በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወቷ የምትረካ እናት

በሕይወቷ የምትረካ እናት

በሕይወቷ የምትረካ እናት

በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አብዛኞቹ ሴቶች በሥራው ዓለም ተሰማርተዋል። በበለጸጉ አገሮች ውስጥ ከወንዶች ጋር ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ተቀጥረው ይሠራሉ። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ደግሞ ሴቶች የቤተሰባቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ብዙውን ጊዜ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው ለረጅም ሰዓታት ይለፋሉ።

በርካታ ሴቶች በአንድ በኩል መተዳደሪያ ለማግኘት መሥራት ሲኖርባቸው በሌላ በኩል ደግሞ ቤተሰባቸውን መንከባከብና ቤታቸውን ጥሩ አድርገው መያዝ አለባቸው። እነዚህ ሴቶች ለምግብ፣ ለልብስና ለመጠለያ የሚሆን ገንዘብ ከማምጣታቸውም በተጨማሪ ምግብ ማብሰል፣ ልብስ ማጠብና ቤት ማጽዳት ይኖርባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያን እናቶች ልጆቻቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ለማስተማር ጥረት ያደርጋሉ። ሁለት ትንንሽ ሴቶች ልጆች ያሏት ክርስቲና የተባለች እናት እንዲህ ብላለች:- “እውነቱን ለመናገር፣ ሥራንና የቤተሰብ ኃላፊነቶችን በሚዛናዊነት ማከናወን በጣም ከባድ ነው፤ በተለይም ትንንሽ ልጆች ሲኖሩ ይህን ማድረግ ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ትኩረት መስጠት ቀላል አይደለም።”

ይሁን እንጂ እናቶች ወደ ሥራው ዓለም እንዲገቡ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው? እነዚህ እናቶች ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? ደግሞስ አንዲት እናት በሕይወቷ እርካታ ለማግኘት የግድ ወደ ሥራው ዓለም መግባት ያስፈልጋታል?

እናቶች በሥራው ዓለም የሚሰማሩት ለምንድን ነው?

በርካታ እናቶች ሙሉ ቀን መሥራታቸው የግድ አስፈላጊ ነው። አንዳንዶች ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር በማቅረብ ረገድ የሚያግዛቸው የትዳር ጓደኛ የላቸውም። ሌሎች ባለትዳሮች ደግሞ የቤተሰባቸውን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የአንድ ሰው ገቢ ብቻ ስለማይበቃ ሁለቱም ለመሥራት ይገደዳሉ።

እርግጥ ነው፣ ሙሉ ቀን የሚሠሩ እናቶች ሁሉ እንዲህ የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ሁኔታ አስገድዷቸው አይደለም። ብዙ እናቶች በሥራው ዓለም የተሰማሩት ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ስለሚፈልጉ ነው። አንዳንዶች ደግሞ የሚሠሩት፣ እንደፈለጉ የሚያወጡት ገንዘብ ለማግኘት ወይም የቅንጦት ሕይወት ለመምራት ሲሉ ነው። ብዙዎቹም በሥራቸው የተዋጣላቸው ስለሆኑ ሥራቸውን ይወዱታል።

አንዳንድ እናቶች፣ መሥራት እንዳለባቸው የሚሰማቸው ሌሎች ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩባቸው ሊሆን ይችላል። በርካታ ሰዎች፣ በሥራው ዓለም ላይ የተሰማሩ እናቶች ዘወትር እንደሚጨነቁና በጣም እንደሚደክማቸው ቢገነዘቡም ለመሥራት የማይፈልጉ እናቶችን አመለካከት ብዙውን ጊዜ አይረዱላቸውም፤ እንዲያውም ይቀልዱባቸዋል። አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “‘የቤት እመቤት እንደሆንሽና እንደማትሠሪ’ ለሰዎች ማስረዳት ቀላል አይደለም። አንዳንድ ሰዎች፣ ሕይወትሽን እያባከንሽ እንደሆነ የሚጠቁም ነገር ይናገራሉ ወይም ፊታቸው ላይ ይነበባል።” ሁለት ዓመት የሆናት ሴት ልጅ ያለቻት ሬቤካ “ባለንበት ኅብረተሰብ ውስጥ ሴቶች፣ ልጆቻቸውን መንከባከብ እንዳለባቸው ቢታመንም በሥራው ዓለም ያልተሰማሩ እናቶች ዝቅ ተደርገው እንደሚታዩ ይሰማኛል” ብላለች።

እውነታው ምንድን ነው?

በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች፣ የመገናኛ ብዙኃን “ስኬታማ ሴት” የምትባለው በተሰማራችበት የሙያ መስክ የተዋጣላት እንደሆነች ይኸውም ዳጎስ ያለ ደሞዝ እንደሚከፈላት፣ ይህ ቀረሽ የማይባል አለባበስ እንደሚኖራትና ሙሉ በሙሉ በራሷ እንደምትተማመን አድርገው ያቀርቧታል። ይህች ሴት ቤቷ ስትገባ ደግሞ ልጆቿ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት፣ የባሏን ስህተቶች ለማረም እንዲሁም በቤት ውስጥ ለሚፈጠረው ለማንኛውም ችግር መፍትሔ ለማግኘት ጥንካሬ ይኖራታል። በገሃዱ ዓለም ግን እንዲህ ማድረግ የሚችሉ ሴቶች በጣም ጥቂት እንደሆኑ ግልጽ ነው።

እውነቱን ለመናገር ሴቶች የሚያገኟቸው አብዛኞቹ ሥራዎች አሰልቺ ሲሆኑ በአንጻራዊ ሁኔታ ክፍያቸውም ዝቅተኛ ነው። በሥራው ዓለም የተሰማሩ እናቶች ሥራቸው የተፈጥሮ ችሎታቸውን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም እንደማያስችላቸው ሲመለከቱ ቅሬታ ያድርባቸው ይሆናል። ሶሻል ሳይኮሎጂ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “[በሴቶች] እኩልነት ረገድ መሻሻል ቢኖርም አሁንም በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉና ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኙ ሥራዎችን የሚይዙት ወንዶች ናቸው። በመሆኑም ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ከፍ ለማድረግ ሲሉ በሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች እንደሚጎዱ ግልጽ ነው።” ኤል ፓይስ የተባለው የስፔን ጋዜጣ እንደሚከተለው በማለት ዘግቧል:- “አብዛኞቹ ሴቶች ሁለት ሥራ ስለሚሠሩ (በቤታቸውና በሥራ ቦታቸው) በውጥረት ምክንያት በሚመጣ ጭንቀት የመሠቃየት አጋጣሚያቸው ከወንዶች በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ ተደርሶበታል።”

ባሎች ሚስቶቻቸውን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

እርግጥ ነው፣ አንዲት ክርስቲያን እናት መሥራት አለባት ወይስ የለባትም የሚለው ጉዳይ የግል ውሳኔዋ ነው። ባለትዳር ከሆነች ግን እሷና ባሏ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት በጉዳዩ ላይ መወያየትና ከዚህ ጋር የተያያዙ ነገሮችን በጥንቃቄ ማሰብ ይገባቸዋል።—ምሳሌ 14:15

አንድ ባልና ሚስት የቤተሰባቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ሁለቱም ሙሉ ቀን መሥራት እንዳለባቸው ቢወስኑስ? በዚህ ጊዜ አስተዋይ የሆነ ባል የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በጥሞና ሊያስብበት ይገባል:- “እናንተ ባሎች ሆይ፣ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ . . . አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።” (1 ጴጥሮስ 3:7 የ1954 ትርጉም) አንድ ባል የሚስቱን አቅምና ስሜት በመረዳት ለሚስቱ አክብሮት ያሳያታል። በተቻለው መጠን በቤት ውስጥ ሥራዎች ያግዛታል። አንድ ባል ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎች ክብሩን እንደሚነኩበት በማሰብ እነዚህን ሥራዎች ከማከናወን ወደ ኋላ አይልም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ኢየሱስ በትሕትና ለመሥራት ፈቃደኛ ይሆናል። (ዮሐንስ 13:12-15) እንዲህ ያለው ባል እነዚህን ሥራዎች፣ ታታሪ ሠራተኛ ለሆነችው ሚስቱ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ እንደሚያስችሉት አጋጣሚዎች አድርጎ ይመለከታቸዋል። ሚስቱም በዚህ መንገድ ሲያግዛት ትደሰታለች።—ኤፌሶን 5:25, 28, 29

ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ከቤት ውጭ መሥራት ካለባቸው በቤት ውስጥም መረዳዳት እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በስፔን የሚታተም ኤቢሲ የተባለ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ላይ እንዲህ የማድረግ አስፈላጊነት ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። በዚህ ዘገባ ላይ፣ የቤተሰብ ጉዳዮች ተቋም የተባለው ድርጅት ባካሄደው ጥናት ላይ የተመሠረተ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን ዘገባው እንደገለጸው በስፔን የፍቺ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲያሻቅብ ያደረገው “ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ መሥፈርቶች መቅረታቸው” ብቻ ሳይሆን “ሴቶች ወደ ሥራው ዓለም መግባታቸውና ወንዶች [ሚስቶቻቸውን] በቤት ውስጥ ሥራዎች የማያግዟቸው መሆኑ” ጭምር ነው።

አንዲት ክርስቲያን እናት ያላት ትልቅ ሚና

ይሖዋ፣ ልጆችን የማሠልጠኑን ኃላፊነት በዋነኝነት የሰጠው ለአባቶች ቢሆንም ክርስቲያን እናቶች በተለይም ልጁ ሕፃን እያለ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ይገነዘባሉ። (ምሳሌ 1:8፤ ኤፌሶን 6:4) ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ሕጉን ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ የሰጠው መመሪያ እናቶችንም አባቶችንም ይመለከታል። በተለይም ልጁ በባሕርይውና በአመለካከቱ ረገድ እድገት በሚያደርግባቸው ዓመታት ይህን ማድረግ ጊዜና ትዕግሥት እንደሚጠይቅ ይሖዋ ያውቅ ነበር። በዚህም ምክንያት አምላክ፣ ወላጆች በቤት ሲቀመጡና በመንገድ ሲሄዱ እንዲሁም ሲተኙና ሲነሱ ልጆቻቸውን እንዲያሠለጥኗቸው ነግሯቸዋል።—ዘዳግም 6:4-7

የአምላክ ቃል፣ እናቶች ጠቃሚና የተከበረ ሚና እንዳላቸው ጎላ አድርጎ ሲገልጽ ልጆችን “የእናትህንም ሕግ አትተው” በማለት አዟቸዋል። (ምሳሌ 6:20 የ1954 ትርጉም) እርግጥ ነው፣ አንዲት ያገባች ሴት ለልጆቿ ምንም ዓይነት ሕግ ከማውጣቷ በፊት ባሏን ማማከር አለባት። ሆኖም ጥቅሱ እንደሚያመለክተው እናቶች ሕግ የማውጣት መብት አላቸው። ልጆች፣ አምላክን የምትፈራ እናት የምታስተምራቸውን መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ደንቦች ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ ከፍተኛ ጥቅም ያገኛሉ። (ምሳሌ 6:21, 22) ቴሬሳ የተባለች የሁለት ወንዶች ልጆች እናት በሥራው ዓለም መሠማራት የማትፈልገው ለምን እንደሆነ ስትገልጽ እንደሚከተለው በማለት ተናግራለች:- “ከሁሉ የሚበልጠው ሥራዬ ልጆቼ የአምላክ አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ ነው። ይህንን ሥራ ደግሞ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ማከናወን እፈልጋለሁ።”

ትልቅ ሥራ ያከናወኑ እናቶች

የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ልሙኤል እናቱ ባደረገችው ትጋት የተሞላበት ጥረት እንደተጠቀመ ጥርጥር የለውም። እናቱ “ያስተማረችው ቃል” በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንኳ እንዲካተት ተደርጓል። (ምሳሌ 31:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህች እናት፣ ጠባየ መልካም ስለሆነች ሚስት የሰጠችው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወንዶች ልጆችም በትዳር ጓደኛ ረገድ ጥሩ ምርጫ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። የልሙኤል እናት የሥነ ምግባር ብልግናን እንዲሁም ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣትን በተመለከተ የሰጠቻቸው ማስጠንቀቂያዎችም እንደተጻፉበት ዘመን ሁሉ ዛሬም ጠቃሚ ናቸው።—ምሳሌ 31:3-5, 10-31

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኤውንቄ የተባለች እናት ጢሞቴዎስ የተባለውን ልጇን በማስተማር ረገድ ያከናወነችውን መልካም ሥራ አድንቋል። ኤውንቄ፣ ባሏ የማያምን ስለነበር (ምናልባትም የግሪክ አማልክትን ያመልክ ይሆናል) ጢሞቴዎስ ‘በቅዱሳት መጻሕፍት’ ላይ እምነት እንዲያሳድር ማስረዳት ያስፈልጋት ነበር። ኤውንቄ፣ ለጢሞቴዎስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማስተማር የጀመረችው መቼ ነበር? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ ‘ከሕፃንነቱ ጀምሮ’ እንደነበር ይገልጻል። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15) የኤውንቄ እምነትና ምሳሌነት እንዲሁም የሰጠችው ትምህርት ጢሞቴዎስን ለሚስዮናዊነት አገልግሎት እንዳዘጋጀው ጥርጥር የለውም።—ፊልጵስዩስ 2:19-22

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ታማኝ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮችን በእንግድነት በመቀበል ልጆቻቸው ግሩም ምሳሌ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ እንዲያገኙ ስላደረጉ እናቶችም ይናገራል። ለአብነት ያህል፣ አንዲት ሱነማዪት ሴት ነቢዩ ኤልሳዕን ቤቷ ሁልጊዜ በእንግድነት ትቀበለው ነበር። ከጊዜ በኋላ ልጇ ሲሞት ኤልሳዕ አስነስቶላታል። (2 ነገሥት 4:8-10, 32-37) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው የማርቆስ እናት ማርያምንም እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል። ማርያም በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤቷ የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት እንዲሰበሰቡ ፈቅዳ የነበረ ይመስላል። (የሐዋርያት ሥራ 12:12) ማርቆስ ቤታቸው አዘውትረው ይመጡ ከነበሩት ሐዋርያትና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መገናኘቱ እንደጠቀመው ምንም ጥርጥር የለውም።

በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ የእሱን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለልጆቻቸው የሚያስተምሩ ታማኝ ሴቶች የሚያደርጉትን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። እነዚህ ሴቶች ታማኝ ስለሆኑና በቤታቸው ውስጥ መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ ስለሚጥሩ ይሖዋ ይወዳቸዋል።—2 ሳሙኤል 22:26፤ ምሳሌ 14:1

ከሁሉ በላይ የሚያረካ ምርጫ

ከላይ ያየናቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት አንዲት እናት የቤተሰቧን አካላዊና መንፈሳዊ ፍላጎት በሚገባ ማሟላቷ እንዲሁም ስሜታቸውን የምትረዳላቸው መሆኗ ልዩ በረከት ያስገኛል። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለም። አንዲት እናት በቤት ውስጥ የምታከናውናቸው ተግባሮች አብዛኛውን ጊዜ በሥራው ዓለም ከፍ ተደርጎ ከሚታይ ማንኛውም ሥራ የበለጠ ጊዜና ጥረት ሊጠይቅባት ይችላል።

አንዲት እናት ከባሏ ጋር ከተማከረች በኋላ በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት ወይም ሰዓታት ብቻ ለመሥራት ከመረጠች ቤተሰቡ አኗኗሩን ቀላል ማድረግ እንደሚያስፈልገው እንዲሁም አመለካከቷን የማይረዱላት ሰዎች የሚሰነዝሯቸውን ትችቶች መቻል እንደሚኖርባት እሙን ነው። ሆኖም ይህን በማድረጓ የሚገኘው በረከት ከምትከፍለው መሥዋዕትነት በጣም የላቀ ነው። ፓኪ ሦስት ልጆች ያሏት ሲሆን በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓታት መሥራት አለባት። ፓኪ “ልጆቹ ከትምህርት ቤት ሲመጡ የሚያዋራቸው ሰው እንዲኖር ስል በዚያ ሰዓት ቤት ለመገኘት እፈልጋለሁ” ብላለች። እንዲህ በማድረጓ ልጆቿ የተጠቀሙት እንዴት ነው? ፓኪ እንዲህ ትላለች:- “የቤት ሥራቸውን ሲሠሩ እረዳቸዋለሁ፤ እንዲሁም ችግሮች ካጋጠሟቸው ወዲያው ልፈታው እችላለሁ። በየቀኑ አብረን የምናሳልፈው ጊዜ ግልጽ ውይይት ለማድረግ አስችሎናል። በዚህ ዓይነት ከልጆቼ ጋር በማሳልፈው ጊዜ በጣም ስለምደሰት ሙሉ ቀን እንድሠራ የቀረበልኝን ግብዣ አልተቀበልኩም።”

ብዙ ክርስቲያን እናቶች ከቤት ውጭ በመሥራት የሚያሳልፉትን ጊዜ መቀነስ ከቻሉ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት እንደሚጠቀሙ ተገንዝበዋል። ቀደም ብለን የጠቀስናት ክርስቲና እንዲህ ብላለች:- “ሥራ ሳቆም ቤተሰባችን የሚያጋጥሙት ችግሮች እየቀነሱ ሄዱ። ልጆቼን ለማዋራት እንዲሁም ባለቤቴን በተለያዩ መንገዶች ለመርዳት ጊዜ አገኘሁ። ሴት ልጆቼ ሲማሩና እድገት ሲያደርጉ ስመለከት እነሱን ማስተማር ያስደስተኝ ጀመር።” ክርስቲና ያጋጠማት አንድ የማትረሳው ነገር አለ። “ትልቋ ልጄ በእግሯ መሄድ የጀመረችው በሕፃናት መዋያ ነበር፤ ሁለተኛዋን ልጄን ግን መሄድ ያስተማርኳት እኔው ራሴ ነኝ። መሄድ የጀመረች ጊዜ ትንሽ ከተራመደች በኋላ ልትወድቅ ስትል እጄን ዘርግቼ እቅፍ አደረግኳት። በዚያች ቅጽበት ምን ያህል እንደተደሰትኩ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል!”

ሌላም ሊታሰብበት የሚገባ ነገር አለ፤ አንዲት እናት ከቤት ውጭ በመሥራት የምታሳልፈውን ሰዓት በመቀነሷ የምታጣው ገንዘብ የሚታሰበውን ያህል ብዙ ላይሆን ይችላል። ክርስቲና እንዲህ ብላለች:- “ከማገኘው ገቢ አብዛኛው የሚውለው ለሕፃናት መዋያ ክፍያና ለትራንስፖርት ወጪ ነበር። ከባለቤቴ ጋር በጉዳዩ ላይ በደንብ ስንወያይበት የእኔ ደሞዝ ያን ያህል ተጨማሪ ገንዘብ እንደማያስገኝ ተገነዘብን።”

አንዳንድ ባልና ሚስት ሁኔታቸውን ከገመገሙ በኋላ፣ ሚስት ቤት ውላ ለቤተሰቡ ሙሉ ጊዜዋን መስጠቷ የሚያስገኘው ጥቅም እሷ ባለመሥራቷ ከሚያጡት ገንዘብ እንደሚበልጥ ተገንዝበዋል። የክርስቲና ባል ፖል እንዲህ ብሏል:- “ባለቤቴ ሁለቱን ትንንሽ ልጆቻችንን ለመንከባከብ ቤት መዋሏ አስደስቶኛል። እሷ ከቤት ውጭ ትሠራ በነበረበት ወቅት የሁለታችንም ሕይወት በውጥረት የተሞላ ነበር።” እነዚህ ባልና ሚስት ያደረጉት ውሳኔ ለልጆቹ ምን ጥቅም አስገኝቷል? ፖል “ልጆቹ ምንም የማይሰጉ ከመሆኑም ሌላ በልጅነታቸው ሊደርስባቸው ከሚችለው መጥፎ ተጽዕኖ ተጠብቀዋል” ብሏል። እነዚህ ባልና ሚስት ከልጆቻቸው ጋር በተቻለ መጠን ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፋቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ፖል “እኛ ወላጆች በምሳሌያዊ አነጋገር በልጆቻችን ልብ ላይ ካልጻፍን ሌላ ሰው እንዲህ ማድረጉ እንደማይቀር ስለማምን ነው” ብሏል።

ባልና ሚስት ሁኔታቸውን መገምገም እንዳለባቸው ግልጽ ነው፤ ሌሎች የሚያደርጉትን ውሳኔ ማንም ሰው ሊተች አይገባም። (ሮሜ 14:4፤ 1 ተሰሎንቄ 4:11) ያም ሆኖ ግን አንዲት እናት በሥራ ዓለም ተሰማርታ ሙሉ ቀን አለመሥራቷ ለቤተሰቡ የሚያስገኛቸውን በርካታ ጥቅሞች ልብ ማለቱ ተገቢ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ቴሬሳ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚሰማት ጠቅለል አድርጋ ስትገልጽ “ከልጆችሽ ጋር በተቻለ መጠን ረዘም ያለ ጊዜ በማሳለፍ እነሱን ከመንከባከብና ከማስተማር የበለጠ እርካታ የሚያስገኝ ምንም ነገር የለም” ብላለች።—መዝሙር 127:3

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን እናቶች ልጆቻቸውን በማሠልጠኑ አስፈላጊ ሥራ ይካፈላሉ