የዓመታዊ ስብሰባ ሪፖርት
አንድነት የተንጸባረቀበትና አስደሳች ዕቅዶች ይፋ የተደረጉበት ስብሰባ
ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ የሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ስብሰባዎች ምንጊዜም ቢሆን ልዩ ስሜት የሚፈጥሩ ናቸው። ይህ እውነት መሆኑ ቅዳሜ፣ ጥቅምት 1, 2011 በተደረገው 127ኛው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ታይቷል። ከመላው ዓለም የተጋበዙ እንግዶች በኒው ጀርሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ባለችው ጀርሲ ሲቲ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰባስበዋል።
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ የደስታ ስሜት ለሚነበብባቸው ተሰብሳቢዎች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገላቸው። ወደ 85 ከሚሆኑ አገሮች የመጡት ልዑካን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዓለም አቀፋዊ አንድነት እንዳላቸው ገለጸ። እንዲህ ያለው አንድነት ጥሩ ምሥክርነት የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ያስከብራል። እንዲያውም በዚህ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ጎልቶ ሲጠቀስ የነበረው አንድነት ነው።
ከሜክሲኮ የተገኘ መልካም ዜና
በፕሮግራሙ ላይ የቀረበው የመጀመሪያ ክፍል በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን አንድነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው። ወንድም ባልታሳር ፔርላ በማዕከላዊው አሜሪካ የሚገኙት ስድስት ቅርንጫፍ ቢሮዎች በሜክሲኮ ሥር መጠቃለላቸውን አስመልክቶ በሜክሲኮ ቤቴል አብረውት ለሚያገለግሉ ሦስት ወንድሞች ቃለ ምልልስ አደረገላቸው። በዚህ አዲስ ለውጥ የተነሳ በሜክሲኮ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ የተለያዩ ባሕሎች የሚንጸባረቁበትና ከበርካታ አገሮች የመጡ ወንድሞችን ያቀፈ ሊሆን ችሏል። ከተለያዩ አገሮች የመጡ በርካታ የእምነት ባልደረቦች አብረው ማገልገላቸው እርስ በርስ ለመበረታታት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። አምላክ በአገሮች መካከል ያለውን ድንበር በትልቅ ላጲስ ያጠፋው ያህል ነበር።
ስድስቱ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በመታጠፋቸው ምክንያት የተከሰተው አንዱ ተፈታታኝ ሁኔታ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያሉት አስፋፊዎች ከይሖዋ ድርጅት እንደተነጠሉ ሆኖ እንዳይሰማቸው ማድረግ ነው። ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቅረፍ እያንዳንዱ ጉባኤ ሚስጥራዊነቱ አስተማማኝ የሆነ የኢ-ሜይል መስመር ስለተከፈተለት ገለልተኛ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎች ሳይቀሩ ከሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር በቀጥታ መገናኘት ችለዋል።
ከጃፓን የተገኘ ወቅታዊ ዜና
ከጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ የመጣው ወንድም ጄምስ ሊንተን መጋቢት 2011 የተከሰተው የመሬት ነውጥና ሱናሚ፣ አደጋ ባደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙት ወንድሞች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰባቸውንና ንብረታቸውን አጥተዋል። ጉዳት ባልደረሰባቸው የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከ3,100 የሚበልጡ ቤቶችና በመቶዎች የሚቆጠሩ መኪናዎች ሰጥተዋል። የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች ከአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች ጋር በመተባበር አላንዳች ፋታ የወንድሞችን ቤቶች ጠግነዋል። ከ1,700 የሚበልጡ ወንድሞች እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥተዋል። ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣ አንድ ቡድን የመንግሥት አዳራሾችን በማደሱ ሥራ እገዛ ያበረከተ ሲሆን በአጠቃላይ በዚህ ፕሮጀክት 575 የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች ተካፍለዋል።
አደጋው በደረሰባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ እንዲሁም ስሜታዊ ደኅንነት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል። ከ400 የሚበልጡ ሽማግሌዎች በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር እረኝነት የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞች ጠይቀዋል። የበላይ አካሉ፣ ከዋናው መሥሪያ ቤት ሁለት የዞን የበላይ ተመልካቾችን አደጋው ወደደረሰበት አካባቢ በመላክ ማጽናኛ እንዲሰጡ ዝግጅት ማድረጉ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንደሰጠ ያሳያል። በመላው ዓለም የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት አሳቢነት የጃፓን ወንድሞችን በእጅጉ አጽናንቷቸዋል።
ሕግ ነክ ድሎች
ከብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ የመጣው ወንድም ስቲቨን ሃርዲ በቅርቡ የተገኙ ሕግ ነክ ድሎችን በተመለከተ በውይይት የቀረበውን ክፍል ሲመራ ተሰብሳቢዎች በሙሉ ያዳመጡት በከፍተኛ ትኩረት ነበር። ለምሳሌ የፈረንሳይ መንግሥት በዚያ አገር የምንጠቀምበት ማኅበር 82 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ግብር እንዲከፍል ጠይቆ ነበር። የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ የፈረንሳይ መንግሥት ለሃይማኖታዊ ነፃነት ከለላ የሚሰጠውን በአውሮፓ ድንጋጌ ላይ የሚገኘውን አንቀጽ 9 ጥሷል በማለት ለእኛ ስለፈረደልን ጉዳዩ እልባት አግኝቷል። የውሳኔው ቃል በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ለአንድ ሃይማኖታዊ ማኅበር እውቅና መንፈግና እንዲፈርስ ማድረግ እንዲሁም አንድን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ የሚያጥላላ ነገር መናገር በድንጋጌው ላይ ያለው አንቀጽ 9 የሚሰጠውን መብት እንደመጋፋት ይቆጠራል።” በመሆኑም ጉዳዩ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ብቻ አልነበረም።
የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከአርሜንያ መንግሥት ጋር የነበረውን ክርክር በመመልከት ለእኛ ፈርዶልናል። ከ1965 ጀምሮ የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ የአውሮፓ ድንጋጌ ግለሰቦችን ከግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ነፃ ማድረግ ነበረበት የሚል አቋም ይዞ ቆይቶ ነበር። የአውሮፓ የመጨረሻ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሆነው ታላቁ ሸንጎ “አስገዳጅ በሆነ ምክንያት የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆን” መብት በአውሮፓ ድንጋጌ ውስጥ ሊካተት እንደሚገባ ብያኔ አስተላልፏል። ይህ ውሳኔ አርሜንያን ጨምሮ እንደ አዘርባጃንና ቱርክ ያሉ ሌሎች አገሮች ይህን መብት እንዲያከብሩ ያስገድዳል።
የግንባታ ፕሮጀክቶች
ቀጣዩን ንግግር ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጋይ ፒርስ ሲሆን በዚያ የተገኙት ሁሉ በኒው ዮርክ ግዛት ውስጥ ስለሚካሄዱት የግንባታ ፕሮጀክቶች ለማወቅ እንደሚጓጉ ገለጸ። በዎልኪል፣ ፓተርሰን በመካሄድ ላይ ስላለው ግንባታ እንዲሁም በዋርዊክ እና ተክሲዶ፣ ኒው ዮርክ በቅርቡ ስለተገዛው መሬት የሚያሳየውን ቪዲዮ እንዲመለከቱ ጋበዛቸው። በዎልኪል የሚገነባውና በ2014 የሚጠናቀቀው አዲሱ የመኖሪያ ሕንፃ ከ300 የሚበልጡ ክፍሎች ይኖሩታል።
በዋርዊክ፣ 100 ሄክታር በሚሸፍን ስፍራ ላይ የግንባታ ሥራ ለማካሄድ ዕቅድ ተይዟል። ወንድም ፒርስ እንዲህ ብሏል፦ “በዋርዊክ የሚከናወነውን ሥራ በተመለከተ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም የይሖዋ ምሥክሮችን ዋና መሥሪያ ቤት ወደዚህ ለማዘዋወር የሚያስችለንን ግንባታ ለማካሄድ በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን።” በተጨማሪም ከዋርዊክ በስተሰሜን 10 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘውን 20 ሄክታር ስፋት ያለውን አንድ አነስተኛ ቦታ የተለያዩ ማሽኖችንና የግንባታ ቁሳቁሶችን ለማስቀመጫነት ለመጠቀም በዕቅድ ላይ ነው። ወንድም ፒርስ “የግንባታው ፈቃድ እንደተገኘ ጠቅላላውን ፕሮጀክት በአራት ዓመት ውስጥ እናጠናቅቃለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከዚያ በኋላ በብሩክሊን የሚገኘውን ንብረት መሸጥ ይቻላል” ብሏል።
ወንድም ፒርስ “የበላይ አካሉ ታላቁ መከራ መቅረቡን በተመለከተ ያለውን አቋም ለውጧል ማለት ነው?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም “በፍጹም አልለወጠም። ግንባታውን እያከናወንን ሳለ ታላቁ መከራ ቢመጣ እሰየው ነው!” በማለት መልሷል።
ከሚያገሳው አንበሳ ተጠንቀቁ
የበላይ አካል አባል የሆነው ስቲቨን ሌት ደግሞ “የማስተዋል ስሜቶቻችሁን ጠብቁ፤ ንቁዎች ሆናችሁ ኑሩ። ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” የሚለውን በ1 ጴጥሮስ 5:8 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አብራራ። ወንድም ሌት፣ አንበሳ ያሉትን የተለያዩ ባሕርያት መመርመራችን ጴጥሮስ ዲያብሎስን በአንበሳ መመሰሉ ተስማሚ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጿል።
አንበሳ ከሰው የበለጠ ጉልበትና ፍጥነት ስላለው በራሳችን ኃይል ከሰይጣን ጋር ለመታገል ወይም ከእሱ ሮጠን ለማምለጥ መሞከር የለብንም። የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። (ኢሳ. 40:31) አንበሳ የሚያድነው አድብቶ ነው፤ በመሆኑም በሰይጣን እጅ እንዳንወድቅ ከመንፈሳዊ ጨለማ መራቅ ይገባናል። አንበሳ ሰላማዊ የሆነችን ሚዳቋ ወይም በእንቅልፍ ላይ ያለችን የሜዳ አህያ ውርንጭላ ከመግደል የማይመለስ እንደሆነ ሁሉ ሰይጣንም ጨካኝ በመሆኑ እኛን መግደል በጣም ያስደስተዋል። አንበሳ አንድን እንስሳ ቅርጥፍጥፍ አድርጎ ከበላው በኋላ በአብዛኛው የእንስሳውን ምንነት መለየት እንደሚያስቸግር ሁሉ የሰይጣን ሰለባዎችም “ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ” ይሆንባቸዋል። (2 ጴጥ. ) በመሆኑም ሰይጣንን መቃወምና የተማርናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ መከተል ያስፈልገናል።— 2:201 ጴጥ. 5:9
በይሖዋ ቤት ውስጥ ያላችሁን ቦታ ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ
ቀጣዩን ንግግር ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ኸርድ ሲሆን “ሁላችንም በይሖዋ ቤት ውስጥ ቦታ አለን” በማለት ተናገረ። ሁሉም ክርስቲያኖች በአምላክ “ቤት” ማለትም በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ ቦታ አላቸው፤ ይህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት እሱን እንድናመልከው ሲል ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። ይህ ውድ መብት በመሆኑ ከፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ልክ እንደ ዳዊት ‘በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በይሖዋ ቤት መኖር’ እንፈልጋለን።—መዝ. 27:4
ወንድም ኸርድ መዝሙር 92:12-14ን ከጠቀሰ በኋላ “ይሖዋ እንድናብብ የሚያደርገን እንዴት ነው?” ሲል ጠየቀ። ከዚያም መልሱን ሲሰጥ “አምላክ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ተመችቶን እንድንኖር ያደርገናል፣ ከጉዳት ይጠብቀናል፣ እንዲሁም የሚያረካ የእውነት ውኃ ይሰጠናል። ለዚህ ሁሉ ይሖዋን ልናመሰግነው ይገባል” ብሏል። አክሎም “ለአጭር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም በይሖዋ ቤት በመኖራችን እንርካ” በማለት አድማጮቹን አሳሰበ።
ክርስቲያኖች ለአምላክ ቃል አክብሮት አላቸው
በመቀጠል የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን ባቀረበው ንግግር ላይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዳላቸው ገልጿል። በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ስለ ግርዘት ለተነሳው ጥያቄ እልባት ለማስገኘት የተጠቀሙት መጽሐፍ ቅዱስን ነው። (ሥራ 15:16, 17) ይሁን እንጂ የግሪኮችን ፍልስፍና ያጠኑ በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያን ነን ባዮች አዋቂ መስለው ለመታየት ሲሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን ችላ ማለት ጀመሩ። ከጊዜ በኋላም ሌሎች ሰዎች፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይልቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ተብለው የሚጠሩት የሃይማኖት መሪዎችና የሮም ንጉሠ ነገሥታት የሚናገሩትን ነገር ከፍ አድርገው መመልከታቸው በርካታ የሐሰት ትምህርቶች እንዲስፋፉ በር ከፍቷል።
ወንድም ስፕሌን፣ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ምንጊዜም በዚህች ምድር ላይ ለእውነት ጥብቅና የሚቆሙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደማይታጡ የሚጠቁም መሆኑን ተናግሯል። (ማቴ. 13:24-30) እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች እነማን እንደነበሩ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ይሁን እንጂ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ እምነቶችንና ልማዶችን ያጋለጡ በርካታ ሰዎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ነበሩ። ከእነዚህ መካከል በ9ኛው መቶ ዘመን የኖረው የሊዮን ከተማ ሊቀ ጳጳሳት አጎባርድ፣ የብሪው ፒተር፣ የሎዛኑ ሄንሪ፣ በ12ኛው መቶ ዘመን የኖረው ቫልደስ (ወይም ዋልዶ)፣ በ14ኛው መቶ ዘመን የኖረው ጆን ዊክሊፍ፣ በ16ኛው መቶ ዘመን የኖረው ዊልያም ቲንደል እንዲሁም በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩት ሄንሪ ግሩ እና ጆርጅ ስቶርዝ ይገኙበታል። በዛሬው ጊዜም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ከፍ አድርገው ይመለከታሉ፤ እንዲሁም ለእውነት መሠረት አድርገው የሚጠቀሙት መጽሐፍ ቅዱስን ነው። የበላይ አካሉ “ቃልህ እውነት ነው” የሚለውን ዮሐንስ 17:17ን የ2012 የዓመት ጥቅስ እንዲሆን የመረጠው ለዚህ ነው።
ከሥልጠና እና ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የተደረጉ አስደሳች ማስተካከያዎች
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ከሚስዮናውያንና ከልዩ አቅኚዎች ጋር በተያያዘ ማስተካከያዎች መደረጋቸውን አስታወቀ። ከመስከረም 2012 ጀምሮ ለባለትዳሮች የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በተመረጡ አገሮች ውስጥ ይካሄዳል። የጊልያድ ትምህርት ቤት የትኩረት አቅጣጫ ላይም ለውጥ ተደርጓል። ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በጊልያድ ገብተው እንዲሠለጥኑ የሚጠሩት በአንድ ዓይነት የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የተሰማሩ ክርስቲያኖች ማለትም ጊልያድ ያልገቡ ሚስዮናውያን፣ ልዩ አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ወይም ቤቴላውያን ናቸው። ከትምህርት ቤቱ የሚመረቁት ተማሪዎች የአምላክን ሕዝቦች እንዲያጽናኑና እንዲያረጋጉ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ይመደባሉ፤ አንዳንዶቹ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ እንዲያገለግሉ ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንዲሆኑ ሲመደቡ ሌሎቹ ደግሞ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎች በስብከቱ ሥራ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ይላካሉ።
ገለልተኛና ሩቅ በሆኑ አካባቢዎች አዳዲስ ክልሎችን እንዲከፍቱ ተጨማሪ ልዩ አቅኚዎች ይመደባሉ። ከጥር 1, 2012 ጀምሮ ለነጠላ ወንድሞች ከተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እና ለባለትዳሮች ከተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተመረቁ አንዳንድ ተማሪዎች ጊዜያዊ ልዩ አቅኚ ሆነው መመደብ የጀመሩ ሲሆን ዓላማውም ራቅ ባሉ አካባቢዎች አዳዲስ ክልሎችን እንዲከፍቱና የስብከቱን ሥራ እንዲያስፋፉ ማድረግ ነው። እነዚህ ተመራቂዎች ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜያዊ ልዩ አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ይመደባሉ፤ በዚህ መልክ ለሦስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ውጤታማ መሆናቸው ሲረጋገጥ ቋሚ ልዩ አቅኚ እንዲሆኑ ይደረጋል።
የ2011 ዓመታዊ ስብሰባ በጣም አስደሳች ነበር። እነዚህ አዳዲስ ዝግጅቶች የስብከቱ እንቅስቃሴያችን ከፍ እንዲል እንዲሁም የወንድማማች ማኅበራችን አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚያደርጉና በዚህ ረገድ የይሖዋ በረከት እንደማይለየን ተስፋ እናደርጋለን፤ ይህም ለእሱ ክብርና ውዳሴ ያስገኛል።
[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ይበልጥ እንድናውቃቸው አጋጣሚ ፈጥሯል
በዚህ ስብሰባ ላይ ከቀረቡት ፕሮግራሞች አንዱ መበለት ከሆኑ ዘጠኝ የበላይ አካል አባላት ሚስቶች መካከል ለአምስቱ የተደረገው ቃለ ምልልስ ነው። እህት ማሪና ሲድሊክ፣ እህት ኤዲት ሱተር፣ እህት ሜሊታ ጃራዝ፣ እህት ሜልባ ባሪና እህት ሲድኒ ባርበር እውነትን የሰሙትና ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት የገቡት እንዴት እንደሆነ ተናግረዋል። ሁሉም እህቶች ግሩም ትዝታዎቻቸውን፣ ስለ ባሎቻቸው የሚሰማቸውንና አብረው ያገኟቸውን በረከቶች ለአድማጮች አካፍለዋል። በዚያ የተገኙት ሁሉ “ታማኝ ሴቶች፣ ክርስቲያን እህቶች” የሚል ርዕስ ያለውን መዝሙር ቁጥር 86 መዘመራቸው ለቃለ ምልልሱ ስሜት ቀስቃሽ መደምደሚያ ሆኗል።
[ሥዕሎች]
(ከላይ) ማሪና እና ዳንኤል ሲድሊክ፣ ኤዲት እና ግራንት ሱተር፣ ሜሊታ እና ቴዎዶር ጃራዝ
(ከታች) ሜልባ እና ሎይድ ባሪ፣ ሲድኒ እና ኬሪ ባርበር
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ስድስት ቅርንጫፍ ቢሮዎች በሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ተጠቃልለዋል
ሜክሲኮ
ጓቲማላ
ሆንዱራስ
ኤል ሳልቫዶር
ኒካራጉዋ
ኮስታ ሪካ
ፓናማ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዋርዊክ፣ ኒው ዮርክ ሊገነባ የታሰበው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ንድፍ