የሕይወት ታሪክ
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የከፈተልኝ ግሩም አጋጣሚዎች
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን 65 ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ሕይወቴ በደስታ የተሞላ እንደነበረ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ይህን ስል ግን ያዘንኩበት ወይም ተስፋ የቆረጥኩበት ጊዜ አልነበረም ማለት አይደለም። (መዝ. 34:12፤ 94:19) ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ያሳለፍኩት ሕይወት እጅግ በጣም የሚክስና ዓላማ ያለው ነው!
መስከረም 7, 1950 የብሩክሊን ቤቴል ቤተሰብ አባል ሆንኩ። በወቅቱ ዕድሜያቸው ከ19 እስከ 80 ዓመት ባለው ክልል ውስጥ የሚገኙ ከበርካታ አገራት የመጡ 355 ወንድሞችና እህቶች በቤቴል ያገለግሉ ነበር። ከእነሱ መካከል አብዛኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበሩ።
ይሖዋን ማገልገል ጀመርኩ
‘ደስተኛ የሆነውን አምላክ’ እንዳገለግል ያስተማረችኝ እናቴ ናት። (1 ጢሞ. 1:11) እናቴ ይሖዋን ማገልገል የጀመረችው እኔ ትንሽ ልጅ እያለሁ ነበር። ሐምሌ 1, 1939 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኮለምበስ፣ ነብራስካ በተካሄደ አንድ የዞን ስብሰባ ላይ (በአሁኑ ጊዜ የወረዳ ስብሰባ ይባላል) በአሥር ዓመቴ ተጠመቅሁ። በወቅቱ፣ መቶ የምንሆን ተሰብሳቢዎች በአንድ የተከራየነው ሕንፃ ውስጥ ሆነን “ፋሺዝም ወይስ ነፃነት” የተሰኘውን የጆሴፍ ራዘርፎርድ በሸክላ የተቀረጸ ንግግር እያዳመጥን ነበር። የንግግሩን ግማሽ ያህል እንዳዳመጥን ከተሰበሰብንበት ትንሽ አዳራሽ ውጭ ረብሸኛ ሰዎች ተሰባሰቡ። በጉልበት ወደ አዳራሹ ከገቡ በኋላ ስብሰባችንን አስቁመው ከከተማዋ አስወጡን። በዚህ ጊዜ ከከተማዋ ብዙም በማይርቅ በአንድ ወንድም እርሻ ተሰብስበን ቀሪውን ንግግር አዳመጥን። በመሆኑም የተጠመቅሁበትን ቀን ፈጽሞ አልረሳውም!
እናቴ እኔን በእውነት ውስጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። አባቴ ጥሩ ሰውና ጥሩ አባት ቢሆንም ለሃይማኖትም ሆነ ለእኔ መንፈሳዊነት ግድ አልነበረውም። እናቴና በኦማሃ ጉባኤ የሚገኙ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች አስፈላጊውን ማበረታቻ ሰጥተውኛል።
ሕይወቴ ሌላ አቅጣጫ ያዘ
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ላጠናቅቅ ስቃረብ በሕይወቴ ላደርግ ስለምፈልገው ነገር ውሳኔ ማድረግ ነበረብኝ። በየዓመቱ ክረምት ላይ ትምህርት ቤት ሲዘጋ የእረፍት ጊዜ አቅኚ (በአሁኑ ጊዜ ረዳት አቅኚ ይባላል) ሆኜ ከእኩዮቼ ጋር አገለግል ነበር።
ከጊልያድ ትምህርት ቤት ሰባተኛ ክፍል የተመረቁት ጆን ቺሚክሊስ እና ቴድ ጃራዝ የሚባሉ ሁለት ያላገቡ ወጣት ወንድሞች በአካባቢያችን እንዲያገለግሉ ተመድበው ነበር። ዕድሜያቸው ገና በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ መሆኑን ሳውቅ ገረመኝ። እኔ በዚያን ጊዜ ዕድሜዬ 18 ዓመት ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለማጠናቀቅም ተቃርቤ ነበር። ወንድም ቺሚክሊስ በሕይወቴ ላደርግ የምፈልገውን ነገር በተመለከተ ጥያቄ ያቀረበልኝን ጊዜ እስካሁን አስታውሰዋለሁ። ምን መሆን እንደምፈልግ ስነግረው “አዎ፣ አሁኑኑ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀምር። ምን ይታወቃል? ግሩም አጋጣሚዎችን ይከፍትልህ ይሆናል” በማለት አበረታታኝ። ይህ ምክር፣ ከእነዚህ ወንድሞች ምሳሌነት ጋር ተዳምሮ በጥልቅ ነካኝ። ስለዚህ ትምህርቴን ስጨርስ በ1948 አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ።
ቤቴል መግባት
ሐምሌ 1950 እኔና ወላጆቼ ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ በያንኪ ስታዲየም በሚካሄድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሄድን። በዚያም ቤቴል ገብተው ማገልገል ለሚፈልጉ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ከዚያም የቤቴል ማመልከቻ ቅጽ ሞልቼ አስገባሁ።
አባቴ፣ ከእነሱ ጋር አየኖርኩ አቅኚ ሆኜ ማገልገሌን ባይቃወምም ለምኖርበት ክፍልና ለቀለቤ መጠነኛ ገንዘብ መክፈል እንዳለብኝ ተሰማው። ስለዚህ አንድ ቀን ሥራ ፍለጋ ወጣሁ፤ ጊዜው ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ሲሆን በቅድሚያ የፖስታ ሣጥናችንን ከፈትኩ። በዚህ ጊዜ ከብሩክሊን ለእኔ የተላከ አንድ ደብዳቤ አገኘሁ። ደብዳቤው የናታን ኖር ፊርማ ያለበት ሲሆን እንዲህ ይላል፦ “ቤቴል ለማገልገል ያስገባኸው ማመልከቻ ደርሶናል። እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ ድረስ በቤቴል ለመቆየት እንደተስማማህ ተረድቻለሁ። ስለዚህ መስከረም 7, 1950 በ124 ኮሎምቢያ ሃይትስ፣ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ቤቴል መጥተህ ርፖርት አድርግ።”
ያን ዕለት አባቴ ከሥራ ወደ ቤት ሲመለስ ሥራ እንዳገኘሁ ነገርኩት። እሱም “ጥሩ ነው፣ የት ልትሠራ ነው?” አለኝ። እኔም “የምሠራው በብሩክሊን ቤቴል ነው፤ በወር 10 ዶላር ይሰጠኛል” ብዬ መለስኩ። ይህን መስማቱ ትንሽ ቢያስደነግጠውም ምርጫዬ ይህ ከሆነ ስኬታማ ለመሆን እንድጣጣር ነገረኝ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ማለትም በ1953 በያንኪ ስታዲየም በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠመቀ!
ደስ የሚለው፣ የአቅኚነት ጓደኛዬ የሆነው አልፍሬድ ነስራላ ቤቴል እንዲገባ በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ተጠርቶ ስለነበረ አንድ ላይ ሄድን። አልፍሬድ ነስራላ ከጊዜ በኋላ ትዳር የመሠረተ ሲሆን እሱና ሚስቱ ጆአን ጊልያድ ገብተው ተመረቁ፤ ከዚያም በሊባኖስ በሚስዮናዊነት እንዲያገለግሉ ተላኩ፤ በኋላም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመልሰው በተጓዥነት ሥራ ማገልገል ጀመሩ።
በቤቴል የተሰጡኝ የሥራ ምድቦች
በቤቴል መጀመሪያ የተመደብኩት በጽሑፍ ጥረዛ ክፍል ሲሆን የምሠራውም የመጽሐፍ ወረቀቶችን መስፋት ነበር። መጀመሪያ የሰፋሁት መጽሐፍ ሃይማኖት ለሰው ልጆች ምን አድርጎላቸዋል? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ነበር። በጥረዛ ክፍሉ ውስጥ ለስምንት ወራት ያህል ከሠራሁ በኋላ በወንድም ቶማስ ሱሊቫን ሥር ሆኜ በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ እንድሠራ ተመደብኩ። ከእሱ ጋር መሥራትና በድርጅቱ ውስጥ ለዓመታት ካካበተው መንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ተጠቃሚ መሆን አስደሳች ነገር ነበር።
በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ወደ ሦስት ዓመታት የሚጠጋ ጊዜ ካሳለፍኩ በኋላ ወንድም ኖር ሊያናግረኝ እንደሚፈልግ የፋብሪካ የበላይ ተመልካች የሆነው ማክስ ላርሰን ነገረኝ። እኔም ‘ምን ጥፋት ሠርቼ ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። ወንድም ኖር ያስጠራኝ በቅርቡ ከቤቴል የመውጣት ሐሳብ እንዳለኝ ለማወቅ ፈልጎ እንደሆነ ስረዳ እፎይ አልኩ። በእሱ ቢሮ በጊዜያዊነት ሊሠራለት የሚችል ሰው ስለፈለገ እኔ ሥራውን ማከናወን እችል እንደሆነ ማወቅ ፈልጎ ነበር። እኔም ከቤቴል የመውጣት እቅድ እንደሌለኝ ተናገርኩ። በመሆኑም በቀጣዮቹ 20 ዓመታት በእሱ ቢሮ ውስጥ የመሥራት መብት አገኘሁ።
ከወንድም ሱሊቫንና ከወንድም ኖር እንዲሁም በቤቴል አብረውኝ ከነበሩ እንደ ሚልተን ሄንሸል፣ ክላውስ ጄንሰን፣ ማክስ ላርሰን፣ ሂዩጎ ሪመር እና ግራንት ሱተር ያሉ ሌሎች ወንድሞች ጋር በመሥራት ያገኘሁት ሥልጠና በገንዘብ ሊተመን እንደማይችል ብዙ ጊዜ እናገራለሁ። *
አብሬያቸው ያገለገልኳቸው ወንድሞች በድርጅቱ ውስጥ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት መንገድ በጣም የተደራጀ ነበር። ወንድም ኖር፣ ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በተቻለ መጠን ከፍተኛ እድገት ላይ እንዲደርሱ የሚፈልግ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል ሠራተኛ ነበር። በእሱ ቢሮ የሚሠሩ ወንድሞች እሱን ቀርቦ ማነጋገር አይከብዳቸውም። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከእሱ የተለየ አመለካከት ቢኖረንም ሐሳባችንን በነፃነት መግለጽና በእሱ ዘንድ ያለንን አመኔታ ይዘን መቀጠል እንችል ነበር።
በአንድ ወቅት ወንድም ኖር ትናንሽ በሚባሉ ጉዳዮች ረገድ ጠንቃቃ የመሆንን አስፈላጊነት በሚመለከት አነጋግሮኝ ነበር። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት የራሱን ተሞክሮ ነገረኝ፤ የፋብሪካ የበላይ ተመልካች በነበረበት ጊዜ ወንድም ራዘርፎርድ ይደውልለትና እንዲህ ይለው ነበር፦ “ወንድም ኖር፣ ከፋብሪካው ለምሳ ወደዚህ ስትመጣ ጥቂት ላጲሶች አምጣልኝ። ምንጊዜም ጠረጴዛዬ ላይ እንዲኖሩ እፈልጋለሁ።” ወንድም ኖር በዚህ ጊዜ በመጀመሪያ የሚያደርገው ነገር፣ ወደ ዕቃ ማስቀመጫ ክፍሉ በመሄድ ላጲሶቹን አንስቶ ኪሱ ውስጥ መክተት እንደነበረ ነገረኝ። ከዚያም ምሳ ሰዓት ላይ ወደ ወንድም ራዘርፎርድ ቢሮ ሄዶ ላጲሶቹን ያስቀምጥለታል። ይህ በጣም ትንሽ ነገር ቢሆንም ለወንድም ራዘርፎርድ ግን ይጠቅመው ነበር። ከዚያም ወንድም ኖር እንዲህ አለኝ፦ “የተቀረጹ እርሳሶች ጠረጴዛዬ ላይ እንዲኖሩ እፈልጋለሁ። ስለዚህ እባክህ በየዕለቱ ጠዋት ቀርጸህ አዘጋጅልኝ።” እኔም ለብዙ ዓመታት፣ እርሳሶችን በመቅረጽ ጠረጴዛው ላይ አስቀምጥለት ነበር።
ወንድም ኖር፣ አንድ ተግባር እንድንፈጽም ስንጠየቅ በጥንቃቄ የማዳመጥን አስፈላጊነት ብዙ ጊዜ ይናገር ነበር። በአንድ ወቅት አንድን ጉዳይ እንዴት መያዝ እንዳለብኝ የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ ሰጥቶኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን በጥንቃቄ ሳላዳምጥ ቀረሁ። በዚህም የተነሳ በእኔ ምክንያት ለኃፍረት ተዳረገ። በጣም አዘንኩ፤ ስለዚህ አጭር ደብዳቤ ጽፌ በጥፋቴ እንዳዘንኩና ከእሱ ቢሮ ብለቅቅ የተሻለ እንደሆነ ገለጽኩለት። ያን ዕለት ጠዋት ጥቂት ቆይቶ ወንድም ኖር እኔ ወዳለሁበት ጠረጴዛ መጣ። ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ሮበርት፣ የጻፍከው ማስታወሻ ደርሶኛል። ስህተት ሠርተህ ነበር። እኔም ስለ ጉዳዩ አነጋግሬሃለሁ፤ ደግሞም ለወደፊቱ ይበልጥ ጠንቃቃ እንደምትሆን እርግጠኛ ነኝ። አሁን ሁለታችንም ወደ ሥራችን እንመለስ።” እኔም አሳቢነት ስላሳየኝ በጣም ተደነቅሁ።
ትዳር ለመመሥረት ፈለግሁ
ፍላጎቴ በቤቴል አገልግሎት መቀጠል ቢሆንም ለስምንት ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ ሐሳቤን እንድለውጥ የሚያደርግ ነገር አጋጠመኝ። በ1958 በያንኪ ስታዲየምና በፖሎ ግራውንድስ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በተደረገበት ጊዜ ሎሬይን ብሩክስ ከምትባል እህት ጋር ተገናኘሁ፤ ከዚህች እህት ጋር የምንተዋወቀው በ1955 በሞንትሪዮል፣ ካናዳ በአቅኚነት ስታገለግል ነው። ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያላት አመለካከትና የይሖዋ ድርጅት ወደሚልካት ማንኛውም ቦታ ለመሄድ ያላት ፈቃደኝነት አስደነቀኝ። የሎሬይን ግብ ጊልያድ ትምህርት ቤት መግባት ነበር። በ22 ዓመቷ ማለትም በ1956 በ27ኛው ክፍል ገብታ እንድትማር ተጠራች። ከተመረቀች በኋላ በሚስዮናዊነት እንድታገለግል ብራዚል ተመደበች። እኔና ሎሬይን በ1958 ስንገናኝ ወዳጅነታችንን አጠናከርን፤ በመጨረሻም ለጋብቻ ያቀረብኩላትን ጥያቄ ተቀበለች። በቀጣዩ ዓመት ለመጋባትና ከዚያ በኋላ ወደ ሚስዮናዊነት አገልግሎት ለመግባት አቀድን።
ይህን ሐሳቤን ለወንድም ኖር ስነግረው ለሦስት ዓመት እንድንቆይና ከዚያ በኋላ ተጋብተን በብሩክሊን ቤቴል እንድናገለግል ሐሳብ አቀረበልኝ። በዚያን ጊዜ አንድ ባልና ሚስት ከተጋቡ በኋላ በቤቴል ማገልገል ከፈለጉ ከሁለት አንዳቸው በቤቴል ለአሥር ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት ማገልገል፣ ሌላኛቸው ደግሞ ቢያንስ ለሦስት ዓመት ማገልገል ነበረባቸው። ስለዚህ ሎሬይን ከመጋባታችን በፊት ሁለት ዓመት በብራዚል ቤቴል፣ አንድ ዓመት ደግሞ በብሩክሊን ቤቴል ለማገልገል ተስማማች።
ከተጫጨን በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል የምንገናኘው በደብዳቤ ብቻ ነበር። ስልክ መደወል ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ኢ-ሜይል የሚባል ነገር አልነበረም! መስከረም 16, 1961 ስንጋባ የጋብቻ ንግግር ያቀረበልን ወንድም ኖር ነው፤ ይህ ለእኛ ልዩ መብት ነበር። እውነት ነው፣ ለመጋባት በመጠበቅ ያሳለፍናቸው እነዚያ ጥቂት ዓመታት ረጅም ጊዜ ይመስሉ ነበር። ይሁን እንጂ እርካታና ደስታ የሞላበትን ለ50 ዓመታት የዘለቀውን የትዳር ሕይወታችንን መለስ ብለን ስንመለከት መጠበቃችን የማያስቆጭ እንደሆነ ይሰማናል!
ያገኘኋቸው የአገልግሎት መብቶች
በ1964 የዞን የበላይ ተመልካች ሆኜ ሌሎች አገሮችን የመጎብኘት መብት ተሰጠኝ። በወቅቱ እንዲህ ያለ ጉዞ በሚደረግበት ጊዜ ሚስቶች ከባሎቻቸው ጋር አብረው እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም ነበር። በ1977 ግን ማስተካከያ ስለተደረገ ሚስቶች ከባሎቻቸው ጋር መጓዝ ጀመሩ። በዚያ ዓመት ግራንት ሱተር እና ኢዲት ሱተር በጀርመን፣ በኦስትሪያ፣ በግሪክ፣ በቆጵሮስ፣ በቱርክ እና በእስራኤል የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለመጎብኘት ሲሄዱ እኔና ሎሬይን አብረናቸው ሄድን። በጠቅላላው 70 ወደሚያህሉ አገሮች ሄጃለሁ።
በ1980 የዞን ጉብኝት ለማድረግ ወደ ብራዚል ስንጓዝ በፕሮግራማችን መሠረት ቤሌም ወደተባለች ከተማ ሄድን፤ በምድር ወገብ ላይ በምትገኘው በዚህች ከተማ ሎሬይን በሚስዮናዊነት አገልግላለች። በማናውስ ያሉ ወንድሞችንም የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝተን ነበር። በአንድ ስታዲየም ውስጥ ንግግር እየተሰጠ ሳለ ነጠል ብለው በቡድን የተቀመጡ ሰዎችን አየን፤ በብራዚላውያን ባሕል ሴቶቹ ጉንጭ ለጉንጭ በመሳሳም ወንዶቹ ደግሞ እጅ ለእጅ በመጨባበጥ ሰላምታ መስጠታቸው የተለመደ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች ይህን አያደርጉም ነበር። ‘ለምን ይሆን?’ ብለን አሰብን።
እነዚህ ሰዎች በአማዞን ደን ውስጥ ከሚገኝ የሥጋ ደዌ ሕመምተኞች መንደር የመጡ ውድ የእምነት አጋሮቻችን ነበሩ። በባሕሉ መሠረት ሰላምታ ያልተለዋወጡት በስብሰባው ላይ ላሉ ሌሎች ወንድሞች ደኅንነት ሲሉ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ወንድሞች ልባችንን በጥልቅ ነክተውታል፤ በፊታቸው ላይ የሚነበበውን ደስታ ፈጽሞ አንረሳውም! “ባሮቼ፣ ከልብ በመነጨ ደስታ ይዘምራሉ” የሚሉት የኢሳይያስ ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው!—ኢሳይያስ 65:14
የሚክስና ዓላማ ያለው ሕይወት
እኔና ሎሬይን ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ያሳለፍናቸውን ከስልሳ የሚበልጡ ዓመታት ዘወትር መለስ ብለን እናስባለን። ይሖዋ በድርጅቱ ውስጥ እንዲመራን በመፍቀዳችን በብዙ መንገዶች እንደተባረክን ስናስብ በጣም ደስ ይለናል። አሁን እንደ በፊቱ ወደተለያዩ አገሮች መጓዝ ባልችልም በአስተባባሪዎች ኮሚቴና በአገልግሎት ኮሚቴ ውስጥ በመሥራት ለበላይ አካሉ ረዳት ሆኜ እያገለገልኩ ነው። ትንሽም ቢሆን ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር በዚህ መንገድ የመደገፍ መብት በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች ኢሳይያስ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” በማለት ያሳየውን ዝንባሌ በመያዝ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲገቡ ማየት ምንጊዜም ያስደንቀናል። (ኢሳ. 6:8) እነዚህ በርካታ ወጣቶች ያደረጉት ውሳኔ ከረጅም ጊዜ በፊት የወረዳ የበላይ ተመልካቹ እንዲህ በማለት የነገረኝ ሐሳብ እውነት መሆኑን ያሳያሉ፦ “አሁኑኑ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀምር። ምን ይታወቃል? ግሩም አጋጣሚዎችን ይከፍትልህ ይሆናል።”
^ አን.20 ከእነዚህ ወንድሞች የአንዳንዶቹን የሕይወት ታሪክ ለማንበብ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች (እንግሊዝኛ) ተመልከት፦ ቶማስ ሱሊቫን (ነሐሴ 15, 1965)፣ ክላውስ ጄንሰን (ጥቅምት 15, 1969)፣ ማክስ ላርሰን (መስከረም 1, 1989)፣ ሂዩጎ ሪመር (መስከረም 15, 1964) እና ግራንት ሱተር (መስከረም 1, 1983)