ተለውጣችኋል?
“አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።”—ሮም 12:2
1, 2. አስተዳደጋችንና አካባቢያችን ተጽዕኖ የሚያደርጉብን እንዴት ነው?
ሁላችንም ቢሆን አስተዳደጋችንና አካባቢያችን ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረውብናል። አሁን ያለን አለባበስ፣ የምግብ ምርጫና ባሕርይ ሊመጣ የቻለው በተወሰነ መጠን በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች እንዲሁም በሕይወታችን ያጋጠሙን ነገሮች ተጽዕኖ ስላደረጉብን ነው።
2 እርግጥ ነው፣ ከምግብና ከአለባበስ ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ከልጅነታችን ጀምሮ ምን ነገር ትክክል እንደሆነ ወይም ተቀባይነት እንዳለው አሊያም ምን ነገር ስህተት እንደሆነ ወይም ተቀባይነት እንደሌለው ስንማር ኖረናል። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ግን የግል ጉዳይ በመሆናቸው ሰዎች የሚወስዱት ምርጫ ከግለሰብ ወደ ግለሰብ ይለያያል። በተጨማሪም ሕሊናችን በምናደርጋቸው ምርጫዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። አብዛኛውን ጊዜ “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ በተፈጥሮ በሕጉ ውስጥ ያሉትን ነገሮች [እንደሚያደርጉ]” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮም 2:14) ታዲያ እንዲህ ሲባል በአምላክ ቃል ውስጥ ስለ አንድ ነገር በግልጽ የተቀመጠ ሕግ ከሌለ ያደግንበትን ወይም በአካባቢያችን የተለመደውን መንገድ ለመከተል ነፃነት አለን ማለት ነው?
3. ክርስቲያኖች፣ ሰዎች በተለምዶ የሚከተሏቸውን መንገዶችና የሚመሩባቸውን መሥፈርቶች የማይቀበሉት በየትኞቹ ሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው?
3 ክርስቲያኖች እንዲህ የማያደርጉባቸው ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው ምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።” (ምሳሌ 16:25) ፍጽምና የሚጎድለን በመሆናችን በእርግጥ የሚጠቅመንን ማወቅና አካሄዳችንን ፍጹም በተቃና መንገድ መምራት አንችልም። (ምሳሌ 28:26፤ ኤር. 10:23) ሁለተኛው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ዓለም ከሚከተላቸው ልማዶችና መሥፈርቶች በስተ ጀርባ ያለው “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው ሰይጣን ስለሆነ ነው። (2 ቆሮ. 4:4፤ 1 ዮሐ. 5:19) በመሆኑም የይሖዋን በረከትና ሞገስ ማግኘት ከፈለግን በሮም 12:2 (ጥቅሱን አንብብ።) ላይ የሚገኘውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን ነገሮችን እንመረምራለን?
4 ይህ ርዕስ በሮም 12:2 ላይ የሚገኙ ትኩረታችንን የሚስቡ ጠቃሚ ነጥቦች ይዟል፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦ (1) ‘መለወጥ’ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (2) መለወጥ ምን ነገሮችን ይጨምራል? እና (3) መለወጥ የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች እንመርምር።
መለወጥ ለምን አስፈለገ?
5. በሮም 12:2 ላይ የሚገኘው ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ ልዩ ትርጉም የነበረው ለእነማን ነው?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም የላከውን ደብዳቤ የጻፈው የሮምን ሕዝብ በጅምላ አስቦ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ደብዳቤውን የጻፈው እንደ እሱ በመንፈስ ለተቀቡ ክርስቲያኖች ነው። (ሮም 1:7) ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች እንዲለወጡና “የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ [እንዲያቆሙ]” አጥብቆ መክሯቸዋል። በዚያ ወቅት ማለትም በ56 ዓ.ም. በሮም ለሚኖሩት ክርስቲያኖች “ሥርዓት” የሚለው ቃል ሮማውያን ተለይተው የሚታወቁበትን መሥፈርት፣ ባሕል፣ ምግባርና የአኗኗር ዘይቤ ያመለክት ነበር። ጳውሎስ “አቁሙ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ በዚያ የነበረው ሥርዓት በአንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ ተጽዕኖ እያደረገባቸው እንደነበረ ያሳያል። ይሁንና በዚያን ጊዜ በነበሩት ወንድሞችና እህቶች ላይ ሥርዓቱ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው እንዴት ነው?
6, 7. በጳውሎስ ዘመን በሮም የነበረው ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወት ለክርስቲያኖች ተፈታታኝ የሆነባቸው እንዴት ነው?
6 በዛሬው ጊዜ ሮምን የሚጎበኙ ቱሪስቶች በጥንት ጊዜ የነበሩ ቤተ መቅደሶችን፣ የመቃብር ሥፍራዎችን፣ ሐውልቶችን እንዲሁም የስፖርትና የኪነ ጥበብ ማሳያ ስፍራዎችን ብሎም ሌሎች ቅርሶችን ማየታቸው አይቀርም። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የተሠሩት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ነው። እነዚህ ቅርሶች በጥንቷ ሮም የነበረው ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበረ ይጠቁማሉ። በተጨማሪም በሮም ውስጥ ከሰውና ከእንስሳ ጋር የሚደረጉ ዘግናኝ ፍልሚያዎች፣ የሠረገላ ውድድሮች እንዲሁም የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ቲያትሮችና ሙዚቃዎች ይቀርቡ እንደነበር ከታሪክ መጻሕፍት ማንበብ እንችላለን፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የብልግና ይዘት ያላቸው ናቸው። በተጨማሪም ሮም የንግድ ማዕከል ስለነበረች ሰዎች በቁሳዊ ለመበልጸግ የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎች ነበሯቸው።—ሮም 6:21፤ 1 ጴጥ. 4:3, 4
7 ሮማውያን፣ በውስጣቸው የተለያዩ አማልክቶች ያሉባቸው በርካታ ቤተ መቅደሶች የነበሯቸው ቢሆንም ከአማልክቶቻቸው ጋር ልባዊ የሆነ የቅርብ ዝምድና የመመሥረት ልማድ አልነበራቸውም። ለእነሱ ሃይማኖት ከልደት፣ ከጋብቻና ከሞት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ያሉበት የማኅበራዊ ሕይወት አንዱ ገጽታ ነው። ይህ ሁሉ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን ያህል ተፈታታኝ ሊሆንባቸው እንደሚችል መገመት አያዳግትም። አብዛኞቹ ደግሞ ቀደም ሲል እንዲህ ያለ ሕይወት ይመሩ ስለነበር እውነተኛ ክርስቲያን ለመሆን መለወጥ ያስፈልጋቸው እንደነበረ ግልጽ ነው፤ ለውጡ ደግሞ በተጠመቁበት ቀን የሚያበቃ አይደለም።
8. ይህ ዓለም ለክርስቲያኖች ተፈታታኝ የሆነው በምን መንገድ ነው?
8 ልክ እንደ ጥንቷ ሮም ሁሉ የምንኖርበት ዓለምም ራሳቸውን ለወሰኑ ክርስቲያኖች ተፈታታኝ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የዓለም መንፈስ በተለያዩ መንገዶች ተጽዕኖ ስለሚያደርግብን ነው። (ኤፌሶን 2:2, 3ን እና 1 ዮሐንስ 2:16ን አንብብ።) በእያንዳንዷ ዕለት ለዚህ ዓለም ፍላጎት፣ አስተሳሰብ፣ እሴት እንዲሁም የሥነ ምግባር አቋም የተጋለጥን በመሆናችን በዓለም የመዋጥ አደጋ አጥልቶብናል። በመሆኑም “የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ አቁሙ” የሚለውን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ለማድረግና ‘ለመለወጥ’ በቂ ምክንያት አለን። ታዲያ እኛ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
መለወጥ የሚኖርበት ምንድን ነው?
9. ብዙዎች ለመጠመቅ ብቁ እንዲሆኑ ምን ዓይነት ለውጦች አድርገዋል?
9 አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሲማርና የተማረውን ተግባራዊ ሲያደርግ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ይጀምራል። መንፈሳዊ እድገት ማድረጉ ደግሞ በተማረው መሠረት እንዲለወጥ ያነሳሳዋል። ከዚያም የሐሰት ሃይማኖት ልማዶችንና ቀደም ሲል የነበሩትን መጥፎ ምግባሮች በማስወገድ የክርስቶስ ዓይነት ስብዕና ያዳብራል። (ኤፌ. 4:22-24) በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ያለ እድገት አድርገው ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ሲያሳዩ መመልከት የሚያስደስት ነው። በወሰዱት እርምጃ የይሖዋ ልብ እንደሚደሰት እርግጠኞች ነን። (ምሳሌ 27:11) ይሁንና ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ ‘ታዲያ እነዚህ ሰዎች ከዚህ በኋላ መለወጥ አያስፈልጋቸውም ማለት ነው?’ የሚለው ነው።
10. መለወጥ ከመሻሻል የሚለየው እንዴት ነው?
10 እርግጥ ነው፣ መለወጥ እድገት ከማድረግ ወይም ከመሻሻል ባሻገር ሌሎች ነገሮችንም ይጨምራል። አንድ ምርት ‘ተሻሽሎ የቀረበ’ የሚል ጽሑፍ ይለጠፍበት ይሆናል፤ ሆኖም ምርቱ ከበፊቱ ምንም ለውጥ ላይኖረው ይችላል። ምናልባትም አንድ አዲስ ንጥረ ነገር ገብቶበት ይሆናል፤ አሊያም ማሸጊያው ይበልጥ ማራኪ ተደርጎ ሊሆን ይችላል። በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ “ተለወጡ” የሚለውን ቃል ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “በሮም 12:2 ላይ በዚህ ዘመን [ወይም ሥርዓት] ውስጥ ባሉ ነገሮች ውጫዊ ለውጥ ማድረግ መንፈስ ቅዱስ ባለው ኃይል አማካኝነት ውስጣዊ አስተሳሰብን ከማደስ ጋር ተነጻጽሯል።” በመሆኑም ክርስቲያኖች የሚያደርጉት ለውጥ መጥፎ ልማዶችን፣ ጸያፍ አነጋገሮችንና የብልግና ድርጊቶችን ማስወገድ ብቻ የሚያመለክት አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የሌላቸው አንዳንድ ሰዎችም እንኳ ከእነዚህ ነገሮች ለመራቅ የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። ታዲያ የአንድ ክርስቲያን ለውጥ ምን ነገሮችን ሊያካትት ይገባል?
11. ጳውሎስ ለውጥ ለማድረግ ምን ነገር እንደሚያስፈልግ ገልጿል?
11 ጳውሎስ “አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ” በማለት ጽፏል። ‘አእምሮ’ የሚያመለክተው ሐሳብ የሚመነጭበትን ቦታ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ግን ዝንባሌያችንን፣ አመለካከታችንንና የማሰብ ችሎታችንን ጭምር ለማመልከት ነው። ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘ተቀባይነት የሌለው አስተሳሰብ’ ስላዳበሩ ሰዎች ተናግሮ ነበር። እነዚህ ሰዎች “በዓመፅ፣ በኃጢአተኝነት፣ በመጎምጀት፣ በክፋት፣ በቅናት፣ በነፍሰ ገዳይነት፣ በጥል፣ በማታለልና” በሌሎች ጎጂ ድርጊቶች የተሞሉ ነበሩ። (ሮም 1:28-31) በመሆኑም ጳውሎስ እንዲህ ባለ ሁኔታ ላደጉና በኋላ ላይ የአምላክ አገልጋይ ለሆኑ ክርስቲያኖች ‘መለወጥና አእምሯቸውን ማደስ’ እንደሚኖርባቸው መናገሩ ተገቢ ነው።
‘ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከእናንተ መካከል ይወገድ።’—ኤፌ. 4:31
12. በዛሬው ጊዜ ያሉ የአብዛኞቹ ሰዎች አመለካከት ምንድን ነው? ይህ አስተሳሰብ ለክርስቲያኖች አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?
12 የሚያሳዝነው ዛሬም የምንኖረው ጳውሎስ የጠቀሳቸው ዓይነት ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። እነዚህ ሰዎች በመሥፈርቶች ወይም በመሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ጊዜ ያለፈበትና የማያፈናፍን እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። በርካታ አስተማሪዎችና ወላጆች ልል አቋም ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ለልጆች “ነፃነት” እንደሚሰጡ ይናገራሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሚባል ነገር እንደሌለና ሁሉም ነገር አንጻራዊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ብዙ ሰዎችም እንኳ አምላክንና ሕግጋቱን መታዘዝ ሳያስፈልጋቸው ትክክል ነው ብለው ያመኑበትን ነገር የማድረግ ነፃነት እንዳላቸው ይሰማቸዋል። (መዝ. 14:1) ይህ አመለካከት ለእውነተኛ ክርስቲያኖች አደገኛ ነው። አንዳንዶች ባለመጠንቀቃቸው ከቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶች ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ አመለካከት አዳብረዋል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አሠራሮችን ለመከተል ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ፤ እንዲያውም ለእነሱ የማይጥማቸውን ነገር ሁሉ ሊተቹ ይችላሉ። አሊያም መዝናኛን፣ የኢንተርኔት አጠቃቀምን እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት መከታተልን በተመለከተ የሚሰጡትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶች ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ።
13. ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?
13 እንግዲያው የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ እንዳንኮርጅ ወይም በሥርዓቱ እንዳንቀረጽ ውስጣዊ ማንነታችንን፣ ፍላጎታችንን፣ ግቦቻችንንና እሴቶቻችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። እነዚህ ነገሮች ከሰዎች የተሰወሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባትም ሌሎች ጥሩ እያደረግን እንደሆነ ይነግሩን ይሆናል። ያም ቢሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርነው ነገር በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ በእርግጥ ለውጦን እንደሆነና ወደፊትም መለወጣችንን እንደምንቀጥል ልናውቅ የምንችለው እኛ ብቻ ነን።—ያዕቆብ 1:23-25ን አንብብ።
ለውጡ የሚከናወነው እንዴት ነው?
14. አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?
14 ለውጡ የሚካሄደው በውስጣዊው ማንነታችን ላይ ነው፤ ስለዚህ በዚያ የሚገኘውን መጥፎ ነገር ለመለወጥ ውስጥ ድረስ ዘልቆ ሊገባ የሚችል ነገር ያስፈልጋል። ታዲያ እንዲህ ለማድረግ ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ይሖዋ ምን ዓይነት ሰው እንድንሆን እንደሚፈልግ እንማራለን። በዚህ ወቅት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ላነበብነው ነገር የምንሰጠው ምላሽ በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ይገልጣል። ይህ ደግሞ ‘ፍጹም ከሆነው የአምላክ ፈቃድ’ ጋር ለመስማማት ምን ማስተካከያዎችን ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ ይረዳናል።—ሮም 12:2፤ ዕብ. 4:12
15. በይሖዋ መቀረጽ ምን ዓይነት ለውጥ ያስገኛል?
15 ኢሳይያስ 64:8ን አንብብ። ነቢዩ ኢሳይያስ የተጠቀመው ዘይቤያዊ አገላለጽ ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባ አንድ ነጥብ እንዳለ ያስገነዝበናል። በሸክላ ሠሪ የተመሰለው ይሖዋ እንደ ሸክላ አፈር የምንቆጠረውን እኛን የሚቀርጸን እንዴት ነው? ይሖዋ ይበልጥ ማራኪ እንድንሆን ወይም ጥሩ ቁመና እንዲኖረን በአካላችን ላይ ለውጥ እንደማያደርግ የታወቀ ነው። ይሖዋ አካላዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ሥልጠና የምናገኝበትን ዝግጅት አድርጎልናል። ይሖዋ እንዲቀርጸን የምንፈቅድ ከሆነ ውስጣዊ ወይም መንፈሳዊ ለውጥ እናደርጋለን፤ ይህ ደግሞ የዓለምን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም ያስችለናል። ታዲያ ይሖዋ የሚቀርጸን እንዴት ነው?
16, 17. (ሀ) አንድ ሸክላ ሠሪ ምርጥ የሸክላ ዕቃ ለመሥራት አፈሩን ምን ያደርገዋል? (ለ) የአምላክ ቃል፣ ተለውጠን በይሖዋ ፊት ውድ ዋጋ ያለን ሰዎች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
16 ሸክላ ሠሪው ጥሩ የሸክላ ዕቃ ለመሥራት በጣም ምርጥ የሆነ የሸክላ አፈር ይጠቀማል። ከዚህም በተጨማሪ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ አፈሩ ከማያስፈልጉ ባዕድ ነገሮች ነፃ እንዲሆን መታጠብ ይኖርበታል። ከዚያም በተገቢው መጠን ውኃ ከተደረገበት በኋላ በደንብ መቦካት አለበት፤ ይህ ደግሞ ተፈላጊውን ቅርጽ እንዲይዝ ይረዳዋል።
17 ውኃው ለሁለት ዓላማ ይኸውም አፈሩን ከማያስፈልጉ ባዕድ ነገሮች ለማንጻትና የተፈለገውን ቅርጽ ለመስጠት በሚያስችል መጠን ጭቃውን ለማቡካት እንደሚያገለግል ልብ በል፤ በዚህ መንገድ የተለያዩ ዕቃዎችን አልፎ ተርፎም ውድ የሆኑ ቁሳቁሶችን መሥራት ይቻላል። የአምላክ ቃልም ቢሆን በሕይወታችን ውስጥ ተመሳሳይ ሚና ይጫወታል። ቃሉ አምላክን ከማወቃችን በፊት የነበረንን አስተሳሰብ እንድናስወግድ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ እንድንለወጥና በእሱ ፊት ውድ ዋጋ ያለን ሰዎች እንድንሆን ያስችለናል። (ኤፌ. 5:26) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንድናነብና የአምላክ ቃል በሚጠናባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን እንድንገኝ ምን ያህል ጊዜ ምክር እንደተሰጠን እስቲ አስበው። እነዚህን ነገሮች እንድናደርግ የምንበረታታው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን በይሖዋ ለመቀረጽ ራሳችንን ማቅረባችንን የሚያሳይ ነው።—መዝ. 1:2፤ ሥራ 17:11፤ ዕብ. 10:24, 25
18. (ሀ) የአምላክ ቃል በእኛ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድርና እንዲለውጠን የምንፈልግ ከሆነ ማሰላሰል አስፈላጊ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው?
18 የአምላክ ቃል አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ እንዲረዳን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማግኘት ይኖርብናል፤ ነገር ግን ይህ የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው። ብዙ ሰዎች አልፎ አልፎ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚያነቡ ምን እንደሚል በደንብ ያውቃሉ። ምናልባትም በአገልግሎት ላይ እንዲህ ያሉ ሰዎች አጋጥመውህ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች ጥቅሶችን በቃላቸው መናገር ይችላሉ። * ሆኖም ይህ እውቀት በአስተሳሰባቸው ወይም በአኗኗራቸው ላይ ያን ያህል ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ለመሆኑ የጎደላቸው ነገር ምንድን ነው? አንድ ሰው የአምላክ ቃል በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድርበትና እንዲለውጠው ከፈለገ ቃሉ ልቡ ውስጥ ዘልቆ እንዲገባ ሊፈቅድለት ይገባል። በመሆኑም ጊዜ ወስደን በተማርነው ነገር ላይ ማሰላሰል ያስፈልገናል። ራሳችንን እንዲህ በማለት መጠየቃችን ጥሩ ነው፦ ‘ይህ እውቀት ሃይማኖታዊ ትምህርት ከመሆን ባለፈ ለእኔ ጥቅም እንደሚያስገኝ ተገንዝቤያለሁ? እውነት መሆኑን በራሴ ሕይወት መመልከት ችያለሁ? በተጨማሪም የተማርኩትን ነገር ለሌሎች ለማስተማር ብቻ ሳይሆን በራሴ ሕይወት ጭምር እጠቀምበታለሁ? ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እያናገረኝ እንዳለ ይሰማኛል?’ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ማሰላሰላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። ለእሱ ያለን ፍቅርም እያደገ ይሄዳል። ልባችን ሲነካ ደግሞ አስደሳች ለውጦችን ማድረግ እንችላለን።—ምሳሌ 4:23፤ ሉቃስ 6:45
19, 20. የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ጥቅም ያስገኝልናል?
19 የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበባችንና በዚያ ላይ ማሰላሰላችን ቀደም ሲል በተወሰነ መጠን የወሰድናቸውን እርምጃዎች በቀጣይነት ማድረጋችንን እንድቀጥል ያነሳሳናል፤ ይኸውም ‘አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፈን እንድንጥል እንዲሁም በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ስብዕና እንድንለብስ’ ይረዳናል። (ቆላ. 3:9, 10) አዎ፣ የአምላክን ቃል በትክክል ስንረዳና የተረዳነውን ነገር በተግባር ላይ ለማዋል ስንጥር አዲሱን ስብዕና በመልበስ ረገድ ይሳካልናል። አዲሱን ክርስቲያናዊ ስብዕና መልበሳችን ደግሞ በሰይጣን መሠሪ ወጥመዶች ውስጥ እንዳንወድቅ ያደርገናል።
20 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን ተዉ፤ ከዚህ ይልቅ . . . በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” በማለት አሳስቦናል። (1 ጴጥ. 1:14, 15) ቀደም ሲል የነበረንን አስተሳሰብም ሆነ ዝንባሌ አውጥተን ለመጣልና ለመለወጥ የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረጋችን በረከት ያስገኝልናል፤ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይህን ጉዳይ እንመረምራለን።
^ አን.18 በየካቲት 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 10 አንቀጽ 7 ላይ የተጠቀሰውን ምሳሌ ተመልከት።