በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ሞገስ ማግኘት ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራል

የአምላክን ሞገስ ማግኘት ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራል

የአምላክን ሞገስ ማግኘት ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራል

“እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ አንተ ጻድቃንን ትባርካቸዋለህ፤ በሞገስህም እንደ ጋሻ ትከልላቸዋለህ።”—መዝ. 5:12

1, 2. ኤልያስ፣ በሰራፕታ የምትገኘውን መበለት ምን እንድታደርግለት ጠየቃት? ምን ማረጋገጫስ ሰጣት?

ሴትየዋም ሆነ ልጇ ርቧቸዋል፤ የአምላክ ነቢይም እንዲሁ የሚበላ ነገር ይፈልጋል። በሰራፕታ የምትገኘው ይህች መበለት ለማብሰያ የሚሆናት ጭራሮ እየለቃቀመች ሳለ ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ተገናኘች፤ ነቢዩም ውኃና እንጀራ እንድትሰጠው ጠየቃት። ይህች ሴት የሚጠጣ ነገር ልትሰጠው ፈቃደኛ ብትሆንም “በማድጋ ካለው ዕፍኝ ዱቄትና በማሰሮ ካለው ጥቂት ዘይት በቀር” ምንም የሚበላ ነገር አልነበራትም። ለኤልያስ ልታካፍለው የምትችለው በቂ ምግብ እንደሌላት ስለተሰማት ይህንኑ ነገረችው።—1 ነገ. 17:8-12

2 ኤልያስ ግን “በመጀመሪያ . . . ከዚያችው ካለችሽ ትንሽ እንጎቻ ጋግረሽ አምጪልኝ” አላት። “ከዚያም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ . . . ‘ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አያልቅም።’”—1 ነገ. 17:13, 14

3. እያንዳንዳችን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምን ጥያቄ ተደቅኖብናል?

3 ይህች መበለት፣ የቀረቻትን ትንሽ ምግብ ለነቢዩ ማካፈል ይኖርባት እንደሆነና እንዳልሆነ ከመወሰን የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጥያቄ ተደቅኖባታል። ይሖዋ፣ እሷንም ሆነ ልጇን በረሃብ ከመሞት ሊታደጋቸው እንደሚችል ትተማመን ይሆን? ወይስ የአምላክን ሞገስ ከማግኘትና ከእሱ ጋር ወዳጅነት ከመመሥረት ይልቅ ሥጋዊ ፍላጎቷን ታስቀድማለች? ሁላችንም ተመሳሳይ ጥያቄ ተደቅኖብናል። ይበልጥ የሚያሳስበን የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ነው ወይስ በቁሳዊ ረገድ የተደላደለ ሕይወት መምራት? በአምላክ እንድንታመንና እሱን እንድናገለግል የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉን። የአምላክን ሞገስ ለመሻትና ሞገሱን ለማግኘት ከፈለግን ልንወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችም አሉ።

አምልኮ “ልትቀበል ይገባሃል”

4. ይሖዋን ልናመልከው ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ፣ ሰዎች እሱ በሚፈልገው መንገድ እንዲያገለግሉት የመጠበቅ መብት አለው። በሰማይ የሚገኙት አገልጋዮቹ በአንድነት እንደሚከተለው በማለት ይህን ሐቅ ጎላ አድርገው ገልጸዋል፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ያሉትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።” (ራእይ 4:11) ይሖዋ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ስለሆነ አምልኮ ይገባዋል።

5. አምላክ ለእኛ ያለው ፍቅር እሱን እንድናገለግለው ሊያነሳሳን ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?

5 ይሖዋን እንድናገለግል የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ደግሞ ለእኛ ያሳየው አቻ የሌለው ፍቅሩ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ይላል። (ዘፍ. 1:27) ይሖዋ ሰዎችን ሲፈጥር እሱን ለማገልገል ይፈልጉ እንደሆነና እንዳልሆነ የመምረጥ መብት ብሎም ኃላፊነት የሰጣቸው ሲሆን እንዲህ ያለውን ምርጫ ለማድረግ ችሎታውም አላቸው። ይሖዋ ሕይወት ስለ ሰጠን ለሰው ዘር ሁሉ አባት ነው። (ሉቃስ 3:38) አንድ ጥሩ አባት ለልጆቹ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር እንደሚያቀርብ ሁሉ ይሖዋም ሕይወትን እንድናጣጥም የሚያስችለንን ነገር በሙሉ ሰጥቶናል። ምድር የተትረፈረፈ ምግብ ማምረት እንድትችልና ውብ የሆነ አካባቢ እንዲኖረን ለማድረግ ሲል ይሖዋ “ፀሐዩን ያወጣል” እንዲሁም “ዝናብ ያዘንባል።”—ማቴ. 5:45

6, 7. (ሀ) አዳም በዘሮቹ ሁሉ ላይ ምን ጉዳት አስከትሏል? (ለ) የክርስቶስ መሥዋዕት የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ለሚጥሩ ሰዎች ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?

6 ይሖዋ ኃጢአት ካስከተለው አስከፊ መዘዝም ታድጎናል። አዳም ኃጢአት በመሥራቱ ቁማር ለመጫወት ሲል ከቤተሰቡ እንደሚሰርቅ አባት ሆኗል። አዳም በይሖዋ ላይ ሲያምፅ፣ ልጆቹ ለዘላለም በደስታ ለመኖር የነበራቸውን አጋጣሚ እንዲያጡ አድርጓል። በራስ ወዳድነት የወሰደው እርምጃ የሰው ዘሮችን ጨካኝ ጌታ የሆነው የኃጢአት ባሪያ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ስለሆነም የሰው ልጆች በሙሉ ከሕመም፣ ከሐዘንና ውሎ አድሮም ከሞት ማምለጥ አይችሉም። አንድን ባሪያ ነፃ ለማውጣት መከፈል ያለበት ነገር አለ፤ ይሖዋም ኃጢአት ካስከተለው አስከፊ መዘዝ እኛን ለማዳን የሚያስፈልገውን ክፍያ ፈጽሟል። (ሮም 5:21ን አንብብ።) ኢየሱስ ክርስቶስ “በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ” በመስጠት የአባቱን ፈቃድ አከናውኗል። (ማቴ. 20:28) በአምላክ ዘንድ ሞገስ ያገኙ ሰዎች በቅርቡ የዚህን ቤዛ ሙሉ ጥቅም ያገኛሉ።

7 ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ ደስተኛና ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲኖረን ለማድረግ ሲል ማንም ሊያደርገው ከሚችለው የላቀ ነገር አከናውኗል። የእሱን ሞገስ ካገኘን፣ በሰው ልጆች ላይ የደረሰውን ጉዳት ሁሉ ለማስተካከል ምን እርምጃ እንደሚወስድ መመልከት እንችላለን። ይሖዋ “ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ” የሚሆነው እንዴት እንደሆነ እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ እንድንመለከት ያደርገናል።—ዕብ. 11:6

“ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል”

8. ከኢሳይያስ ጋር በተያያዘ ይሖዋ ያደረገው ነገር እሱን ስለ ማገልገል ምን ያስተምረናል?

8 የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ነፃ ምርጫችንን በተገቢው መንገድ መጠቀም ይኖርብናል። እንዲህ የምንለው ይሖዋ ማንኛውም ሰው እሱን እንዲያገለግል ስለማያስገድድ ነው። በኢሳይያስ ዘመን፣ አምላክ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” በማለት ጠይቆ ነበር። ይሖዋ፣ ነቢዩ የራሱን ውሳኔ እንዲያደርግ መፍቀዱ ለእሱ አክብሮት እንዳለው ያሳያል። ኢሳይያስ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” ብሎ ሲመልስ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን መገመት ትችላለህ!—ኢሳ. 6:8

9, 10. (ሀ) አምላክን የምናገለግለው በምን ዓይነት ዝንባሌ ተነሳስተን ሊሆን ይገባል? (ለ) ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን ማገልገላችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

9 ሰዎች አምላክን ለማገልገልም ሆነ ላለማገልገል መምረጥ ይችላሉ። ይሖዋ በፈቃደኝነት እንድናገለግለው ይፈልጋል። (ኢያሱ 24:15ን አንብብ።) አምላክ፣ ቅር እያለው ወይም ሌሎች ሰዎችን ለማስደሰት ሲል ብቻ እሱን በሚያገለግል ሰው አይደሰትም። (ቆላ. 3:22) ከዓለም የምናገኛቸው ነገሮች ለአምልኳችን እንቅፋት እንዲሆኑብን በመፍቀድ ቅዱስ አገልግሎት ከማቅረብ ‘ወደ ኋላ የምንል’ ከሆነ የአምላክን ሞገስ አናገኝም። (ዘፀ. 22:29) ይሖዋ እሱን በሙሉ ነፍስ ማገልገላችን ጥቅሙ ለራሳችን እንደሆነ ያውቃል። እስራኤላውያን ‘አምላክን በመውደድ፣ ቃሉን በማዳመጥና ከእሱ ጋር በመጣበቅ’ ሕይወትን እንዲመርጡ ሙሴ አሳስቧቸው ነበር።—ዘዳ. 30:19, 20

10 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት እንዲህ በማለት ለይሖዋ ዘምሯል፦ “ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል፤ ከንጋት ማሕፀን፣ በቅዱስ ግርማ ደምቀህ፣ የጐልማሳነትህን ልምላሜ እንደ ጠል ትቀበላለህ።” (መዝ. 110:3) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጡት በቁሳዊ ረገድ የተደላደለና የተመቻቸ ኑሮ ማግኘትን ነው። ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ግን ከምንም ነገር በላይ የሚያስቀድሙት ቅዱስ አገልግሎታቸውን ነው። ምሥራቹን በቅንዓት መስበካቸው ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ በግልጽ ያሳያል። ይሖዋ በየዕለቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት እንደሚችል ሙሉ እምነት አላቸው።—ማቴ. 6:33, 34

የአምላክን ሞገስ የሚያስገኙ መሥዋዕቶች

11. እስራኤላውያን ለይሖዋ መሥዋዕት ሲያቀርቡ ምን እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጉ ነበር?

11 በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር የይሖዋ ሕዝቦች የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ሲሉ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መሥዋዕቶችን ያቀርቡ ነበር። ዘሌዋውያን 19:5 “የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ አድርጋችሁ አቅርቡ” ይላል። ይኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲህ የሚል መመሪያም ይዟል፦ “ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጋችሁ አቅርቡት።” (ዘሌ. 22:29) እስራኤላውያን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የእንስሳት መሥዋዕቶችን በይሖዋ መሠዊያ ላይ ሲያቀርቡ ሽታው ‘ደስ እንደሚያሰኝ’ መዓዛ ወደ እውነተኛው አምላክ ይወጣ ነበር። (ዘሌ. 1:9, 13) ይሖዋ፣ ሕዝቡ ለእሱ ያላቸውን ፍቅር በሚያሳየው በዚህ ተግባር የተደሰተ ከመሆኑም ሌላ መሥዋዕታቸውን ተቀብሏል። (ዘፍ. 8:21) ከዚህ የሕጉ ገጽታ በዛሬው ጊዜ ተግባራዊ ልናደርገው የምንችለው መሠረታዊ ሥርዓት እናገኛለን። በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሰዎች የእሱን ሞገስ ያገኛሉ። ይሖዋ የሚቀበለው ምን ዓይነት መሥዋዕቶችን ነው? እስቲ ሁለት አቅጣጫዎችን ይኸውም ምግባራችንንና አንደበታችንን የምንጠቀምበትን መንገድ እንመልከት።

12. ‘ሰውነታችንን ለአምላክ መሥዋዕት አድርገን ስናቀርብ’ ተቀባይነት እንድናጣ ሊያደርጉን የሚችሉ ተግባሮች የትኞቹ ናቸው?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ እንድታቀርቡ . . . እለምናችኋለሁ፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።” (ሮም 12:1) አንድ ሰው የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከፈለገ ሰውነቱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ ከሚያደርጉ ተግባሮች መራቅ ይኖርበታል። በትንባሆ፣ በቢትል ነት፣ በጫት፣ በዕፅ ወይም አልኮልን ከመጠን በላይ በመጠጣት ሰውነቱን የሚያረክስ ከሆነ የሚያቀርበው መሥዋዕት ምንም ዋጋ አይኖረውም። (2 ቆሮ. 7:1) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ዝሙት የመፈጸም ልማድ ያለው . . . በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው” ስለሚል ማንኛውንም ዓይነት የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽም ሰው መሥዋዕቱ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው። (1 ቆሮ. 6:18) አንድ ሰው አምላክን ለማስደሰት ከፈለገ ‘በምግባሩ ሁሉ ቅዱስ’ መሆን ይኖርበታል።—1 ጴጥ. 1:14-16

13. ይሖዋን ማወደሳችን የተገባ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋን የሚያስደስተው ሌላው መሥዋዕት አንደበታችንን የምንጠቀምበት መንገድ ነው። ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ምንጊዜም ስለ ይሖዋ መልካምነት በሕዝብ ፊትም ሆነ በቤታቸው ሲሆኑ ይናገራሉ። (መዝሙር 34:1-3ን አንብብ።) መዝሙር 148 እስከ 150⁠ን በማንበብ እነዚህ ሦስት መዝሙሮች ይሖዋን እንድናወድስ ምን ያህል ደጋግመው እንደሚያበረታቱን ለማስተዋል ሞክሩ። በእርግጥም “ቅኖች [አምላክን] ሊወድሱት ይገባቸዋል።” (መዝ. 33:1) ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ምሥራቹን በመስበክ አምላክን ማወደስ አስፈላጊ መሆኑን አጉልቷል።—ሉቃስ 4:18, 43, 44

14, 15. ሆሴዕ፣ እስራኤላውያንን ምን ዓይነት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ አሳስቧቸዋል? ይሖዋስ እንዲህ ዓይነት መሥዋዕት ላቀረቡት ሰዎች ምን አመለካከት ነበረው?

14 በቅንዓት መስበካችን ይሖዋን እንደምንወደውና የእሱን ሞገስ ለማግኘት እንደምንፈልግ ያሳያል። ለምሳሌ የሐሰት አምልኮን በመከተላቸው የአምላክን ሞገስ ላጡት እስራኤላውያን ነቢዩ ሆሴዕ ምን ማሳሰቢያ እንደሰጣቸው ልብ በሉ። (ሆሴዕ 13:1-3) ሆሴዕ፣ ይሖዋን እንዲህ ብለው እንዲማጸኑ አሳስቧቸዋል፦ “ኀጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ የከንፈራችንንም ፍሬ እንድናቀርብ፣ በምሕረትህ ተቀበለን።”—ሆሴዕ 14:1, 2

15 ‘የከንፈራችን ፍሬ’ የሚለው አገላለጽ እውነተኛውን አምላክ ለማወደስ የምንጠቀምባቸውን የታሰበባቸውና ከልብ የመነጩ ቃላት ያመለክታል። ይሖዋ እንዲህ ያለ መሥዋዕት ላቀረቡት ሰዎች ምን አመለካከት ነበረው? “እንዲሁ እወዳቸዋለሁ” ብሏል። (ሆሴዕ 14:4) እንዲህ ያለውን የምስጋና መሥዋዕት ላቀረቡት ሰዎች ይሖዋ ምሕረት አድርጎላቸዋል፣ ሞገሱን አሳይቷቸዋል እንዲሁም ከእነሱ ጋር ወዳጅነት መሥርቷል።

16, 17. አንድ ሰው በአምላክ ላይ ባለው እምነት ተነሳስቶ ምሥራቹን ሲሰብክ ይሖዋ ይህ ሰው የሚያቀርበውን ውዳሴ እንዴት ይመለከተዋል?

16 ይሖዋን በሕዝብ ፊት ማወደስ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ምንጊዜም ትልቅ ቦታ ነበረው። መዝሙራዊው፣ እውነተኛውን አምላክ ማወደስን ከፍ አድርጎ ይመለከተው ስለነበር “እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቅጄ ያቀረብሁትን የአፌን የምስጋና መሥዋዕት ተቀበል” በማለት አምላክን ለምኗል። (መዝ. 119:108) በዛሬው ጊዜስ? ኢሳይያስ በጊዜያችን ያሉትን እጅግ ብዙ ሕዝብ በተመለከተ “የእግዚአብሔርን ምስጋና እያወጁ [ይመጣሉ]” የሚል ትንቢት ተናግሯል፤ አክሎም ሕዝቡ የሚያመጧቸው ስጦታዎች በአምላክ መሠዊያ ላይ “ተቀባይነት የሚኖራቸው መሥዋዕቶች ይሆናሉ” ብሏል። (ኢሳ. 60:6, 7) በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ “የምስጋና መሥዋዕት” እያቀረቡ ሲሆን “ይህም ስለ ስሙ በይፋ [የሚያውጁበት] የከንፈር ፍሬ ነው።”—ዕብ. 13:15

17 አንተስ? ለአምላክ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እያቀረብክ ነው? ካልሆነ አስፈላጊውን ለውጥ አድርገህ ይሖዋን በሕዝብ ፊት ማወደስ ልትጀምር ትችላለህ? በአምላክ ላይ ባለህ እምነት ተገፋፍተህ ምሥራቹን መስበክ ስትጀምር የምታቀርበው መሥዋዕት “ከበሬ ይልቅ . . . እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።” (መዝሙር 69:30, 31ን አንብብ።) የምስጋና መሥዋዕትህ “መልካም መዐዛ” ወደ ይሖዋ እንደሚደርስና እሱም ሞገሱን እንደሚያሳይህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ሕዝ. 20:41) ይህም ወደር የሌለው ደስታ ያስገኝልሃል።

ይሖዋ ‘ጻድቃንን ይባርካቸዋል’

18, 19. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች አምላክን ስለ ማገልገል ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው? (ለ) የአምላክን ሞገስ ማጣት ወደ ምን ይመራል?

18 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች በሚልክያስ ዘመን እንደነበሩት እስራኤላውያን “እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ እርሱ የሚፈልገውን ሁሉ በማድረግ . . . ምን ተጠቀምን?” የሚል አመለካከት አላቸው። (ሚል. 3:14) በቁሳዊ ነገሮች ላይ ስለሚያተኩሩ የአምላክ ዓላማ ሊፈጸም እንደማይችልና ሕግጋቱም ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ ምሥራቹን መስበክ ጊዜ የሚያባክን ብሎም ሰዎችን የሚያበሳጭ ተግባር እንደሆነ ያስባሉ።

19 እንዲህ ያለው አመለካከት መጀመሪያ የታየው በኤደን ገነት ነው። ሰይጣን፣ ሔዋንን በማታለል ይሖዋ የሰጣት ግሩም ሕይወት ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳለው እንዳታደንቅና የአምላክን ሞገስ ማግኘትን አቅልላ እንድትመለከተው አደረጋት። በዛሬው ጊዜም ሰይጣን፣ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ትርፉ ድካም ብቻ እንደሆነ ሰዎችን ለማሳመን እየጣረ ነው። ይሁን እንጂ ሔዋንና ባሏ፣ የአምላክን ሞገስ ማጣታቸው ሕይወታቸውንም እንደሚያሳጣቸው ለመገንዘብ ተገደዋል። በአሁኑ ጊዜም የእነሱን የተሳሳተ አካሄድ የሚከተሉ ሁሉ ይህንን መራራ ሐቅ ለመገንዘብ ይገደዳሉ።—ዘፍ. 3:1-7, 17-19

20, 21. (ሀ) የሰራፕታዋ መበለት ምን አደረገች? ውጤቱስ ምን ሆነ? (ለ) የሰራፕታዋን መበለት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ የምናደርገውስ ለምንድን ነው?

20 አዳምና ሔዋን የወሰዱት እርምጃ ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት በመግቢያችን ላይ የተመለከትነው የኤልያስና የሰራፕታዋ መበለት ታሪክ ከተደመደመበት ሁኔታ ጋር ለማወዳደር ሞክር። ሴትየዋ፣ ኤልያስ የተናገረውን የሚያበረታታ ሐሳብ ካዳመጠች በኋላ ትንሽ እንጎቻ ጋግራ መጀመሪያ ለነቢዩ ሰጠችው። ከዚያም ይሖዋ በኤልያስ አማካኝነት የገባውን ቃል ፈጸመ። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ኤልያስ፣ መበለቲቱና ቤተ ሰቧ ብዙ ቀን ተመገቡ፤ በኤልያስ በተነገረው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ከማድጋው ዱቄት አልጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አላለቀም።”—1 ነገ. 17:15, 16

21 የሰራፕታዋ መበለት በአሁኑ ጊዜ ከሚኖሩት በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የማያደርጉትን ነገር አድርጋለች። አዳኝ በሆነው አምላክ ላይ ሙሉ እምነቷን የጣለች ሲሆን እሱም ቢሆን ያለ ረዳት አልተዋትም። ይህ ታሪክም ሆነ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ልንታመንበት የሚገባ አምላክ እንደሆነ ያረጋግጣሉ። (ኢያሱ 21:43-45⁠ን እና 23:14ን አንብብ።) በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ተሞክሮዎችም ይሖዋ የእሱን ሞገስ ያገኙ ሰዎችን ፈጽሞ እንደማይተዋቸው ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጡናል።—መዝ. 34:6, 7, 17-19 *

22. ሳንዘገይ የአምላክን ሞገስ መፈለጋችን አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?

22 የአምላክ የፍርድ ቀን “በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ” መምጣቱ የማይቀር ነው። (ሉቃስ 21:34, 35) ከዚህ ቀን ማምለጥ የማይቻል ነገር ነው። ሀብትም ሆነ ማንኛውም ቁሳዊ ንብረት፣ አምላክ በሾመው ፈራጅ “እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፣ . . . የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” የመባልን ያህል ዋጋ ሊኖረው አይችልም። (ማቴ. 25:34) አዎን፣ ይሖዋ ራሱ ‘ጻድቃንን ይባርካቸዋል፤ በሞገሱም እንደ ጋሻ ይከልላቸዋል።’ (መዝ. 5:12) ታዲያ የአምላክን ሞገስ መፈለግ አይኖርብንም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.21 የመጋቢት 15, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13 አንቀጽ 15⁠ን እና የነሐሴ 1, 1997 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 20-25 ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋ በሙሉ ነፍስ የሚቀርብ አምልኮ ይገባዋል የምንለው ለምንድን ነው?

• ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት መሥዋዕቶችን ይቀበላል?

• ‘የከንፈራችን ፍሬ’ የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? ይህንንስ ለይሖዋ ማቅረብ ያለብን ለምንድን ነው?

• የአምላክን ሞገስ መሻት ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ነቢይ፣ ችግረኛ ለሆነች አንዲት እናት ምን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጥያቄ አቀረበላት?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለይሖዋ የምስጋና መሥዋዕት በማቅረባችን ምን ጥቅም እናገኛለን?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልብህ በይሖዋ ላይ በመታመንህ ፈጽሞ አታፍርም