መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የተሟላ ጥቅም አግኝ
“በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል።”—ሮም 7:22
1-3. መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ትምህርቶቹን በሥራ ላይ በማዋል ምን ጥቅሞች ማግኘት ይቻላል?
“ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንድችል ስለረዳኝ በየማለዳው አመሰግነዋለሁ።” ይህን የተናገሩት አንዲት አረጋዊት እህት ሲሆኑ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ከ40 ጊዜ በላይ አንብበውታል፤ አሁንም እያነበቡት ነው። አንዲት ሌላ እህት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቧ ይሖዋ እውን እንዲሆንላት እንደረዳት ጽፋለች። በዚህም የተነሳ በሰማይ ወዳለው አባቷ ይበልጥ መቅረብ ችላለች። “በሕይወቴ ውስጥ እንዲህ ተደስቼ አላውቅም” ብላለች።
2 ሐዋርያው ጴጥሮስ ሁሉም ክርስቲያኖች “በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው ያልተበረዘ ወተት ጉጉት” እንዲያዳብሩ ማበረታቻ ሰጥቷል። (1 ጴጥ. 2:2) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይህን ጉጉታቸውን የሚያረኩና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች ንጹሕ ሕሊና ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት ችለዋል። በተጨማሪም እውነተኛውን አምላክ ከሚወዱና ከሚያገለግሉ ጋር ዘላቂ ወዳጅነት መሥርተዋል። እነዚህ ነገሮች “በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ” እንድንሰኝ የሚያደርጉ አሳማኝ ምክንያቶች ናቸው። (ሮም 7:22) ይሁንና ሌሎች ጥቅሞችም አሉት። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
3 ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ይበልጥ እያወቅክ በሄድክ መጠን ለእነሱም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። ትክክለኛውን የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት መቅሰምህ አምላክ በቅርቡ ታዛዥ የሆኑትን የሰው ልጆች ሊጠፋ ከተቃረበው ከዚህ ሥርዓት እንዴት እንደሚያድን እንድትረዳ ያስችልሃል። በአገልግሎት ለሰዎች የምታካፍለው ምሥራች አለህ። የአምላክን ቃል በማንበብ ያገኘኸውን እውቀት ለሌሎች ስታካፍል ይሖዋ ይባርክሃል።
ማንበብና ማሰላሰል
4. መጽሐፍ ቅዱስን “በለሆሳስ” ማንበብ ሲባል ምን ማለት ነው?
4 ይሖዋ አገልጋዮቹ ቃሉን በጥድፊያ እንዲያነቡት አይፈልግም። በጥንት ጊዜ ይኖር የነበረውን ኢያሱን “ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ . . . ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው [“በለሆሳስ አንብበው፣” NW]” ብሎታል። (ኢያሱ 1:8፤ መዝ. 1:2 NW) በዚህ መመሪያ መሠረት ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በሙሉ ቃል በቃል በለሆሳስ ወይም ድምፅህን ዝቅ አድርገህ ማንበብ አለብህ ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለማሰላሰል በሚያስችል መንገድ ረጋ ብለህ ማንበብ አለብህ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን “በለሆሳስ” ማንበብህ በወቅቱ ካለህበት ሁኔታ አንጻር ይበልጥ ሊጠቅሙህና ሊያበረታቱህ በሚችሉ ሐሳቦች ላይ ትኩረት እንድታደርግ ይረዳሃል። እንዲህ ያሉ ሐረጎች፣ ጥቅሶች ወይም ዘገባዎች ስታገኝ ቀስ ብለህ ምናልባትም ምላስህንና ከንፈርህን እያንቀሳቀስክ ልታነባቸው ትችላለህ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ የሚያስተላልፈው ትልቅ ትርጉም ያዘለ መልእክት አንተን በግለሰብ ደረጃ በእጅጉ ሊነካህ ይችላል። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አምላክ በቃሉ አማካኝነት የሚሰጠውን ምክር መረዳትህ ምክሩን በተግባር እንድታውል ስለሚያነሳሳህ ነው።
5-7. የአምላክን ቃል በለሆሳስ ማንበብ (ሀ) በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኖ ለመኖር፣ (ለ) ሌሎችን በትዕግሥትና በደግነት ለመያዝ፣ (ሐ) በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ በይሖዋ ላይ እምነት ለማሳደር፣ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
5 እምብዛም የማታውቃቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በለሆሳስ ማንበብህ ጠቃሚ ነው። ይህን በግልጽ ለመረዳት እስቲ ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት። በመጀመሪያ፣ በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራሙ የሆሴዕን ትንቢት እያነበበ ያለን አንድ ወጣት ወንድም አስብ። ምዕራፍ 4 ላይ ከቁጥር 11 እስከ 13 ድረስ ያለውን ሐሳብ በለሆሳስ ካነበበ በኋላ ቆም ይላል። (ሆሴዕ 4:11-13ን አንብብ።) ለምን? በትምህርት ቤት ውስጥ የሥነ ምግባር ብልግና እንዲፈጽም ተጽዕኖ እየደረሰበት በመሆኑ እነዚህ ጥቅሶች ትኩረቱን ይስቡታል። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ በማሰላሰል ‘ይሖዋ ሰዎች በድብቅ የሚሠሩትን መጥፎ ነገር ሳይቀር ይመለከታል። እሱን ማሳዘን ደግሞ አልፈልግም’ ብሎ ያስባል። በመሆኑም ይህ ወንድም በአምላክ ፊት ንጹሕ ሥነ ምግባር ይዞ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋል።
6 በሁለተኛው ምሳሌ ደግሞ አንዲት እህት የኢዩኤልን ትንቢት እያነበበች ምዕራፍ 2 ቁጥር 13 ላይ ደርሳለች እንበል። (ኢዩኤል 2:13ን አንብብ።) ይህን ጥቅስ በለሆሳስ ስታነብ “መሓሪና ርኅሩኅ፣ ቍጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ” የሆነውን ይሖዋን እንዴት መምሰል እንዳለባት ታሰላስላለች። አንዳንድ ጊዜ ከባሏና ከሌሎች ሰዎች ጋር ስትነጋገር የምትሰነዝራቸውን አሽሙርና ቁጣ ያዘሉ ቃላት በተቻለ መጠን ለማስወገድ ቁርጥ ውሳኔ ታደርጋለች።
7 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ሥራውን በማጣቱ የባለቤቱና የልጆቹ ሁኔታ ያሳሰበውን አንድ ክርስቲያን አባት ለማሰብ ሞክር። ይህ ወንድም ይሖዋ ‘ለሚታመኑበት እንደሚጠነቀቅላቸው፣ በጭንቅ ጊዜም መሸሸጊያ’ በመሆን እንደሚጠብቃቸው የሚገልጸውን ናሆም 1:7 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በለሆሳስ ያነባል። ይህ ሐሳብ ያጽናናዋል። ይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው በማሰብ ከልክ በላይ መጨነቅ እንደሌለበት ይገነዘባል። ከዚያም ቁጥር 15ን በለሆሳስ ያነበዋል። (ናሆም 1:15ን አንብብ።) ይህ ወንድም በአስቸጋሪ ጊዜያት ምሥራቹን መስበኩ ይሖዋን መሸሸጊያው አድርጎ እንደሚመለከተው የሚያሳይ ተግባር እንደሆነ ይገነዘባል። በመሆኑም ወንድም ሰብዓዊ ሥራ መፈለጉን ሳያቋርጥ በሳምንቱ መሃል የሚደረገውን የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴም ለመደገፍ ይነሳሳል።
8. በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ወቅት ያገኘኸውን መንፈሳዊ ዕንቁ በአጭሩ ተናገር።
8 ከላይ የተጠቀሱት ጠቃሚ ሐሳቦች የተወሰዱት አንዳንዶች ለመረዳት አስቸጋሪ እንደሆኑ አድርገው ከሚያስቧቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ነው። ለራስህ የሚሆን ትምህርት ለማግኘት በማሰብ የሆሴዕን፣ የኢዩኤልንና የናሆምን መጻሕፍት በምትመረምርበት ጊዜ በእነዚህ መጻሕፍት ላይ የሚገኙ ሌሎች ጥቅሶችንም በለሆሳስ ማንበብህ ጠቃሚ ነው። እነዚህ ነቢያት ከጻፏቸው መጻሕፍት ምን ያህል ጥበብና ማጽናኛ ልታገኝ እንደምትችል አስብ! ስለ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችስ ምን ማለት ይቻላል? የአምላክ ቃል ብዙ አልማዝ እንደሚገኝበት የማዕድን ማውጫ ነው። በመሆኑም በደንብ መቆፈር ይኖርብሃል! አዎ፣ በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን ዕንቁዎች ይኸውም መለኮታዊ መመሪያዎችና ማጽናኛዎች የማግኘት ግብ ይዘህ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብብ።
ማስተዋል ለማግኘት ጥረት አድርግ
9. ስለ አምላክ ፈቃድ ያለንን ግንዛቤ ማስፋት የምንችለው እንዴት ነው?
9 በየዕለቱ የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ማንበብህ አስፈላጊ የመሆኑን ያህል ጥልቅ ማስተዋልና ግንዛቤ ለማግኘት ጥረት ማድረግህም ጠቃሚ ነው። እንግዲያው እያነበብከው ባለኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የተጠቀሱትን ሰዎች፣ ቦታዎችና ክንውኖች በተመለከተ ጥልቅ ምርምር ለማድረግ የይሖዋ ድርጅት ባዘጋጃቸው ጽሑፎች በሚገባ ተጠቀም። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሕይወትህ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ልታደርግ እንደምትችል ግልጽ ካልሆነልህ የጉባኤህን ሽማግሌ ወይም ሌላ የጎለመሰ ክርስቲያን መጠየቅ ትችላለህ። ግንዛቤያችንን ለማስፋት ጥረት ማድረጋችን ያለውን ጥቅም ለመረዳት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ ለማድረግ ይጥር የነበረን የአንድ ክርስቲያን ምሳሌ እንመልከት። ይህ ሰው አጵሎስ ነው።
10, 11. (ሀ) አጵሎስ የተዋጣለት የምሥራቹ አገልጋይ እንዲሆን እርዳታ የተደረገለት እንዴት ነው? (ለ) ስለ አጵሎስ ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? (“የምታስተምረው ትምህርት ወቅታዊ ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
10 አጵሎስ “ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ” እንዲሁም ‘በመንፈስ የሚቃጠል’ አይሁዳዊ ክርስቲያን ነበር። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስለ እሱ ሲገልጽ “ኢየሱስን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች በትክክል ይናገርና ያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ እሱ የሚያውቀው የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ነበር” ይላል። አጵሎስ አይወቀው እንጂ ስለ ጥምቀት ያስተምረው የነበረው ትምህርት ጊዜ ያለፈበት ነበር። ጵርስቅላና አቂላ የተባሉ ክርስቲያን ባልና ሚስት አጵሎስ በኤፌሶን ሲያስተምር በሰሙት ጊዜ “የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል አብራሩለት።” (ሥራ 18:24-26) ይህ አጵሎስን የጠቀመው እንዴት ነው?
11 አጵሎስ በኤፌሶን ከሰበከ በኋላ ወደ አካይያ ሄደ። “እዚያ በደረሰ ጊዜም ከአምላክ ጸጋ የተነሳ አምነው የነበሩትን በእጅጉ ረዳቸው፤ ምክንያቱም ከአይሁዳውያን ጋር የጦፈ ክርክር በማድረግ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ በማስረዳት በይፋ ይረታቸው ነበር።” (ሥራ 18:27, 28) በዚህ ጊዜ አጵሎስ ክርስቲያናዊ ጥምቀት ያለውን ትርጉም በትክክል ማስረዳት ችሎ ነበር። ያገኘውን አዲስ እውቀት በመጠቀም አዳዲስ አማኞች በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ እድገት እንዲያደርጉ “በእጅጉ ረዳቸው።” ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? እኛም እንደ አጵሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናነበውን ነገር ለመረዳት ጥረት እናደርጋለን። ይሁንና አንድ ተሞክሮ ያለው የእምነት ባልንጀራችን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት ማስተማር እንደምንችል ሲጠቁመን የሰጠንን ሐሳብ በትሕትናና በአመስጋኝነት መንፈስ መቀበል ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ጥራት ይሻሻላል።
ያገኘኸውን እውቀት ሌሎችን ለመርዳት ተጠቀምበት
12, 13. የአምላክን ቃል በጥበብ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት እንዲያደርጉ እንዴት መርዳት እንደሚቻል በምሳሌ አስረዳ።
12 እንደ ጵርስቅላ፣ አቂላና አጵሎስ ሁሉ እኛም ለሌሎች በረከት መሆን እንችላለን። አንድ ፍላጎት ያሳየ ሰው የሰጠኸው ማበረታቻ መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርግ እንቅፋት የሆነበትን ነገር መወጣት እንዲችል እንደረዳው ስታውቅ ምን ይሰማሃል? ሽማግሌ ከሆንክ ደግሞ አንድ የእምነት አጋርህ፣ የሰጠኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የገጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም እንዲችል እንደረዳው በመግለጽ ሲያመሰግንህ ምን ይሰማሃል? የአምላክን ቃል በመጠቀም ሌሎች ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት መቻል ደስታና እርካታ እንደሚያስገኝ ጥርጥር የለውም። * ይህን ግብ ዳር ማድረስ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
13 በኤልያስ ዘመን የነበሩ በርካታ እስራኤላውያን ከእውነተኛውና ከሐሰተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ መሃል ሰፋሪ ነበሩ። ኤልያስ ለሕዝቡ የሰጠው ምክር፣ እየወላወለ ያለን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ሊረዳው ይችላል። (1 ነገሥት 18:21ን አንብብ።) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ፍላጎት ያሳየ ሰው ጓደኞቼ ወይም ቤተሰቦቼ ሊቃወሙኝ ይችላሉ የሚል ፍራቻ ካለው ኢሳይያስ 51:12, 13ን ተጠቅመህ ይሖዋን ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርግ ልትረዳው ትችላለህ።—ጥቅሱን አንብብ።
14. ሌሎችን መርዳት ትችል ዘንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለማስታወስ ምን ሊረዳህ ይችላል?
14 መጽሐፍ ቅዱስ ሊያበረታቱ፣ እርማት ሊሰጡ ወይም ሊያጠነክሩ የሚችሉ በርካታ ሐሳቦችን እንደያዘ ግልጽ ነው። ይሁንና ‘አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ተስማሚ ጥቅሶችን መጥቀስ የምችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን አንብብ እንዲሁም ባነበብከው ሐሳብ ላይ አሰላስል። በዚህ መንገድ በርካታ ጥቅሶችን በአእምሮህ መያዝ የምትችል ሲሆን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የይሖዋ መንፈስ እነዚህን ጥቅሶች እንድታስታውስ ይረዳሃል።—ማር. 13:11፤ ዮሐንስ 14:26ን አንብብ። *
15. የአምላክን ቃል በተሻለ ሁኔታ መረዳት እንድትችል ምን ሊረዳህ ይችላል?
15 እንደ ንጉሥ ሰለሞን አንተም ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችህን መወጣት እንድትችል ጥበብ እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (2 ዜና 1:7-10) እንደ ጥንቶቹ ነቢያት ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት በአምላክ ቃል ላይ “ትጋት የተሞላበት ምርምርና ጥልቅ ጥናት” አድርግ። (1 ጴጥ. 1:10-12) ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‘የእምነትን ቃሎችና መልካሙን ትምህርት’ እንዲመገብ አበረታቶታል። (1 ጢሞ. 4:6) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት የሚያስችል የተሻለ ብቃት ይኖርሃል። ከዚህም በተጨማሪ የራስህን እምነት ታጎለብታለህ።
የአምላክ ቃል አስተማማኝ ጥበቃ ያስገኝልናል
16. (ሀ) የቤርያ ሰዎች ‘በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ መመርመራቸው’ የጠቀማቸው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
16 በመቄዶንያ፣ ቤርያ በተባለች ከተማ ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን “በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ [የመመርመር]” ልማድ ነበራቸው። ጳውሎስ ምሥራቹን ሲሰብክላቸው የሰሙትን ነገር ቀደም ሲል ከነበራቸው የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት ጋር አወዳድረው ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? ብዙዎች እውነትን እንደሚያስተምር ስለተገነዘቡ “አማኞች ሆኑ።” (ሥራ 17:10-12) ከዚህ ዘገባ መረዳት እንደምንችለው በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ይረዳናል። ከጥፋት ተርፈን አምላክ ወደሚያመጣው አዲስ ዓለም መግባት ከፈለግን እንዲህ ያለ እምነት ማዳበር ማለትም “ተስፋ የተደረጉ ነገሮችን በእርግጠኝነት መጠበቅ” ይኖርብናል።—ዕብ. 11:1
17, 18. (ሀ) ጠንካራ እምነትና ፍቅር የአንድን ክርስቲያን ምሳሌያዊ ልብ ሊጠብቁ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ተስፋ ከአደጋ ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው?
17 ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ መጻፉ ተገቢ ነው፦ “የብርሃን ሰዎች የሆንነው እኛ ግን የማመዛዘን ችሎታችንን እንጠብቅ እንዲሁም የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ፤ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንድፋ።” (1 ተሰ. 5:8) አንድ ወታደር ልቡ በጠላት ጥቃት እንዳይደርስበት መከላከያ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም የአንድ ክርስቲያን ምሳሌያዊ ልብ በኃጢአት እንዳይጠቃ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል። አንድ የይሖዋ አገልጋይ አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት ሲገነባ እንዲሁም ለይሖዋና ለሌሎች ሰዎች ጥልቅ ፍቅር ሲያድርበት ምሳሌያዊ ልቡን ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ጥሩር ይኖረዋል። በመሆኑም የአምላክን ሞገስ የሚያሳጣ ነገር ሊፈጽም የሚችልበት አጋጣሚ የጠበበ ይሆናል።
18 ከዚህም ሌላ ጳውሎስ ‘የመዳን ተስፋ’ የሆነውን የራስ ቁር ጠቅሷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረ አንድ ወታደር ጭንቅላቱን ከጥቃት የሚጠብቅ ነገር ካላደረገ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ሕይወቱን በቀላሉ ሊያጣ ይችላል። ይሁንና ጠንካራ የሆነ የራስ ቁር ካደረገ በጭንቅላቱ ላይ ጥቃት ቢሰነዘርበትም እንኳ ከባድ ጉዳት አይደርስበትም። እኛም ቃሉን በማጥናት በይሖዋ የማዳን ኃይል ላይ ተስፋችንን እንገነባለን። ጠንካራ ተስፋ ካለን ከሃዲዎችም ሆኑ እንደተመረዘ ቁስል የሆነው ‘ከንቱ ንግግራቸው’ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መቋቋም እንችላለን። (2 ጢሞ. 2:16-19) በተጨማሪም ሌሎች በይሖዋ ዘንድ የተወገዘ ድርጊት እንድንፈጽም ሲገፋፉን እምቢ ለማለት የሚያስችል ጥንካሬ ይኖረናል።
ለመዳን ወሳኝ ነው
19, 20. የአምላክን ቃል ከፍ አድርገን የምንመለከተው ለምንድን ነው? ለቃሉ ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለውስ እንዴት ነው? (“ይሖዋ የሚያስፈልገኝን ነገር ሰጥቶኛል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
19 ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረብን በሄድን መጠን በይሖዋ ቃል ላይ ይበልጥ መታመን ያስፈልገናል። ቃሉ የሚሰጠን ምክር መጥፎ ልማዶችን እንድናስወግድና የኃጢአት ዝንባሌዎቻችንን እንድንቆጣጠር ይረዳናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው ማበረታቻና ማጽናኛ ሰይጣንም ሆነ እሱ የሚገዛው ዓለም የሚያመጡብንን ፈተናዎች እንድንቋቋም ያስችለናል። ይሖዋ በቃሉ በኩል የሚሰጠንን አመራር ተከትለን ወደ ሕይወት በሚመራው መንገድ ላይ መጓዛችንን እንቀጥላለን።
20 አምላክ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ” እንደሚፈልግ አትዘንጋ። የይሖዋ አገልጋዮች ‘ከሁሉም ዓይነት ሰዎች’ የተውጣጡ ናቸው። የምንሰብክላቸውና የምናስተምራቸው ሰዎችም ቢሆኑ የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ናቸው። ይሁንና መዳን የሚፈልጉ ሁሉ “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት” ማግኘት አለባቸው። (1 ጢሞ. 2:4) በመሆኑም የመጨረሻዎቹን ቀናት በሕይወት ማለፍ መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብና በውስጡ የሚገኙትን በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መመሪያዎች በተግባር ከማዋል ጋር የተቆራኘ ነገር ነው። አዎ፣ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን ውድ የሆነውን የይሖዋን ቃል ምን ያህል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ያሳያል።—ዮሐ. 17:17
^ စာပိုဒ်၊ 12 እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ሌሎችን ለመጫን ወይም ለማውገዝ አንጠቀምበትም። የይሖዋን ምሳሌ በመከተል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ትዕግሥትና ደግነት ልናሳያቸው ይገባል።—መዝ. 103:8
^ စာပိုဒ်၊ 14 የአንድን ጥቅስ ዋና ሐሳብ አስታውሰህ ጥቅሱ የሚገኝበት መጽሐፍ፣ ምዕራፍና ቁጥር ቢጠፋህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ያስታወስካቸውን ቃላት በአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ጀርባ በሚገኘው ማውጫ፣ በዎችታወር ላይብረሪ፣ ወይም በአዲስ ዓለም ትርጉም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማውጫ (ኮንኮርዳንስ) ላይ በመፈለግ ጥቅሱን ማግኘት ትችላለህ።