በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ያውቃችኋል?

ይሖዋ ያውቃችኋል?

ይሖዋ ያውቃችኋል?

“ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል።”​—2 ጢሞ. 2:19

1, 2. (ሀ) ኢየሱስን ምን ነገር ያሳስበው ነበር? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች በቁም ነገር ልናስብባቸው ይገባል?

አንድ ቀን አንድ ፈሪሳዊ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” ሲል መለሰለት። (ማቴ. 22:35-37) ኢየሱስ በሰማይ ለሚኖረው አባቱ ታላቅ ፍቅር የነበረው ሲሆን እነዚህንም ቃላት በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ አድርጓል። በተጨማሪም ኢየሱስ ታማኝ ሆኖ በመኖር አምላክ ለእሱ ያለው አመለካከት በቁም ነገር ያሳስበው እንደነበር አሳይቷል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ትእዛዛቱን በታማኝነት እንደሚጠብቅ ሰው ተደርጎ በአምላክ ዘንድ እንደሚታወቅ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ገልጿል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ከይሖዋ ፍቅር ሳይወጣ ኖሯል።​—ዮሐ. 15:10

2 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ ሰዎች አምላክን እንደሚወዱ ይናገራሉ። እኛም ራሳችንን ከእነዚህ ሰዎች መካከል እንደምንመድብ ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በቁም ነገር ልናስብባቸው ይገባል፦ ‘አምላክ እኔን ያውቀኛል? ይሖዋ ለእኔ ምን ዓይነት አመለካከት አለው? የእሱ ንብረት እንደሆንኩ አድርጎ ያውቀኛል?’ (2 ጢሞ. 2:19) ከአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ጋር እንዲህ ያለ የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንደምንችል ማሰብ እጅግ አስደሳች ነው!

3. አንዳንዶች የይሖዋ ንብረት መሆን እንደማይችሉ ሆኖ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? እንዲህ ያለውን አፍራሽ አስተሳሰብ ለማስወገድስ ምን ይረዳቸዋል?

3 ያም ሆኖ ይሖዋን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች እንኳ ‘አምላክ በግለሰብ ደረጃ ሊያውቀኝ ይችላል’ ብለው ማመን ሊከብዳቸው ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች የዋጋ ቢስነት ስሜት ስለሚሰማቸው የይሖዋ ንብረት መሆን እንደማይችሉ አድርገው ያስባሉ። ይሁንና አምላክ ለእኛ ከዚህ የተለየ አመለካከት እንዳለው ማወቃችን እንዴት የሚያስደስት ነው! (1 ሳሙ. 16:7) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “አንድ ሰው አምላክን የሚወድ ከሆነ አምላክ ይህን ሰው ያውቀዋል” ብሏቸዋል። (1 ቆሮ. 8:3) አምላክ እንዲያውቅህ ከፈለግህ እሱን መውደድ ይኖርብሃል። እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ይህን መጽሔት የምታነበው ለምንድን ነው? ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ ነፍስህ፣ አእምሮህና ኃይልህ ለማገልገል ጥረት የምታደርገውስ ለምንድን ነው? ራስህን ለአምላክ ወስነህ የተጠመቅህ ከሆንክ ደግሞ እነዚህን እርምጃዎች እንድትወስድ ያነሳሳህ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ልብን የሚመረምረው ይሖዋ እንደ ውድ ሀብት አድርጎ የሚያያቸውን ሰዎች ወደ ራሱ እንደሚስባቸው ይገልጻል። (ሐጌ 2:7ን እና ዮሐንስ 6:44ን አንብብ።) እንግዲያው ይሖዋን የምታገለግለው እሱ ወደ ራሱ ስለሳበህ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ታማኞች እስከሆኑ ድረስ አምላክ ወደ እሱ የሳባቸውን ሰዎች ፈጽሞ አይተዋቸውም። አምላክ እነዚህን ሰዎች እጅግ ውድ አድርጎ የሚመለከታቸው ከመሆኑም በላይ በጣም ይወዳቸዋል።​—መዝ. 94:14

4. ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ምንጊዜም ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ ወደ እሱ ከሳበን በኋላ ከፍቅሩ ሳንወጣ ለመኖር ጥረት ማድረግ አለብን። (ይሁዳ 20, 21ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ከእምነት ጎዳና ቀስ በቀስ እየራቀ ሊሄድ አልፎ ተርፎም ከአምላክ ጨርሶ ሊርቅ እንደሚችል ያሳያል። (ዕብ. 2:1፤ 3:12, 13) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 2:19 ላይ ያለውን ሐሳብ ከመናገሩ በፊት ሄሜኔዎስንና ፊሊጦስን ጠቅሷል። እነዚህ ሁለት ሰዎች በአንድ ወቅት የይሖዋ ንብረት የነበሩ ሊሆኑ ቢችሉም በኋላ ላይ ከእውነት ርቀዋል። (2 ጢሞ. 2:16-18) በአምላክ ዘንድ ይታወቁ የነበሩ አንዳንድ የገላትያ ጉባኤ አባላት በመንፈሳዊ ብርሃን ውስጥ መመላለሳቸውን እንዳልቀጠሉም አስታውስ። (ገላ. 4:9) ስለሆነም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ፈጽሞ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም።

5. (ሀ) አምላክ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው አንዳንድ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? (ለ) የትኞቹን ምሳሌዎች እንመለከታለን?

5 ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው አንዳንድ ባሕርያት አሉ። (መዝ. 15:1-5፤ 1 ጴጥ. 3:4) አምላክ ያውቃቸው የነበሩ ሰዎች በእምነታቸውና በትሕትናቸው ተለይተው ይታወቁ ነበር። እነዚህን ባሕርያት በማንጸባረቃቸው በይሖዋ ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ የሁለት ሰዎችን ምሳሌ እንመልከት። በተጨማሪም አምላክ እንደሚያውቀው አድርጎ ቢያስብም ኩራት በሚንጸባረቅበት አካሄዱ የተነሳ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ስላጣ አንድ ሰው እንመለከታለን። ከእነዚህ ምሳሌዎች እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን።

እምነት ላላቸው ሁሉ አባት

6. (ሀ) አብርሃም ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ምን ዓይነት እምነት እንዳለው አሳይቷል? (ለ) ይሖዋ አብርሃምን ያውቀው የነበረው እንዴት ነው?

6 አብርሃም ‘በእግዚአብሔር የሚያምን’ ሰው ነበር። እንዲያውም “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘፍ. 15:6፤ ሮም 4:11) አብርሃም እምነት ስለነበረው ቤቱን፣ ወዳጅ ዘመዶቹንና ያለውን ንብረት ትቶ ወደ ሩቅ አገር ሄዷል። (ዘፍ. 12:1-4፤ ዕብ. 11:8-10) ከበርካታ ዓመታት በኋላም የአብርሃም እምነት ጠንካራ ነበር። የይሖዋን መመሪያ ለመፈጸም ሲል ልጁን “ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ድረስ” በታዘዘበት ጊዜ ይህ በግልጽ ታይቷል። (ዕብ. 11:17-19) አብርሃም ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንዳለው በማሳየቱ በአምላክ ዘንድ እጅግ የተወደደ ነበር፤ በእርግጥም ይሖዋ አብርሃምን በሚገባ ያውቀው ነበር። (ዘፍጥረት 18:19ን በNW አንብብ። *) ይህም ሲባል ይሖዋ፣ አብርሃም በሕይወት ያለ ሰው መሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን እንደ ወዳጁ አድርጎ ይመለከተው ነበር ማለት ነው።​—ያዕ. 2:22, 23

7. አብርሃም ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች አስመልክቶ ምን ነገር ተገንዝቦ ነበር? እንዲህ ያለ እምነት እንደነበረውስ ያሳየው እንዴት ነው?

7 አብርሃም በሕይወት በኖረበት ዘመን፣ ቃል የተገባለትን ምድር እንዳልወረሰ ልብ ሊባል ይገባል። በተጨማሪም ዘሩ “እንደ ባሕር ዳር አሸዋ” ሲሆን አልተመለከተም። (ዘፍ. 22:17, 18) እነዚህ ተስፋዎች አብርሃም በሕይወት እያለ ፍጻሜያቸውን ባያገኙም እንኳ አብርሃም በይሖዋ ላይ ያለውን ጽኑ እምነት ጠብቆ ኖሯል። አምላክ የገባው ቃል መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኛ ነበር። አኗኗሩም ይህን በግልጽ አሳይቷል።። (ዕብራውያን 11:13ን አንብብ።) ይሖዋ እኛንስ እንደ አብርሃም ዓይነት እምነት ያለን ሰዎች እንደሆንን አድርጎ ያውቀናል?

ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቃችን እምነት እንዳለን ያሳያል

8. አንዳንዶች የትኞቹ ነገሮች እውን ሆነው ለማየት ሊጓጉ ይችላሉ?

8 እውን ሆነው ለማየት የምንጓጓላቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆናል። ሰዎች ትዳር የመመሥረት፣ ልጆች የመውለድና ጤናማ ሆኖ የመኖር ተፈጥሯዊ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን እነዚህን ነገሮች መፈለግም ስህተት አይደለም። ያም ሆኖ ብዙዎች የፈለጉትን ሁሉ አያገኙም። የእኛም ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ከሆነ በዚህ ረገድ የምንወስደው እርምጃ እምነታችን ምን ያህል ጥንካሬ እንዳለው ሊያሳይ ይችላል።

9, 10. (ሀ) አንዳንዶች ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ምን አድርገዋል? (ለ) አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን ስለሚያገኙበት መንገድ ምን ይሰማሃል?

9 ከአምላካዊ ጥበብ ጋር የሚቃረን ድርጊት በመፈጸም እንዲህ ያሉ ፍላጎቶችን ለማሟላት መጣር ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው። አንድ ሰው እንዲህ የሚያደርግ ከሆነ መንፈሳዊነቱ ይጎዳል። ለምሳሌ አንዳንዶች ከይሖዋ ምክር ጋር የሚጋጩ የሕክምና ዓይነቶችን ለመቀበል መርጠዋል። ሌሎች ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከጉባኤ ስብሰባዎች ሊያርቋቸው በሚችሉ ሥራዎች ላይ ተቀጥረው ይሠራሉ። ከማያምን ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ስለመመሥረትስ ምን ሊባል ይችላል? አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ጎዳና መከተል ጀምሮ ከሆነ በይሖዋ ዘንድ መታወቅ ይፈልጋል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል? አብርሃም፣ አምላክ የሰጠውን ተስፋ በትዕግሥት መጠባበቅ ቢሳነው ኖሮ ይሖዋ ምን ይሰማው ነበር? አብርሃም ይሖዋን በትዕግሥት ከመጠበቅ ይልቅ በራሱ መንገድ በመሄድ እንደ ቀድሞው በአንድ ቦታ ላይ የተረጋጋ ሕይወት ለመምራትና ስሙን ለማስጠራት መርጦ ቢሆን ኖሮስ? (ከዘፍጥረት 11:4 ጋር አወዳድር።) የይሖዋ ወዳጅ እንደሆነ መቀጠል ይችል ነበር?

10 አንተስ ምን ነገሮች ሲፈጸሙልህ ለማየት ትጓጓለህ? የሚያስፈልጉህን ነገሮች ሁሉ እንደሚያሟላልህ ቃል የገባውን ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠባበቅ የሚያስችል ጠንካራ እምነት አለህ? (መዝ. 145:16) በአብርሃም ላይ እንደታየው ሁሉ አምላክ ከሰጠን ተስፋዎች መካከል አንዳንዶቹ እኛ በፈለግነው ጊዜ ፍጻሜያቸውን አያገኙ ይሆናል። ያም ሆኖ ይሖዋ እንደ አብርሃም ያለ ጠንካራ እምነት ማዳበራችንንና ከዚያ ጋር ተስማምተን ለመኖር ጥረት ማድረጋችንን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። እንዲህ ማድረጋችን ደግሞ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝልን ጥርጥር የለውም።​—ዕብ. 11:6

በትሕትና እና በኩራት መካከል ያለው ልዩነት

11. ቆሬ ምን መብቶች ነበሩት? ይህስ ከአምላክ ጋር ስለነበረው ዝምድና ምን ይጠቁማል?

11 ሙሴና ቆሬ፣ ለይሖዋ ዝግጅት እንዲሁም እሱ ላደረገው ውሳኔ አክብሮት ከማሳየት ጋር በተያያዘ ያላቸው አመለካከት ፈጽሞ የተለያየ ነበር። ያደረጉት ውሳኔ ይሖዋ ለእነሱ ባለው አመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ቆሬ ከቀዓት ወገን የሆነ ሌዋዊ ሲሆን በርካታ መብቶችም ነበሩት። እነዚህም እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ሲሻገሩ መመልከትን፣ ይሖዋ በሲና ተራራ በዓመፀኞቹ እስራኤላውያን ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ መደገፍንና የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክሞ መሄድን የሚያካትቱ ይመስላል። (ዘፀ. 32:26-29፤ ዘኍ. 3:30, 31) ቆሬ ለብዙ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገለ ሲሆን በዚህም የተነሳ በበርካታ እስራኤላውያን ዘንድ አክብሮት አትርፎ ነበር።

12. በገጽ 28 ላይ ያለው ሥዕል እንደሚያሳየው ቆሬ ኩራተኛ መሆኑ ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነት የነካበት እንዴት ነው?

12 ይሁንና የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር እየተጓዘ ሳለ፣ ቆሬ የይሖዋ ዝግጅት አንዳንድ ችግሮች እንዳሉት ሆኖ ተሰማው። ከዚያም የማኅበረሰቡ መሪዎች የነበሩ 250 ሰዎች ለውጥ ለማምጣት በማሰብ ከቆሬ ጋር አበሩ። ቆሬና ግብረ አበሮቹ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳላቸው እርግጠኞች ነበሩ። ሙሴን እና አሮንን እንዲህ አሏቸው፦ “ምነው ከልክ አላለፋችሁም! የማኅበረ ሰቡ አባላት ሁሉ እያንዳንዳቸው የተቀደሱ ናቸው፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነው።” (ዘኍ. 16:1-3) ይህ እንዴት ያለ ከልክ ያለፈ በራስ የመተማመን ስሜትና ኩራት የሚንጸባረቅበት አነጋገር ነው! ሙሴም፣ ይሖዋ ‘የእርሱ የሆነውን ይለያል’ አላቸው። (ዘኍልቍ 16:5ን አንብብ።) በቀጣዩ ቀን አመሻሹ ላይ ቆሬና ከእሱ ጋር ያመፁት ሰዎች ሁሉ ሞቱ።​—ዘኍ. 16:31-35

13, 14. ሙሴ ትሑት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

13 ከቆሬ በተቃራኒ ሙሴ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር።” (ዘኍ. 12:3) ሙሴ የይሖዋን አመራር ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ልኩን የሚያውቅና ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ዘፀ. 7:6፤ 40:16) ሙሴ ይሖዋ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ ጥያቄ አንስቶ አሊያም ይሖዋ የሰጠውን አሠራር በመከተሉ ተበሳጭቶ እንደነበር የሚገልጽ ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ለምሳሌ ያህል፣ የማደሪያው ድንኳን በተሠራበት ወቅት ይሖዋ ጥቅም ላይ የሚውሉትን ክሮች ቀለምና በድንኳኑ ላይ ያሉትን ቀለበቶች ብዛት ጨምሮ ሌሎች ጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (ዘፀ. 26:1-6) በአምላክ ድርጅት ውስጥ የሚያገለግል አንድ የበላይ ተመልካች ጥቃቅን የሚመስሉ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዙ መመሪያዎች የሚሰጥህ ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ትበሳጭ ይሆናል። ይሖዋ ግን ፍጹም የሆነ የበላይ ተመልካች ነው፤ ለሌሎች ብዙ ኃላፊነቶችን የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ አገልጋዮቹ ሥራውን በብቃት እንደሚወጡ ይተማመናል። እንዲሁም በርካታ ዝርዝር መመሪያዎችን የሚሰጥበት በቂ ምክንያት አለው። ያም ሆኖ ሙሴ፣ ይሖዋ እንዲህ ያሉ ዝርዝር መመሪያዎችን ስለሰጠው አልተበሳጨም፤ እንዲሁም ዝቅ አድርጎ እንደተመለከተው አሊያም አዲስ ነገር የመፍጠር ችሎታውን ወይም ነፃነቱን እንደገደበበት ሆኖ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ሙሴ፣ ሠራተኞቹ በአምላክ መመሪያ መሠረት ‘ልክ እንደታዘዙት መሥራታቸውን’ ይከታተል ነበር። (ዘፀ. 39:32) እንዴት ያለ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አካሄድ ነው! ሙሴ ሥራው የይሖዋ መሆኑንና እሱ ሥራውን ለመሥራት የሚያገለግል መሣሪያ ብቻ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።

14 ሙሴ የግል ሕይወቱን የሚመለከቱ አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በገጠሙት ጊዜም ትሑት መሆኑን አሳይቷል። በአንድ ወቅት ሙሴ፣ ሕዝቡ ሲያጉረመርሙ ራሱን መግዛት ስለተሳነው ለይሖዋ ክብር ሳይሰጥ ቀርቶ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ፣ ሙሴ ሕዝቡን ይዞ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደማይገባ ነገረው። (ዘኍ. 20:2-12) ሙሴና ወንድሙ አሮን ለብዙ ዓመታት የእስራኤላውያንን ማጉረምረም ችለው ኖረዋል። ይሁንና ሙሴ በዚህ ጊዜ በፈጸመው አንድ ስህተት የተነሳ ለብዙ ዓመታት በጉጉት ሲጠባበቀው የቆየው ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ ላይመለከት ነው! ሙሴ በዚህ ወቅት ምን ተሰማው? በሁኔታው ሊያዝን እንደሚችል ግልጽ ቢሆንም የይሖዋን ውሳኔ በትሕትና ተቀብሏል። ይሖዋ ጻድቅ አምላክና መንገዱም ሁሉ ትክክል እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ዘዳ. 3:25-27፤ 32:4) ስለ ሙሴ ስታስብ በአምላክ ዘንድ የሚታወቅ ሰው እንደነበር አይሰማህም?​—ዘፀአት 33:12, 13ን አንብብ።

ለይሖዋ መገዛት ትሕትና ይጠይቃል

15. ቆሬ ኩራት የሚንጸባረቅበት ድርጊት መፈጸሙ ካስከተለበት ውድቀት ምን መማር እንችላለን?

15 በዓለም አቀፉ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚደረጉት ማስተካከያዎችና ግንባር ቀደም ሆነው ጉባኤውን የሚመሩ ወንድሞች ለሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች የምንሰጠው ምላሽ ይሖዋ ለእኛ ባለው አመለካከት ላይ ለውጥ ያመጣል። ቆሬና ግብረ አበሮቹ ከልክ በላይ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ኩሩዎችና እምነት የለሾች መሆናቸው ከአምላክ እንዲርቁ አድርጓቸዋል። ቆሬ፣ አረጋዊ የሆነው ሙሴ በየዕለቱ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሲያደርግ ቢመለከትም ብሔሩን የሚመራው ይሖዋ ነበር። ቆሬ ይህን እውነታ ማገናዘብ ስለተሳነው አምላክ ይጠቀምባቸው ለነበሩት ሰዎች ታማኝነት ሳያሳይ ቀርቷል። ቆሬ፣ ይሖዋ ነገሮችን ግልጽ እስኪያደርግ ወይም አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ሁኔታውን እስከሚያስተካክል ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ነበረበት። ቆሬ ኩራት የሚንጸባረቅበት ድርጊት መፈጸሙ ለብዙ ዓመታት ለይሖዋ በታማኝነት ያቀረበውን አገልግሎት ከንቱ አድርጎበታል።

16. ሙሴ በትሕትና ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተላችን ይሖዋ ለእኛ ባለው አመለካከት ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?

16 ይህ ዘገባ በዛሬው ጊዜ ለሽማግሌዎችና በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ይዟል። ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቅና ጉባኤውን ግንባር ቀደም ሆነው እንዲመሩ የተሾሙ ወንድሞች የሚሰጡትን መመሪያ መቀበል ትሑት መሆንን ይጠይቃል። እኛስ ልክ እንደ ሙሴ ትሑትና ገር መሆናችንን እናሳያለን? ግንባር ቀደም ሆነው ጉባኤውን በመምራት ላይ የሚገኙት ወንድሞች ያላቸውን ኃላፊነት እናከብራለን? የሚሰጡንን መመሪያ ተግባራዊ እናደርጋለን? የሚያበሳጭ ነገር ሲገጥመን ስሜታችንን እንቆጣጠራለን? ከሆነ እኛም በይሖዋ ዘንድ የታወቅን እንሆናለን። ትሑትና ታዛዦች ከሆንን የይሖዋ ወዳጆች እንሆናለን።

ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃቸዋል

17, 18. የይሖዋን ሞገስ ላለማጣት ምን ሊረዳን ይችላል?

17 ይሖዋ የሚያውቃቸውና ወደ እሱ የሳባቸው ሰዎች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው። አብርሃምና ሙሴ ልክ እንደ እኛ ፍጽምና የጎደላቸው ከመሆናቸውም ሌላ እንከን የለሽ አልነበሩም። ያም ሆኖ ይሖዋ ያውቃቸውና የእሱ እንደሆኑ አድርጎ ይቆጥራቸው ነበር። ይሁንና የቆሬ ምሳሌ ከይሖዋ ልንርቅና ሞገሱን ልናጣ እንደምንችል ያሳያል። በመሆኑም እያንዳንዳችን እንደሚከተለው ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘ይሖዋ ለእኔ ምን አመለካከት አለው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሰፈሩት ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ትምህርት ማግኘት እችላለሁ?’

18 ይሖዋ ወደ ራሱ የሳባቸውን ታማኝ አገልጋዮቹን የእሱ እንደሆኑ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ማወቅህ በእጅጉ ሊያጽናናህ ይገባል። ይበልጥ በአምላክ እንድትወደድ የሚያደርጉህን እንደ እምነትና ትሕትና ያሉ ባሕርያትን ማዳበርህን ቀጥል። በይሖዋ ዘንድ መታወቅ እጅግ ታላቅ መብት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እርካታ ያለው ሕይወት እንድንመራ ወደፊት ደግሞ ግሩም በረከቶችን እንድንወርስ ያስችለናል።​—መዝ. 37:18

ታስታውሳለህ?

• ከይሖዋ ጋር ምን ዓይነት ውድ ዝምድና ሊኖርህ ይችላል?

• የአብርሃምን ዓይነት እምነት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

• ከቆሬና ከሙሴ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኛም እንደ አብርሃም ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽም እምነት አለን?

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቆሬ የተሰጠውን መመሪያ በትሕትና ለመታዘዝ ፈቃደኛ አልነበረም

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ዘንድ የምትታወቀው መመሪያዎችን በትሕትና በመታዘዝ ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ዘፍጥረት 18:19 (NW)፦ “እኔ ከአብርሃም ጋር የተዋወቅኩት ትክክለኛና ተገቢ የሆነውን ነገር በማድረግ የይሖዋን መንገድ እንዲጠብቁ ልጆቹንና ከእሱ በኋላ የሚመጣውን ቤተሰቡን እንዲያዝዝ ነው።”