ሕይወትን መልሶ መስጠት የሚችል አምላክ
ወደ አምላክ ቅረብ
ሕይወትን መልሶ መስጠት የሚችል አምላክ
የምትወደውን ሰው በሞት አጥተሃል? ከሆነ፣ በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ በጣም አሳዛኝ ነገሮች መካከል አንዱ ደርሶብሃል ማለት ነው። ፈጣሪያችን የደረሰብህን ሐዘን በሚገባ ይረዳል። ያም ብቻ ሳይሆን ሞት የሚያስከትላቸውን ጉዳቶችም ማስወገድ ይችላል። አምላክ ሕይወት ሰጪ ብቻ ሳይሆን የሞቱ ሰዎችንም ማስነሳት የሚችል መሆኑን ለማሳየት በጥንት ጊዜ ስለተከናወኑ ትንሣኤዎች የሚገልጹ ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው እንዲቆዩልን አድርጓል። እስቲ ከእነዚህ ታሪኮች መካከል ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአምላክ ባገኘው ኃይል አማካኝነት ከሞት ስላስነሳው አንድ ልጅ የሚናገረውን ሐሳብ እንመልከት። ታሪኩ የሚገኘው በሉቃስ 7:11-15 ላይ ነው።
ጊዜው 31 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። ኢየሱስ ናይን ወደምትባል በገሊላ ውስጥ ወደምትገኝ ከተማ እየተጓዘ ነበር። (ቁጥር 11) ወደ ከተማዋ መግቢያ የደረሰው አመሻሹ ላይ ሳይሆን አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ወደ ከተማዋ መግቢያ በር ሲደርስም፣ እነሆ፤ ሰዎች የአንድ ሰው አስከሬን ተሸክመው ከከተማዋ ወጡ፤ ሟቹም ለእናቱ አንድ ልጅ ብቻ ነበር፤ እናቱም መበለት ነበረች፤ ብዙ የከተማውም ሕዝብ ከእርሷ ጋር ነበረ።” (ቁጥር 12) ይህቺ መበለት ምን ያህል አዝና እንደነበር ገምት! አንድ ልጇ ሞተ ማለት የሚያስፈልጋትን ነገር የሚያሟላላትንና የሚንከባከባትን ሰው ለሁለተኛ ጊዜ አጣች ማለት ነው።
ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው በሐዘን በተደቆሰችውና ምናልባትም የልጇን አስከሬን ከተሸከሙት ሰዎች አጠገብ ትሄድ በነበረችው እናት ላይ ነበር። ዘገባው “ጌታም ባያት ጊዜ ራራላትና፣ ‘አይዞሽ፤ አታልቅሺ’ አላት” ይላል። (ቁጥር 13) ኢየሱስ የመበለቷ ሁኔታ አንጀቱን በልቶታል። ምናልባትም በዚያን ወቅት ባሏን በሞት አጥታ ስለነበረችውና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ በእሱ ሞት ምክንያት ከፍተኛ ሐዘን ስለሚደርስባት እናቱ አስቦ ሊሆን ይችላል።
ኢየሱስ ወደ ቃሬዛው ጠጋ አለ፤ ይህን ያደረገው ግን አስከሬኑን ለማጀብ ብሎ አልነበረም። ሥልጣን እንዳለው በሚያሳይ መንገድ ‘ቃሬዛውን ነካና’ የተሸከሙት ሰዎች እንዲቆሙ አደረገ። ከዚያም በሞት ላይ ኃይል የተሰጠው መሆኑን በሚያሳይ አነጋገር “‘አንተ ጐበዝ፤ ተነሥ እልሃለሁ!’ አለው። የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ። ኢየሱስም ወስዶ ለእናቱ ሰጣት።” (ቁጥር 14, 15) ይህ ወጣት በሞት ምክንያት ከእናቱ ተለይቶ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ወጣቱን ‘ወስዶ ለእናቱ ሲሰጣት’ ዳግም አንድ ቤተሰብ ሆኑ። የዚህች መበለት ሐዘን በደስታ እንባ እንደተተካ ምንም ጥርጥር የለውም።
አንተስ፣ በሞት ካጣሃቸው የምትወዳቸው ሰዎች ጋር ዳግመኛ የምትተያይበትንና እንዲህ ያለውን ደስታ የምታገኝበትን ጊዜ ትናፍቃለህ? አምላክ ስለ አንተ እንደሚያስብ እርግጠኛ ሁን። ኢየሱስ የአባቱ ነጸብራቅ በመሆኑ በሐዘን ለተደቆሰችው መበለት ያሳየው አሳቢነት የአምላክን ርኅራኄ የሚያንጸባርቅ ነው። (ዮሐንስ 14:9) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በትንሳኤ የሚያስባቸውን ሙታን ለማስነሳት እንደሚናፍቅ ያስተምረናል። (ኢዮብ 14:14, 15) ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ አስደናቂ ተስፋ ማለትም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖርና የምንወዳቸው ሰዎች ትንሣኤ ሲያገኙ የመመልከት ተስፋ ይዞልናል። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ሕይወትን መልሶ መስጠት ስለሚችለው አምላክም ሆነ የምትወዳቸውን ሰዎች ዳግመኛ እንደምታገኛቸው ስለሚገልጸው ተስፋ ይበልጥ እንድትማር እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ። ኢየሱስም ወስዶ ለእናቱ ሰጣት”