በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወጣቶች—የእኩዮቻችሁን ተጽዕኖ ተቋቋሙ

እናንት ወጣቶች—የእኩዮቻችሁን ተጽዕኖ ተቋቋሙ

እናንት ወጣቶች—የእኩዮቻችሁን ተጽዕኖ ተቋቋሙ

“ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ  . . በጨው የተቀመመ ይሁን።”—ቆላ. 4:6

1, 2. በርካታ ወጣቶች ከሌሎች የተለየ አቋም መያዝን በተመለከተ ምን ይሰማቸዋል? ለምንስ?

“የእኩዮች ተጽዕኖ” የሚለውን አገላለጽ ከመስማትም አልፈህ በራስህ ሕይወት ተመልክተኸው ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። አንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ጊዜያት፣ ትክክል እንዳልሆነ የምታውቀውን ነገር እንድትፈጽም ግፊት ተደርጎብህ ያውቅ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምን ይሰማሃል? የ14 ዓመቱ ክሪስቶፈር እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ መሬት ተከፍታ ብትውጠኝ ብዬ እመኛለሁ፤ አሊያም አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች የተለየሁ ከመሆን ይልቅ እንደነሱ ብሆን ብዬ አስባለሁ።”

2 እኩዮችህ የሚያሳድሩብህ ጫና በጣም ያስጨንቅሃል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ ለምን ሊሆን ይችላል? በእኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስለምትፈልግ ይሆን? በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መፈለግ ያለ ነገር ነው። ትልልቅ ሰዎችም እንኳ በእኩዮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይፈልጋሉ። ወጣትም ሆነ አዋቂ ማንኛውም ሰው ቢሆን ሰዎች ሲያገሉት ደስ አይለውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ትክክል እንደሆነ ላመንክበት ነገር አቋም መውሰድህ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝልህ ሁልጊዜ ላይሆን ይችላል። ኢየሱስም እንኳ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ያም ቢሆን ምንጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል። አንዳንዶች ኢየሱስን የተከተሉት ከመሆኑም በላይ ደቀ መዛሙርቱ ለመሆን ችለዋል፤ ሌሎች ግን የአምላክን ልጅ በመናቅ ‘ሳያከብሩት’ ቀርተዋል።—ኢሳ. 53:3

እኩዮቻችሁን እንድትመስሉ የሚደረግባችሁ ግፊት—ምን ያህል ኃይል አለው?

3. እኩዮችህን መምሰልህ ስህተት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

3 አንዳንድ ጊዜ በእኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት ላለማጣት ስትል ብቻ እነሱን ለመምሰል ትፈተን ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ማድረግ ስህተት ነው። ክርስቲያኖች ‘እንደ ሕፃናት በማዕበል የሚነዱ’ መሆን የለባቸውም። (ኤፌ. 4:14) ትንንሽ ልጆች በሌሎች ተጽዕኖ በቀላሉ ሊሸነፉ ይችላሉ። አንተ ግን አዋቂ ሰው ወደ መሆን እየተሸጋገርህ ነው። በመሆኑም የይሖዋ መመሪያዎች ለአንተ የሚበጁ እንደሆኑ የምታምን ከሆነ የምታምንበትን ነገር ተግባራዊ ማድረግህ የጥበብ እርምጃ ነው። (ዘዳ. 10:12, 13) እንዲህ አለማድረግ ሕይወትህን ሌሎች እንዲቆጣጠሩት የመፍቀድ ያህል ይሆናል። እውነቱን ለመናገር፣ ሌሎች ጫና እንዲያደርጉብህ የምትፈቅድ ከሆነ እንደ አሻንጉሊት ይጫወቱብሃል።—2 ጴጥሮስ 2:19ን አንብብ።

4, 5. (ሀ) አሮን ለእኩዮች ተጽዕኖ የተሸነፈው እንዴት ነው? ከዚህስ ምን ትምህርት ታገኛለህ? (ለ) እኩዮችህ በአንተ ላይ ጫና ለማሳደር የትኞቹን ዘዴዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ?

4 የሙሴ ወንድም የሆነው አሮን በአንድ ወቅት ለሌሎች ተጽዕኖ ተሸንፎ ነበር። እስራኤላውያን ጣዖት እንዲሠራላቸው ሲወተውቱት ያሉትን አድርጎላቸዋል። አሮን ይህን ያደረገው ፈሪ ስለነበረ አይደለም። ከዚያ ቀደም ብሎ አሮን ከሙሴ ጋር በመሆን ኃያል ለነበረው ለግብፁ ፈርዖን የአምላክን መልእክት በድፍረት ተናግሮ ነበር። ሆኖም ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያን ጠንከር ያለ ግፊት ሲያደርጉበት በተጽዕኖው ተሸነፈ። ሌሎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምን ያህል ኃይለኛ ነው! አሮን በግብፅ ንጉሥ ፊት ከመቆም ይልቅ የእኩዮቹን ተጽዕኖ መቋቋም ከብዶት ነበር።—ዘፀ. 7:1, 2፤ 32:1-4

5 በአሮን ላይ ከደረሰው ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው የእኩዮች ተጽዕኖ የሚያጋጥማቸው ወጣቶች ወይም መጥፎ የሆነውን ነገር የማድረግ አዝማሚያ ያላቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም። አንተን ጨምሮ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎችም ጭምር የእኩዮች ተጽዕኖ ሊያጋጥማቸው ይችላል። እኩዮችህ መጥፎ ነገር እንድትፈጽም አንተ ላይ ጫና ለማሳደር ሲሉ ትክክል ያልሆነ ነገር እንድታደርግ ሊገዳደሩህ፣ ስለ አንተ እውነት ያልሆነ ነገር ሊናገሩ አሊያም ሊያፌዙብህ አልፎ ተርፎም ሊሰድቡህ ይችላሉ። የእኩዮች ተጽዕኖ በምንም መልኩ ቢመጣ ጫናውን ተቋቁሞ ማለፍ ከባድ ነው። በእኩዮች ተጽዕኖ ላለመሸነፍ ልትወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ስለምታምንበት ነገር እርግጠኛ መሆን ነው።

“ማንነታችሁን ለማወቅ ራሳችሁን ዘወትር ፈትኑ”

6, 7. (ሀ) የምታምንባቸው ነገሮች ትክክል ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆንህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) እምነትህን ለማጠናከር የትኞቹን ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅ ትችላለህ?

6 የእኩዮችን ተጽዕኖ ለመቋቋም እንድትችል የሚረዳህ የመጀመሪያው እርምጃ የምታምንባቸው ነገሮችና የምትመራባቸው መሥፈርቶች ትክክል ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን ነው። (2 ቆሮንቶስ 13:5ን አንብብ።) እንዲህ ማድረግህ በተፈጥሮህ ዓይናፋር ብትሆንም ድፍረት እንድታገኝ ይረዳሃል። (2 ጢሞ. 1:7, 8) አንድ ሰው በተፈጥሮው ደፋር ቢሆንም እንኳ ከልቡ ለማያምንበት ነገር አቋም መውሰድ ከባድ ሊሆንበት ይችላል። ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርከው ነገር እውነት መሆኑን ለምን ራስህ አታረጋግጥም? መሠረታዊ ከሆኑት ትምህርቶች ጀምር። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ መኖሩን ታምናለህ፤ ሌሎችም አምላክ መኖሩን እንዲያምኑ ያደረጓቸውን ምክንያቶች ሲገልጹ ሰምተሃል። ሆኖም ‘አምላክ መኖሩን እኔን ያሳመነኝ ምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ የምታነሳበት ዓላማ ጥርጣሬ እንዲያድርብህ ለማድረግ ሳይሆን እምነትህን ለማጠናከር ነው። በተመሳሳይም ‘ቅዱሳን መጻሕፍት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ መሆናቸውን እንዴት አውቃለሁ?’ እያልህ ራስህን ጠይቅ። (2 ጢሞ. 3:16) ‘አሁን ያለነው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ መሆኑን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?’ (2 ጢሞ. 3:1-5) ‘ይሖዋ ያወጣቸው መሥፈርቶች እንደሚጠቅሙኝ እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?’—ኢሳ. 48:17, 18

7 ምናልባት መልስ ባላገኝስ ብለህ በመፍራት እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎችን ከማንሳት ወደኋላ ትል ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ብሎ ማሰብ በመኪና ውስጥ ያለው የነዳጅ መጠን ጠቋሚ መሣሪያ ነዳጁ “ባዶ” መሆኑን እያመለከተ እንዳይሆን በመፍራት መሣሪያውን ከማየት ወደኋላ እንደ ማለት ይቆጠራል። መኪናው ነዳጅ ከሌለው መሙላት እንድትችል የነዳጅ መጠን አመልካቹን መመልከትህ አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይም ከምታምንባቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ እርግጠኛ ያልሆንክባቸውን ነገሮች ለይተህ ማወቁና እምነትህን ማጠናከሩ የጥበብ እርምጃ ነው።—ሥራ 17:11

8. አምላክ ከዝሙት እንድንርቅ የሰጠንን ትእዛዝ መከተልህ የጥበብ አካሄድ መሆኑን ራስህን ማሳመን የምትችለው እንዴት ነው? አብራራ።

8 አንድ ምሳሌ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። ‘ይህን መመሪያ መከተሌ የጥበብ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ከዚያም እኩዮችህ እንዲህ ያለውን ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚያነሳሷቸውን ምክንያቶች ለማሰብ ሞክር። እንዲሁም ዝሙት የመፈጸም ልማድ ያለው ሰው “በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው” የተባለው ለምን እንደሆነ አስብ። (1 ቆሮ. 6:18) በእነዚህ ነጥቦች ላይ ቆም ብለህ ካሰብክ በኋላ እንደሚከተለው በማለት ራስህን ጠይቅ፦ ‘ከሁሉ የተሻለው አካሄድ የትኛው ነው? የፆታ ብልግና ያን ያህል መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባ ነገር ነው?’ እንዲሁም በነገሩ ላይ ይበልጥ ማሰብ እንድትችል ‘የፆታ ብልግና ብፈጽም ምን ይሰማኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። የፆታ ብልግና ብትፈጽም ለጊዜው በአንዳንድ እኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት ታገኝ ይሆናል፤ ይሁንና በኋላ ላይ ከወላጆችህ ወይም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ስትሆን ምን የሚሰማህ ይመስልሃል? ወደ አምላክ ለመጸለይ ብትፈልግስ ምን ይሰማሃል? አብረውህ የሚማሩትን ልጆች ለማስደሰት ስትል በአምላክ ፊት ያለህን ንጹሕ አቋም ማጣት ትፈልጋለህ?

9, 10. ስለምታምንባቸው ነገሮች እርግጠኛ መሆንህ እኩዮችህ ተጽዕኖ ሲያሳድሩብህ ጫናውን በልበ ሙሉነት ለመጋፈጥ የሚረዳህ እንዴት ነው?

9 በጉርምስና ዕድሜ ላይ የምትገኝ ከሆነ ‘የማሰብ ችሎታህ’ በእጅጉ በሚዳብርበት ወቅት ላይ ነህ። (ሮም 12:1, 2ን አንብብ።) በዚህ ጊዜ፣ የይሖዋ ምሥክር መሆን ለአንተ ምን ትርጉም እንዳለው በቁም ነገር ማሰብህ ጠቃሚ ነው። እንዲህ ማድረግህ ስለምታምንባቸው ነገሮች እርግጠኛ እንድትሆን ይረዳሃል። ይህ ደግሞ እኩዮችህ ጫና ሲያሳድሩብህ ሳታንገራግር በልበ ሙሉነት መልስ ለመስጠት ያስችልሃል። እንዲህ በማድረግ እንደሚከተለው በማለት የተናገረችውን ወጣት ክርስቲያን ስሜት ለመጋራት ትችላለህ፤ እንዲህ ብላለች፦ “ለማምንበት ነገር አቋም ስወስድ ሌሎች ስለ ማንነቴ እንዲያውቁ እያደረግሁ ነው። የይሖዋ ምሥክር መሆን ለእኔ የአንድ ሃይማኖት አባል ከመሆን ያለፈ ትርጉም አለው። አስተሳሰቤ፣ ግቤ፣ የሥነ ምግባር አቋሜና መላው ሕይወቴ በእምነቴ ላይ የተመሠረተ ነው።”

10 በእርግጥም ትክክል እንደሆነ ለምታምንበት ነገር አቋም መውሰድ ጥረት ይጠይቃል። (ሉቃስ 13:24) በመሆኑም ‘እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጉ ያን ያህል አስፈላጊ ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይሁንና ልትዘነጋው የማይገባ ነገር አለ፦ ሁኔታህ በእምነትህ እርግጠኛ እንዳልሆንህ ወይም እንደምታፍር የሚያሳይ ከሆነ ሌሎች ይህን ማስተዋላቸው ስለማይቀር ይበልጥ ጫና ሊያሳድሩብህ ይችላሉ። በሌላ በኩል ግን በልበ ሙሉነት መልስ ከሰጠህ እኩዮችህ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ካሰብከው ይበልጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያቆማል!—ከ⁠ሉቃስ 4:12, 13 ጋር አወዳድር።

‘የምትሰጠውን መልስ አመዛዝን’

11. እኩዮችህ ለሚያሳድሩብህ ተጽዕኖ አስቀድመህ መዘጋጀትህ ምን ጥቅም አለው?

11 የእኩዮችን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚረዳው ሌላው ጠቃሚ እርምጃ ዝግጅት ነው። (ምሳሌ 15:28ን አንብብ።) ዝግጁ መሆን ሲባል ምን ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥምህ እንደሚችል አስቀድመህ ማሰብ ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ፣ ሊገጥምህ የሚችለውን ችግር አስቀድመህ ማሰብህ እኩዮችህ የሚያሳድሩብህን ተጽዕኖ ለመወጣት ያስችልሃል። ለምሳሌ አብረውህ የሚማሩ ልጆች ወደ አንተ አቅጣጫ እየመጡ ነው እንበል፤ ሲጋራ እያጨሱ እንደሆነ ይታይሃል። እነዚህ ልጆች እንድታጨስ የሚጋብዙህ ይመስልሃል? ሊያጋጥምህ የሚችለውን ሁኔታ አስቀድመህ በማሰብ ምን ማድረግ ትችላለህ? ምሳሌ 22:3 “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል። በሌላ አቅጣጫ በመሄድ ከልጆቹ ጋር አለመገናኘት ትችላለህ። እንዲህ ስላደረግህ ፈሪ እንደሆንክ ሊሰማህ አይገባም፤ እንዲያውም ይህ የጥበብ እርምጃ ነው።

12. የእኩዮች ተጽዕኖ ሲያጋጥም መልስ መስጠት የሚቻልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

12 ይሁንና ወጣቶች ሊሸሹት የማይችሉት ሁኔታ ቢያጋጥማቸውስ? ለምሳሌ ያህል፣ አንዲትን ወጣት እኩዮቿ “አሁንም ድንግል ነኝ እንዳትይ ብቻ” ቢሏትስ? ከሁሉ የተሻለው ነገር በቆላስይስ 4:6 ላይ የሚገኘውን “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለውና በጨው የተቀመመ ይሁን” የሚለውን ምክር መከተል ነው። ጥቅሱ እንደሚያሳየው ይህች ወጣት የምትሰጠው መልስ እንደ ሁኔታው ይለያያል። ድንግል መሆኗን በተመለከተ ለተሰነዘረው ሐሳብ መልስ ስትሰጥ መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ ላያስፈልጋት ይችላል። ምናልባትም ጠንከር ያለ አጭር መልስ መስጠት ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ “አዎን፣ ነኝ” ብላ መመለስ አሊያም “ይህ የግል ጉዳዬ ስለሆነ አንቺን አይመለከትሽም” ማለት ትችላለች።

13. እኩዮችህ በፌዝ መልክ ለሚሰነዝሩት ሐሳብ መልስ በምትሰጥበት ጊዜ አስተዋይ መሆንህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ኢየሱስ ሰፋ ያለ ማብራሪያ መስጠት ምንም እንደማይፈይድ ሲሰማው ብዙውን ጊዜ አጠር ያለ መልስ ይሰጥ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ሄሮድስ ጥያቄ ሲያቀርብለት ዝምታን መርጧል። (ሉቃስ 23:8, 9) ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች ሲቀርቡልን ብዙውን ጊዜ የተሻለው ነገር መልስ አለመስጠት ነው። (ምሳሌ 26:4፤ መክ. 3:1, 7) በሌላ በኩል ግን አንድ ሰው መጀመሪያ ላይ ቢያፌዝብህም ስለምታምንባቸው ነገሮች (ለምሳሌ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር) ለማወቅ ከልቡ እንደሚፈልግ ታስተውል ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:4) በዚህ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው አቋምህ ሰፋ ያለ ማብራሪያ መስጠት ሊያስፈልግህ ይችላል። ፍርሃት ይህን ከማድረግ እንዲያግድህ አትፍቀድ። “መልስ ለመስጠት” ዘወትር ዝግጁ ሁን።—1 ጴጥ. 3:15

14. አንዳንድ ጊዜ የሚደርስብህን ተጽዕኖ በዘዴ ወደ እኩዮችህ ማዞር የምትችለው እንዴት ነው?

14 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ተጽዕኖውን ወደ እኩዮችህ ማዞር ትችላለህ። ይሁንና ይህን የምታደርገው በዘዴ መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል፣ አብሮህ የሚማር ልጅ ሲጋራ እንድታጨስ ጫና ቢያደርግብህ “አይ አልፈልግም” ካልክ በኋላ “አንተም ማጨስህ አስገርሞኛል! ብልጥ ትመስለኝ ነበር!” ልትለው ትችላለህ። ተጽዕኖውን ወደ ልጁ እንዴት ማዞር እንደሚቻል አስተዋልህ? የማታጨሰው ለምን እንደሆነ ማብራራትህ ቀርቶ እሱ ራሱ የሚያጨሰው ለምን እንደሆነ እንዲያስብ አደረግኸው ማለት ነው። *

15. እኩዮችህ ተጽዕኖ ሲያሳድሩብህ ትተሃቸው መሄድ የሚኖርብህ ምን ጊዜ ነው? ለምንስ?

15 ይሁንና ከላይ የተዘረዘሩትን እርምጃዎች ወስደህም እኩዮችህ ተጽዕኖ ማድረጋቸውን ቢቀጥሉስ? በዚህ ጊዜ የተሻለው እርምጃ ትተሃቸው መሄድ ነው። አብረሃቸው በቆየህ መጠን በተጽዕኖው የመሸነፍህ አጋጣሚ እየሰፋ ይሄዳል። ስለዚህ ጥለሃቸው ሂድ። እንዲህ በማድረግህ እንደተሸነፍክ ሊሰማህ አይገባም። እንዲያውም ሁኔታውን በሚገባ ተወጥተኸዋል። እኩዮችህ እንደ አሻንጉሊት እንዲጫወቱብህ አልፈቀድህም፤ እንዲሁም የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝተሃል!—ምሳሌ 27:11

‘ወደ ትርፍ የሚያመራ’ ዕቅድ ይኑርህ

16. ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚናገሩ አንዳንድ ወጣቶች በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉት እንዴት ነው?

16 አንዳንድ ጊዜ ተገቢ ባልሆነ ተግባር እንድትካፈል ተጽዕኖ የሚያደርጉብህ የይሖዋ አገልጋዮች ነን የሚሉ ወጣቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ እንደነዚህ ያሉ ወጣቶች ባዘጋጁት ግብዣ ላይ ብትገኝና ግብዣውን የሚቆጣጠር አንድም ትልቅ ሰው እንደሌለ ብታስተውልስ? ወይም ደግሞ በግብዣው ላይ መጠጥ በገፍ ቢቀርብና አንዳንዶች ያለ ገደብ መጠጣት ቢጀምሩስ? በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነው ሕሊናህ መመራትን የሚጠይቁ በርካታ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። አንዲት ወጣት ክርስቲያን እንዲህ ብላለች፦ “የሚታየው ፊልም ጸያፍ አነጋገሮች የሞሉበት በመሆኑ እኔና እህቴ ፊልም ቤቱን ለቀን ወጣን። አብረውን የገቡት ግን ለመቆየት መረጡ። ወላጆቻችን እንዲህ ዓይነት እርምጃ በመውሰዳችን አደነቁን። ይሁንና ፊልም ቤት ውስጥ የቀሩት ወጣቶች እንዳሳጣናቸው ስለተሰማቸው ተናደዱ።”

17. በግብዣ ላይ በምትገኝበት ጊዜ የአምላክን መመሪያዎች ማክበር እንድትችል የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?

17 ከላይ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነው ሕሊናህ መመራትህ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲያጋጥምህ ሊያደርግ ይችላል። ያም ቢሆን ትክክል እንደሆነ የምታምንበትን ነገር ማድረግ ይኖርብሃል። ሊያጋጥምህ የሚችለውን ሁኔታ በማሰብ አስቀድመህ ተዘጋጅ። ወደ አንድ ግብዣ ልትሄድ ስትነሳ፣ ነገሮች እንደጠበቅኸው ሳይሆኑ ቢቀሩ እንዴት ግብዣውን ትተህ መውጣት እንደምትችል አስብ። አንዳንድ ወጣቶች ግብዣው ላይ ያለው ሁኔታ ካላማራቸው ወላጆቻቸው መጥተው እንዲወስዷቸው ስልክ እንደሚደውሉ አስቀድመው ከወላጆቻቸው ጋር ይነጋገራሉ። (መዝ. 26:4, 5) እንዲህ ያለው “ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል።”—ምሳሌ 21:5

“በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ”

18, 19. (ሀ) ይሖዋ ደስተኛ እንድትሆን እንደሚፈልግ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው? (ለ) የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ ስለሚቋቋሙ ወጣቶች አምላክ ምን ይሰማዋል?

18 ይሖዋ የፈጠረህ በሕይወት እንድትደሰት አድርጎ ስለሆነ ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። (መክብብ 11:9ን አንብብ።) በርካታ እኩዮችህ የሚያገኙት ‘በኃጢአት የሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ’ ብቻ መሆኑን አትዘንጋ። (ዕብ. 11:25) እውነተኛው አምላክ ከዚህ የላቀ ነገር እንድታገኝ ይፈልጋል። ለዘላለም ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። በመሆኑም አምላክ እንደማይወደው የምታውቀውን ነገር እንድትፈጽም በምትፈተንበት ጊዜ ይሖዋ ያወጣቸውን መመሪያዎች መታዘዝ ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ለአንተው መሆኑን አስታውስ።

19 በወጣትነትህ ወቅት በእኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት ብታገኝም ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ አብዛኞቹ ስምህን እንኳ ላያስታውሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልግሃል። ከዚህ በተቃራኒ ግን የእኩዮችህን ተጽዕኖ ስትቋቋም ይሖዋ ጥረትህን የሚመለከት ከመሆኑም ሌላ አንተንም ሆነ ያሳየኸውን ታማኝነት ፈጽሞ አይረሳም። ይሖዋ ‘የሰማይን መስኮት ይከፍትልሃል፤ እንዲሁም የተትረፈረፈ በረከትን ማስቀመጫ እስክታጣ ድረስ ያፈስልሃል።’ (ሚል. 3:10) ከዚህም በተጨማሪ የሚደርስብህን ተጽዕኖ ለመቋቋም አቅም እንደሌለህ በሚሰማህ ጊዜ በአቋምህ መጽናት እንድትችል አንተን ለማጠናከር ቅዱስ መንፈሱን በልግስና ይሰጥሃል። አዎን፣ ይሖዋ የእኩዮችህን ተጽዕኖ መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

ታስታውሳለህ?

• የእኩዮች ተጽዕኖ ምን ያህል ኃይል አለው?

• ስለምታምንበት ነገር እርግጠኛ መሆንህ የእኩዮችን ተጽዕኖ ለመቋቋም ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

• የእኩዮችን ተጽዕኖ ለመቋቋም መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

• ይሖዋ ታማኝነትህን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እንዴት ማወቅ ትችላለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሮን የወርቁን ጥጃ ለመሥራት የተስማማው ለምንድን ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዝግጁ ሁን—ምን እንደምትል አስቀድመህ ወስን