የእነሱ ትርፍ የሌሎችን ጉድለት ሸፈነ
ጊዜው 49 ዓ.ም. ነው። “እንደ ዓምድ የሚታዩት” ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ለሐዋርያው ጳውሎስና ለአገልግሎት ጓደኛው ለበርናባስ አንድ ተልእኮ ሰጧቸው። እነዚህ አገልጋዮች ለአሕዛብ በሚሰብኩበት ጊዜ በድህነት የተጠቁ ክርስቲያኖችን እንዳይዘነጉ መመሪያ ተሰጣቸው። (ገላ. 2:9, 10) ይህን ኃላፊነታቸውን ዳር ያደረሱት እንዴት ነው?
ጳውሎስ የጻፋቸው ደብዳቤዎች ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መስጠቱን ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለቅዱሳን የሚሰባሰበውን መዋጮ በተመለከተ ደግሞ በገላትያ ለሚገኙ ጉባኤዎች በሰጠሁት መመሪያ መሠረት እናንተም እንዲሁ አድርጉ። መዋጮ የሚሰባሰበው እኔ በምመጣበት ጊዜ እንዳይሆን ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን እንደ ገቢው ሁኔታ የተወሰነ መጠን በቤቱ ያስቀምጥ። በምመጣበት ጊዜ ግን መርጣችሁ የድጋፍ ደብዳቤ የምትጽፉላቸውን ሰዎች የልግስና ስጦታችሁን ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ።”—1 ቆሮ. 16:1-3
ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈስ መሪነት በጻፈላቸው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ገንዘብ የሚሰባሰብበትን ዓላማ በድጋሚ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “የእናንተ ትርፍ የእነሱን ጉድለት እንዲሸፍን፣ . . . ይህም ሸክሙን እኩል እንድትጋሩ” ለማስቻል ነው።—2 ቆሮ. 8:12-15
ጳውሎስ በ56 ዓ.ም. ገደማ በሮም ለሚገኙት ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት መዋጮ የማሰባሰቡ ሥራ ለመጠናቀቅ ተቃርቦ ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ቅዱሳንን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም ልጓዝ ነው። በመቄዶንያና በአካይያ ያሉት ወንድሞች በኢየሩሳሌም ላሉት ችግረኛ የሆኑ ቅዱሳን መዋጮ በመስጠት ያላቸውን ነገር በደስታ አካፍለዋል።” (ሮም 15:25, 26) ጳውሎስ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተልእኮውን አጠናቆ ነበር፤ ምክንያቱም ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሰና በዚያ ተይዞ ከታሰረ በኋላ ለሮማዊው አገረ ገዥ ለፊሊክስ “ለወገኖቼ ምጽዋት ለመስጠትና ለአምላክ መሥዋዕት ለማቅረብ መጣሁ” ብሎ ተናግሯል።—ሥራ 24:17
ጳውሎስ በመቄዶንያ ስላሉ ክርስቲያኖች ከተናገረው ነገር በመነሳት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መንፈስ እንዳሳዩ መረዳት እንችላለን። እነዚህ ክርስቲያኖች “የልግስና ስጦታ ለመስጠት . . . የሚያስችል መብት እንዲሰጣቸው በራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው ይለምኑን” ነበር ሲል ገልጿል። ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችም እንዲከተሉ አሳስቧል። በደብዳቤው ላይ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ” ብሏል። እነዚህ ጉባኤዎች እንዲህ ያለ ልግስና እንዲያሳዩ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ዓላማቸው “ቅዱሳን የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በተትረፈረፈ ሁኔታ እንዲሟሉላቸው” ማድረግ ብቻ ሳይሆን “ለአምላክ በሚቀርብ ብዙ ምስጋና የተሞላ” እንዲሆን ጭምር ነው። (2 ቆሮ. 8:4፤ 9:7, 12) እኛም ልግስና የምናሳየው በተመሳሳይ ዓላማ ተነሳስተን ነው። ይሖዋ አምላክ እንዲህ ያለውን የሚደነቅ፣ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንደሚባርክ የተረጋገጠ ነው፤ በረከቱ ደግሞ አንድን ሰው ባለጸጋ ያደርጋል።—ምሳሌ 10:22
አንዳንዶች ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች
በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ያሉ ብዙ ሰዎች፣ “ለዓለም አቀፉ ሥራ” ተብሎ የተለጠፈባቸው የጉባኤ ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩት “የተወሰነ መጠን” ያለው ገንዘብ ‘ያስቀምጣሉ’ ወይም ይመድባሉ። (1 ቆሮ. 16:2) ጉባኤዎች የተዋጣውን ገንዘብ በአገራቸው ሥራውን ለሚመራው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በየወሩ ይልካሉ። ከዚህ በተጨማሪ አንተም በግለሰብ ደረጃ በአገርህ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚጠቀሙበት ሕጋዊ ተቋም የገንዘብ መዋጮ በቀጥታ መላክ ትችላለህ። በምትኖርበት አገር የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበትን የዋናውን ሕጋዊ ተቋም ስም ለማወቅ በአገሪቱ የሚካሄደውን ሥራ የሚመራውን ቅርንጫፍ ቢሮ ማነጋገር ትችላለህ። የቅርንጫፍ ቢሮው አድራሻ www.dan124.com በተባለው ድረ ገጽ ላይ ይገኛል። ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ዓይነት መዋጮዎች በቀጥታ ለቢሮው መላክ ትችላለህ፦
የገንዘብና የቁሳቁስ መዋጮዎች
የገንዘብ መዋጮ፣ ውድ ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ንብረቶችን መስጠት ይቻላል።
የምትልከው ገንዘብ ወይም ዕቃ በመዋጮ መልክ የተሰጠ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ አያይዘህ ላክ።
ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ የሚሰጥበት ዝግጅት
አንድ ሰው ገንዘብ ሊሰጥና ባስፈለገው ጊዜ ገንዘቡ እንዲመለስለት ሊጠይቅ ይችላል።
የሰጠኸው ገንዘብ እንዲመለስልህ የምትፈልግ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ አያይዘህ ላክ።
በእቅድ የሚደረግ ስጦታ
ገንዘብና ውድ ንብረቶች በስጦታ ከመለገስ በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። እነሱም ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል። መዋጮ ለመስጠት የምትጠቀምበት መንገድ ምንም ሆነ ምን ከቀረቡት አማራጮች መካከል በአገሪቱ የሚሠራባቸው የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ አስቀድመህ አንተ በምትኖርበት አገር ለሚካሄደው ሥራ አመራር የሚሰጠውን ቅርንጫፍ ቢሮ አነጋግር። የየአገሩ ሕጋዊ አሠራሮችና የቀረጥ ደንቦች የተለያዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ መዋጮ የምታደርግበትን የተሻለ መንገድ ከመምረጥህ በፊት ከቀረጥና ከሕግ ጋር በተያያዘ ብቃት ያለው ባለሙያ ማማከርህ በጣም አስፈላጊ ነው።
ኢንሹራንስ፦ በምትኖርበት አገር ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበት ሕጋዊ ተቋም፣ የሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ማዛወር ትችላለህ።
የባንክ ሒሳብ፦ የአገሩ የባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚጠቀሙበት ሕጋዊ ተቋም ሊሰጥ ይችላል።
አክሲዮኖችና ቦንዶች፦ አክሲዮኖችንና ቦንዶችን በስጦታ መልክ ማበርከት ወይም ደግሞ ግለሰቡ ሲሞት የይሖዋ ምሥክሮች ለሚጠቀሙበት ሕጋዊ ተቋም እንዲሰጥ ስም ማዛወር ይቻላል።
የማይንቀሳቀስ ንብረት፦ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚጠቀሙበት ሕጋዊ ተቋም ሊሸጥ ሊለወጥ የሚችል የማይንቀሳቀስ ንብረት በስጦታ መስጠት ወይም መኖሪያ ቤት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ባለ ንብረቱ በሕይወት እስካለ ድረስ ሲጠቀምበት ቆይቶ ከዚያ በኋላ ማውረስ ይቻላል።
የስጦታ አበል፦ አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም የባለቤትነት መብቱን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን የይሖዋ ምሥክሮችን ወክሎ ለሚሠራው ተቋም በስጦታ መልክ መስጠት ይችላል። በምላሹም ለጋሹ ወይም እሱ የወከለው ግለሰብ በሕይወት እስካለበት ጊዜ ድረስ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ በአበል መልክ ይከፈለዋል። ለጋሹ የስጦታ አበሉን ለማስተላለፍ በተስማማበት ዓመት የገቢ ግብር ቅናሽ ያገኛል።
ኑዛዜዎችና አደራዎች፦ ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተቀባይነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮች ለሚጠቀሙበት ሕጋዊ ተቋም በውርስ ሊሰጥ ወይም ሕጋዊ ተቋሙ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዛወር ይችላል። ይህ ዝግጅት ከቀረጥ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጥቅሞች ሊያስገኝ ይችላል።
“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው አገላለጽ፣ እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች የሚያደርገው ግለሰብ እቅድ ማውጣት እንደሚያስፈልገው ይጠቁማል። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ በእቅድ በሚደረግ ስጦታ መደገፍ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ዓለም አቀፉን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ለመደገፍ በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ሰዎች ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ በኑዛዜ ውርስ ለመተው የሚችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች አስመልክቶ መረጃ ለመስጠት ነው። በዚህ ብሮሹር ላይ የቀረበው መረጃ አንተ በምትኖርበት አገር ከሚሠራበት የቀረጥ ወይም ሌሎች ጉዳዮችን ከሚመለከቱ ሕጎች ጋር ሙሉ በሙሉ ላይጣጣም ይችላል። በመሆኑም ይህን ብሮሹር ካነበብክ በኋላ ከሕግ ወይም ከቀረጥ አማካሪዎችህ ጋር መመካከር ይኖርብሃል። በዕቅድ ስጦታ ማድረግ የሚቻልባቸውን እነዚህን ዘዴዎች በመጠቀም ብዙዎች በዓለም ዙሪያ የምናከናውነውን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴና ሰብዓዊ እርዳታ መደገፍ ከመቻላቸውም በላይ ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የተሻለ ጥቅም ማግኘት ችለዋል። ይህ ብሮሹር አንተ ባለህበት አገር ውስጥ የሚገኝ ከሆነ የጉባኤህን ጸሐፊ በመጠየቅ አንድ ቅጂ ማግኘት ትችላለህ።
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከታች ያለውን አድራሻ ወይም ስልክ ቁጥር ተጠቅመህ ቅርንጫፍ ቢሮውን መጠየቅ ትችላለህ። አሊያም ላለህበት አገር ለሥራው አመራር የሚሰጠውን ቅርንጫፍ ቢሮ አነጋግር።