የታሰበበት ዘመቻ ያስገኘው ውጤት
ማሪያ ኢሳቤል በደቡብ አሜሪካ በምትገኘው በቺሊዋ የሳን በርናርዶ ከተማ ውስጥ የምትኖር ቀናተኛ አስፋፊ ናት። ማሪያ ኢሳቤልና ቤተሰቧ የማፑቺ ጎሳ ተወላጅ ናቸው። መላው ቤተሰብ ማፑዱንጉን ተብሎም በሚጠራው የማፑቺ ጎሳ ቋንቋ ጉባኤ እንዲመሠረት ቅንዓት የተሞላበት ጥረት ሲያደርግ ነበር።
የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በማፑዱንጉን ቋንቋም ጭምር እንደሚካሄድ ማስታወቂያ ሲነገርና ለዚህ ዓላማ 2,000 የመጋበዣ ወረቀቶች እንደታተሙ ስታውቅ ማሪያ ኢሳቤል በጉዳዩ ላይ አሰበችበት። ታዲያ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ምን ማድረግ ትችል ይሆን? ለክፍል ጓደኞቻቸውና ለአስተማሪዎቻቸው በመመሥከር ረገድ ስለተሳካላቸው ወጣቶች የሚናገሩ ተሞክሮዎች ትዝ አሏት። በጉዳዩ ላይ ከወላጆቿ ጋር ከተወያየች በኋላ የመጋበዣ ወረቀቶቹን በትምህርት ቤት ብታሰራጭ ጥሩ እንደሚሆን አሰበች። ይሁንና ምን ዓይነት ዘዴ ትጠቀም ይሆን?
በመጀመሪያ በትምህርት ቤቱ ዋና መግቢያ ላይ አንድ የመጋበዣ ወረቀት ለመለጠፍ ኃላፊዎቹን አስፈቀደች። እነሱም ወረቀቱን እንድትለጥፍ የፈቀዱላት ሲሆን እንዲህ ያለ ተነሳሽነት በማሳየቷም አደነቋት። እንዲያውም አንድ ቀን ጠዋት ላይ ደውል ሲደወል የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በድምፅ ማጉያ ተጠቅሞ ስለ በዓሉ ማስታወቂያ ተናገረ!
ከዚያም ማሪያ ኢሳቤል በየክፍሉ እየሄደች ለመጋበዝ ጥያቄ አቀረበች። ከአስተማሪዎቹ ፈቃድ ካገኘች በኋላ በየክፍሉ በመሄድ የማፑቺ ጎሳ አባል የሆኑ ተማሪዎች ይኖሩ እንደሆነ ትጠይቅ ጀመር። ማሪያ ኢሳቤል እንዲህ ብላለች፦ “በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያሉት የማፑቺ ጎሳ አባላት ከ10 ወይም ከ15 እንደማይበልጡ ተሰምቶኝ ነበር። ሆኖም በጣም ብዙ ነበሩ፤ 150 መጋበዣዎችን ማሰራጨት ችያለሁ።”
“የጠበቀችው ትልቅ ሰው ነበር”
አንዲት ሴት፣ በትምህርት ቤቱ በር ላይ የተለጠፈውን ማስታወቂያ ስትመለከት ጉዳዩን በተመለከተ ማንን ማነጋገር እንዳለባት ማጠያየቅ ጀመረች። ይህች ሴት፣ ወደ አንዲት የአሥር ዓመት ልጅ ሲመሯት ምን ያህል ተገርማ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ማሪያ ኢሳቤል ስለ ሴትየዋ ስትናገር ፈገግ ብላ “የጠበቀችው ትልቅ ሰው ነበር” ብላለች። ማሪያ ኢሳቤል ለሴትየዋ የመጋበዣ ወረቀት በመስጠት ስለ ጉዳዩ አጠር አድርጋ አብራራችላት፤ ከዚያም ስለ አምላክ መንግሥት ይበልጥ ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ ከወላጆቿ ጋር ሆና ወደ ቤቷ መምጣት እንድትችል አድራሻዋን ጠየቀቻት። በማፑዱንጉን ቋንቋ የሚያገለግሉ 20 አስፋፊዎች፣ ይህች ሴት ከሌሎች 26 ሰዎች ጋር በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘቷ በጣም ተደስተው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ቡድን በአሁኑ ጊዜ እድገት በማድረግ ላይ የሚገኝ ጉባኤ ነው።
በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ብትሆንም አብረውህ የሚማሩትን ወይም የሚሠሩትን ሰዎች በመታሰቢያው በዓል፣ በሕዝብ ንግግር ወይም በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመጋበዝ ተመሳሳይ ጥረት ታደርጋለህ? በዚህ ረገድ ስኬታማ ለመሆን የሚያስችልህን ሐሳብ ለማግኘት በጽሑፎቻችን ውስጥ በሚገኙ ተሞክሮዎች ላይ ለምን ምርምር አታደርግም? በተጨማሪም ይሖዋ ስለ እሱ ለሌሎች በድፍረት መናገር እንድትችል የሚረዳህን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ በጸሎት ጠይቀው። (ሉቃስ 11:13) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የታሰበበት ጥረትህ በሚያስገኘው ውጤት ልትደሰትና ልትበረታታ ትችላለህ።