በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት ከአሁኑ ተዘጋጁ
‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀው መያዝ ይችሉ ዘንድ መልካም ነገር እንዲያደርጉ ምከራቸው።’—1 ጢሞ. 6:18, 19
መዝሙሮች፦ 125, 40
1, 2. (ሀ) ምድር ገነት ስትሆን ለማግኘት በጣም የሚያጓጓህ በረከት የትኛው ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን ዓይነት መንፈሳዊ በረከቶች እናገኛለን?
‘እውነተኛ የሆነው ሕይወት።’ አብዛኞቻችን ይህን አገላለጽ ስንሰማ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት እንስባለን። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ‘ከዘላለም ሕይወት’ ጋር አያይዞ ገልጾታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19ን አንብብ።) በመሆኑም ዘላለማዊ የሆነ እንዲሁም ማብቂያ የሌለው እርካታና ደስታ የሚያስገኝልንን ሕይወት በተስፋ እንጠባበቃለን። በየዕለቱ በአካልም ሆነ በአእምሮ ጤናማ ሆነን እንዲሁም መንፈሳችን ታድሶ ከእንቅልፋችን ስንነቃ ምን ሊሰማን እንደሚችል መገመት ይከብዳል። (ኢሳ. 35:5, 6) ከሞት የተነሱትን ጨምሮ ከቤተሰቦቻችንና ከጓደኞቻችን ጋር መገናኘት ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን አስበው! (ዮሐ. 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) በተጨማሪም በሳይንስ፣ በሙዚቃ፣ በሥነ ሕንፃ ወይም በሌሎች መስኮች ችሎታችንን እያሻሻልን የመሄድ አጋጣሚ ይኖረናል።
2 በአዲሱ ዓለም ውስጥ እነዚህን ጥሩ ነገሮች ለማግኘት የምንጓጓ ቢሆንም በዚያ የምናገኛቸው መንፈሳዊ በረከቶች ትልቁን ቦታ ይይዛሉ። የይሖዋ ስም እንደተቀደሰና ሉዓላዊነቱ እንደተረጋገጠ ማወቃችን እንዴት ያለ ጥልቅ ደስታ ያመጣልናል! (ማቴ. 6:9, 10) ይሖዋ ለሰዎችም ሆነ ለምድር ከመጀመሪያው የነበረው ዓላማ ሲፈጸም ስናይ እጅግ እንደሰታለን። ከዚህም ሌላ ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ስንደርስ ወደ ይሖዋ መቅረብ ምን ያህል ቀላል እንደሚሆንልን አስበው!—መዝ. 73:28፤ ያዕ. 4:8
3. አሁን ለየትኛው ጊዜ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል?
3 ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል” የሚል ማረጋገጫ ስለሰጠን እነዚህን በረከቶች እንደምናገኝ ጥያቄ የለውም። (ማቴ. 19:25, 26) ይሁንና በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር፣ ብሎም ከክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ባሻገር በሕይወት ለመቀጠል ተስፋ የምናደርግ ከሆነ የዘላለምን ሕይወት ‘አጥብቀን ለመያዝ’ እርምጃ መውሰድ ያለብን ዛሬ ነው። የዚህን ክፉ ዓለም ፍጻሜ እየተጠባበቅን መኖር ያለብን ከመሆኑም ሌላ በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት ለመዘጋጀት የሚረዱንን እርምጃዎች አሁኑኑ መውሰድ ያስፈልገናል። ታዲያ በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ እየኖርን ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
4. በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት በአሁኑ ጊዜ እንዴት መዘጋጀት እንደምንችል በምሳሌ አስረዳ።
4 አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚኖረው ሕይወት አሁን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ ወደ ሌላ አገር ለመዛወር አስበናል እንበል። እዚያ ስንሄድ ለሚያጋጥመን ለውጥ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? መጀመሪያ፣ የዚያ አገር ሰዎች የሚናገሩትን ቋንቋ እንማር ይሆናል። ስለ ባሕላቸው ለማወቅ ጥረት ማድረጉ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ምግቦቻቸውንም እንሞክር ይሆናል። በተወሰነ መጠን፣ የዚያ አገር ነዋሪ ስንሆን በምንኖርበት መንገድ ሕይወታችንን መምራት እንጀምራለን። ደግሞም እዚያ ከደረስን በኋላ የምንኖረው በዚህ መንገድ ነው። በተመሳሳይም በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንደምንኖር በምናስበው መንገድ በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችንን በመምራት በዚያ ወቅት ለሚኖረው ሕይወት መዘጋጀት እንችላለን። በዚህ ረገድ እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት።
5, 6. ለቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶች መገዛትን መማር ለአዲሱ ዓለም ሕይወት የሚያዘጋጀን እንዴት ነው?
5 በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሁሉም ፍጥረታት የአምላክን ሉዓላዊነት ይደግፋሉ። በዚያ የሚኖረው ሁኔታ ሰይጣን የሚቆጣጠረው ይህ ዓለም ከሚያስፋፋው በራስ ፈቃድ የመመራት ዝንባሌ ምንኛ የተለየ ይሆናል! አንዳንዶች በራስ መንገድ መሄድና እንደምንም ብሎ የግል ምርጫ እንዲከበር ማድረግ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ሆኖም ይህ ምን አስከትሏል? የአምላክን አመራር አለመቀበል መከራና ጉስቁልና አልፎ ተርፎም ከባድ ሥቃይ አምጥቷል። (ኤር. 10:23) የሰው ዘር በሙሉ፣ ፍቅራዊ የሆነውን የይሖዋ ሉዓላዊ አገዛዝ የሚቀበልበትን ጊዜ ምንኛ በጉጉት እንጠባበቃለን!
6 በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን አመራር እየተከተልን ምድርን ማስዋብ፣ ከሞት የተነሱ ሰዎችን ማስተማርና አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ፈቃድ መፈጸም ትልቅ ደስታ የሚያመጣ ነገር ይሆናል። ሆኖም ብዙም የማያስደስተንን ሥራ እንድንሠራ መመሪያ ቢሰጠንስ? ይህን መመሪያ አክብረን አቅማችን በፈቀደው መጠን ሥራውን ጥሩ አድርገን ለማከናወንና ከሥራው ደስታ ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን? ብዙዎቻችን ‘አዎ’ ብለን እንመልስ ይሆናል። ይህ ከሆነ ታዲያ ዛሬስ ለቲኦክራሲያዊ መመሪያ እየተገዛን ነው? እንዲህ እያደረግን ከሆነ በይሖዋ አገዛዝ ሥር ለሚኖረው የዘላለም ሕይወት እየተዘጋጀን ነው።
7, 8. (ሀ) የመተባበር መንፈስ ማዳበር ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ለውጥ አጋጥሟቸዋል? (ሐ) በአዲሱ ዓለም በምድር ላይ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
7 በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት ለመዘጋጀት በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ላደረገው ዝግጅት ከመገዛት ባለፈ ባለን ነገር የመርካትና ተባብሮ የመሥራት መንፈስ ማዳበርም ይኖርብናል። በዛሬው ጊዜ አመራር ከሚሰጡት ጋር ተባብረን የምንሠራ፣ ለምሳሌ በሚሰጠን አዲስ የአገልግሎት ምድብ እርካታና ደስታ የምናገኝ ከሆነ በአዲሱ ዓለም ውስጥም እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይችላል። (ዕብራውያን 13:17ን አንብብ።) እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ከወረሱ በኋላ ውርሻቸውን የተከፋፈሉት በዕጣ ነው። (ዘኁ. 26:52-56፤ ኢያሱ 14:1, 2) እርግጥ ነው፣ በአዲሱ ሥርዓት እንድንኖር የምንመደበው የት እንደሚሆን ዛሬ የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና በዚያ ጊዜ በምድር ላይ የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ የትብብር መንፈስ ካለን የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ እርካታና ጥልቅ ደስታ እናገኛለን።
8 በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የመኖር መብት ለማግኘት ስንል ከይሖዋ ድርጅት ጋር ለመተባበርና ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ማንኛውንም ጥረት ብናደርግ የሚያስቆጭ አይሆንም። እርግጥ ነው፣ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ያለንበት ሁኔታ ሊለወጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ የዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል ቤተሰብ አባላት መስክ ላይ እንዲያገለግሉ ተመድበዋል፤ አሁን በሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች እየተካፈሉ በመሆናቸው የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል። ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆነው ያገለግሉ የነበሩ አንዳንድ ወንድሞች ደግሞ በዕድሜ መግፋት ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ልዩ አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። ባለን ነገር የምንረካ፣ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት የምንጸልይና በእሱ አገልግሎት የቻልነውን ያህል ለማድረግ የምንጥር ከሆነ በዚህ አስጨናቂ ዘመንም ቢሆን ደስታና ብዙ በረከት ማግኘት እንችላለን። (ምሳሌ 10:22ን አንብብ።) ወደፊትስ ምን ይጠብቀናል? በአዲሱ ዓለም ውስጥ መኖሪያችን እንዲሆን የምንመርጠው ቦታ ሊኖር ቢችልም ወደ ሌላ አካባቢ እንድንሄድ እንጠየቅ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የምናገለግለው የትም ይሁን የት እንዲሁም የምንሠራው ሥራ ምንም ይሁን ምን በደስታ እየተፍለቀለቅን፣ በአመስጋኝነትና በእርካታ ስሜት ተሞልተን እንደምንኖር እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—ነህ. 8:10
9, 10. (ሀ) በአዲሱ ዓለም በየትኞቹ አቅጣጫዎች ትዕግሥት ማሳየት ሊያስፈልገን ይችላል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ትዕግሥተኛ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
9 በአዲሱ ዓለም አንዳንድ ነገሮችን በትዕግሥት መጠበቅ ሊያስፈልገን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ግለሰቦች ከሞት እንደተነሱና በዚህም የተነሳ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው እጅግ እንደተደሰቱ እንሰማ ይሆናል። እኛ ግን የምንወዳቸው ሰዎች ከሞት እስኪነሱ መጠበቅ ሊያስፈልገን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ከሌሎች ጋር መደሰትና በትዕግሥት መጠበቅ እንችላለን? (ሮም 12:15) ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች እስኪፈጸሙ ድረስ አሁን በትዕግሥት መጠበቅ ከተማርን በዚያን ጊዜ መታገሥ አያስቸግረንም።—መክ. 7:8
10 የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን በተመለከተ ባለን ግንዛቤ ላይ ከሚደረግ ማስተካከያ ጋር በተያያዘ ትዕግሥት በማሳየትም ለአዲሱ ዓለም መዘጋጀት እንችላለን። በዛሬው ጊዜ ቀስ በቀስ እየጠራ የሚሄደውን እውነት በትጋት እናጠናለን? ማስተካከያዎቹ ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይሆኑልንስ ትዕግሥት እናሳያለን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይሖዋ ከሰው ልጆች የሚጠብቀውን ብቃት በየጊዜው ሲያሳውቀን ትዕግሥት ማሳየት አይከብደንም።—ምሳሌ 4:18፤ ዮሐ. 16:12
11. በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ ምን እያስተማረን ነው? ይህ ለአዲሱ ዓለም የሚጠቅመን እንዴት ነው?
11 በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት የሚጠቅመን ሌላው ባሕርይ ደግሞ የይቅር ባይነት መንፈስ ነው። በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት፣ ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች የአለፍጽምና ውጤት የሆኑ ባሕርያትን ገፍፈው ለመጣል የተወሰነ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። (ሥራ 24:15) በዚያን ጊዜ አንዳችን ሌላውን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ መያዝ እንችል ይሆን? አሁን በነፃ ይቅር የምንባባል እንዲሁም በመካከላችን የሻከረ ግንኙነት እንዳይኖር የምንጥር ከሆነ ያን ጊዜ ይህን ማድረግ አይከብደንም።—ቆላስይስ 3:12-14ን አንብብ።
12. ወደፊት ስለሚኖረን ሕይወት በምንጠብቀው ነገርና አሁን በምንከተለው አኗኗር መካከል ያለውን ዝምድና አብራራ።
12 በአዲሱ ዓለም ውስጥ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ በፈለግነው ጊዜ እናገኛለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዚያ በምንኖርበት ጊዜ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፣ ፍቅር ለሚንጸባረቅበት የይሖዋ ሉዓላዊነት መገዛት ለሚያስገኝልን ጥቅም አመስጋኝ መሆንና ባለን መርካት ይኖርብናል። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እንድናዳብራቸው እያስተማረን ያሉትን ባሕርያት ማሳየትም ያስፈልገናል። ዕብ. 2:5፤ 11:1) በተጨማሪም በምድር ላይ የሚኖረውን ጽድቅ የሰፈነበት ሁኔታ ለማየት ምን ያህል እንደምንጓጓ እናሳያለን። በእርግጥም በአምላክ አዲስ ዓለም ለምናገኘው የዘላለም ሕይወት እየተዘጋጀን ነው ማለት ይቻላል።
በዚያን ጊዜ እንደምንኖር በምናስበው መንገድ አሁን የምንኖር ከሆነ ለዘላለም ልናንጸባርቃቸው የሚገቡ ባሕርያትን እያዳበርን ነው። እንዲሁም ‘መጪው ዓለም’ እውን እንደሚሆን ያለንን እምነት እያጠናከርን ነው። (በአሁኑ ጊዜ ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት ስጡ
13. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ለየትኞቹ ነገሮች ነው?
13 ከፊታችን ለሚጠብቀን እውነተኛ ሕይወት የምንዘጋጅበትን ሌላ መንገድ ደግሞ እንመልከት። በአዲሱ ዓለም ውስጥ በምድር ላይ የተትረፈረፈ ምግብ እንደምናገኝና ሌሎች ነገሮች እንደሚሟሉልን ቃል የተገባልን ቢሆንም ከሁሉ የላቀ እርካታ የምናገኘው መንፈሳዊ ፍላጎታችን በመሟላቱ ነው። (ማቴ. 5:3) ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሲሆን በይሖዋ ሐሴት እንደምናደርግ እናሳያለን። (መዝ. 37:4) እንግዲያው በአሁኑ ጊዜ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ወደፊት ለምናገኘው እውነተኛ ሕይወት እንዘጋጃለን።—ማቴዎስ 6:19-21ን አንብብ።
14. ወጣቶች በዘላለም ሕይወት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የትኞቹ መንፈሳዊ ግቦች ይረዷቸዋል?
14 በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል የምናገኘውን ደስታ ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ መንፈሳዊ ግቦችን በማውጣት ነው። ወጣት ከሆንክና በይሖዋ አገልግሎት በሙሉ ጊዜህ ለመሰማራት በቁም ነገር እያሰብክ ከሆነ ስለተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች የወጡ አንዳንድ ጽሑፎችን ለምን አትከልስም? ከዚያም ከእነዚህ በአንዱ ለመካፈል ግብ ልታወጣ ትችላለህ። * በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ብዙ ዓመታት ያሳለፉ አንዳንድ ወንድሞችን ማነጋገርም ትችላለህ። ይሖዋን በማገልገል የምታሳልፈው ሕይወት፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ አምላክን ማገልገልህን እንድትቀጥል ያዘጋጅሃል፤ አሁን ያገኘኸው ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና እና ያዳበርከው ልምድ በዚያ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል።
15. የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የትኞቹ መንፈሳዊ ግቦች ላይ መድረስ ይችላሉ?
15 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን መጠን ምን ዓይነት መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት እንችላለን? በአንድ የአገልግሎት መስክ ችሎታችንን ለማሻሻል ግብ ማውጣት እንችላለን። አሊያም ደግሞ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ተግባራዊ ሊሆኑ ስለሚችሉበት መንገድ ያለንን እውቀት ለማሳደግ መጣር እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ በሕዝብ ፊት በማንበብና ንግግር በማቅረብ ወይም በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ ትችላለህ። ሌሎች ግቦችም ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። ነጥቡ ይህ ነው፦ መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ያለህ ቅንዓት እንዲጨምር
ያደርጋል፤ ይህም በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት ራስህን እንድታዘጋጅ ይረዳሃል።በረከቱ ከአሁኑ ጀምሯል!
16. ይሖዋን ማገልገል ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ለመምራት ያስችለናል የምንለው ለምንድን ነው?
16 አምላክ ለሚያመጣው አዲስ ዓለም በመዘጋጀት ጊዜያችንን ማሳለፋችን በዛሬው ጊዜ የተሻለ ወይም ይበልጥ የሚያረካ ሕይወት እንዳናገኝ ያደርገን ይሆን? በጭራሽ! አንድ ሰው ይሖዋን ማገልገሉ ከምንም በላይ አርኪ የሆነ ሕይወት ለመምራት ያስችለዋል። አምላክን የምናገለግለው ታላቁን መከራ በሕይወት ለማለፍ ስንል ግዴታ ሆኖብን አይደለም። የተፈጠርነው ይሖዋን እያገለገልን እንድንኖር ከመሆኑም ሌላ ይህን ማድረጋችን የላቀ ደስታ ያስገኝልናል። የይሖዋን መመሪያ ማግኘትና ታማኝ ፍቅሩን መቅመስ ከእሱ ርቀን ከምንመራው ሕይወት እጅግ የተሻለ ነው። (መዝሙር 63:1-3ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል የሚያስገኘውን መንፈሳዊ በረከት ለማጣጣም አዲሱን ዓለም መጠበቅ አያስፈልገንም፤ አሁንም ቢሆን በረከቱን ማጣጣም እንችላለን! በእርግጥም አንዳንዶቻችን ይህን በረከት ለብዙ አሥርተ ዓመታት ስናጭድ ቆይተናል፤ እንዲሁም ከዚህ የላቀ እርካታ የሚያስገኝ ሌላ የሕይወት መንገድ እንደሌለ ከተሞክሮ ተገንዝበናል።—መዝ. 1:1-3፤ ኢሳ. 58:13, 14
17. የምንወዳቸውና የሚያስደስቱን ነገሮች በገነት ውስጥ ምን ቦታ ይኖራቸዋል?
17 አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የምንወዳቸውንና የሚያስደስቱንን ነገሮች ለማከናወን አጋጣሚ እናገኛለን። ደግሞም ይሖዋ እነዚህን ፍላጎቶች እንድናሟላ ባይፈልግ ኖሮ በሥራችን የመርካትና ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች የመደሰት ፍላጎት በውስጣችን ይፈጥር ነበር? (መክ. 2:24) በዚህም ሆነ በሌሎች መንገዶች ይሖዋ ምንጊዜም ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት ያሟላል።’ (መዝ. 145:16) እረፍትና መዝናኛ የራሳቸው ቦታ አላቸው፤ ሆኖም ከእነዚህ ነገሮች የበለጠ ደስታ ማግኘት የምንችለው ከይሖዋ ጋር ላለን ግንኙነት ቅድሚያ ስንሰጥ ነው። ምድር ገነት ስትሆንም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እንግዲያው አስቀድመን መንግሥቱን በመፈለግና የይሖዋ ሕዝቦች አሁን በሚያገኟቸው መንፈሳዊ በረከቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለግል ፍላጎቶቻችን ሁለተኛ ቦታ መስጠትን መልመዳችን ምንኛ ጥበብ ነው!—ማቴ. 6:33
18. በገነት ውስጥ ለምናገኘው የዘላለም ሕይወት እየተዘጋጀን እንደሆነ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
18 ምድር ገነት ስትሆን ከዚህ በፊት አይተን በማናውቀው መጠን ደስታ እናገኛለን። ለእውነተኛው ሕይወት ከአሁኑ በመዘጋጀት ይህን ሕይወት ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን እናሳይ። አምላካዊ ባሕርያትን እናዳብር፤ እንዲሁም እንድናከናውን በተሰጠን የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በቅንዓት በመካፈል የሚገኘውን ታላቅ ደስታ እናጣጥም። መንፈሳዊ ግቦችን በመከታተል ሐሴት እናድርግ። በተጨማሪም ይሖዋ በገባው ቃል ሙሉ በሙሉ እምነት በማሳደር በአሁኑ ጊዜ፣ የአዲሱን ዓለም ሕይወት እንደምንጠባበቅ በሚያሳይ መንገድ እንኑር!