመሩ። በዚህ አካባቢ እያለን ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንኳ አይጎበኙንም ነበር። ቤተሰቤ ከቤቴል ጋር ይጻጻፍ የነበረ ሲሆን በትላልቅ ስብሰባዎች ላይም ይገኝ ነበር፤ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከወንድሞች ጋር ከዚህ ያለፈ ግንኙነት አልነበረንም።
በስደት ወቅት መጽናት
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ባላቸው የገለልተኝነት አቋም የተነሳ ብዙ ስደት ደርሶባቸዋል። በወቅቱ ወደ ማውንቴን ሆም፣ አርከንሶ ተዛውረን ነበር። አንድ ቀን ከአባቴ ጋር መንገድ ላይ እያገለገልን ሳለ አንድ ሰው ድንገት ከአባቴ መጽሔቶችን በመቀማት እሳት ለኩሶ ፊት ለፊታችን አቃጠላቸው። ሰውየው ወደ ጦርነት ባለመሄዳችን ፈሪዎች ብሎ ሰደበን። በዚህ ጊዜ ማልቀስ ጀመርኩ፤ በወቅቱ ገና አምስት ዓመቴ ነበር። አባቴ ግን ምንም ሳይናገር ሰውየውን በእርጋታ ይመለከተው ነበር፤ በመጨረሻም ሰውየው ትቶን ሄደ።
ለእኛ በጎ አመለካከት ያላቸው ጥሩ ሰዎችም ነበሩ። በአንድ ወቅት መኪናችን ውስጥ እያለን ረብሻ ሊያስነሱ የፈለጉ ሰዎች ከበቡን። አንድ አቃቤ ሕግ በዚያ ሲያልፉ ሁኔታውን ስለተመለከቱ “ምን ተፈጠረ?” ብለው ጠየቁ። ከሰዎቹ መካከል አንዱ “እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ለአገራቸው አይዋጉም!” በማለት መለሰ። አቃቤ ሕጉ በመኪናችን መወጣጫ ላይ በመቆም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፦ “በአንደኛ የዓለም ጦርነት ላይ ተዋግቻለሁ፤ በዚህኛውም ጦርነት ላይ እዋጋለሁ! እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው፤ እነሱ ማንንም አይነኩም!” በዚህ ጊዜ የተሰበሰቡት ሰዎች ቀስ በቀስ ተበተኑ። እንዲህ ያሉ ጥሩ ሰዎች ሰብዓዊ ደግነት ስላሳዩን በጣም አመስጋኝ ነን!—ሥራ 27:3
የአውራጃ ስብሰባዎች አጠናክረውናል
በ1941 በሴይንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ የተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ በወቅቱ የሚያስፈልገንን ማበረታቻ ሰጥቶናል። በስብሰባው ላይ ከ115,000 በላይ ሰዎች እንደተገኙ ይገመታል። በዚያ ወቅት 3,903 የሚሆኑ ሰዎች የተጠመቁ ሲሆን ይህም ከፍተኛ ቁጥር ነበር! “የንጉሡ ልጆች” በሚል ርዕስ ወንድም ራዘርፎርድ የሰጠውን ንግግር በደንብ አስታውሰዋለሁ። ወንድም ራዘርፎርድ ንግግሩን ያቀረበው በቀጥታ ለእኛ ለልጆች ነበር፤ ሁላችንም ሰማያዊ ቀለም ያለው ልጆች የተባለው መጽሐፍ ተሰጠን። ይህ የአውራጃ ስብሰባ በቀጣዩ ዓመት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ስጀምር ያጋጠመኝን ሁኔታ ለመቋቋም እንድችል አጠናክሮኛል። እኔና የአጎቴ ልጆች ለባንዲራ ሰላምታ ባለመስጠታችን ከትምህርት ቤት ተባረርን። እኛም የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ሐሳባቸው ከለወጡ ብለን በየቀኑ ትምህርት ቤት እንመላለስ ነበር። ለበርካታ ቀናት ጠዋት ጠዋት እየተነሳን ጫካውን በማቋረጥ ትምህርት ቤት ብንሄድም ወደ ቤታችን ይመልሱን ነበር። ያም ሆኖ የወሰድነው አቋም ለአምላክ መንግሥት ታማኝ መሆናችንን የምናሳይበት አጋጣሚ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ግን የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት ግዴታ እንዳልሆነ የሚገልጽ ድንጋጌ አስተላለፈ። በመሆኑም ትምህርት ቤት እንድንገባ ተፈቀደልን። አስተማሪው በጣም ደግ ስለነበር ያመለጠንን ትምህርት እንድናገኝና ሌሎቹ ተማሪዎች ላይ እንድንደርስ ረዳን። አብረውን የሚማሩት ልጆችም ለእኛ አክብሮት ነበራቸው።
በ1942 በክሌቭላንድ፣ ኦሃዮ የተካሄደውን የአውራጃ ስብሰባም አልረሳውም፤ በዚህ ስብሰባ ላይ ወንድም ናታን ኖር “ሰላም—ዘላቂ ሊሆን ይችላል?” የሚል ንግግር ሰጥቶ ነበር። ራዕይ ምዕራፍ 17ን የሚያብራራው ይህ ንግግር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አንጻራዊ ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ እንደሚመጣ አመላክቶ ነበር። በመሆኑም የስብከቱ ሥራ ይበልጥ እንደሚስፋፋ ተስፋ ተደርጎ ነበር። ለዚህ እድገት ለመዘጋጀት ሲባል በ1943 የጊልያድ ትምህርት ቤት ተቋቋመ። ይህ ትምህርት ቤት አንድ ቀን በሕይወቴ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በወቅቱ አልተገነዘብኩም ነበር። በእርግጥም ከጦርነቱ በኋላ ሰላም የመጣ ከመሆኑም በላይ ስደቱም እየበረደ ሄደ። ይሁንና በ1950 የኮሪያ ጦርነት ሲጀመር በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት የስብከቱ ሥራችን እንደገና ተቃውሞ ገጠመው።
ምሥራቹን በማስፋፋት የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ
በ1954 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀቅሁ፤ ከአንድ ወር በኋላ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። በኬነት፣ ሚዙሪ (በ1950 ረብሸኞች ከበውን የነበረበት ቦታ ነው) ሳገለግል ከቆየሁ በኋላ በመጋቢት ወር 1955 በቤቴል እንዳገለግል ተጠራሁ። እኔ የተመደብኩበት ጉባኤ ክልል፣ በኒው ዮርክ ሲቲ የሚገኝ ታይምስ ስኩዌር የሚባል አካባቢንም ይጨምር ነበር። የገጠራማውን አካባቢ ሕይወት ለምጄ በዚህ መኖር ለእኔ በጣም ትልቅ ለውጥ ነበር! ሩጫ የበዛበት ሕይወት የሚመሩ የኒው ዮርክ ነዋሪዎችን ትኩረት ለመሳብ ከመጽሔቶቻችን ላይ ስሜታቸውን የሚኮረኩር ርዕስ አውጥቼ ካሳየኋቸው በኋላ “እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ጠይቀው ያውቃሉ?” ብዬ እጠይቃቸዋለሁ። ብዙዎች መጽሔቶችን ይወስዳሉ።
በቤቴል ቆይታዬ በጣም ከሚያስደስቱኝ ነገሮች አንዱ ወንድም ኖር የሚመራው የማለዳ አምልኮ ነበር። ወንድም ኖር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የሚያብራራበትና እንዴት ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንደምንችል የሚያጎላበት መንገድ በጣም አስገራሚ ነበር! ነጠላ የሆንነውን ወጣት ወንድሞች እንደ ልጆቹ ቆጥሮ ያነጋግረን የነበረ ሲሆን ብዙውን ጊዜም ተቃራኒ ፆታን እንዴት መያዝ እንዳለብን ግሩም ምክር ይሰጠን ነበር።
በ1960 ለማግባት ወሰንኩ። ከ30 ቀን በኋላ ቤቴልን እንደምለቅ ማመልከቻ ባስገባም ምንም ምላሽ አላገኘሁም። ምንም እንኳ ዓይናፋር ብሆንም ሠላሳው ቀን ሲያበቃ እንደምንም ራሴን አደፋፍሬ ያቀረብኩት ማመልከቻ ደርሷቸው እንደሆነ ጠየቅኩ። ስልኩን ያነሳው ወንድም ሮበርት ዎለን ሲሆን እኔ የምሠራበት ድረስ መጣና ልዩ አቅኚ ወይም የወረዳ የበላይ ተመልካች ስለመሆን ምን እንደሚሰማኝ ጠየቀኝ። “እንዴ ቦብ፣ እኔ እኮ ገና 24 ዓመቴ ነው፤ ልምዱ የለኝም” አልኩት።
በወረዳ ሥራ ያሳለፍኩት ጊዜ
የዚያን ዕለት ማታ ክፍሌ ውስጥ አንድ ትልቅ ፖስታ ተቀምጦ አገኘሁ። በፖስታው ውስጥ ለልዩ አቅኚነትና ለወረዳ ሥራ ለማመልከት የሚሞሉ ቅጾች ነበሩበት። ይህ ያልጠበቅኩት ነገር ስለነበር የምለው ጠፋኝ! እኔም ይህን ታላቅ መብት በመቀበል በደቡብ ምዕራብ ሚዙሪ እና ምሥራቅ ካንሳስ አካባቢ የሚገኙትን ወንድሞቼን ማገልገል ጀመርኩ። ይሁንና ቤቴልን ከመልቀቄ በፊት ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ወንድም ኖር በመደምደሚያ ንግግሩ ላይ እንዲህ አለ፦ “የወረዳና
የአውራጃ የበላይ ተመልካች በመሆናችሁ ከአካባቢው ወንድሞች የበለጠ ታውቃላችሁ ማለት አይደለም። አንዳንዶች ከእናንተ የበለጠ ብዙ ተሞክሮ አላቸው። ነገር ግን ሁኔታዎች ስላልፈቀዱላቸው እናንተ የተሰጣችሁን መብት ማግኘት አልቻሉም። ከእነሱ ብዙ መማር ትችላላችሁ።”የተናገረው ነገር በእርግጥም እውነት ነበር። ለአብነት ያህል፣ በፓርሰንዝ፣ ካንሳስ የሚኖሩት ወንድም ቻርሊ እና ወንድማቸው የሆኑት ወንድም ፍሬድ ሞሎሃን ከነባለቤታቸው በጣም ግሩም ምሳሌዎች ነበሩ። እነዚህ ወንድሞች እውነትን የሰሙት በ1900ዎቹ ነው። በዚያን ጊዜ ስለነበረው ሁኔታ ተሞክሯቸውን ሲናገሩ መስማት በጣም ያስደስታል፤ በወቅቱ እኔ ገና አልተወለድኩም ነበር! ሌላው ወንድም ደግሞ በጆፕሊን፣ ሚዙሪ የሚኖሩት ወንድም ጆን ሪስተን ናቸው፤ ደግ የሆኑት እኚህ አረጋዊ ወንድም ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በአቅኚነት አገልግለዋል። እነዚህ ውድ ወንድሞች ለቲኦክራሲያዊው ሥርዓት ጥልቅ አክብሮት ነበራቸው። ወጣት ብሆንም እንኳ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እነሱን ሳገለግል ጠቃሚ ተግባር እያከናወንኩ እንደሆነ እንዲሰማኝ አድርገውኛል።
በ1962 ክሎሪስ ክኖኬ የምትባል ተጫዋች የሆነችና ቀላ ያለ ፀጉር ያላት አንዲት አቅኚ አገባሁ። ከክሎሪስ ጋር በመሆን በወረዳ ሥራ ማገልገሌን ቀጠልኩ። ወንድሞች ጋ ስናርፍ እነሱን የበለጠ ለማወቅ አጋጣሚ እናገኝ ነበር። ወጣቶች፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ ማበረታታት ችለን ነበር። በወረዳችን ውስጥ የሚገኙ ጄይ ኮሲንስኪ እና ጆአን ክሬስማን የተባሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወጣቶች እንዲህ ያለው ማበረታቻ ቢሰጣቸው ለመቀበል ዝግጁ ነበሩ። ከእኛ ጋር አብረው ማገልገላቸውና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚያስገኘውን ደስታ በእኛ ሕይወት መመልከታቸው ለራሳቸው ግብ እንዲያወጡ አነሳሳቸው። ጆአን ልዩ አቅኚ ስትሆን ጄይ ደግሞ ቤቴል ገባ። እነዚህ ወጣቶች ከጊዜ በኋላ ትዳር የመሠረቱ ሲሆን በወረዳ ሥራ እስከ ዛሬ ድረስ 30 ዓመታት ያህል አሳልፈዋል።
የሚስዮናዊነት አገልግሎት
በ1966 ወንድም ኖር በሌሎች አገሮች ማገልገል እንፈልግ እንደሆነ ጠየቀን። “አሁን ባለንበት ቦታ ደስተኞች ነን። እርዳታ የሚያስፈልግበት ቦታ ካለ ግን ለመሄድ ዝግጁ ነን” ብለን መለስንለት። ከሳምንት በኋላ ወደ ጊልያድ ትምህርት ቤት ተጠራን። በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ወደ ቤቴል መመለስ ብሎም ከምወዳቸውና ከማከብራቸው በርካታ ወንድሞች ጋር እንደገና መገናኘት መቻል ምንኛ አስደሳች ነው! አብረውን ከሚማሩት ወንድሞች ጋርም ወዳጅነት የመሠረትን ሲሆን እነዚህ ወንድሞች አሁንም ድረስ በታማኝነት እያገለገሉ ነው።
እኔና ክሎሪስ፣ ዴኒስና ኤድዊና ክሪስት ከተባሉት ባልና ሚስት እንዲሁም አና ሮድሪገስ እና ዴሊያ ሳንቼስ ከተባሉት እህቶች ጋር በደቡብ አሜሪካ በምትገኘው በኢኳዶር እንድናገለግል ተመደብን። ዴኒስና ኤድዊና ወደ ዋና ከተማዋ ኪቶ ሄዱ። አና እና ዴሊያ፣ ኢኳዶር ውስጥ ከሚገኙት ከተሞች በትልቅነቷ ሦስተኛ በሆነችው በኩዌንካ ከእኛ ጋር እንዲያገለግሉ ተመደቡ። ክልላችን ሌሎች ሁለት አካባቢዎችንም ይጨምር ነበር። በኩዌንካ የመጀመሪያው ጉባኤ መሰብሰብ የጀመረው እኛ ቤት ነበር። በስብሰባው ላይ የምንገኘው ሌሎች ሁለት ሰዎችን ጨምሮ እኛ አራታችን ብቻ ነበርን። በወቅቱ ምሥራቹን እንዴት ማዳረስ እንደምንችል አሳስቦን ነበር።
በኩዌንካ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን በበዓል ቀናት ከተማዋ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን ለማክበር በሚወጡ ሰዎች ትጥለቀለቅ ነበር። ይሁንና የኩዌንካ ነዋሪዎች በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በብስክሌት ውድድር ሻምፒዮን የሆነውን ማርዮ ፖሎን
መጀመሪያ ባገኘሁት ወቅት “በራእይ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰችው ጋለሞታ ማን ናት?” በማለት ያልጠበቅኩት ጥያቄ አቀረበልኝ።በሌላ ጊዜ ደግሞ ማርዮ አንድ የረበሸው ነገር ስለነበር በምሽት ወደ ቤታችን መጣ። አንድ የኢቫንጀሊካን ፓስተር የይሖዋ ምሥክሮችን የሚነቅፉ አንዳንድ ጽሑፎች ሰጥቶት ነበር። ነቀፋ የተሰነዘረበት አካል ስለ ራሱ ለመናገር ዕድል ሊሰጠው እንደሚገባ ማርዮን አስረዳሁት። በመሆኑም በቀጣዩ ቀን ማርዮ ፓስተሩንና እኔን ወደ ቤቱ በመጋበዝ ለተሰነዘረብን ነቀፋ መልስ እንድሰጥ አጋጣሚ ሰጠኝ። ከፓስተሩ ጋር ስንገናኝ በሥላሴ ትምህርት ላይ እንድናተኩር ሐሳብ አቀረብኩ። ፓስተሩ ዮሐንስ 1:1ን ሲያነብ ማርዮ ራሱ ጥቅሱ በግሪክኛ ያለውን ትርጉም በትክክል አብራራው። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይም በዚህ ዓይነት ውይይቱ ቀጠለ። ፓስተሩ የሥላሴ ትምህርት ትክክል መሆኑን አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ሳይችል ተለያየን። ማርዮና ባለቤቱ ይህን ሲመለከቱ እውነት ያለው እኛ ጋ እንደሆነ ያመኑ ሲሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጥብቅና በመቆም ረገድ የተዋጣላቸው ሆኑ። በኩዌንካ ከተማ የሚገኙት ጉባኤዎች ቁጥር ወደ 33 ሲያድግና ይህን ከተማ ጨምሮ ሰፊ አካባቢዎችን በሚሸፍነው የመጀመሪያው ክልላችን ውስጥ በአጠቃላይ 63 ጉባኤዎች ሲቋቋሙ መመልከት ምንኛ አስደሳች ነበር፤ ይህ በእርግጥም አስደናቂ እድገት ነው!
በቅርንጫፍ ቢሮ ሆኖ እድገቱን መመልከት
በ1970 በጉዋያኪል በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ከአል ስኩሎ ጋር እንዳገለግል ተጋበዝኩ። ሁለታችን በቅርንጫፍ ቢሮው የሚከናወነውን ሥራ በኃላፊነት እንከታተል ነበር። ጆ ሴከራክ፣ በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓታት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው እየመጣ በመላው አገሪቱ ለሚገኙት 46 ጉባኤዎች ጽሑፎችን ያሽግ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ያህል እኔ ቤቴል ስሠራ ክሎሪስ ደግሞ መስክ ላይ ትሠራ ነበር። ክሎሪስ 55 ሰዎች ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ የረዳች ሲሆን ብዙውን ጊዜ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ከሦስት እስከ አምስት የሚሆኑ ጥናቶቿ ይጠመቁላታል።
ለምሳሌ ክሎሪስ፣ ሉክሬሲያ ከተባለች ሴት ጋር ታጠና ነበር። ሉክሬሲያ ባሏ ተቃዋሚ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ የተጠመቀች ሲሆን የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ልጆቿንም የይሖዋን መንገዶች አስተምራቸዋለች። በአሁኑ ጊዜ ሁለቱ ወንዶች ልጆቿ ሽማግሌዎች፣ አንደኛው ልዩ አቅኚ፣ ሴቷ ልጇ ደግሞ የዘወትር አቅኚ ሆነው ያገለግላሉ። የልጅ ልጇ ደግሞ መንፈሳዊ የሆነ ወንድም አግብታ ልዩ አቅኚ ሆነው አብረው እያገለገሉ ነው። ይህ ቤተሰብ ብዙዎች እውነትን እንዲያውቁ ረድቷል።
በ1980 በኢኳዶር 5,000 የሚያህሉ አስፋፊዎች ነበሩ። ትንሿ ቅርንጫፍ ቢሯችን ሥራውን ለማስተናገድ እየጠበበችን ነበር። አንድ ወንድም ከጉዋያኪል ወጣ ብሎ የሚገኝ 32 ሄክታር ስፋት ያለው ቦታ ሰጠን። በ1984 በዚህ ቦታ ላይ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮና የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ መገንባት የጀመርን ሲሆን በ1987 ሥራው ተጠናቅቆ ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰነ።
ብዙዎች ራሳቸውን በማቅረብ ለእድገቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል
ባለፉት ዓመታት በርካታ አስፋፊዎችና አቅኚዎች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ከሌሎች አገሮች ወደ ኢኳዶር ሲመጡ መመልከታችን በጣም አስደስቶናል። ከእነዚህም መካከል አንዲ ኪድ የተባሉ ከካናዳ የመጡ ጡረታ የወጡ አስተማሪ ከአእምሮዬ አይጠፉም። ወንድም አንዲ በ1985 ወደ ኢኳዶር ሲመጡ የ70 ዓመት አዛውንት የነበሩ ሲሆን በ2008 በ93 ዓመታቸው እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት አገልግለዋል። በተመደቡበት ቦታ መጀመሪያ በተገናኘንበት ወቅት በአንድ ትንሽ ጉባኤ ውስጥ ያገለግሉ የነበረ ሲሆን በጉባኤው ውስጥ ያሉት የበላይ ተመልካች እሳቸው ብቻ ነበሩ። ስፓንኛ መናገር ቢያስቸግራቸውም የሕዝብ ንግግሩን ከሰጡ በኋላ መጠበቂያ ግንብ ይመሩ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ይመሩ እንዲሁም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ አብዛኞቹን ክፍሎች ያቀርቡ ነበር! በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ 200 ያህል አስፋፊዎች ያሏቸው ሁለት ትልልቅ ጉባኤዎች ተቋቁመዋል፤ እነዚህ ጉባኤዎች በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ የጉባኤ ሽማግሌዎች አሏቸው።
ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኢኳዶር ከቤተሰቡ ጋር የተዛወረው ኤርኔስቶ ዲያዝ የተባለ ወንድም በኢኳዶር ስምንት ወራት ከቆየ በኋላ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሦስቱ ልጆቻችን ቋንቋውን ቶሎ በመልመድ ግሩም አስተማሪዎች ሆነዋል። እኔም አባት እንደመሆኔ በዚህ ሥርዓት ፈጽሞ ይሳካልኛል ብዬ ያላሰብኩት ግብ ላይ መድረስ ይኸውም የዘወትር አቅኚ ሆኜ ከቤተሰቤ ጋር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ችያለሁ። በአጠቃላይ 25 የመጽሐፍ
ቅዱስ ጥናቶች አሉን። ይህ ሁሉ ቤተሰባችን ይበልጥ አንድነት እንዲኖረው አድርጓል፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከይሖዋ ጋር ለመቀራረብ አስችሎኛል።” እንደነዚህ ያሉ ውድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በጣም እናደንቃቸዋለን!በ1994 ቅርንጫፍ ቢሮውን የማስፋፋት ሥራ የተካሄደ ሲሆን የበፊቱን እጥፍ የሚሆን ስፋት እንዲኖረው ተደረገ። በ2005 በኢኳዶር ያሉት አስፋፊዎች ቁጥር ከ50,000 በላይ በመሆኑ ቅርንጫፍ ቢሮውን እንደገና ማስፋት አስፈለገ። አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ከበፊቱ የሚበልጥ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ፣ አዲስ የመኖሪያ ሕንፃ እንዲሁም የትርጉም ቢሮዎችን ያካተተ ነበር። ይህ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ጥቅምት 31, 2009 ተወሰነ።
በ1942 ከትምህርት ቤት በተባረርኩበት ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 60,000 ገደማ ነበር። አሁን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሆነዋል። በ1966 ወደ ኢኳዶር ስንመጣ 1,400 የሚሆኑ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ነበሩ። አሁን ከ68,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። በዚያ አገር 120,000 የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መኖራቸውና በ2009 በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከ232,000 የሚበልጡ ሰዎች መገኘታቸው ወደ እውነት የሚመጡ ገና ብዙ ሰዎች እንዳሉ ያሳያል። በእርግጥም ይሖዋ ፈጽሞ ባላሰብነው መንገድ ሕዝቡን ባርኳል። በጣም አስደናቂ እድገት በተከናወነበት ወቅትና ቦታ መኖር ምንኛ አስደሳች ነው! *
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.34 ይህ ርዕስ ለኅትመት በሚዘጋጅበት ወቅት ወንድም ሃርሊ ሃሪስ ለይሖዋ ታማኝነታቸውን እንደጠበቁ ሞተዋል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከቤት ውጪ የተደረገ ትልቅ ስብሰባ (በ1981) እንዲሁም በዚሁ ቦታ ላይ የተሠራው የጉዋያኪል የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ (2009)