ልጆቻችሁን አስተምሩ
ማርቆስ ተስፋ አልቆረጠም
ስለ ኢየሱስ ሕይወት ከሚተርኩት አራት የወንጌል መጻሕፍት መካከል አንደኛውን የጻፈው ማርቆስ ነው። ይህ መጽሐፍ ከሁሉም አጭር ከመሆኑም በላይ ለማንበብ ቀላል ነው። ይሁን እንጂ ማርቆስ ማን ነበር? ኢየሱስን ያውቀው የነበረ ይመስልሃል?— * ማርቆስ ያጋጠሙትን ከባድ ፈተናዎች እንዲሁም ይህ ደቀ መዝሙር ተስፋ ቆርጦ የክርስትናን ጎዳና እንዳይተው የረዳው ምን እንደሆነ እንመልከት።
የማርቆስ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስን ወኅኒ ቤት ካስገባው በኋላ ነው። አንድ መልአክ በሌሊት ጴጥሮስን ከእስር ቤት ካስወጣው በኋላ ጴጥሮስ ወዲያውኑ የሄደው በኢየሩሳሌም ወደምትኖረው ማርያም ወደተባለችው የማርቆስ እናት ቤት ነበር። ጴጥሮስ ከወኅኒ ቤት ነፃ የወጣው ኢየሱስ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በፋሲካ ዕለት ከተገደለ ከአሥር ዓመት በኋላ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 12:1-5, 11-17
ጴጥሮስ ወደ ማርያም ቤት የሄደው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— እንዲህ ያደረገው ቤተሰቧን ስለሚያውቃቸው ወይም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቤቷ እንደሚሰበሰቡ ያውቅ ስለነበር ሊሆን ይችላል። የማርቆስ አክስት ልጅ የሆነው በርናባስ ደቀ መዝሙር ከሆነ ቆይቷል፤ ቢያንስ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል አንስቶ ደቀ መዝሙር ነበር። በርናባስ በዚያ ወቅት ለአዲስ ደቀ መዛሙርት ያደረገው ልግስና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ በርናባስን እንዲሁም አክስቱን ማርያምንና ልጇን ማርቆስን ሳያውቃቸው አይቀርም።—የሐዋርያት ሥራ 4:36, 37፤ ቈላስይስ 4:10
ማርቆስ በወንጌል ዘገባው ላይ እንደገለጸው ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት “ዕርቃኑን ለመሸፈን” በፍታ ያገለደመ አንድ ወጣት ነበር። ኢየሱስን ጠላቶቹ ሲይዙት ይህ ወጣት ሸሽቶ እንዳመለጠ ማርቆስ ዘግቧል። ይህ ወጣት ማን ይመስልሃል?— አዎን፣ ማርቆስ ሳይሆን አይቀርም! ኢየሱስና ሐዋርያቱ የዚያን ዕለት በሌሊት ሲወጡ ማርቆስ በችኮላ ልብስ ጣል አድርጎ ሳይከተላቸው አልቀረም።—ማርቆስ 14:51, 52
በእርግጥም ማርቆስ ከአምላክ አገልጋዮች ጋር የመገናኘትና ከአምላክ ዓላማ ጋር የተያያዙ ጉልህ ክንውኖችን የመመልከት አጋጣሚ ነበረው። ማርቆስ፣ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ተከታዮች ላይ ሲወርድ በቦታው ሳይገኝ አልቀረም፤ እንዲሁም እንደ ጴጥሮስ ካሉ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ጋር የቀረበ ወዳጅነት ነበረው። ከዚህም በላይ የአክስቱ ልጅ ከሆነው ከበርናባስ ጋርም አብሮ የነበረ ይመስላል፤ ኢየሱስ ለሳውል በራእይ ከተገለጠለት ከሦስት ዓመት በኋላ በርናባስ፣ ሳውልን ከጴጥሮስ ጋር አስተዋውቆታል። ከዓመታት በኋላ ደግሞ በርናባስ ሳውልን ለመፈለግ ወደ ጠርሴስ ሄዷል።—የሐዋርያት ሥራ 9:1-15, 27፤ 11:22-26፤ 12:25፤ ገላትያ 1:18, 19
በ47 ከክርስቶስ ልደት በኋላ፣ በርናባስ እና ሳውል በሚስዮናዊነት እንዲያገለግሉ ተመረጡ። ማርቆስ ከእነሱ ጋር ቢሄድም በኋላ ትቷቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ ማርቆስ እንዲህ ያደረገበትን ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። በሮማዊ ስሙ ጳውሎስ በመባል የሚታወቀው ሳውል በዚህ ሁኔታ በጣም ተናደደ። ጳውሎስ፣ ማርቆስ ትልቅ ጥፋት እንዳጠፋ ስለተሰማው ጉዳዩን በቸልታ አልተመለከተውም።—ጳውሎስና በርናባስ ከሚስዮናዊ ጉዟቸው ሲመለሱ፣ ያገኙትን አስደሳች ውጤት ለወንድሞች ነገሯቸው። (የሐዋርያት ሥራ 14:24-28) ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሁለቱም ቀደም ሲል ወደሰበኩበት ቦታ በመመለስ አዳዲሶቹን ደቀ መዛሙርት ለመጎብኘት ወሰኑ። በዚህ ጊዜ በርናባስ፣ ማርቆስን ይዞ ለመሄድ ፈለገ፤ ሆኖም ጳውሎስ ምን ተሰምቶት እንደነበር ታውቃለህ?— ከዚህ ቀደም ማርቆስ ትቷቸው ወደ ቤቱ ስለተመለሰ ጳውሎስ “እርሱን ይዞ ለመሄድ አልፈለገም።” ከዚህ በኋላ የተከሰተው ነገር ማርቆስን ሳያሳዝነው እንዳልቀረ ምንም ጥርጥር የለውም!
ጳውሎስም ሆነ በርናባስ በመናደዳቸው በመካከላቸው “የከረረ አለመግባባት” ተፈጠረ። በዚህም የተነሳ ሁለቱ ጓደኛሞች ተለያዩ፤ በርናባስ ማርቆስን ይዞ ለስብከት ወደ ቆጵሮስ ሲሄድ ጳውሎስ ደግሞ ቀደም ሲል እንዳሰበው አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን ለመጎብኘት ሲላስን ይዞ ሄደ። ማርቆስ፣ በጳውሎስና በበርናባስ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት በመሆኑ እንዴት አዝኖ ይሆን!—የሐዋርያት ሥራ 15:36-41
ማርቆስ ከዚህ ቀደም ወደ ቤቱ ለምን እንደተመለሰ አናውቅም። ምናልባት እንዲህ ለማድረግ የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት እንዳለው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ማርቆስ እንደገና እንዲህ እንደማያደርግ በርናባስ እርግጠኛ ነበር። ደግሞም አልተሳሳተም። ማርቆስ ተስፋ ቆርጦ ወደ ኋላ 1 ጴጥሮስ 5:13
አልተመለሰም! ከጊዜ በኋላም ከቤቱ ርቆ በሚገኘው በባቢሎን በሚስዮናዊነት አገልግሏል። ጴጥሮስ ከባቢሎን በላከው ደብዳቤ ላይ “ልጄ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል” ብሏል።—ጴጥሮስና ማርቆስ አብረው አምላክን በማገልገላቸው የቅርብ ወዳጅነት መሥርተው ነበር! የማርቆስን ወንጌል ስናነብም ይህን በግልጽ እናያለን። በኢየሱስ አገልግሎት ወቅት እያንዳንዱን ነገር ያስተውል የነበረው ጴጥሮስ ለማርቆስ ዝርዝር መረጃ እንደሰጠው ከወንጌሉ መመልከት እንችላለን። ለአብነት ያህል፣ በገሊላ ባሕር ላይ ስለተነሳው ማዕበል የሚገልጹትን ዘገባዎች እናወዳድር። ማርቆስ፣ ኢየሱስ በጀልባው ውስጥ የት ቦታ እንደተኛ እንዲሁም ምን ላይ እንደተኛ ገልጿል፤ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ሊያስተውል የሚችለው እንደ ጴጥሮስ ያለ ዓሣ አጥማጅ ነው። እስቲ በማቴዎስ 8:24፤ በማርቆስ 4:37, 38፤ በሉቃስ 8:23 ላይ የሚገኘውን ይህን ዘገባ አብረን እናንብብና በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች እናወዳድር።
ከጊዜ በኋላ፣ ጳውሎስ በሮም በታሰረበት ወቅት ማርቆስ በታማኝነት ላደረገለት ድጋፍ አመስግኖታል። (ቈላስይስ 4:10, 11) ጳውሎስ እንደገና በሮም በታሰረበት ወቅትም ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ማርቆስ በአገልግሎቴ ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና” ብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 4:11) በእርግጥም ማርቆስ ተስፋ ቆርጦ ወደኋላ ባለማለቱ ልዩ የአገልግሎት መብቶች ማግኘት ችሏል!
^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።