አንድነት እውነተኛውን አምልኮ ለይቶ ያሳውቃል
አንድነት እውነተኛውን አምልኮ ለይቶ ያሳውቃል
“በጕረኖ ውስጥ እንዳሉ በጎች . . . በአንድነት እሰበስባቸዋለሁ።”—ሚክ. 2:12
1. ፍጥረት የአምላክን ጥበብ የሚገልጠው እንዴት ነው?
አንድ መዝሙራዊ “[ይሖዋ] ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች” በማለት በአድናቆት ተናግሯል። (መዝ. 104:24) በምድራችን ላይ ባለውና እጅግ ውስብስብ በሆነው ብዝሃ ሕይወት ውስጥ የተካተቱት የተለያየ ዝርያ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዕፅዋት፣ ነፍሳት፣ እንስሳትና ባክቴሪያዎች እርስ በርስ ያላቸው መደጋገፍ የአምላክን ጥበብ ይገልጣል። ከዚህም በተጨማሪ ትልልቅ ከሆኑት የአካል ክፍሎች አንስቶ በዓይን እስከማይታዩት ሴሎች ድረስ በሰውነትህ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱ ሲሆን እነዚህም በአንድነት ተቀናጅተው የተሟላህና ጤናማ ሰው እንድትሆን ያስችሉሃል።
2. በገጽ 13 ላይ ያለው ሥዕል እንደሚያሳየው በክርስቲያኖች መካከል የነበረው አንድነት ተአምር ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
2 የሰው ዘር የተለያየ መልክ፣ ባሕርይና ችሎታ እንዳለው በግልጽ መመልከት የሚቻል ቢሆንም ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠረው እርስ በርስ ተደጋግፈው እንዲኖሩ አድርጎ ነው። በተጨማሪም አምላክ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አምላካዊ ባሕርያት እንዲኖራቸው አድርጎ የፈጠራቸው ሲሆን ይህም እርስ በርስ ተባብረውና ተደጋግፈው እንዲኖሩ ያስችላቸው ነበር። (ዘፍ. 1:27፤ 2:18) ሆኖም ሰብዓዊው ኅብረተሰብ በጥቅሉ ሲታይ በአሁኑ ጊዜ ከአምላክ የራቀ ከመሆኑም ሌላ መላው የዓለም ሕዝብ አንድነት ኖሮት አያውቅም። (1 ዮሐ. 5:19) በመሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ በኤፌሶን የሚኖሩ ባሪያዎችን፣ የታወቁ ግሪካውያን ሴቶችን፣ የተማሩ አይሁዳውያን ወንዶችንና ጣዖት አምላኪ የነበሩ ሰዎችን ያቀፈ ከመሆኑ አንጻር በመካከላቸው የነበረው አንድነት እንደ ተአምር ሳይቆጠር አልቀረም።—ሥራ 13:1፤ 17:4፤ 1 ተሰ. 1:9፤ 1 ጢሞ. 6:1
3. መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት ከምን ጋር ያነጻጽረዋል? በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?
3 የአካል ክፍሎቻችን ተስማምተው እንደሚሠሩ ሁሉ ሰዎችም ተባብረው እንዲሠሩ እውነተኛው አምልኮ አስተዋጽኦ ያደርጋል። (1 ቆሮንቶስ 12:12, 13ን አንብብ።) በዚህ ርዕስ ውስጥ ከምንመረምራቸው ነጥቦች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦ እውነተኛ አምልኮ ሰዎችን አንድ የሚያደርገው እንዴት ነው? ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አንድ ማድረግ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ ለአንድነት እንቅፋት የሚሆኑ የትኞቹን ነገሮች መወጣት እንድንችል ይረዳናል? እንዲሁም ከአንድነት አንጻር እውነተኛ ክርስትና ከሕዝበ ክርስትና የሚለየው እንዴት ነው?
እውነተኛ አምልኮ ሰዎችን አንድ የሚያደርገው እንዴት ነው?
4. እውነተኛ አምልኮ ሰዎችን አንድ የሚያደርገው እንዴት ነው?
4 በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ የታቀፉ ሰዎች ይሖዋ ሁሉን ነገር ስለፈጠረ፣ የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት ያለው እሱ መሆኑን ይገነዘባሉ። (ራእይ 4:11) ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር የሚኖሩ ቢሆኑም ሁሉም አምላክ ያወጣላቸውን አንድ ዓይነት ሕግ የሚታዘዙ ከመሆኑም ሌላ የሚመሩትም በአንድ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ይሖዋን “አባታችን” ብለው መጥራታቸው ተገቢ ነው። (ኢሳ. 64:8፤ ማቴ. 6:9) በመሆኑም ሁሉም በመንፈሳዊ ሁኔታ ወንድማማች ናቸው፤ እንዲሁም መዝሙራዊው “ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” በማለት የገለጸው ዓይነት ግሩም አንድነት በመካከላቸው አለ።—መዝ. 133:1
5. እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች አንድነት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ ያደረገው የትኛው ባሕርይ ነው?
5 እውነተኛ ክርስቲያኖች ፍጹማን ባይሆኑም አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ማሳየት እንዳለባቸው ስለተማሩ ይሖዋን በአንድነት ያመልኩታል። ይሖዋ ማንም ሊያስተምራቸው ከሚችለው በላይ ፍቅርን አስተምሯቸዋል። (1 ዮሐንስ ን አንብብ።) ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ። አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ። ይሁንና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤ ምክንያቱም ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።” ( 4:7, 8ቆላ. 3:12-14) ፍጹም የሆነው የአንድነት ማሰሪያ ይኸውም ፍቅር እውነተኛ ክርስቲያኖች በዋነኝነት ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ ነው። አንተስ ይህ አንድነት የእውነተኛው አምልኮ መለያ መሆኑን በሕይወትህ አልተመለከትክም?—ዮሐ. 13:35
6. የመንግሥቱ ተስፋ አንድነታችንን ለመጠበቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
6 እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው ሌላው ምክንያት የሰው ዘር ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ አድርገው መመልከታቸው ነው። አምላክ በቅርቡ ሰብዓዊ መንግሥታትን በማስወገድ የራሱን መስተዳድር እንደሚያቋቁምና ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች እውነተኛና ዘላቂ ሰላም በመስጠት እንደሚባርካቸው ያውቃሉ። (ኢሳ. 11:4-9፤ ዳን. 2:44) በመሆኑም ክርስቲያኖች “እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም” በማለት ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ የተናገረውን ሐሳብ ተግባራዊ ያደርጋሉ። (ዮሐ. 17:16) እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለም ላይ በሚካሄዱት ግጭቶች ውስጥ ጣልቃ አይገቡም፤ ስለሆነም በአካባቢያቸው ያሉ ሌሎች ሰዎች በጦርነት ላይ በሚካፈሉበት ጊዜም እንኳ እነሱ አንድነታቸውን መጠበቅ ችለዋል።
መንፈሳዊ መመሪያ የምናገኝበት ብቸኛው ምንጭ
7, 8. መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎች ለአንድነታችን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት በምን መንገድ ነው?
7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች አንድነት የነበራቸው ሁሉም ከአንድ ምንጭ መመሪያ ያገኙ ስለነበር ነው። ኢየሱስ፣ በኢየሩሳሌም የሚገኙ ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን ባቀፈው የበላይ አካል አማካኝነት ጉባኤውን እንደሚያስተምርና እንደሚመራ ተገንዝበው ነበር። ታማኝ የሆኑት እነዚህ ወንዶች ውሳኔ የሚያደርጉት በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተው ሲሆን ያወጡትን መመሪያ በተጓዥ የበላይ ተመልካቾች አማካኝነት በተለያዩ አገሮች ውስጥ ለሚገኙ ጉባኤዎች ይልኩ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደነዚህ ስላሉት አንዳንድ የበላይ ተመልካቾች ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በየከተማዎቹ ሲያልፉም በዚያ ለሚያገኟቸው ሁሉ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች እንዲጠብቁ ያሳውቋቸው ነበር።”—ሥራ 15:6, 19-22፤ 16:4
8 ዛሬም በተመሳሳይ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ያቀፈው የበላይ አካል ለዓለም አቀፉ ጉባኤ አንድነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። የበላይ አካሉ መንፈሳዊ ማበረታቻ የያዙ ጽሑፎችን በበርካታ ቋንቋዎች ያዘጋጃል። ይህ መንፈሳዊ ምግብ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ነው። በመሆኑም ይህ ትምህርት የመነጨው ከሰዎች ሳይሆን ከይሖዋ ነው።—ኢሳ. 54:13
9. አምላክ የሰጠን ሥራ አንድነት እንዲኖረን የረዳን እንዴት ነው?
9 ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችም በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም በመሆን ለአንድነቱ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። አምላክን በኅብረት የሚያገለግሉ ሰዎችን አንድ ያደረጋቸው በመካከላቸው ያለው የጠበቀ ዝምድና፣ በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነት ለመመሥረት ሲሉ ብቻ ከሚፈጥሩት ዝምድና በእጅጉ የላቀ ነው። የክርስቲያን ጉባኤ ከሰዎች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ብቻ ተብሎ የተቋቋመ ክበብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ለማክበርና እሱ ሮም 1:11, 12፤ 1 ተሰ. 5:11፤ ዕብ. 10:24, 25) በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ “አንድ ላይ ሆናችሁ ለምሥራቹ እምነት በአንድ ነፍስ በመጋደል በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ [ቆማችኋል]” ለማለት ችሎ ነበር።—ፊልጵ. 1:27
የሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ይኸውም የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ፣ ደቀ መዛሙርት ለማድረግና ጉባኤውን ለማነጽ የተቋቋመ ነው። (10. እኛ የአምላክ ሕዝቦች አንድነት እንዲኖረን የረዱን የትኞቹ ነገሮች ናቸው?
10 እስካሁን መመልከት እንደቻልነው እኛ የይሖዋ ሕዝቦች አንድነት ሊኖረን የቻለው የይሖዋን ሉዓላዊነት ስለምንቀበል፣ ወንድሞቻችንን ስለምንወድ፣ ተስፋ የምናደርገው በአምላክ መንግሥት ላይ ስለሆነ እንዲሁም አምላክ በመካከላችን ግንባር ቀደም ሆነው አመራር እንዲሰጡን ለሚጠቀምባቸው ሰዎች አክብሮት ስለምናሳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ፍጽምና የሚጎድለን በመሆናችን ለአንድነታችን ጠንቅ የሆኑ አንዳንድ መጥፎ ዝንባሌዎች አሉብን፤ እነዚህን ዝንባሌዎች እንድናሸንፍ ይሖዋ ይረዳናል።—ሮም 12:2
የኩራትና የቅናት ስሜትን ማሸነፍ
11. ኩራት ሰዎችን ይከፋፍላል የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ ይህን ባሕርይ እንድናሸንፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
11 ኩራት ሰዎችን ይከፋፍላል። ኩራተኛ ሰው ራሱን ከሌሎች አስበልጦ የሚመለከት ከመሆኑም ሌላ ጉራ በመንዛት የራሱን ደስታ ብቻ ለማግኘት ይጥራል። እንዲህ ያለው ዝንባሌ ብዙውን ጊዜ ለአንድነት ፀር ነው፤ ጉራውን የሚነዛባቸው ሰዎች በእሱ ላይ ቅናት ሊያድርባቸው ይችላል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “እንዲህ ያለው ኩራት ሁሉ ክፉ ነው” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ያዕ. 4:16) ሌሎችን ዝቅ አድርጎ መመልከት ፍቅር የጎደለው ምግባር ነው። የሚገርመው ነገር ይሖዋ ትሕትና በማሳየት ረገድ ምሳሌ ነው፤ ይህንንም ያሳየው ፍጽምና ከጎደለን ከእኛ ጋር ዝምድና በመመሥረት ነው። ዳዊት ‘እኔን ታላቅ የሚያደርገኝ ትሕትናህ ነው’ በማለት ስለ አምላክ ጽፏል። (2 ሳሙ. 22:36 NW) የአምላክ ቃል ተገቢውን አስተሳሰብ እንድናዳብር በማስተማር ኩራትን እንድናሸንፍ ይረዳናል። ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ እንደሚከተለው በማለት ጠይቋል፦ “አንተን ከሌላው የተለየህ እንድትሆን ያደረገህ ማን ነው? ደግሞስ ያልተቀበልከው ምን ነገር አለህ? ከተቀበልክ ደግሞ እንዳልተቀበልክ ሆነህ የምትኩራራው ለምንድን ነው?”—1 ቆሮ. 4:7
12, 13. (ሀ) የቅናት ስሜት በቀላሉ ሊያድርብን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ለሌሎች ያለውን ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን ምን ጥቅም ያስገኛል?
12 ለአንድነት ፀር የሆነው ሌላው ነገር ቅናት ነው። በወረስነው አለፍጽምና የተነሳ ሁላችንም በውስጣችን ‘የቅናት ዝንባሌ’ አለን፤ በእውነት ቤት ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ክርስቲያኖችም እንኳ ሌሎች ያሉበትን ሁኔታ በመመልከት አሊያም ያላቸውን ንብረት፣ መብት ወይም ችሎታ በማየት አልፎ አልፎ የቅናት ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። (ያዕ. 4:5) ለምሳሌ ያህል፣ ቤተሰብ ያለው አንድ ወንድም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ ሌላ ወንድም ባገኘው መብት የቅናት ስሜት ሊያድርበት ይችላል፤ ይሁንና ይህ ወንድም ልጆች በመውለዱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዩ ትንሽ ቅናት ቢጤ ሊያድርበት እንደሚችል አይገነዘብ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ያለው የቅናት ስሜት አንድነታችንን እንዳያናጋው መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?
13 መጽሐፍ ቅዱስ፣ በመንፈስ የተቀቡ የክርስቲያን ጉባኤ አባላትን ከሰው የአካል ክፍሎች ጋር እንደሚያነጻጽራቸው ማስታወሳችን የቅናት ስሜትን ለማስወገድ ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 12:14-18ን አንብብ።) ለምሳሌ፣ ዓይንህ ከልብህ ይልቅ በቀላሉ የሚታይ ቢሆንም ሁለቱም የአካል ክፍሎች ለአንተ ጠቃሚ አይደሉም? በተመሳሳይም በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለጊዜው ከሌሎች ጎላ ብለው ሊታዩ ቢችሉም ይሖዋ ሁሉንም የጉባኤ አባላት ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። በመሆኑም ይሖዋ ለወንድሞቻችን ያለውን ዓይነት አመለካከት እናዳብር። በሌሎች ከመቅናት ይልቅ ለእነሱ አሳቢነት ልናሳያቸው እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ በእውነተኛ ክርስቲያኖችና በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ልዩነት ጎልቶ እንዲታይ አስተዋጽኦ እናበረክታለን።
በመከፋፈል የታወቀችው ሕዝበ ክርስትና
14, 15. የክህደት ክርስትና የተከፋፈለው እንዴት ነው?
14 በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከሚታየው መከፋፈል በተቃራኒ እውነተኛ ክርስቲያኖች ያላቸው አንድነት ጎልቶ ይታያል። በአራተኛው መቶ ዘመን የክህደት ክርስትና በጣም ተስፋፍቶ ስለነበር አረማዊ የነበረው የሮም ንጉሠ ነገሥት በክርስትና እምነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ጀመረ፤ ይህም ለሕዝበ ክርስትና መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከዚያም ቀስ በቀስ ከሮም የተገነጠሉ በርካታ መንግሥታት የራሳቸውን የመንግሥት ሃይማኖት መሠረቱ።
15 ከእነዚህ መንግሥታት መካከል አብዛኞቹ ለበርካታ ዘመናት እርስ በርስ ሲዋጉ ኖረዋል። በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ዘመን በብሪታንያ፣ በዩናይትድ ስቴትስና በፈረንሳይ የሚኖሩ ሰዎች ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር እየጨመረ በመምጣቱ ብሔራዊ ስሜት እንደ ሃይማኖት መታየት ጀመረ። በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ዘመን ብሔራዊ ስሜት በአብዛኛው የሰው ዘር አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሮ ነበር። ውሎ አድሮ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በበርካታ ቡድኖች የተከፋፈሉ ሲሆን አብዛኞቹም ብሔራዊ ስሜትን በቸልታ ተመልክተውታል። ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ ሰዎችም እንኳ ሳይቀሩ በሌላ አገር የሚገኝን የእምነት ባልንጀራቸውን ለመውጋት ጦርነት ዘምተዋል። በዛሬው ጊዜ ሕዝበ ክርስትና በእምነትም ሆነ በብሔር ተከፋፍላለች።
16. በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉትን ሰዎች የሚከፋፍሉት የትኞቹ ነገሮች ናቸው?
16 በ20ኛው መቶ ዘመን በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ከሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሃይማኖት ቡድኖች መካከል አንዳንዶቹ ልዩነቶቻቸውን በማስወገድ በመካከላቸው አንድነት እንዲኖር ለማስቻል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ጥረት ቢደረግም ውሕደት የፈጠሩት ቤተ ክርስቲያኖች ቁጥር ጥቂት ነው፤ ያም ቢሆን በዝግመተ ለውጥ፣ ጽንስ በማስወረድ፣ በግብረ ሰዶምና ለሴቶች የቅስና ማዕረግ በመስጠት ረገድ በምዕመኖቻቸው መካከል አሁንም ድረስ ልዩነት አለ። በአንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ክፍሎች ያሉ የሃይማኖት መሪዎች፣ ቀደም ሲል ለመከፋፈል ምክንያት የሆኗቸውን መሠረተ ትምህርቶች ወደ ጎን በመተው የተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖችን አንድ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ይሁንና መሠረተ ትምህርቶችን ወደ ጎን መተው ሰዎች እምነታቸው እንዲዳከም ከማድረግ ውጪ የፈየደው ነገር የለም፤ ደግሞም የተከፋፈሉትን የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች አንድ እንደማያደርጋቸው የተረጋገጠ ነው።
ከብሔራዊ ስሜት የጸዳ
17. እውነተኛው አምልኮ “በመጨረሻው ዘመን” ሰዎችን አንድ እንደሚያደርግ አስቀድሞ የተነገረው እንዴት ነው?
17 በዘመናችን የሰው ልጆች ከመቼውም ጊዜ በላይ በአስከፊ ሁኔታ የተከፋፈሉ ቢሆንም አንድነት እስከ ዛሬ ድረስ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችን ለይቶ የሚያሳውቅ ምልክት ሆኗል። የአምላክ ነቢይ የሆነው ሚክያስ “በጕረኖ ውስጥ እንዳሉ በጎች . . . በአንድነት እሰበስባቸዋለሁ” በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ሚክ. 2:12) ሚክያስ እውነተኛው አምልኮ ከየትኛውም ዓይነት አምልኮ ማለትም የሐሰት አማልክትን ከማምለክም ሆነ አገርን እንደ አምላክ ከማየት ልቆ እንደሚገኝ አስቀድሞ ተናግሯል። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በመጨረሻው ዘመን፣ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቤተ መቅደስ ተራራ፣ ከተራሮች ልቆ ይታያል፤ ከኰረብቶች በላይ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።”—ሚክ. 4:1, 5
18. እውነተኛው አምልኮ ምን ለውጦችን እንድናደርግ ረድቶናል?
18 በተጨማሪም ሚክያስ እውነተኛው አምልኮ ቀድሞ ጠላቶች የነበሩ ሰዎች አንድነት እንዲኖራቸው የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “[ከብዙ ብሔራት የተውጣጡ] አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ ‘ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንሂድ፤ በመንገዱ እንድንሄድ፣ መንገዱን ያስተምረናል።’ . . . ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል። አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም።” (ሚክ. 4:2, 3) የይሖዋን አምልኮ ለመቀበል ሲሉ ሰው ሠራሽ አማልክትን ወይም አገራቸውን ማምለክ የተዉ ሰዎች ዓለም አቀፍ አንድነት ይኖራቸዋል። አምላክ የፍቅርን መንገድ እንዲማሩ ያደርጋል።
19. በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በእውነተኛው አምልኮ አንድ መሆናቸው ለምን ነገር ግልጽ ማስረጃ ነው?
19 በዛሬው ጊዜ በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል የሚታየው ዓለም አቀፋዊ አንድነት በዓይነቱ ልዩ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሱ አማካኝነት እየመራ እንዳለ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አንድ ሆነዋል። ይህም በራእይ 7:9, 14 ላይ የተገለጸው ሐሳብ አስገራሚ በሆነ መንገድ መፈጸሙን ያሳያል፤ ይህ ሁኔታ መፈጸሙ የአምላክ መላእክት አሁን ያለውን ክፉ ሥርዓት የሚያጠፉትን “ነፋሳት” በቅርቡ እንደሚለቁ ይጠቁማል። (ራእይ 7:1-4, 9, 10, 14ን አንብብ።) አንድነት ባለው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ መታቀፍ ታላቅ መብት አይደለም? ታዲያ እያንዳንዳችን ለዚህ አንድነት አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ጥያቄ ያብራራል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• እውነተኛው አምልኮ ሰዎችን አንድ የሚያደርገው እንዴት ነው?
• ቅናት አንድነታችንን እንዳያናጋብን መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?
• ብሔራዊ ስሜት እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችን መከፋፈል ያልቻለው ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ከተለያዩ አገሮችና የኅብረተሰብ ክፍሎች የመጡ ነበሩ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከመንግሥት አዳራሽ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ላይ መካፈላችን ለአንድነት አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?