የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
የኢየሱስ ስብከት ጭብጥ ምን ነበር? እሱ ራሱ እንደገለጸው የስብከቱ ጭብጥ የአምላክ መንግሥት ነበር። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ብዙ ጊዜ ይጠቅስ ነበር። ይህን በማድረጉ ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ግራ ተጋብተው ወይም ሐሳቡ እንቆቅልሽ ሆኖባቸው አሊያም የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነ ጠይቀውት ነበር? አልነበረም። በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን አናገኝም። ታዲያ በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ያውቁ ነበር ማለት ነው?
አይሁዳውያን እንደ ቅዱስ አድርገው የሚመለከቷቸው ጥንታዊ መጻሕፍት፣ ስለ አምላክ መንግሥት ምንነትና ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ግልጽ በሆነ መንገድ ተናግረዋል። በዛሬው ጊዜም መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ስለ አምላክ መንግሥት ይበልጥ ማወቅ እንችላለን። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ መንግሥት የሚያስተምረንን ሰባት ነጥቦች እንመልከት። መጀመሪያ የምንመለከታቸውን ሦስት ነጥቦች በኢየሱስ ዘመንም ሆነ ከዚያ በፊት የነበሩ አይሁዳውያን ያውቋቸው ነበር። ቀጥሎ የቀረቡት ሦስት ነጥቦች ደግሞ ክርስቶስ አሊያም ሐዋርያቱ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የገለጿቸው ናቸው። የመጨረሻው የታወቀው በእኛ ዘመን ነው።
1. የአምላክ መንግሥት ለዘላለም የሚገዛ እውን መስተዳድር ነው። የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አምላክ ለታማኝ የሰው ልጆች አዳኝ እንደሚልክ የሚገልጽ ነበር። ‘ዘር’ ተብሎ የተጠራው ይህ አዳኝ የአዳም፣ የሔዋንና የሰይጣን ዓመጽ ያስከተላቸውን ችግሮች በሙሉ ያስተካክላል። (ዘፍጥረት 3:15) ይህ ትንቢት ከተነገረ ከብዙ ጊዜ በኋላ ታማኙ ንጉሥ ዳዊት ስለዚህ ‘ዘር’ ወይም መሲሕ አስደሳች ነገር ተነገረው። ይህ ዘር የአንድ መንግሥት ንጉሥ ይሆናል። ይህ መንግሥት ለዘላለም ስለሚገዛ ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ የተለየ ነው።—2 ሳሙኤል 7:12-14
2. የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ያጠፋል። ነቢዩ ዳንኤል፣ በታሪክ ውስጥ እስከ ዘመናችን ድረስ በተከታታይ ስለተነሱት የዓለም ኃያል መንግሥታት የሚገልጽ ራእይ ተመልክቶ ነበር። የዚህን ራእይ አስደሳች መደምደሚያ ልብ በል:- “በነዚያ [የመጨረሻዎቹ ሰብዓዊ] ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” በዚህ ራእይ መሠረት የዚህ ዓለም መንግሥታትም ሆኑ የሚያካሂዱት ጦርነት እንዲሁም የሚፈጽሙት ጭቆናና ምግባረ ብልሹነት ለዘላለም ይጠፋሉ። የዳንኤል ትንቢት እንደሚያሳየው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ መላውን ምድር ይገዛል። (ዳንኤል 2:44, 45) እውን የሆነው ይህ መንግሥት በምድር ላይ የሚገዛው ብቸኛ መስተዳድር ይሆናል። *
3. የአምላክ መንግሥት ጦርነትን፣ በሽታን፣ ረሃብንና ሞትንም ሳይቀር ያስወግዳል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ምን እንደሚያከናውን የሚገልጹ አስደሳች ትንቢቶች ይዟል። ይህ መንግሥት የትኛውም ሰብዓዊ አገዛዝ ያላከናወነውን ወይም ሊያከናውነው የማይችለውን ነገር ይፈጽማል። የጦር መሣሪያዎች ሁሉ ለዘላለም ሲወገዱ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር መገመት ትችላለህ! አምላክ “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል።” (መዝሙር 46:9) ሐኪሞችና ሆስፒታሎች አይኖሩም፤ እንዲሁም ማንኛውም በሽታ ይወገዳል። “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” (ኢሳይያስ 33:24) ረሃብ፣ የምግብ እጥረት ወይም የተመጣጠነ ምግብ እጦት አይኖርም። “በምድሪቱ ላይ እህል [ይትረፈረፋል]።” (መዝሙር 72:16) የቀብር ሥነ ሥርዓትና አስከሬን እየጠበቁ ማደር እንዲሁም መካነ መቃብሮች፣ የአስከሬን ማስቀመጫ ክፍሎች ወይም ከእነዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሐዘን ሁሉ ይቀራል። በመጨረሻም ምሕረት የማያውቀው ጠላታችን ሞት ይወገዳል። አምላክ “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”—ኢሳይያስ 25:8
4. የአምላክ መንግሥት በአምላክ የተመረጠ ገዥ አለው። መሲሑ፣ ራሱን የሾመ መሪ ወይም ፍጽምና በሌላቸው ሰዎች የተመረጠ ገዥ አይደለም። መሲሑን የመረጠው ይሖዋ አምላክ ነው። መሲሕ እና ክርስቶስ የሚሉት የማዕረግ ስሞች ይህንን የሚጠቁሙ ናቸው። ሁለቱም ቃላት “የተቀባ” የሚል ትርጉም አላቸው። ስለዚህ ይህ ንጉሥ የተቀባ ወይም ለሚያከናውነው ልዩ ሥራ በይሖዋ የተመረጠ ነው። አምላክ ስለ እሱ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ደግፌ የያዝሁት አገልጋዬ፣ በእርሱም ደስ የሚለኝ ምርጤ ይህ ነው፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ለአሕዛብም ፍትሕን ያመጣል።” (ኢሳይያስ 42:1፤ ማቴዎስ 12:17, 18) ምን ዓይነት ገዥ እንደሚያስፈልገን ከፈጣሪያችን የበለጠ ማን ሊያውቅ ይችላል?
5. የአምላክ መንግሥት ገዥ ብቁ መሆኑን ለሰው ዘር በሙሉ አሳይቷል። የናዝሬቱ ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ መሆኑን አረጋግጧል። ኢየሱስ የመጣው አምላክ ከመረጠው የዘር ሐረግ ነበር። (ዘፍጥረት 22:18፤ 1 ዜና መዋዕል 17:11፤ ማቴዎስ 1:1) ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ስለ መሲሑ የተነገሩ በርካታ ትንቢቶች ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት በእሱ ላይ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ከዚህም በላይ መሲሕ መሆኑን ከሰማይ ተመሥክሮለታል። ይህ የሆነው እንዴት ነው? አምላክ፣ ልጁ እንደሆነ ከሰማይ ሆኖ መሥክሮለታል፤ መላእክትም ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ እንደሆነ ጠቁመዋል። እንዲሁም ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ በመቶዎች እንዲያውም በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ፊት ተአምራት የፈጸመ ሲሆን ይህንንም ያደረገው በአምላክ ኃይል እንደሆነ ግልጽ ነው። * ኢየሱስ ምን ዓይነት ገዥ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ባደረጋቸው ነገሮች አሳይቷል። ሰዎችን ለመርዳት ኃይል ብቻ ሳይሆን ፍላጎቱም ነበረው። (ማቴዎስ 8:1-3) ኢየሱስ ራስ ወዳድ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ርኅሩኅ፣ ደፋርና ትሑት ነበር። በምድር ላይ እያለ ያከናወናቸውን ነገሮች ሁሉም ሰው ማንበብ እንዲችል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረዋል።
6. የአምላክ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር የሚገዙ 144,000 ተባባሪ ገዥዎች አሉት። ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱን ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም) ቆየት ብሎም ሐዋርያው ዮሐንስ የዚህ ታናሽ መንጋ ቁጥር 144,000 እንደሆነ ተነገረው። እነዚህ ሰዎች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታት ሆነው በመግዛትና ካህናት ሆነው በማገልገል አስደሳች ሥራ ያከናውናሉ።—ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3
ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ከእሱ ጋር በሰማይ እንደሚገዙ ተናግሯል። ይህንን ቡድን “ታናሽ መንጋ” በማለት ጠርቶታል። (7. የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በሰማይ እየገዛ ሲሆን በመላው ምድር ላይ ለመግዛት ተዘጋጅቷል። ይህ ሰባተኛ እውነት እስካሁን ከተማርነው ሁሉ ይበልጥ አስደሳች ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ለመግዛት ሥልጣን እንደተሰጠው የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎችን ይዟል። በአሁኑ ጊዜ በሰማይ እየገዛ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በመላዋ ምድር ላይ መግዛት ሲጀምር ቀደም ብለን የተመለከትናቸው አስደናቂ ትንቢቶች በሙሉ ይፈጸማሉ። ሆኖም የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ እየገዛ መሆኑን እንዴት እናውቃለን? በምድር ላይ መግዛት የሚጀምረውስ መቼ ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 ብዙዎች እንደተማሩት የአምላክ መንግሥት በውስጣችን ያለ ነገር አለመሆኑን እንደነዚህ ያሉት ትንቢቶች ያሳያሉ። በገጽ 13 ላይ የሚገኘውን “አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.8 በማቴዎስ 3:17፤ ሉቃስ 2:10-14፤ ዮሐንስ 6:5-14 ላይ የሚገኙትን ዘገባዎች እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል።