‘በመከራ ቀናት’ ይሖዋን ማገልገል
“ያለብኝ የጤና እክል እያደር ይበልጥ እያስቸገረኝ መጥቷል” በማለት በ70ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ኧርነስት የተባሉ አረጋዊ በትካዜ ይናገራሉ። * እናንተስ እንዲህ ይሰማችኋል? ዕድሜያችሁ እየገፋ እንዲሁም ጤና እያጣችሁና ጉልበታችሁ እየከዳችሁ ከሆነ በመክብብ ምዕራፍ 12 ላይ የሚገኙትን መግለጫዎች በደንብ ትረዷቸዋላችሁ። በቁጥር 1 ላይ የእርጅና ዘመን፣ “አስጨናቂ የሆኑት ዘመናት” ወይም “የመከራ ቀናት” (የግርጌ ማስታወሻ) ተብሎ ተጠርቷል። ይህ ማለት ግን ሕይወታችሁ ደስታ የራቀው ይሆናል ማለት አይደለም። አሁንም ቢሆን ይሖዋን በደስታ በማገልገል አርኪ ሕይወት መምራት ትችላላችሁ።
ጠንካራ እምነት ይዞ መቀጠል
ውድ አረጋውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ እንዲህ ያለ መከራ የሚደርስባችሁ እናንተ ብቻ እንዳልሆናችሁ ማወቃችሁ ያጽናናችሁ ይሆናል። በጥንት ዘመን የነበሩት በዕድሜ የገፉ የይሖዋ አገልጋዮችም ተመሳሳይ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና አኪያህ ማየት ተስኗቸው ነበር። (ዘፍ. 27:1፤ 48:10፤ 1 ነገ. 14:4) ንጉሥ ዳዊትም ዕድሜው እየገፋ ስለሄደ “ሊሞቀው አልቻለም።” (1 ነገ. 1:1) ባለጸጋው ቤርዜሊ ምግብ ማጣጣም ወይም በሙዚቃ መደሰት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። (2 ሳሙ. 19:32-35) አብርሃምና ናኦሚ ደግሞ የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም አስፈልጓቸዋል።—ዘፍ. 23:1, 2፤ ሩት 1:3, 12
ታዲያ ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ለመሆንና ደስታቸውን ለመጠበቅ የረዳቸው ምንድን ነው? አብርሃም በእርጅና ዘመኑም በአምላክ ተስፋዎች ማመኑ ‘በእምነት እንዲበረታ’ አድርጎታል። (ሮም 4:19, 20) እኛም ብንሆን ጠንካራ እምነት ያስፈልገናል። እንዲህ ዓይነቱ እምነት በዕድሜያችን፣ በችሎታችን ወይም በሁኔታችን ላይ የተመካ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ ያዕቆብ ሰውነቱ በደከመበት፣ ማየት በተሳነውና የአልጋ ቁራኛ በነበረበት ጊዜ እንኳ በአምላክ ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለው አሳይቷል። (ዘፍ. 48:1-4, 10፤ ዕብ. 11:21) በዛሬው ጊዜም እንዲህ ያሉ አረጋውያን አሉ። የ93 ዓመት አረጋዊት የሆኑት ኢኔስ፣ ጡንቻ የሚያዝል ሕመም የሚያሠቃያቸው ቢሆንም እንዲህ ብለዋል፦ “በየቀኑ ይሖዋ አብዝቶ እንደባረከኝ ይሰማኛል። ስለ ገነት በየዕለቱ አስባለሁ። ይህ ደግሞ ተስፋ ይሰጠኛል።” እንዴት ያለ አዎንታዊ መንፈስ ነው!
እኛም በጸሎት፣ የአምላክን ቃል በመመርመርና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እምነታችንን ማጠናከር እንችላለን። አረጋዊ የሆነው ነቢዩ ዳንኤል ዘወትር በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልይ እንዲሁም የአምላክን ቃል በቋሚነት ያጠና ነበር። (ዳን. 6:10፤ 9:2) አረጋዊቷ መበለት ሐናም “ከቤተ መቅደስ ፈጽሞ አትጠፋም ነበር።” (ሉቃስ 2:36, 37) እናንተም በተቻላችሁ መጠን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስትገኙና የአቅማችሁን ያህል ተሳትፎ ስታደርጉ ራሳችሁን ብቻ ሳይሆን በስብሰባው ላይ የተገኙትን ሁሉ ታበረታታላችሁ። ደግሞም ማድረግ የምትችሉት ነገር ውስን ቢሆንም እንኳ ይሖዋ በምታቀርቧቸው ጸሎቶች ምንጊዜም ደስ ይለዋል።—ምሳሌ 15:8
እናንት ታማኝ አረጋውያን፣ ራሳችሁ ብታነቡ እንዲሁም በስብሰባ ላይ ለመገኘት ብርታት ቢኖራችሁ እንደምትደሰቱ ጥያቄ የለውም፤ ይሁንና እንዲህ ማድረጉ እያደር አስቸጋሪ ምናልባትም የማይቻል ሆኖባችኋል። ታዲያ ምን ብታደርጉ ይሻላል? ያላችሁን ነገር ሁሉ ጥሩ አድርጋችሁ ተጠቀሙበት። በስብሰባዎች ላይ መገኘት የማይችሉ ብዙዎች በስልክ አማካኝነት ትምህርቱን ያዳምጣሉ። የ79 ዓመት አረጋዊት የሆኑት ኢንገ የማየት ችሎታቸው እየደከመ ቢመጣም በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወንድም በትላልቅ ፊደላት እያተመ የሚያመጣላቸውን ጽሑፎች በመጠቀም ለስብሰባዎች ይዘጋጃሉ።
በተጨማሪም ሌሎች ቢኖራቸው ደስ የሚላቸው ነገር ይኸውም ጊዜ ይኖራችሁ ይሆናል። ታዲያ ጊዜያችሁን በድምፅ የተቀዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲሁም ንግግሮችንና ድራማዎችን ለማዳመጥ ለምን አትጠቀሙበትም? ከዚህም ሌላ ቅድሚያውን በመውሰድ ለእምነት አጋሮቻችሁ ስልክ ደውላችሁ መንፈሳዊ ስጦታ በማካፈል ‘እርስ በርስ መበረታታት’ ትችላላችሁ።—ሮም 1:11, 12
በአምላክ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ
በ80ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙ ክሪስታ የተባሉ እህት “በአንድ ወቅት ታደርጉት እንደነበረው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለመቻል ስሜትን የሚጎዳ ነገር ነው” በማለት በሐዘን ተናግረዋል። ታዲያ አረጋውያን ደስተኛ ሆነው መኖር የሚችሉት እንዴት ነው? የ75 ዓመት አረጋዊ የሆኑት ፒተር “አዎንታዊ
አመለካከት በመያዝ ነው” ብለዋል፤ አክለውም “እንደ ቀድሞው ልታከናውኑት ስለማትችሉት ነገር ሁልጊዜ ከማሰብ ይልቅ ማድረግ በምትችሉት ነገር መደሰት” ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸዋል።አሁንም ልትካፈሉ የምትችሉባቸው የስብከት ዘርፎችን ማሰብ ትችላላችሁ? እህት ሃይዲ እንደ ቀድሟቸው ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ አይችሉም። እኚህ እህት ኮምፒውተር ተጠቅመው ደብዳቤ መጻፍ የተማሩት በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሆነው ነው። አንዳንድ አረጋውያን አስፋፊዎች፣ በመናፈሻ ውስጥ ወይም በአውቶቡስ ፌርማታ ተቀምጠው ከሰዎች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ይጀምራሉ። የምትኖሩት በአረጋውያን መጦሪያ ተቋም ውስጥ ከሆነ ደግሞ ይህን ቦታ እንደ ክልላችሁ በመመልከት ለሚንከባከቧችሁ የሕክምና ባለሙያዎችና እዚያ ለሚኖሩ ሌሎች ሰዎች መስበክ ትችሉ ይሆን?
ንጉሥ ዳዊት በእርጅና ዘመኑ እውነተኛውን አምልኮ ለማራመድ ጉጉት ነበረው። ለቤተ መቅደስ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ የለገሰ ከመሆኑም ሌላ ለዚሁ ዓላማ መዋጮ እንዲሰባሰብ አድርጓል። (1 ዜና 28:11 እስከ 29:5) እናንተም በተመሳሳይ በመላው ዓለም ከመንግሥቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን እየተከናወነ እንዳለ በንቃት መከታተል ትችላላችሁ። በጉባኤያችሁ ያሉትን አቅኚዎች ወይም ሌሎች ቀናተኛ አስፋፊዎች የሚያበረታቱ ቃላት በመናገር፣ አነስተኛ ስጦታ በመስጠት ወይም ቀለል ያለ ምግብና መጠጥ በመጋበዝ ለምን አትደግፏቸውም? ከዚህም ሌላ ወጣቶችንና ቤተሰብ ያላቸውን ክርስቲያኖች፣ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን፣ የታመሙትን እንዲሁም ከባድ ኃላፊነት ያለባቸውን በጸሎታችሁ ላይ ማካተት ትችሉ ይሆናል።
የምታቀርቡት አገልግሎትም ሆነ እናንተ ራሳችሁ በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ አላችሁ። እናንት ውድ አረጋውያን፣ የሰማዩ አባታችን ፈጽሞ አይተዋችሁም። (መዝ. 71:9) ይሖዋ ይወዳችኋል፤ እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከታችኋል። በቅርቡ ደግሞ ሁላችንም እርጅና ከሚያስከትለው ሥቃይና ችግር ጋር መታገል ሳያስፈልገን ረጅም ዕድሜ መኖር እንችላለን። አዎን፣ ሙሉ ኃይልና ፍጹም ጤንነት ኖሮን አፍቃሪውን አምላካችንን ይሖዋን ለዝንተ ዓለም እያገለገልን እንኖራለን!
^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።