በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ጥበብ ያለበትን መመሪያ” በመሻት ጥበበኛ ሁኑ

“ጥበብ ያለበትን መመሪያ” በመሻት ጥበበኛ ሁኑ

“ጥበብ ያለበትን መመሪያ” በመሻት ጥበበኛ ሁኑ

ሕይወት፣ ከጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የሰዎችን የሕይወት አቅጣጫ በተሳካ መንገድ በመምራት ረገድ ሰብዓዊ ጥበብ ያለው ጠቀሜታ ውስን መሆኑ ታይቷል። በመሆኑም ብዙ ሰዎች ማዕበል በሚያናውጠው የሕይወት ባሕር ላይ በሚጓዙበት ወቅት አደጋ ይደርስባቸዋል። (መዝ. 107:23, 27) ለመሆኑ የሕይወት ጉዞ ከባሕር ላይ ጉዞ ጋር መመሳሰሉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

በጥንት ዘመን በባሕር ላይ መጓዝ ተፈታታኝ በመሆኑ ልምድ ይጠይቅ ነበር። አንድ ሰው በዚህ ረገድ ችሎታውን ማዳበር ከፈለገ መርከበኛ በመሆን ተሞክሮ ካካበተ ምናልባትም መርከብ ነጂ ከሆነ ሰው ትምህርት መቅሰም ይኖርበታል። (ሥራ 27:9-11) ጥንታዊ የሆኑ በርካታ ሥዕሎች እንደሚያሳዩት ሰዎች፣ መርከብ ነጂው ወሳኝ ሰው መሆኑን ለማሳየት ከሌሎቹ መርከበኞች ይልቅ ተለቅ አድርገው ይስሉት ነበር። መርከበኞች ዳርቻ ያለው በማይመስለው ባሕር ላይ ለመጓዝ ስለ ነፋስ አቅጣጫ እንዲሁም ስለ ከዋክብትና ስለ ሌሎች አቅጣጫ ጠቋሚ ነገሮች መማር ያስፈልጋቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ መርከበኞችን “ጠቢባን” በማለት ይገልጻቸዋል።​—ሕዝ. 27:8

በዛሬው ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች መፍታት በጥንት ዘመን በባሕር ላይ መጓዝ ተፈታታኝ የሆነውን ያህል አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። ታዲያ በዚህ ረገድ ምን ሊረዳን ይችላል?

‘ጥበብ ያለበት መመሪያ’ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

ከላይ እንደተመለከትነው ሕይወት ከጉዞ ጋር ይመሳሰላል፤ ይህን ዘይቤያዊ አገላለጽ በአእምሮህ በመያዝ ቀጥሎ የተገለጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልብ በል፦ “ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ፤ አስተዋዮችም መመሪያ [“ጥበብ ያለበትን መመሪያ፣” NW] ያግኙበት።” (ምሳሌ 1:5, 6) ‘ጥበብ ያለበት መመሪያ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በጥንት ዘመን የሚኖር አንድ የመርከብ አዛዥ የሚያከናውነውን ተግባር ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። ይህ ቃል፣ ጥበብ በሚንጸባረቅበት መንገድ አቅጣጫን የመምራትና መመሪያ የመስጠት ችሎታን ያመለክታል።

“ጥበብ ያለበትን መመሪያ” በማግኘት በሕይወት ባሕር ላይ የተሳካ ጉዞ ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ መማር እንችላለን፤ እርግጥ ይህን ማድረግ ጥረት ይጠይቃል። የምሳሌ መጽሐፍ እንደሚጠቁመው “ጥበብ” እና “ማስተዋል” ሊኖሩን ይገባል። (ምሳሌ 1:2-6፤ 2:1-9) ክፉ ሰዎችም እንኳ ለመጥፎ ዓላማ ሲሉ ሰዎችን ወደፈለጉት አቅጣጫ ለማዞር ምን ምክር መስጠት እንዳለባቸው የሚያውቁ ከሆነ እኛ ደግሞ የአምላክ መመሪያ ይበልጥ ያስፈልገናል።​—ምሳሌ 12:5

እንግዲያው የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናታችን ወሳኝ ነው። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ስለ ይሖዋና እሱን በመምሰል ረገድ ወደር ስለማይገኝለት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ውድ የሆነ እውቀት መቅሰም እንችላለን። (ዮሐ. 14:9) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይም ጥበብ ያዘሉ ምክሮች እናገኛለን። በተጨማሪም ከወላጆቻችንም ሆነ ከሌሎች ተሞክሮ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።​—ምሳሌ 23:22

ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮችን አስቀድሞ በማሰብ መዘጋጀት

በተለይ በሚናወጥ ባሕር ላይ እንዳለን ሆኖ በሚሰማን ጊዜ ‘ጥበብ ያለበት መመሪያ’ ማግኘታችን አስፈላጊ ነው። ውስብስብ የሆነ አንድ ሁኔታ ሲያጋጥመን መውሰድ ስላለብን እርምጃ ጥርጣሬ የሚገባን ከሆነ ውሳኔ ማድረግ ያቅተናል፤ ይህ ደግሞ አስከፊ መዘዝ ሊያስከትልብን ይችላል።​—ያዕ. 1:5, 6

የሚገርመው ነገር ‘ጥበብ ያለበት መመሪያ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል ከጦርነት ጋር በተያያዘም ተሠርቶበታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ ያለበት አመራር ተቀብለህ ለውጊያ ትወጣለህና፣ ብዙ አማካሪዎችም ባሉበት መዳን ይገኛል” ይላል፤ የ1980 ትርጉም “ጥበብ ያለበት አመራር” የሚለውን ሐረግ “በጥንቃቄ ዕቅድ ማውጣት” በማለት ተርጉሞታል።​—ምሳሌ 20:18፤ 24:6 NW

አንድ የጦር ስልት አዋቂ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት የውጊያ እቅድ እንደሚያወጣ ሁሉ እኛም መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ነገሮችን አስቀድመን ለይተን ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን የተገባ ነው። (ምሳሌ 22:3) ለምሳሌ ያህል፣ አዲስ ሥራ ለመቀጠር ወይም የሥራ እድገት ለመቀበል ከመወሰንህ በፊት ቆም ብለህ ማሰብ ይኖርብህ ይሆናል። እርግጥ ክፍያውን፣ ወደ ሥራ ቦታው ለመሄድና ለመመለስ የሚወስደውን ጊዜ እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ግምት ውስጥ እንደምታስገባ የታወቀ ነው። ይሁንና ልታስብባቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮችም አሉ፤ ለምሳሌ የሥራው ዓይነት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ነው? የፈረቃ ሥራ መሆኑ እንዲሁም ከሥራው ሰዓት ጋር የተያያዙ ሌሎች ነገሮች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቼን ይነኩብኝ ይሆን?​—ሉቃስ 14:28-30

የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ሎሬታ ምግብ በሚያዘጋጅ አንድ ኩባንያ ውስጥ ጥሩ ሥራ ነበራት። ኩባንያው የሥራ ቦታውን ሲቀይር ሎሬታ በአዲሱ አካባቢ ቁልፍ የሆነ ቦታ ተሰጣት። የኩባንያው አስተዳዳሪዎች “ድጋሚ የማይገኝ አጋጣሚ ነው፤ ደግሞም በዚያ አካባቢ የመንግሥት አዳራሽ መኖሩን አረጋግጠናል” በማለት ነገሯት። ይሁን እንጂ ሎሬታ የምትፈልገው ኑሮዋን ቀላል አድርጋ ፈጣሪዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማገልገል ነበር። አዲሱ የሥራ እድገት ለክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቿ የምታውለውን ጊዜ እንደሚሻማባት ተገነዘበች። ከአስተዳዳሪዎቹ አንዱ ይህን የሥራ መደብ መስጠት የሚፈልጉት ለእሷ ብቻ መሆኑን በሚስጥር ቢነግራትም የሥራ መልቀቂያ አስገባች። በዘወትር አቅኚነት በማገልገል በአሁኑ ጊዜ 20 ዓመታት ያስቆጠረችው ሎሬታ መልካም ውጤት ልታገኝ የቻለችው “ጥበብ ያለበትን መመሪያ” ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተከትላ ጥሩ እቅድ በማውጣቷ እንደሆነ እርግጠኛ ናት። ሎሬታ ከይሖዋ ጋር ያላት ዝምድና የተጠናከረ ከመሆኑም በላይ በርካታ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲቀበሉ የመርዳት መብት አግኝታለች።

በቤተሰብ ውስጥም ‘ጥበብ ያለበት መመሪያ’ እንደሚያስፈልግ የተረጋገጠ ነው። ልጆችን ማሳደግ ረጅም ዓመታት የሚያስቆጥር ራሱን የቻለ ሥራ ሲሆን ወላጆች ከመንፈሳዊም ሆነ ከቁሳዊ ነገሮች አንጻር የሚያደረጉት ምርጫ በእያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል የወደፊት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ምሳሌ 22:6) ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያን ወላጆች እንደሚከተለው እያሉ ራሳቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ፦ ‘ልጆቻችን አዋቂ ሲሆኑ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት እንዲችሉ የሚረዷቸውን መንፈሳዊ እሴቶች በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን እያስተማርናቸው ነው? ቀላል ሕይወት በመምራት በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ ማተኮር እርካታ እንደሚያስገኝ ከአኗኗራችን ማስተዋል ይችላሉ?’​—1 ጢሞ. 6:6-10, 18, 19

እውነተኛ ስኬት የሚለካው በዓለም ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች እንደሚያደርጉት ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት ወይም ዝናን በማትረፍ አይደለም። ንጉሥ ሰሎሞን ይህን ተረድቶ ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ “ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች መልካም እንደሚሆንላቸው ዐውቃለሁ” በማለት ጽፎ ነበር። (መክ. 8:12) ይህም በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተና ከቃሉ ጋር የሚስማማ “ጥበብ ያለበትን አመራር” መሻት ጥበብ መሆኑን ያረጋግጣል።​—2 ጢሞ. 3:16, 17

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የመርከብ ነጂ ወሳኝ ሰው መሆኑን ለማሳየት ከሌሎቹ መርከበኞች ይልቅ ተለቅ ተደርጎ ይሳል ነበር

[ምንጭ]

Su concessione del Ministero per i Beni e le Attività Culturali. It is forbidden to reproduce or duplicate this image in any way or by any means.