የሕይወት ታሪክ
በይሖዋ መታመናችን በረከት አስገኝቶልናል
አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ያልጠበቅናቸው አልፎ ተርፎም አስጨናቂ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በራሳቸው ማስተዋል ሳይሆን በእሱ የሚታመኑ ሰዎችን ይባርካቸዋል። እኔና ባለቤቴ አብረን ባሳለፍነው ረጅምና አስደሳች ሕይወት ይህን መመልከት ችለናል። እስቲ ታሪካችንን ቀንጨብ አድርገን እንንገራችሁ።
አባቴና እናቴ የተገናኙት በ1919 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ባደረጉት ትልቅ ስብሰባ ላይ ነው። በዚያው ዓመት ትዳር መሠረቱ። እኔ የተወለድሁት በ1922 ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ወንድሜ ፖል ተወለደ። ባለቤቴ ግሬስ የተወለደችው በ1930 ነው። የባለቤቴ ወላጆች ሮይ ሃወል እና ሩት ሃወል ያደጉት በእውነት ቤት ውስጥ ነው፤ አያቶቿም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሲሆኑ የወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል ወዳጆች ነበሩ።
ከግሬስ ጋር የተገናኘነው በ1947 ሲሆን ሐምሌ 16 ቀን 1949 ተጋባን። ትዳር ከመመሥረታችን በፊት ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን በግልጽ ተነጋግረን ነበር። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ስለፈለግን ልጅ ላለመውለድ ወሰንን። ጥቅምት 1 ቀን 1950 ሁለታችንም በአቅኚነት ማገልገል ጀመርን። ከዚያም በ1952 በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን።
የወረዳ ሥራ እና የጊልያድ ሥልጠና
ሁለታችንም ይህን አዲስ ኃላፊነት ለመወጣት ብዙ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ተሰምቶን ነበር። እኔ ተሞክሮ ካካበቱ ወንድሞች ትምህርት የቀሰምሁ ሲሆን ለግሬስም ቢሆን ሥልጠና ማግኘት የምትችልበትን መንገድ አመቻችቼላት ነበር። የቤተሰባችን የረጅም ጊዜ ወዳጅ የሆነውንና ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለውን ማርቪን ሆሊንን ስለዚህ ጉዳይ አነጋገርኩት፤ “ግሬስ ወጣት ከመሆኗም ሌላ ተሞክሮ የላትም። ለጥቂት ጊዜ አብራት በማገልገል ልታሠለጥናት የምትችል እህት ልትጠቁመኝ ትችላለህ?” ብዬ ጠየቅሁት። እሱም እንዲህ አለኝ፦ “አዎን፤ ኤድና ዊንክል የተባለች ተሞክሮ ያላት አንዲት አቅኚ አውቃለሁ፤ ይህች እህት ግሬስን ብዙ ልትረዳት የምትችል ይመስለኛል።” ከጊዜ በኋላ ግሬስ ስለ ኤድና እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል መረጋጋት እንድችል ረድታኛለች፤ ኤድና ሰዎች ለሚሰነዝሯቸው የተቃውሞ ሐሳቦች እንዴት መልስ እንደምትሰጥ የምታውቅ ከመሆኑም ሌላ ለቤቱ ባለቤት ተገቢውን መልስ መስጠት እንድችል ግለሰቡ ሲናገር በደንብ ማዳመጥ እንዳለብኝ አሠልጥናኛለች። የሚያስፈልገኝ እንዲህ ዓይነት ሥልጠና ነበር!”
እኔና ግሬስ በአዮዋ ግዛት ባሉ ሁለት ወረዳዎች አገልግለናል፤ እነዚህ ወረዳዎች የሚኒሶታ እና የሳውዝ ዳኮታ ግዛቶችን በከፊል ያካትታሉ። ከዚያም በኒው ዮርክ ወረዳ 1 እንድናገለግል ተመደብን፤ ወረዳው ብሩክሊንን እና ኩዊንስን ይጨምራል። ይህ ምድብ ሲሰጠን፣ ልምድ እንደሌለን ስለተሰማን ምን ያህል ጨንቆን እንደነበር መቼም አንረሳውም። በወረዳችን ውስጥ የብሩክሊን ሃይትስ ጉባኤም የሚገኝ ሲሆን ጉባኤው የሚሰበሰበው በቤቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ነው፤ ከጉባኤው አባላት መካከል ተሞክሮ ያላቸው በርካታ ቤቴላውያን ይገኙበታል። በዚህ ጉባኤ ውስጥ የመጀመሪያውን የአገልግሎት ንግግር ከሰጠሁ በኋላ ወንድም ናታን ኖር መጥቶ አነጋገረኝ፤ የተናገረውን ሐሳብ ጠቅለል አድርጌ ባስቀምጠው እንደሚከተለው ይሆናል፦ “ማልኮም፣ ልንሠራበት የሚያስፈልገን ተገቢ ምክር ሰጥተኸናል። ሆኖም ልታስታውሰው የሚገባው አንድ ነገር አለ፤ የምትሰጠን ምክር ደግነት የሚንጸባረቅበት ካልሆነ በድርጅቱ ውስጥ የምታበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ይሆናል። የምታከናውነውን መልካም ሥራ ቀጥልበት።” ከስብሰባው በኋላ ይህንን ለግሬስ ነገርኳት። ነገሩ በጣም ስላስጨነቀን ቤቴል ውስጥ ወዳረፍንበት ክፍል ከተመለስን በኋላ አለቀስን።
“የምትሰጠን ምክር ደግነት የሚንጸባረቅበት ካልሆነ በድርጅቱ ውስጥ የምታበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ይሆናል። የምታከናውነውን መልካም ሥራ ቀጥልበት”
ከጥቂት ወራት በኋላ፣ በጊልያድ ትምህርት ቤት በ24ኛው ክፍል ላይ እንድንሠለጥን የሚጋብዝ ደብዳቤ ደረሰን፤ ትምህርቱ የሚያበቃው የካቲት 1955 ነበር። ሥልጠናውን ወሰድን ማለት ሚስዮናውያን እንሆናለን ማለት እንዳልሆነ ወደ ትምህርት ቤቱ ከመሄዳችን በፊት ተነገረን። ከዚህ ይልቅ ሥልጠናውን የምንወስድበት ዓላማ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን መርዳት ነው። በትምህርት ቤቱ በጣም አስደናቂ ጊዜ ያሳለፍን ሲሆን ትሕትናንም ተምረናል።
ሥልጠናውን ካጠናቀቅን በኋላ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። በአውራጃችን ውስጥ የሚሺገን፣ የኢንዲያና እንዲሁም የኦሃዮ ግዛቶች ይገኙበታል። ከዚያም ታኅሣሥ 1955 ወንድም ኖር የሚያስገርም ደብዳቤ ላከልን፦ “የሚሰማችሁን ነገር ሳትደብቁ በግልጽ ንገሩኝ። ወደ ቤቴል መጥታችሁ እዚሁ እያገለገላችሁ መቀጠል . . . አሊያም ለተወሰነ ጊዜ በቤቴል ካገለገላችሁ በኋላ በሌላ አገር መመደብ የምትፈልጉ ከሆነ አሳውቁኝ። ወይም ደግሞ የአውራጃ እና የወረዳ ሥራን የምትመርጡ ከሆነ ፍላጎታችሁን ንገሩኝ።” እኛም የሚሰጠንን ማንኛውም የሥራ ምድብ ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን አሳወቅን። ወዲያውኑ፣ በቤቴል እንድናገለግል ተጠራን!
በቤቴል ያሳለፍናቸው አስደሳች ዓመታት
በቤቴል ባሳለፍኳቸው አስደሳች ዓመታት፣ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙ ጉባኤዎች እንዲሁም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ንግግር እሰጥ ነበር። ከዚህም ሌላ፣ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ከበድ ባሉ የኃላፊነት ቦታዎች ለማገልገል ብቁ የሆኑ በርካታ ወጣት ወንዶችን ማሠልጠንና መርዳት ችያለሁ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የወንድም ኖር ጸሐፊ ሆኜ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በሚያደራጀው ቢሮ ውስጥ አገልግያለሁ።
በተለይ በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ በመሥራት ያሳለፍኳቸው ዓመታት አስደሳች ነበሩ። በዚህ ክፍል ውስጥ ከቶማስ (በድ) ሱሊቫን ጋር ሠርቻለሁ። ወንድም ሱሊቫን ለበርካታ ዓመታት የዚህ ክፍል የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል። ሌሎች ወንድሞችም ብዙ ሥልጠና ሰጥተውኛል። ከእነዚህም መካከል እኔን እንዲያሠለጥነኝ የተመደበው ፍሬድ ራስክ አንዱ ነው። በአንድ ወቅት ይህን ወንድም “ፍሬድ፣ አንዳንዶቹ ደብዳቤዎቼ ላይ ብዙ እርማት የምታደርገው ለምንድን ነው?” ብዬ እንደጠየቅኩት አስታውሳለሁ። እሱም ሳቀና የሚከተለውን ቁም ነገር ያዘለ ሐሳብ አካፈለኝ፦ “ማልኮም፣ አንድን ነገር በቃልህ ስትናገር ተጨማሪ ሐሳብ በማከል ሐሳብህን ግልጽ ማድረግ ትችላለህ፤ መልእክቱን የምታስተላልፈው በጽሑፍ ከሆነ ግን በተለይ ደግሞ ከዚህ ቢሮ የሚላክ ከሆነ በተቻለ መጠን ትክክለኛና ግልጽ መሆን ይኖርበታል።” ከዚያም በደግነት እንዲህ አለኝ፦ “አይዞህ፣ ተስፋ አትቁረጥ፤ አሁንም ቢሆን ጥሩ እየሠራህ ነው፤ ቀስ በቀስ ደግሞ ይበልጥ እየተሻሻልክ ትሄዳለህ።”
በቤቴል ባሳለፍናቸው ዓመታት ግሬስ በተለያዩ ምድቦች ላይ ሠርታለች፤ ከእነዚህም መካከል የቤት ጽዳት ይኸውም የመኖሪያ ክፍሎቹን ጥሩ አድርጎ መያዝ ይገኝበታል። ግሬስ በሥራዋ ደስተኛ ነበረች። በዚያ ወቅት በቤቴል የነበሩ አንዳንድ ወጣት ወንድሞች ዛሬም እንኳ ግሬስን ሲያገኟት ፈገግ ብለው እንዲህ ይሏታል፦ “አልጋ ማንጠፍ በደንብ ያስተማርሽኝ አንቺ ነሽ፤ እናቴ አልጋ የማነጥፍበትን መንገድ አይታ በጣም ነው ደስ ያላት።” ግሬስ በመጽሔት፣ በደብዳቤ ልውውጥ እና የቴፕ ክሮች በሚባዙበት ክፍልም ሠርታለች። በእነዚህ የተለያዩ ምድቦች ላይ መሥራቷ፣ የምናገለግልበት ቦታ ወይም የምንሠራበት ምድብ የትም ይሁን የት በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ማገልገል መብት እና በረከት እንደሆነ እንድትገነዘብ ረድቷታል። አሁንም ቢሆን የሚሰማት እንደዚያው ነው።
በሕይወታችን ያጋጠሙን ለውጦች
በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ፣ በዕድሜ የገፉት ወላጆቻችን የበለጠ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ማስተዋል ጀመርን። ውሎ አድሮም ከባድ የሆነውን ውሳኔ ለማድረግ ተገደድን። ከቤቴል መውጣትም ሆነ ከልብ ከምንወዳቸው የሥራ ባልደረቦቻችን መለየት አልፈለግንም። ያም ቢሆን ወላጆቻችንን መንከባከብ የእኔ ኃላፊነት እንደሆነ ተሰማኝ። በመሆኑም ከቤቴል ወጣን፤ ሁኔታዎች ሲስተካከሉልን ግን ተመልሰን ለመግባት እቅድ ነበረን።
መተዳደሪያ ለማግኘት በአንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። ለዚህ ሥራ ሥልጠና እየወሰድኩ ሳለ አንድ ሥራ አስኪያጅ የነገረኝን ፈጽሞ አልረሳውም፤ እንዲህ ብሎኝ ነበር፦ “በዚህ ሥራ ስኬታማ እንድትሆን ምሽት ላይ ወደ ሰዎች ቤት መሄድ አለብህ። ሰዎችን ማግኘት የምትችለው በዚህ ወቅት ነው። ምሽት ላይ ሰዎችን ወደ ቤታቸው ሄደህ ከማነጋገር የበለጠ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባ ነገር የለም።” እኔም እንዲህ ብዬ መለስኩለት፦ “ይህን ያልከኝ ከተሞክሮ በመነሳት ስለሆነ አመለካከትህን አከብራለሁ። ይሁን እንጂ ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶችም አሉብኝ፤ እነዚህን ኃላፊነቶች እስከ ዛሬ ችላ ብዬ አላውቅም፤ አሁንም ቢሆን ይህን ማድረግ አልፈልግም። ምሽት ላይ ሰዎችን ቤታቸው ሄጄ ለማነጋገር ጥረት አደርጋለሁ፤ ማክሰኞና ሐሙስ ምሽት ግን በጣም ትልቅ ቦታ የምሰጠው ስብሰባ አለኝ።” ሰብዓዊ ሥራ ለመሥራት ብዬ ከስብሰባዎች ባለመቅረቴ ይሖዋ ባርኮኛል።
እናቴ ሐምሌ 1987 በአረጋውያን መጦሪያ ተቋም ውስጥ ባረፈችበት ወቅት አጠገቧ ነበርን። የነርሶቹ ኃላፊ ወደ ግሬስ መጥታ እንዲህ አለቻት፦ “ሚስዝ አለን፣ አሁን ወደ ቤት ሄደሽ እረፍት አድርጊ። አማትሽን ከአጠገቧ ሳትለዪ ተንከባክበሻታል። የምትችዪውን ሁሉ ስላደረግሽ ምንም የሚጸጽትሽ ነገር ሊኖር አይገባም።”
ታኅሣሥ 1987 ወደምንወደው የቤቴል አገልግሎት እንደገና ለመመለስ አመለከትን። ይሁንና ከጥቂት ቀናት በኋላ ግሬስ የአንጀት ካንሰር እንዳለባት ታወቀ። ቀዶ ጥገና ከተደረገላት እና ከበሽታዋ ካገገመች በኋላ ካንሰሩ እንደጠፋ ተነገራት። በዚህ መሃል፣ በአካባቢያችን ባለው ጉባኤ ውስጥ ማገልገላችንን ብንቀጥል የሚሻል እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ ከቤቴል ደረሰን። እኛም ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን መሥራታችንን ለመቀጠል ቆርጠን ነበር።
ከጊዜ በኋላ በቴክሳስ ሥራ አገኘሁ። ሞቃት አየር ያለው ይህ አካባቢ ለጤንነታችን ተስማሚ እንደሆነ ስለተሰማን ወደዚያ ሄድን፤ ደግሞም ተስማምቶናል። ላለፉት 25 ዓመታት አፍቃሪ በሆኑ ወንድሞችና እህቶች ተከብበን በቴክሳስ ቆይተናል፤ ከእነዚህ ወንድሞች ጋር በጣም እንቀራረባለን።
ያገኘነው ትምህርት
ግሬስ፣ በተለያዩ ጊዜያት የአንጀትና የታይሮይድ ካንሰር በቅርቡ ደግሞ የጡት ካንሰር ይዟት ነበር። ያም ቢሆን ስላጋጠሟት ችግሮች አማርራ አታውቅም፤ እንዲሁም ምንጊዜም የራስነትን ሥርዓት የምታከብር እና ለሥልጣን የምትገዛ ሚስት ነች። ብዙ ሰዎች ግሬስን “የተሳካ እና ደስተኛ ትዳር ሊኖራችሁ የቻለው እንዴት ነው?” ብለው ይጠይቋታል። እሷም ለዚህ የረዱንን አራት ነገሮች ትጠቅስላቸዋለች፦ “ጓደኛሞች ነን። በየቀኑ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እናደርጋለን። በየዕለቱ አብረን ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተናል። እንዲሁም የማንግባባበት ነገር ሲገጥመን ሳንፈታው አናድርም።” እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ አንዳችን ሌላውን ቅር የሚያሰኝ ነገር ማድረጋችን አይቀርም፤ ይሁን እንጂ ይቅር ተባብለን ጉዳዩን እንረሳዋለን፤ ይህ ደግሞ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ተመልክተናል።
“ምንጊዜም በይሖዋ መታመናችንና እሱ የፈቀደውን መቀበላችን አስፈላጊ ነው”
በሕይወታችን ውስጥ ብዙ መከራዎች ያጋጠሙን ሲሆን ካሳለፍነው ተሞክሮ ያገኘናቸው በርካታ ጥሩ ትምህርቶች አሉ፦
ምንጊዜም በይሖዋ መታመናችንና እሱ የፈቀደውን መቀበላችን አስፈላጊ ነው። መቼም ቢሆን በራሳችን ማስተዋል ልንታመን አይገባም።—ምሳሌ 3:5, 6፤ ኤር. 17:7
ምንም ዓይነት ነገር ቢያጋጥመን ከይሖዋ ቃል በምናገኘው መመሪያ መተማመን አለብን። ይሖዋን እና እሱ ያወጣቸውን ሕጎች መታዘዝ ወሳኝ ነው። መሃል ሰፋሪ መሆን አይቻልም፤ አንድ ሰው ታዛዥ ካልሆነ ዓመፀኛ ነው ማለት ነው።—ሮም 6:16፤ ዕብ. 4:12
በሕይወት ውስጥ ትልቁ ነገር በይሖዋ ዘንድ ጥሩ ስም ማትረፍ ነው። ቅድሚያ መስጠት ያለብን ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ሳይሆን የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ነው።—ምሳሌ 28:20፤ መክ. 7:1፤ ማቴ. 6:33, 34
በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ውጤታማ እና ሥራ የበዛልን ለመሆን መጸለይ ይኖርብናል። ትኩረት የምናደርገው ልናከናውነው በማንችለው ነገር ላይ ሳይሆን ማከናወን በምንችለው ነገር ላይ መሆን አለበት።—ማቴ. 22:37፤ 2 ጢሞ. 4:2
ይሖዋ የሚባርከውና የሚደግፈው ይህን ድርጅት ብቻ ነው።—ዮሐ. 6:68
እኔና ግሬስ እያንዳንዳችን ላለፉት ከ75 የሚበልጡ ዓመታት ይሖዋን አገልግለናል፤ ይህም ከተጋባን በኋላ ወደ 65 ለሚጠጉ ዓመታት መሆኑ ነው። በእነዚህ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን አብረን በማገልገል አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል። ሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በይሖዋ መታመን ምን ያህል በረከት እንደሚያስገኝ እንደ እኛ እንዲቀምሱ ምኞታችንና ጸሎታችን ነው።