ለመደሰት የሚያበቃ ምክንያት አላችሁ
ለመደሰት የሚያበቃ ምክንያት አላችሁ
በጣም ትንሽ ከሆነች ሕያው ሴል አንስቶ ግዙፍ እስከ ሆኑ ጋላክሲዎችና የጋላክሲዎች ክምችቶች ድረስ ያሉት የፍጥረት ሥራዎች ሥርዓት ባለው መልክ የተደራጁ ናቸው። ይህ መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ምክንያቱም ፈጣሪያችን “የሁከት አምላክ አይደለም።” (1 ቆሮ. 14:33) አምላክ ለእሱ የሚቀርበውን አምልኮ ያደራጀበት መንገድም በጣም አስደናቂ ነው። እስቲ ይሖዋ ምን እንዳደረገ እንመልከት። ይሖዋ፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የማሰብ ችሎታና ነፃ ምርጫ ያላቸው ሰብዓዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈ አጽናፈ ዓለማዊ ድርጅት አቋቁሟል፤ እነዚህ ፍጥረታት ደግሞ በንጹሕ አምልኮ አንድ ሆነዋል። ይህ እንዴት የሚያስደንቅ ነው!
በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ኢየሩሳሌም የአምላክን ድርጅት ምድራዊ ክፍል ትወክል ነበር፤ የይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚገኘው በዚህች ከተማ ሲሆን ከተማዋ እሱ የቀባቸው ነገሥታት መቀመጫም ነበረች። ወደ ባቢሎን በግዞት የተወሰደ አንድ እስራኤላዊ ስለ ቅድስቲቱ ከተማ ምን እንደሚሰማው ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሳላስታውስሽ ብቀር፣ ኢየሩሳሌምን የደስታዬ ቍንጮ ባላደርግ፣ ምላሴ ከትናጋዬ ጋር ትጣበቅ።”—መዝ. 137:6
እናንተስ በዛሬው ጊዜ ስላለው የአምላክ ድርጅት እንደዚህ ይሰማችኋል? ከዓለም አቀፋዊ ድርጅቱ ጋር በመሆን ይሖዋን ማምለክ ከምንም ነገር በላይ ደስታ ይሰጣችኋል? ልጆቻችሁ የአምላክን ድርጅት ምድራዊ ክፍል ታሪክና ሥራውን የሚያከናውንበትን መንገድ ያውቃሉ? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈው የወንድማማች ማኅበር አባል እንደሆኑ ይገነዘባሉ? ይህን መብታቸውንስ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል? (1 ጴጥ. 2:17) ቤተሰባችሁ ስለ ይሖዋ ድርጅት ያለው እውቀት እንዲሰፋና አድናቆቱ እንዲጨምር በቤተሰብ አምልኳችሁ ወቅት ከዚህ በታች የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ለምን አትሞክሩም?
“በቀድሞ ዘመን” የተከናወኑትን ነገሮች ተናገሩ
እስራኤላውያን ቤተሰቦች በየዓመቱ የፋሲካን በዓል ለማክበር ይሰባሰቡ ነበር። በዓሉ በተቋቋመበት ወቅት ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “በሚመጡት ዘመናት ልጅህ፣ ‘ይህ ምን ማለት ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ እንዲህ በለው፤ ‘ከባርነት ምድር ከግብፅ እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ አወጣን’።” (ዘፀ. 13:14) ይሖዋ ለእስራኤላውያን ያደረገላቸው ነገር ያለፈ ታሪክ እንደሆነ ተቆጥሮ ሊረሳ አይገባውም ነበር። በርካታ እስራኤላውያን አባቶች ሙሴ የሰጣቸውን መመሪያ እንደተከተሉ ጥርጥር የለውም። ብዙ ትውልዶች ካለፉ በኋላ አንድ እስራኤላዊ እንዲህ በማለት ጸልዮአል፦ “አምላክ ሆይ፤ በጆሮአችን ሰምተናል፤ አባቶቻችን በቀድሞ ዘመን፣ እነርሱ በነበሩበት ዘመን፣ ያደረግኸውን ነግረውናል።”—መዝ. 44:1
በዛሬው ጊዜ ያለ አንድ ወጣት ከ100 ዓመት ገደማ በፊት የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ “በቀድሞ ዘመን” የተፈጸመ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ልጆቻችሁ እነዚህ ክንውኖች ሕያው እንዲሆኑላቸው ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ ወላጆች ይህን ለማድረግ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ፣ የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ)፣ በመጽሔቶቻችን ላይ የሚወጡ የሕይወት ተሞክሮዎችን፣ ስለ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች የሚያወሱ ዘገባዎችንና በዘመናችን ያለውን የአምላክ ሕዝቦች እንቅስቃሴ የሚያሳየውን አዲሱን ዲቪዲ ይጠቀማሉ። በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረትና በናዚ ጀርመን የነበሩት ወንድሞቻችን የደረሰባቸውን ስደት አስመልክቶ የተዘጋጁት ፊልሞች ቤተሰባችሁ በፈተና ወቅት በይሖዋ ላይ እንዲታመን ለማስተማር ይረዳሉ። በቤተሰብ አምልኳችሁ ወቅት እነዚህን ፊልሞች ማካተት ትችላላችሁ። ይህ ደግሞ ልጆቻችሁ አቋማቸውን በተመለከተ ፈተና ቢያጋጥማቸው እንኳ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።
ይሁንና ስላለፈው ታሪክ ዝም ብላችሁ ብታወሩላቸው ልጆቻችሁ ቶሎ ሊሰላቹ ይችላሉ። ስለሆነም ልጆቻችሁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አበረታቷቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ የሚወደውን አገር እንዲመርጥ ከዚያም ስለዚህ አገር ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ ምርምር በማድረግ ያገኘውን
ሐሳብ ለቤተሰቡ እንዲያቀርብ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። በጉባኤያችሁ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉ ክርስቲያኖች ይኖሩ ይሆናል፤ እነዚህን ወንድሞች አንድ ቀን የቤተሰብ አምልኮ ስታደርጉ ልትጋብዟቸው ትችላላችሁ። ሴት ልጃችሁ እነዚህ ክርስቲያኖች ተሞክሯቸውን እንዲናገሩ ቃለ መጠይቅ ልታደርግላቸው ትችላለች። አሊያም ደግሞ ልጆቻችሁ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ቲኦክራሲያዊ ክንውኖች ለምሳሌ የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታን፣ ብሔራት አቀፍ ስብሰባን ወይም ንግግር በተቀረጸበት ሸክላ በመጠቀም ከቤት ወደ ቤት ይከናወን የነበረውን አገልግሎት የሚያሳይ ሥዕል እንዲሥሉ ማድረግ ትችሉ ይሆናል።‘እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ የሚያከናውነው’ እንዴት እንደሆነ እወቁ
ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን ከአካል ጋር በማነጻጸር እንዲህ ብሏል፦ “አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል።” (ኤፌ. 4:16 አ.መ.ት) የሰው አካል የሚሠራው እንዴት እንደሆነ ማወቃችን ለፈጣሪያችን ያለንን አድናቆትና አክብሮት ይጨምርልናል። በተመሳሳይም ዓለም አቀፉ ጉባኤ እንዴት እንደሚሠራ ስንመረምር “በርካታ ገጽታዎች [ባሉት] የአምላክ ጥበብ” እንደነቃለን።—ኤፌ. 3:10
ይሖዋ በሰማይ ያለውን የድርጅቱን ክፍል ጨምሮ ድርጅቱ በአጠቃላይ እንዴት እንደሚሠራ ገልጾልናል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ይሖዋ በመጀመሪያ ለኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ የሰጠው ሲሆን ኢየሱስም “መልአኩን ልኮ በእሱ አማካኝነት ለባሪያው ለዮሐንስ በምልክቶች ገለጠለት፤ ዮሐንስም . . . ስላያቸው ነገሮች ሁሉ መሥክሯል።” (ራእይ 1:1, 2) አምላክ፣ የማይታየው የድርጅቱ ክፍል ሥራውን የሚያከናውነው እንዴት እንደሆነ ከገለጸልን በምድር ላይ ያለው “እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ” እንዴት እንደሚያከናውን እንድናውቅ እንደሚፈልግ ጥርጥር የለውም።
ለምሳሌ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በቅርቡ ጉባኤያችሁን የሚጎበኝ ከሆነ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ምን ኃላፊነቶችና መብቶች እንዳሏቸው ከቤተሰባችሁ ጋር ለምን አትወያዩም? እነዚህ ወንድሞች እያንዳንዳችንን የሚረዱን እንዴት ነው? ልትወያዩባቸው የምትችሏቸው ሌሎች ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦ የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ሪፖርት ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የአምላክ ድርጅት ለሚያከናውነው ሥራ ገንዘብ የሚያገኘው ከየት ነው? የበላይ አካሉ የተዋቀረው እንዴት ነው? መንፈሳዊ ምግብ የሚያዘጋጀውስ እንዴት ነው?
የይሖዋ ሕዝቦች እንዴት እንደተደራጁ ማወቃችን ቢያንስ በሦስት መንገዶች ይጠቅመናል፦ ስለ እኛ ሆነው በትጋት ለሚሠሩት ወንድሞች ያለን አድናቆት ይጨምራል። (1 ተሰ. 5:12, 13) ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችን ለመደገፍ እንነሳሳለን። (ሥራ 16:4, 5) በመጨረሻም በኃላፊነት ቦታ ያሉት ወንድሞች የሚያደርጓቸው ውሳኔዎችና ዝግጅቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት እንዳላቸው ስንመለከት በእነሱ ላይ ያለን እምነት ይጠናከራል።—ዕብ. 13:7
“መጠበቂያ ማማዎቿን እዩ”
“በጽዮን አካባቢ ተመላለሱ፤ ዙሪያዋንም ሂዱ፤ የጥበቃ ግንበኞቿንም ቍጠሩ፤ ለሚቀጥለው ትውልድ ትናገሩ ዘንድ፣ መከላከያ ዕርዶቿን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ መጠበቂያ ማማዎቿን እዩ።” (መዝ. 48:12, 13) እዚህ ላይ መዝሙራዊው፣ እስራኤላውያን ኢየሩሳሌምን በደንብ እንዲመለከቷት አሳስቧቸዋል። በየዓመቱ በሚከበሩት በዓላት ላይ ለመገኘት ወደ ቅድስቲቱ ከተማ የተጓዙና እጹብ ድንቅ የሆነውን ቤተ መቅደሷን የተመለከቱ እስራኤላውያን ቤተሰቦች ምን ዓይነት አስደሳች ትዝታ ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት ትችላለህ? የተመለከቱትን ነገር “ለሚቀጥለው ትውልድ” ለመናገር እንደሚነሳሱ ጥርጥር የለውም።
የሳባን ንግሥት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህች ንግሥት መጀመሪያ ላይ አስደናቂ ስለሆነው የሰለሞን ግዛትና ስለ ታላቅ ጥበቡ የሰማችውን አላመነችም ነበር። የሰማችው ነገር እውነት መሆኑን እንድታምን ያደረጋት ምን ነበር? “መጥቼ በዓይኔ እስካየሁ ጊዜ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር” ብላለች። (2 ዜና 9:6) አዎን፣ ‘በዓይናችን’ የምናየው ነገር በጥልቅ ሊነካን ይችላል።
ልጆቻችሁን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያሉትን አስደናቂ ነገሮች ‘በዓይናቸው’ እንዲመለከቱ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? በአካባቢያችሁ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ካለ ለመጎብኘት ጥረት አድርጉ። ማንዲ እና ቤተኒ ያደጉበት አካባቢ በአገራቸው ከሚገኘው ቤቴል 1,500 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። ያም ሆኖ ወላጆቻቸው በተለይ ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ቤቴልን በተደጋጋሚ ጊዜ ለመጎብኘት ዝግጅት ያደርጉ ነበር። ልጆቹ እንዲህ በማለት ይናገራሉ፦ “ቤቴልን ከመጎብኘታችን በፊት ብዙም የማይስብና ለትልልቅ ሰዎች ብቻ የሚሆን ቦታ እንደሆነ
ይሰማን ነበር። ይሁንና ይሖዋን በትጋት የሚያገለግሉና በሥራቸው ደስተኛ የሆኑ ወጣቶችን ተመለከትን! የይሖዋ ድርጅት እኛ በምንኖርበት አካባቢ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በጣም ሰፊ እንደሆነ ተገነዘብን፤ ቤቴልን በጎበኘን ቁጥር ወደ ይሖዋ ይበልጥ የቀረብን ከመሆኑም በላይ እሱን የበለጠ ለማገልገል አነሳስቶናል።” ማንዲ እና ቤተኒ በአምላክ ድርጅት ውስጥ የሚከናወኑትን ነገሮች በቅርበት መመልከታቸው አቅኚ እንዲሆኑ አነሳስቷቸዋል፤ ውሎ አድሮ በቤቴል ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው እንዲያገለግሉ ተጋብዘዋል።የጥንቶቹ እስራኤላውያን ያልነበራቸው የይሖዋን ድርጅት ‘ማየት’ የምንችልበት ሌላም መንገድ አለን። በቅርብ ዓመታት ውስጥ የአምላክ ሕዝቦች፣ ስለ ድርጅቱ የተለያዩ ገጽታዎች የሚያሳዩ ቪዲዮዎችንና ዲቪዲዎችን አግኝተዋል፤ ከእነዚህም መካከል ምሥራቹን ለመስበክ የተደራጁት የይሖዋ ምሥክሮች፣ መላው የወንድማማች ማኅበር፣ እስከ ምድር ዳር ድረስ እንዲሁም በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን የሚሉት ይገኙበታል። ቤቴላውያን፣ የእርዳታ ሠራተኞች፣ ሚስዮናውያን እንዲሁም አውራጃ ስብሰባዎችን የሚያዘጋጁና የሚያደራጁ ወንድሞች የሚያከናውኑትን ሥራ በቤተሰብ ሆናችሁ ስትመለከቱ ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር አድናቆት እንደሚያድርባችሁ ምንም ጥርጥር የለውም።
እያንዳንዱ የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤ፣ ምሥራቹን በመስበክና በአካባቢው የሚገኙትን ክርስቲያኖች በማበርታት ረገድ የጎላ ሚና እንደሚጫወት የታወቀ ነው። ይሁንና “በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ [ስላሉት] ወንድሞቻችሁ” ከቤተሰባችሁ ጋር ጊዜ ወስዳችሁ ማሰባችሁም ጠቃሚ ነው። እንዲህ ማድረጋችሁ እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ ለመደሰት የሚያበቃ ምክንያት እንዳላችሁ በመገንዘብ “በእምነት ጸንታችሁ” እንድትቀጥሉ ይረዳችኋል።—1 ጴጥ. 5:9
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የአምላክ ድርጅት በጥናታችሁ ወቅት ልታካትቱት የምትችሉት ርዕሰ ጉዳይ
ስለ ይሖዋ ድርጅት ታሪክና ድርጅቱ ሥራውን ስለሚያከናውንበት መንገድ ይበልጥ ለማወቅ የሚያስችሉን በርካታ ዝግጅቶች አሉን። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎች እንደ መነሻ ሊሆኗችሁ ይችላሉ፦
☞በዘመናችን ያሉት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሥራቸውን የጀመሩት እንዴት ነበር?—መጠበቂያ ግንብ ኅዳር 15, 1996 ከገጽ 10-15
☞በ1941 በተደረገው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ላይ “የልጆች ቀን” በተሰኘው ዕለት ምን ለየት ያለ ነገር ተከናውኗል?—መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 15, 2001 ገጽ 8
☞የበላይ አካሉ የተደራጀው እንዴት ነው?—መጠበቂያ ግንብ ግንቦት 15, 2008 ገጽ 29