በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈስ ቅዱስ ማንኛውንም መከራ ለማሸነፍ ኃይል ይሰጠናል

መንፈስ ቅዱስ ማንኛውንም መከራ ለማሸነፍ ኃይል ይሰጠናል

መንፈስ ቅዱስ ማንኛውንም መከራ ለማሸነፍ ኃይል ይሰጠናል

“ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ።”—ፊልጵ. 4:13

1. የይሖዋ ሕዝቦች ብዙ መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ መከራ መድረሱ አዲስ ነገር አይደለም። አንዳንድ መከራዎች የሚደርሱብን ፍጹማን ስላልሆንንና በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስለምንኖር ነው። የሌሎች መከራዎች መንስኤ ደግሞ አምላክን በሚያገለግሉትና በማያገለግሉት መካከል ያለው ጠላትነት ነው። (ዘፍ. 3:15) አምላክ ከሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ ታማኝ አገልጋዮቹ ስደትን፣ የእኩዮችን ተጽዕኖና ሌላ ማንኛውንም ዓይነት መከራ እንዲቋቋሙ ረድቷቸዋል። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንዲህ ያሉ ነገሮችን መቋቋም እንድንችል ኃይል ይሰጠናል።

ስደትን ለመቋቋም ይረዳናል

2. ስደት ዓላማው ምንድን ነው? በምን ዓይነት መንገድስ ሊመጣ ይችላል?

2 ስደት ሲባል ሰዎች በእምነታቸው ምክንያት ሆን ተብሎ የሚደርስባቸውን እንግልት ወይም ጉዳት ያመለክታል። ዓላማውም እምነቱን ጨርሶ ማጥፋት፣ ስርጭቱን መግታት ወይም አማኞቹ ታማኝነታቸውን እንዲያጎድሉ ማድረግ ነው። ስደት በቀጥታ አሊያም በተዘዋዋሪ መንገድ ሊመጣ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን የሚያመጣውን ስደት ደቦል አንበሳና እፉኝት ከሚሰነዝሩት ጥቃት ጋር ያመሳስለዋል።—መዝሙር 91:13ን አንብብ።

3. ስደት አንበሳና እፉኝት ከሚሰነዝሩት ጥቃት ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው?

3 ብዙ ጊዜ ሰይጣን ምሕረት የለሽ እንደሆነ አንበሳ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ዓመፅ በማነሳሳት አሊያም እንዲታሰሩ ወይም እገዳ እንዲጣልባቸው በማድረግ ፊት ለፊት የሆነ ቀጥተኛ ጥቃት ይሰነዝራል። (መዝ. 94:20) በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በተመለከተ የዓመት መጽሐፍ ላይ የሚወጡ ሪፖርቶች ሰይጣን እንዲህ ያሉ ዘዴዎችን እንደሚጠቀም የሚያሳዩ በርካታ ዘገባዎችን ይዘዋል። አንዳንድ ጊዜ በቀሳውስት ወይም በአክራሪ ፖለቲከኞች ቆስቋሽነት ረብሻ የሚያስነሱ ሰዎች በብዙ ቦታዎች የአምላክን ሕዝቦች አንገላተዋል። አንበሳ እንደሚሰነዝራቸው ያሉ ፊት ለፊት የሚመጡ እንደነዚህ ዓይነት ጥቃቶች አንዳንዶች ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ አድርገዋቸዋል። በተጨማሪም ዲያብሎስ የሰዎችን አእምሮ ለመመረዝና ተታልለው የእሱን ፈቃድ እንዲፈጽሙ ለማድረግ ሲል እንደ እፉኝት ስውር የሆኑ ጥቃቶችን ይሰነዝራል። እንዲህ ያለው ጥቃት መንፈሳዊነታችንን ለማዳከም ወይም ለመበከል የታቀደ ነው። ያም ሆኖ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት ሁለቱንም ዓይነት ጥቃቶች መቋቋም እንችላለን።

4, 5. ለስደት ለመዘጋጀት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው? እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

4 ለሚደርስብን ስደት ራሳችንን ለማዘጋጀት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ወደፊት ሊያጋጥሙን ይችላሉ ብለን በምናስባቸው ሁኔታዎች ላይ ማውጠንጠን አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ምን ዓይነት ስደት ሊያጋጥመን እንደሚችል ማወቅ አንችልም፤ ምናልባትም ጨርሶ ላይደርስብን በሚችል ነገር ላይ መጨነቅ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ይሁንና ማድረግ የምንችለው ሌላ ነገር አለ። ስደትን በጽናት ከተቋቋሙት ክርስቲያኖች መካከል አብዛኞቹ ይህን ለማድረግ የረዳቸው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው በሚገኙ ታማኝነታቸውን በጠበቁ የይሖዋ አገልጋዮች የሕይወት ታሪክ እንዲሁም በኢየሱስ ትምህርትና ምሳሌ ላይ ማሰላሰላቸው ነው። እንዲህ ማድረጋቸው ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር ጥልቅ እየሆነ እንዲሄድ አስችሏቸዋል። እንዲህ ያለው ፍቅር ደግሞ የደረሰባቸውን ማንኛውንም መከራ ለመቋቋም ረድቷቸዋል።

5 በማላዊ የሚኖሩ የሁለት እህቶቻችንን ምሳሌ እንመልከት። ረብሸኞች እነዚህን እህቶች የፖለቲካ ፓርቲ ካርድ እንዲገዙ ለማስገደድ ሲሉ የደበደቧቸውና ልብሳቸውን የገፈፏቸው ከመሆኑም ሌላ በፆታ እንደሚያስነውሯቸው ዛቱባቸው። ረብሸኞቹ፣ የቤቴል ቤተሰብ አባላትም እንኳ የፓርቲ ካርድ እንደወሰዱ በመናገር ዋሿቸው። ታዲያ እህቶች በዚህ ጊዜ ምን ምላሽ ሰጡ? “እኛ የምናገለግለው ይሖዋ አምላክን ብቻ ነው። በመሆኑም በቅርንጫፍ ቢሮ ያሉ ወንድሞች ካርዱን ቢገዙ ይህ ለእኛ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። ብትገድሉንም እንኳ አቋማችንን አናላላም!” አሏቸው። እህቶች በዚህ መንገድ አቋማቸውን በድፍረት ከገለጹ በኋላ ተለቀቁ።

6, 7. ይሖዋ ስደትን እንዲቋቋሙ ለአገልጋዮቹ ኃይል የሚሰጣቸው እንዴት ነው?

6 ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ የሚገኙ ክርስቲያኖች የእውነትን መልእክት ሲቀበሉ “ብዙ መከራ” ቢደርስባቸውም ‘በመንፈስ ቅዱስ ደስታ’ እንዳገኙ ገልጿል። (1 ተሰ. 1:6) በእርግጥም ስደትን በጽናት የተወጡ ጥንትም ሆነ ዛሬ ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች፣ የሚደርስባቸው መከራ በጣም ከባድ በሆነበት ጊዜ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆነውን ውስጣዊ ሰላም እንዳገኙ ተናግረዋል። (ገላ. 5:22) ይህ ሰላም ደግሞ ልባቸውንና አእምሯቸውን ጠብቆላቸዋል። በእርግጥም ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ የሚደርስባቸውን መከራ እንዲቋቋሙና ችግር ሲያጋጥማቸው የጥበብ እርምጃ እንዲወስዱ ለመርዳት በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ኃይል ይሰጣቸዋል። *

7 አንዳንዶች፣ የአምላክ ሕዝቦች መራር ስደት በደረሰባቸው ጊዜም እንኳ ታማኝነታቸውን ለመጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት ሲመለከቱ ተደንቀዋል። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ከሰው በላይ በሆነ ኃይል የተሞሉ ይመስሉ ነበር፤ ደግሞም እንዲህ ያለ ኃይል ተሰጥቷቸው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል፦ “ለክርስቶስ ስም ስትሉ ብትነቀፉ ደስተኞች ናችሁ፤ ምክንያቱም የክብር መንፈስ እንዲያውም የአምላክ መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋል።” (1 ጴጥ. 4:14) የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች በመከተላችን ምክንያት መሰደዳችን የአምላክ ሞገስ እንዳለን ያረጋግጣል። (ማቴ. 5:10-12፤ ዮሐ. 15:20) የይሖዋ በረከት ከእኛ ጋር እንደሆነ ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው!

የእኩዮችን ተጽዕኖ ለመቋቋም ይረዳናል

8. (ሀ) ኢያሱና ካሌብ የእኩዮችን ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው? (ለ) ኢያሱና ካሌብ ከተዉት ምሳሌ ምን መማር እንችላለን?

8 ክርስቲያኖች ሊቋቋሙት የሚገባው ይበልጥ ስውር የሆነው ስደት የእኩዮች ተጽዕኖ ነው። ይሁንና የይሖዋ መንፈስ ከዓለም መንፈስ ይበልጥ ኃያል በመሆኑ በእኛ ላይ የሚያፌዙ፣ የሐሰት ወሬ የሚያሰራጩ ወይም የእነሱን መንገድ እንድንከተል ጫና ሊያደርጉብን የሚሞክሩ ሰዎችን ተጽዕኖ መቋቋም እንችላለን። ኢያሱንና ካሌብን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ የከነዓንን ምድር እንዲሰልሉ ከተላኩት ከሌሎቹ አሥር ሰላዮች የተለየ አቋም እንዲይዙ ያደረጋቸው ምንድን ነው? የአምላክን መንፈስ አመራር ስለተከተሉ የተለየ “መንፈስ” ወይም አመለካከት ነበራቸው።—ዘኍልቁ 13:30ን እና ዘኍልቁ 14:6-10, 24ን አንብብ።

9. ክርስቲያኖች ከብዙኃኑ የተለዩ መሆን ሊያስፈራቸው የማይገባው ለምንድን ነው?

9 በተመሳሳይም የኢየሱስ ሐዋርያት፣ በብዙዎች ዘንድ የእውነተኛ ሃይማኖት አስተማሪዎች እንደሆኑ ተደርገው ክብር ከሚሰጣቸው ሰዎች ይልቅ አምላክን እንዲታዘዙ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቷቸዋል። (ሥራ 4:21, 31፤ 5:29, 32) አብዛኞቹ ሰዎች ግጭት ወይም ጥል እንዳይፈጠር ሲሉ ብዙኃኑን መከተል ይመርጣሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ትክክለኛ እንደሆነ የሚያውቁትን ነገር ደግፈው መቆም ይኖርባቸዋል። እንደዚያም ሆኖ የአምላክ መንፈስ ብርታት ስለሚሰጣቸው ከብዙኃኑ የተለዩ መሆን አያስፈራቸውም። (2 ጢሞ. 1:7) በእኩዮች ተጽዕኖ ላለመሸነፍ ልንጠነቀቅባቸው ከሚገቡን አቅጣጫዎች መካከል እስቲ አንዱን እንመልከት።

10. አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ?

10 አንዳንድ ወጣቶች፣ ጓደኛቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ተግባር እንደፈጸመ በሚያውቁበት ጊዜ አጣብቂኝ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ጓደኛቸው መንፈሳዊ እርዳታ እንዲያገኝ ሲሉ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች ቢናገሩ ከእሱ ጋር ሚስጥረኞች መሆናቸው እንደሚቀር ይሰማቸው ይሆናል፤ በመሆኑም ጉዳዩን ባለመናገር የተሳሳተ ታማኝነት ያሳያሉ። መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ግለሰብ ራሱም ጓደኞቹ ኃጢአቱን እንዲደብቁለት ጫና ሊያሳድርባቸው ይችላል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነት ችግር የሚታየው በወጣቶች ላይ ብቻ አይደለም። አንዳንድ አዋቂዎችም ጓደኛቸው ወይም የቤተሰባቸው አባል የፈጸመውን መጥፎ ድርጊት ለጉባኤ ሽማግሌዎች መንገር ይከብዳቸው ይሆናል። ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን የእኩዮች ተጽዕኖ መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?

11, 12. አንድ የጉባኤ አባል የፈጸመውን መጥፎ ድርጊት እንዳትናገርበት ቢጠይቅህ ትክክለኛው አካሄድ ምንድን ነው? ለምንስ?

11 እስቲ ይህን ሁኔታ ለማሰብ ሞክር። ዮፍታሔ የተባለ አንድ ወጣት፣ በጉባኤ ውስጥ ያለ ዮናስ የሚባል ጓደኛው የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ እንዳለው አወቀ እንበል። ዮፍታሔ፣ ዮናስን ያነጋገረው ሲሆን ሁኔታው በጣም እንዳሳሰበው ገለጸለት። ይሁንና ዮናስ ጓደኛው የነገረውን ነገር ከመጤፍ አልቆጠረውም። ዮፍታሔ፣ ድርጊቱን ለሽማግሌዎች እንዲናገር ዮናስን ቢያሳስበውም እሱ ግን “እውነት ጓደኛዬ ከሆንክ ሚስጥሬን ልታወጣብኝ አይገባም” ይለዋል። በዚህ ጊዜ ዮፍታሔ ጓደኝነታቸውን ላለማጣት ሲል ዝም ማለት ይኖርበታል? “ደግሞስ ዮናስ ድርጊቱን ሽምጥጥ አድርጎ ቢክድ የትኛው ሽማግሌ ነው እኔን የሚያምነኝ?” ብሎ ሊያስብ ይችላል። በሌላ በኩል ግን ዮፍታሔ ስለ ጉዳዩ ሳይናገር ቢቀር የዮናስ ሁኔታ እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ አይሄድም። እንዲያውም ዮናስ ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ሊያጣ ይችላል። እንግዲያው ዮፍታሔ “ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል” የሚለውን ጥቅስ ማስታወስ ይኖርበታል። (ምሳሌ 29:25) ዮፍታሔ ሌላስ ምን ማድረግ ይችላል? ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ወደ ዮናስ በመቅረብ ችግሩን አንስቶ በግልጽ ሊያወያየው ይችል ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ማድረግ ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም ዮፍታሔ ጉዳዩን በድጋሚ ሲያነሳው ዮናስ ስለ ችግሩ ለመወያየት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ዮናስ ሽማግሌዎችን እንዲያነጋግር ዮፍታሔ በድጋሚ ሊያበረታታውና በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ይህን ካላደረገ እሱ ራሱ እንደሚናገርበት ሊገልጽለት ይገባል።—ዘሌ. 5:1

12 እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ጓደኛህ እሱን ለመርዳት በምታደርገው ጥረት መጀመሪያ ላይደሰት ይችላል። ውሎ አድሮ ግን ያደረግከው ነገር ለእሱ በማሰብ እንደሆነ ይረዳ ይሆናል። መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ግለሰብ የሚሰጠውን እርዳታ ከተቀበለ ላሳየኸው ድፍረትና ታማኝነት ዕድሜ ልኩን ሲያመሰግንህ ይኖራል። በሌላ በኩል ግን ተበሳጭቶ የሚርቅህ ከሆነ ድሮውንስ ቢሆን እንዲህ ያለ ጓደኛ ይበጅሃል? ምንጊዜም ቢሆን ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ከሁሉ የላቀውን ወዳጃችንን ይሖዋን ማስደሰት ነው። ይሖዋን ካስቀደምን እሱን የሚወዱ ሰዎች በታማኝነታችን የሚያከብሩን ከመሆኑም ሌላ እውነተኛ ጓደኞች ይሆኑናል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ዲያብሎስ ስፍራ እንዲያገኝ ፈጽሞ ልንፈቅድ አይገባም። አለበለዚያ የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ እናሳዝናለን። በሌላ በኩል ደግሞ የክርስቲያን ጉባኤን ንጽሕና ለመጠበቅ የምንጥር ከሆነ ከዚህ መንፈስ ጋር ተስማምተን እንኖራለን።—ኤፌ. 4:27, 30

ማንኛውንም ዓይነት መከራ በጽናት ለመቋቋም ኃይል ይሰጠናል

13. የይሖዋ ሕዝቦች ምን ዓይነት መከራዎች ያጋጥሟቸዋል? እንዲህ ያሉ መከራዎች የበዙትስ ለምንድን ነው?

13 መከራ በተለያየ መልኩ ሊመጣ ይችላል፤ ሀብትና ንብረትን ማጣት፣ ከሥራ መፈናቀል፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣትና የጤና መቃወስ ጥቂቶቹ ናቸው። የምንኖረው ‘በዓይነቱ ልዩ በሆነ ዘመን’ ውስጥ በመሆኑ ይዋል ይደር እንጂ ሁላችንም በሆነ መልኩ መከራ ሊደርስብን እንደሚችል የታወቀ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን መርበትበት አይኖርብንም። መንፈስ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት መከራ መቋቋም እንድንችል ኃይል ይሰጠናል።

14. ኢዮብ የደረሱበትን መከራዎች በጽናት መቋቋም እንዲችል ኃይል የሰጠው ምንድን ነው?

14 ኢዮብ ተደራራቢ መከራዎች አጋጥመውት ነበር። ሀብት ንብረቱን አጥቷል፣ ልጆቹን በሞት ተነጥቋል፣ ጓደኞቹ ርቀውታል፣ ጤንነቱ ተቃውሷል፤ ሌላው ቀርቶ ሚስቱ በይሖዋ ላይ እምነት አጥታ ነበር። (ኢዮብ 1:13-19፤ 2:7-9) ይሁንና ኢዮብ ኤሊሁን የመሰለ እውነተኛ አጽናኝ አግኝቷል። ኤሊሁ የሰጠው ማበረታቻና ከይሖዋ ያገኘው ምክር “ኢዮብ ሆይ፤ ይህን ስማ፤ ቆም ብለህ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ዐስብ” በሚለው ሐሳብ ጠቅለል ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። (ኢዮብ 37:14) ኢዮብ የደረሰበትን መከራ ተቋቁሞ እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? እኛስ መከራ ሲደርስብን እንድንጸና ምን ሊረዳን ይችላል? መንፈስ ቅዱስና የይሖዋ ኃይል የሚገለጥባቸውን የተለያዩ መንገዶች ማስታወስና በእነዚህ ላይ ማሰላሰል ለመጽናት ይረዳናል። (ኢዮብ 38:1-41፤ 42:1, 2) አምላክ ስለ እኛ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብ በራሳችን ሕይወት የተመለከትንባቸውን አጋጣሚዎች እናስታውስ ይሆናል። ይሖዋ አሁንም ቢሆን ስለ እኛ ያስባል።

15. ሐዋርያው ጳውሎስ መከራዎችን በጽናት ለመወጣት ብርታት ያገኘው ከየት ነው?

15 ሐዋርያው ጳውሎስ በእምነቱ ምክንያት ያጋጠሙትን ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ብዙ መከራዎች በጽናት ተቋቁሟል። (2 ቆሮ. 11:23-28) ተረጋግቶና ሚዛኑን ሳይስት እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲወጣ የረዳው ምንድን ነው? ጸሎትና በይሖዋ መታመን ነው። ጳውሎስ ሰማዕት ሆኖ ከመሞቱ ቀደም ብሎ በነበረው የፈተና ወቅት እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፦ “የስብከቱ ሥራ በእኔ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸምና ሕዝቦች ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ አጠገቤ ቆሞ ኃይል ሰጠኝ፤ ከአንበሳ አፍም ዳንኩ።” (2 ጢሞ. 4:17) በመሆኑም ጳውሎስ ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት የእምነት ባልንጀሮቹን “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ” ብሎ መምከር ችሏል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13ን አንብብ።

16, 17. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹ የሚያጋጥሟቸውን መከራዎች እንዲቋቋሙ ኃይል የሚሰጣቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

16 ሮክሳና የተባለች አንዲት አቅኚ፣ ይሖዋ ለሕዝቦቹ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚሰጣቸው ካጋጠማት ነገር ተመልክታለች። በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ፈቃድ እንዲሰጣት አሠሪዋን በጠየቀችው ጊዜ ወደ ስብሰባው ለመሄድ ብላ ከሥራ ብትቀር እንደሚያባርራት በቁጣ ነገራት። ያም ቢሆን ሮክሳና ወደ ስብሰባው ሄደች፤ ሆኖም ከሥራ እንዳትባረር አጥብቃ ትጸልይ ነበር። ይህም የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማት አደረጋት። ከስብሰባው በኋላ ሰኞ ሥራ ስትገባ አለቃዋ እንደዛተው አባረራት። ሮክሳና በምታገኘው አነስተኛ ደሞዝ ቤተሰቧን ትረዳ ስለነበር ሥራዋን ማጣቷ አስጨነቃት። በዚህ ጊዜም ወደ ይሖዋ የጸለየች ከመሆኑም ሌላ ‘አምላክ በአውራጃ ስብሰባ ላይ በመንፈሳዊ የሚያስፈልገኝን ሰጥቶኛል፤ በሰብዓዊ ሁኔታም የሚያስፈልገኝን ሊሰጠኝ እንደሚችል ጥርጥር የለውም’ ብላ አሰበች። ወደ ቤት እየተመለሰች ሳለም “ለሥራ ፈላጊዎች” የሚል ማስታወቂያ ተመለከተች፤ ለሥራው የሚፈለገው በፋብሪካ ውስጥ ባሉ የስፌት መኪናዎች ላይ የመሥራት ልምድ ያለው ሰው ሲሆን ሮክሳናም ለሥራው አመለከተች። የመሥሪያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ፣ ሮክሳና ልምድ እንደሌላት ቢያውቅም ቀድሞ ከምታገኘው በእጥፍ ደሞዝ ቀጠራት። ሮክሳና ጸሎቷ መልስ እንዳገኘ ተሰማት። ከሁሉ የላቀው በረከት ግን ምሥራቹን ለብዙ የሥራ ባልደረቦቿ ማካፈል መቻሏ ነው። ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ አምስት የሥራ ባልደረቦቿ ወደ እውነት መጥተዋል።

17 አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችን ወዲያው ወይም እኛ በጠበቅነው ጊዜ እንዳልተመለሰልን ይሰማን ይሆናል። ጸሎታችን መልስ ያላገኘበት በቂ ምክንያት እንደሚኖር ጥርጥር የለውም። ይሖዋ ምክንያቱን ቢያውቀውም ለእኛ ግልጽ የሚሆንልን ወደፊት ይሆናል። ሆኖም አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን እንችላለን፦ አምላክ ታማኞቹን አይጥልም።—ዕብ. 6:10

መከራዎችንና ፈተናዎችን ለመቋቋም ይረዳናል

18, 19. (ሀ) መከራዎችና ፈተናዎች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) መከራዎችን በጽናት ለመወጣት ምን ሊረዳን ይችላል?

18 ፈተናዎች፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት፣ ስደትና የእኩዮች ተጽዕኖ ለይሖዋ ሕዝቦች አዲስ አይደሉም። በጥቅሉ ሲታይ ዓለም ለእኛ ጥላቻ አለው። (ዮሐ. 15:17-19) ያም ሆኖ መንፈስ ቅዱስ፣ አምላክን ስናገለግል የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ሁኔታ መወጣት እንድንችል ይረዳናል። ይሖዋ ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን አይፈቅድም። (1 ቆሮ. 10:13) ፈጽሞ አይተወንም፤ በምንም ዓይነት አይጥለንም። (ዕብ. 13:5) በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ቃሉን ከታዘዝን ጥበቃና ብርታት እናገኛለን። ከዚህም በተጨማሪ እርዳታ በጣም በሚያስፈልገን ጊዜ የእምነት ባልንጀሮቻችን እንዲረዱን የአምላክ መንፈስ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

19 ሁላችንም በመጸለይና ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል። “ሙሉ በሙሉ መጽናትና በደስታ መታገሥ እንድትችሉ የአምላክ ታላቅ ኃይል የሚያስፈልጋችሁን ብርታት ሁሉ እንዲሰጣችሁ” ምኞታችን ነው!—ቆላ. 1:11

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ ተሞክሮዎችን ለማግኘት የግንቦት 1, 2001 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16ን እና የየካቲት 8, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 21 እና 22⁠ን ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ስደትን ለመቋቋም ራስህን ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

• አንድ ሰው የፈጸመውን መጥፎ ድርጊት እንዳትናገርበት ቢጠይቅህ ምን ማድረግ አለብህ?

• ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስብህ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከኢያሱና ከካሌብ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኃጢአት የፈጸመን ጓደኛህን መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?