በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለይሖዋ መባ አድርገን እናቅርብ’

‘ለይሖዋ መባ አድርገን እናቅርብ’

አንድ ሰው ደግነት ሲያሳይህ አድናቆትህን ለመግለጽ ምን ታደርጋለህ? በእስራኤል የነበሩ የጦር አዛዦች ከምድያማውያን ጋር ከተዋጉ በኋላ ለይሖዋ ምስጋናቸውን ለመግለጽ ምን እንዳደረጉ እንመልከት። ጦርነቱ የተካሄደው እስራኤላውያን የፌጎርን በኣል በማምለክ ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ነበር። በዚህ ጦርነት አምላክ ለሕዝቡ ድል ያጎናጸፋቸው ሲሆን የተገኘው ምርኮ ለሁለት ተከፍሎ ለ12,000ዎቹ ወታደሮችና ለተቀሩት እስራኤላውያን ተከፋፈለ። ከዚያም ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ወታደሮቹ ከራሳቸው ድርሻ የተወሰነውን ለካህናቱ የሰጡ ሲሆን የተቀሩት እስራኤላውያን ደግሞ ተከፍሎ ከተሰጣቸው ድርሻ ላይ የተወሰነውን ለሌዋውያኑ ሰጡ።—ዘኍ. 31:1-5, 25-30

ይሁንና የጦር አዛዦቹ በዚህ አልረኩም። ለሙሴ “እኛ አገልጋዮችህ በእጃችን ሥር ያሉትን ወታደሮች ቈጥረናል፤ አንድም የጐደለ የለም” አሉት። በመሆኑም ወርቅና የተለያዩ ጌጣ ጌጦችን ለይሖዋ መባ አድርገው ለመስጠት ወሰኑ። ለይሖዋ የሰጡት የወርቅ ጌጣ ጌጥ በአጠቃላይ ከ190 ኪሎ ግራም በላይ ይመዝን ነበር።—ዘኍ. 31:49-54

በዛሬው ጊዜም በርካታ ሰዎች ይሖዋ ላደረገላቸው ነገር ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ አመስጋኝነታቸውን ይገልጻሉ። ደግሞም እንዲህ ያለ አመስጋኝነት የሚያሳዩት የአምላክ አገልጋዮች ብቻ አይደሉም። በቦሎኛ፣ ጣሊያን በ2009 በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ልዑካንን ወደ ስታዲየም ሲያመላልሳቸው የነበረን አንድ የአውቶቡስ ሹፌር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሹፌሩ በእርጋታና በጥንቃቄ ያሽከረክር ስለነበር በአውቶቡሱ ላይ ተሳፍረው የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ምስጋናቸውን የሚገልጽ ካርድና የተወሰነ ጉርሻ እንዲሁም ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ሊሰጡት ፈለጉ። ሹፌሩም እንዲህ አላቸው፦ “ካርዱንና መጽሐፉን በደስታ እቀበላችኋለሁ፤ ገንዘቡን ግን ለምትሠሩት ሥራ እንድታውሉት መዋጮ ማድረግ እፈልጋለሁ። የይሖዋ ምሥክር ባልሆንም እንኳ የምታደርጉትን ነገር ሁሉ በፍቅር ተነሳስታችሁ እንደምታከናውኑ ስለተመለከትሁ ይህን መዋጮ ማድረግ እፈልጋለሁ።”

ይሖዋ ላደረገልህ ነገር አመስጋኝነትህን መግለጽ የምትችልበት አንዱ መንገድ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያከናውኑት ዓለም አቀፍ ሥራ መዋጮ ማድረግ ነው። (ማቴ. 24:14) አንዳንዶች መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች በሣጥኑ ውስጥ ተዘርዝረዋል።