በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የውሸት ምክንያት እያቀረባችሁ ራሳችሁን አታታልሉ

የውሸት ምክንያት እያቀረባችሁ ራሳችሁን አታታልሉ

የውሸት ምክንያት እያቀረባችሁ ራሳችሁን አታታልሉ

“ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ በበላች ጊዜ አምላክ ይህን ጥያቄ አቅርቦላት ነበር። እሷም “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች። (ዘፍ. 3:13) ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ እንድትጥስ ያደረጋት ተንኮለኛ እባብ ሰይጣን ሲሆን እሱም “መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው . . . የመጀመሪያው እባብ” ተብሎ ተጠርቷል።​—ራእይ 12:9

የዘፍጥረት ዘገባ፣ ሰይጣን ያልጠረጠሩ ሰዎችን ለማታለል ውሸትን የሚያጠነጥን መሠሪ አካል እንደሆነ ይገልጻል። ሔዋን በሰይጣን ተታልላ ወጥመዱ ውስጥ እንደወደቀች ግልጽ ነው። ይሁንና ሊያታልለን የሚችለው ሰይጣን ብቻ እንደሆነ አድርገን ማሰብ የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የውሸት ምክንያት እያቀረብን ራሳችንን ልናታልል’ እንደምንችልም ያስጠነቅቃል።​—ያዕ. 1:22

ራሳችንን ማታለል የሚለው ሐሳብ ፈጽሞ የማይሆን እንዲያውም የማይመስል ነገር እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ይሁንና ይህ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ የተጻፈልን ያለ ምክንያት አይደለም። በመሆኑም ራሳችንን ልናታልል የምንችለው እንዴት እንደሆነና ሊያታልሉን የሚችሉት የውሸት ምክንያቶች የትኞቹ እንደሆኑ መመርመራችን የተገባ ነው። በዚህ ረገድ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ መመልከታችን ጠቃሚ ነው።

ራሳቸውን ካታለሉ ሰዎች የምናገኘው ትምህርት

በ537 ዓ.ዓ. አካባቢ የፋርሱ ንጉሥ ታላቁ ቂሮስ በባቢሎን በግዞት የሚገኙት አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲገነቡ አዋጅ አውጥቶ ነበር። (ዕዝራ 1:1, 2) በቀጣዩ ዓመት ከይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕዝቡ አዲስ ቤተ መቅደስ ለመሥራት መሠረት ጣሉ። ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያን የዚህን አስፈላጊ የግንባታ ሥራ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስለባረከው ይሖዋን ያወደሱት ከመሆኑም ሌላ በጣም ተደስተው ነበር። (ዕዝራ 3:8, 10, 11) ብዙም ሳይቆይ ግን የግንባታው ሥራ ተቃውሞ ገጠመው፤ በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ተስፋ ቆረጡ። (ዕዝራ 4:4) አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ከ15 ዓመታት ገደማ በኋላ የፋርስ ባለሥልጣናት በኢየሩሳሌም ምንም ዓይነት የግንባታ ሥራ እንዳይካሄድ እገዳ ጣሉ። የአካባቢው ባለሥልጣናት እገዳው ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ አይሁዳውያኑ “ሥራውን እንዲያቆሙ አስገደዷቸው።”​—ዕዝራ 4:21-24

አይሁዳውያኑ እንዲህ ያለ እንቅፋት ሲጋረጥባቸው የውሸት ምክንያት በማቅረብ ራሳቸውን ማታለል ጀመሩ። ሕዝቡ “የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ጊዜ ገና ነው” ብለው ያስቡ ነበር። (ሐጌ 1:2) አምላክ ቤተ መቅደሱ ቶሎ እንዲሠራ አልፈለገም የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ከመፈለግ ይልቅ ይህን የተቀደሰ ሥራ ችላ በማለት የራሳቸውን ቤት ማሰማመሩን ተያያዙት። የአምላክ ነቢይ የነበረው ሐጌ “ይህ ቤት [የይሖዋ ቤተ መቅደስ] ፈርሶ ሳለ፣ እናንተ ራሳችሁ በተዋቡ ቤቶቻችሁ ውስጥ ለመኖር ጊዜው ነውን?” በማለት ወቅሷቸዋል።​—ሐጌ 1:4

ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ አስተዋልክ? የአምላክ ዓላማ ስለሚፈጸምበት ጊዜ የተሳሳተ አመለካከት መያዝ የመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን አስፈላጊነት ችላ በማለት የግል ፍላጎቶቻችንን ወደ ማሳደድ ዞር እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል እንግዶች ጋብዘህ እየጠበቅሃቸው ነው እንበል። እንግዶች ይመጡብኛል ብለህ ማሰብህ እነሱን ለመቀበል የሚያስፈልጉትን ነገሮችን ለማሟላት ጉድ ጉድ እንድትል ያደርግህ ይሆናል። ይሁንና እንግዶችህ እንደሚዘገዩ መልእክት ደረሰህ። እነሱን ለመቀበል የምታደርገውን ዝግጅት እርግፍ አድርገህ ትተወዋለህ?

ይሖዋ አሁንም ቢሆን ቤተ መቅደሱ በፍጥነት እንዲሠራ የሚፈልግ መሆኑን አይሁዳውያኑ እንዲገነዘቡ ሐጌና ዘካርያስ እንደረዷቸው አስታውስ። ሐጌ “የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በርቱ፤ . . . ሥሩ” በማለት አበረታቷቸዋል። (ሐጌ 2:4) ሕዝቡ የአምላክ መንፈስ እንደሚረዳቸው በመተማመን ሥራውን መቀጠል ነበረባቸው። (ዘካ. 4:6, 7) ይህ ምሳሌ የይሖዋን ቀን በተመለከተ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዳንደርስ ሊረዳን የሚችል ይመስልሃል?​—1 ቆሮ. 10:11

የውሸት ምክንያትን አስወግዶ ትክክለኛ አስተሳሰብ ማዳበር

ሐዋርያው ጴጥሮስ በሁለተኛ ደብዳቤው ላይ ይሖዋ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” ለማምጣት ቀን መቅጠሩን ተናግሮ ነበር። (2 ጴጥ. 3:13) አንዳንድ ፌዘኞች፣ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ እርምጃ የመውሰዱ ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑን እንደሚናገሩ ጴጥሮስ ገልጿል። ምንም አዲስ ነገር እንደማይመጣ ከዚህ ይልቅ “ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ [እንደሚቀጥል]” በመናገር የተሳሳተ ሐሳብ ያቀርባሉ። (2 ጴጥ. 3:4) ጴጥሮስ እንዲህ ያለው አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን ለመግለጽ ፈልጎ ነበር። በመሆኑም ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ‘ማሳሰቢያ በመስጠት በትክክል ማሰብ እንዲችሉ ለማነቃቃት’ ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። ፌዘኞቹ የሚያቀርቡት ምክንያት የተሳሳተ መሆኑን ለእምነት ባልንጀሮቹ አሳስቧቸዋል። አምላክ ከዚህ ቀደም ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በማምጣት ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ እርምጃ እንደወሰደ አስታውሷቸዋል።​—2 ጴጥ. 3:1, 5-7

ተስፋ በመቁረጥ ሥራውን ላቆሙት አይሁዳውያን ሐጌ በ520 ዓ.ዓ. ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። “እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ” በማለት መክሯቸዋል። (ሐጌ 1:5) የእምነት ባልንጀሮቹ በትክክል ማሰብ እንዲችሉ ለማነቃቃት ሲል አምላክ ከሕዝቡ ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማና የሰጣቸውን ተስፋ አስታውሷቸዋል። (ሐጌ 1:8፤ 2:4, 5) በግንባታው ሥራ ላይ የተጣለው እገዳ ባይነሳም ሐጌ ይህን ማበረታቻ ከሰጠ ብዙም ሳይቆይ ሥራው እንደገና ተጀመረ። በዚህ ጊዜም ቢሆን ተቃዋሚዎቻቸው የግንባታውን ሥራ ለማስቆም ጥረት አድርገው ነበር፤ ሆኖም አልተሳካላቸውም። ውሎ አድሮ እገዳው የተነሳ ሲሆን በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ቤተ መቅደሱ ተሠርቶ ተጠናቀቀ።​—ዕዝራ 6:14, 15፤ ሐጌ 1:14, 15

መንገዳችንን ልብ ማለት

በሐጌ ዘመን እንደነበሩት አይሁዳውያን እኛም ችግሮች ሲያጋጥሙን ተስፋ ልንቆርጥ የምንችል ይመስልሃል? ይህ ከሆነ ምሥራቹን በቅንዓት መስበካችንን መቀጠል አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። ይሁንና ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል? በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚታየው የፍትሕ መጓደል በጣም ያስጨንቀን ይሆናል። “ለርዳታ እየተጣራሁ፣ አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ‘ግፍ በዛ’ ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ ያቀረበውን ዕንባቆምን አስብ። (ዕን. 1:2) አንድ ክርስቲያን የይሖዋ ቀን እንደዘገየ ከተሰማው የጥድፊያ ስሜቱ ሊቀዘቅዝና በሕይወቱ ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ነገር የተደላደለ ሕይወት መምራት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ በአንተ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ይሰማሃል? የይሖዋ ቀን እንደዘገየ ከተሰማን ራሳችንን ልናታልል እንችላለን። ‘መንገዳችንን ልብ እንድንል’ እንዲሁም ‘በትክክል ማሰብ እንድንችል’ ራሳችንን እንድናነቃቃ የተሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች መከተላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ‘ይህ ክፉ ሥርዓት እኔ ከጠበቅሁት በላይ መቆየቱ ሊያስገርመኝ ይገባል?’ በማለት ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመጣ የተነበየው ጊዜ

ኢየሱስ ስለዚህ ሥርዓት መደምደሚያ የተናገረውን ነገር እስቲ ቆም ብለህ አስብበት። ጌታ ስለ መጨረሻዎቹ ቀኖች የተናገረውን ትንቢት የያዘው የማርቆስ ዘገባ ኢየሱስ ነቅተን እንድንጠብቅ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እንደሰጠን ያሳያል። (ማር. 13:33-37) በአርማጌዶን ስለሚፈጸመው ታላቁ የይሖዋ ቀን የሚገልጸው ትንቢትም ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ይዟል። (ራእይ 16:14-16) ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሰዎች ረጅም ለሚመስል ጊዜ እንደጠበቁ በሚሰማቸው ወቅት የጥድፊያ ስሜታቸውን የማጣት አዝማሚያ ስለሚታይባቸው እንዲህ ያሉ ማስጠንቀቂያዎችን መስጠት አስፈላጊ ነው።

ኢየሱስ የሥርዓቱን መጨረሻ ስንጠባበቅ ሁልጊዜ ንቁዎች የመሆንን አስፈላጊነት የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሯል። በምሳሌው ላይ ቤቱ በሌባ ስለተዘረፈበት ሰው ጠቅሷል። ግለሰቡ እንዳይሰረቅ ምን ማድረግ ይችል ነበር? ሌሊቱን ሙሉ ነቅቶ መጠበቅ ነበረበት። ኢየሱስ ምሳሌውን ሲደመድም “የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ” የሚል ምክር ሰጥቶናል።​—ማቴ. 24:43, 44

ይህ ምሳሌ፣ ለረጅም ጊዜም ቢሆን እንኳ ለመጠበቅ ራስን የማዘጋጀትን አስፈላጊነት ያጎላል። ይህ ክፉ ሥርዓት ከጠበቅነው በላይ እንደቆየ በማሰብ ከሚገባው በላይ መጨነቅ የለብንም። የይሖዋ ጊዜ “ገና ነው” የሚል የውሸት ምክንያት በማቅረብ ራሳችንን ማታለልም አይኖርብንም። እንዲህ ያለው አመለካከት የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ፍላጎታችንን ያቀዘቅዝብናል።​—ሮም 12:11

የውሸት ምክንያትን ከሥሩ ነቅሎ መጣል

የውሸት ምክንያት ከማቅረብ ጋር በተያያዘ በ⁠ገላትያ 6:7 ላይ የሚገኘው የሚከተለው መሠረታዊ ሥርዓት ጠቃሚ ምክር ይሰጠናል፦ “አትታለሉ . . . አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።” አንድ መሬት ካልተዘራበት አረም ይወርሰዋል። እኛም በትክክል ማሰብ እንድንችል ራሳችንን ካላነቃቃን የውሸት ምክንያቶች በአእምሯችን ውስጥ ሥር ሊሰዱ ይችላሉ። ለምሳሌ ‘የይሖዋ ቀን መምጣቱ ባይቀርም አሁኑኑ ይመጣል ማለት ግን አይደለም’ ብለን እናስብ ይሆናል። የይሖዋ ቀን ስለሚመጣበት ጊዜ ያለን አመለካከት መለወጡ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን በጥድፊያ ስሜት እንዳናከናውን ሊያደርገን ይችላል። ቀስ በቀስ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን ችላ ማለት ልንጀምር እንችላለን። ከዚያም የይሖዋ ቀን ሳናስበው ሊደርስብን ይችላል።​—2 ጴጥ. 3:10

ይሁንና “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ” አዘውትረን በመመርመር የምናረጋግጥ ከሆነ የውሸት ምክንያት በአእምሯችን ውስጥ ሥር አይሰድም። (ሮም 12:2) እንዲህ ለማድረግ ከሚረዱን ወሳኝ ነገሮች አንዱ የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማንበብ ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ይሖዋ ምንጊዜም እሱ በወሰነው ጊዜ እርምጃ እንደሚወስድ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል።​—ዕን. 2:3

ማጥናት፣ መጸለይ፣ አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ መገኘትና በስብከቱ ሥራ መካፈል እንዲሁም በፍቅር ተነሳስተን ደግነት ማሳየት ‘የይሖዋን ቀን መምጣት በአእምሯችን አቅርበን ለመመልከት’ እንድንችል ይረዳናል። (2 ጴጥ. 3:11, 12) እነዚህን ነገሮች በታማኝነት የምናከናውን ከሆነ ይሖዋ ይህን ያስተውላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ካልታከትን ወቅቱ ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው” በማለት አሳስቦናል።​—ገላ. 6:9

ያለንበት ዘመን፣ በውሸት ምክንያት ተታልለን የይሖዋ ቀን ገና ሩቅ እንደሆነ የምናስብበት ጊዜ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ቀን እየቀረበ በመሆኑ ልባችንን ማጽናት ይኖርብናል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አይሁዳውያን የግንባታውን ሥራ እንዲያከናውኑ ሐጌና ዘካርያስ አሳስበዋቸዋል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤቱ ባለቤቶች ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቁ ኖሮ ምን የሚያደርጉ ይመስልሃል?