አምላክ በተፈጥሮ አደጋዎች አማካኝነት ሰዎችን ይቀጣል?
አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ
አምላክ በተፈጥሮ አደጋዎች አማካኝነት ሰዎችን ይቀጣል?
አምላክ ሰዎችን ለመቅጣት ብሎ የተፈጥሮ አደጋዎችን አያመጣም። ከዚህ ቀደም እንዲህ አድርጎ አያውቅም ወደፊትም አያደርግም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ዮሐንስ 4:8 ላይ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይላል።
አምላክ ማንኛውንም ነገር እንዲያደርግ የሚያነሳሳው ፍቅር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም” በማለት ስለሚናገር ፍቅር በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ነገር አያደርግም። (ሮሜ 13:10) መጽሐፍ ቅዱስ በኢዮብ 34:12 ላይ “በእውነት እግዚአብሔር ክፋትን አይሠራም” ይላል።
እውነት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ “ታላቅ የመሬት መናወጥ” የመሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች በዘመናችን እንደሚከሰቱ አስቀድሞ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ስለ አየር ሁኔታ የሚዘግብ አንድ ሰው፣ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ እንደሚመጣ መተንበዩ ለደረሰው አደጋ ተጠያቂ እንደማያደርገው ሁሉ ይሖዋም በእነዚህ የተፈጥሮ አደጋዎች አማካኝነት ለደረሰው ጉዳት በምንም ዓይነት ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። በተፈጥሮ አደጋዎች አማካኝነት በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ላለው መከራ ተጠያቂው አምላክ ካልሆነ ታዲያ መንስኤው ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ‘መላው ዓለም በክፉው’ ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:19) ሰይጣን፣ የሰው ዘር ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ነፍሰ ገዳይ ነው። (ዮሐንስ 8:44) የሰውን ሕይወት ርካሽና አልባሌ አድርጎ ይቆጥረዋል። ሰይጣን ማንኛውንም ነገር የሚያከናውነው በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ ነው፤ በመሆኑም ራስ ወዳድነት ገንኖ የሚታይበት ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት መፍጠሩ ምንም አያስደንቅም። ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ የሚገኙ ራስ ወዳድ ግለሰቦች፣ ብዙ ሰዎች ለተፈጥሮ አሊያም ለሰው ሠራሽ አደጋዎች በተጋለጡ አደገኛ አካባቢዎች እንዲኖሩ አስገድደዋቸዋል። (ኤፌሶን 2:2፤ 1 ዮሐንስ 2:16) በመሆኑም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሱት አንዳንድ ጉዳቶች ኃላፊነቱን መውሰድ ያለባቸው ስግብግብ የሆኑ ግለሰቦች ናቸው። (መክብብ 8:9) እንዴት?
የሰው ልጆች ብዙ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲከሰቱ በተወሰነ መጠን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ለአብነት ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ የምትገኘው ኒው ኦርሊየንስ ከተማ በጎርፍ በተጥለቀለቀችበት ወቅት በነዋሪዎቿ ላይ የደረሰውን አሳዛኝ መከራ መመልከት ትችላለህ። አሊያም ደግሞ በቬንዙዌላ የባሕር ጠረፍ አካባቢ በሚገኙ ተራሮች አጠገብ ባሉ ቤቶች ላይ በጭቃ ጎርፍ ሳቢያ የደረሰውን ውድመት ተመልከት። በእነዚህና በሌሎች አጋጣሚዎች እንደ ነፋስና ዝናብ ያሉ የተፈጥሮ ክስተቶች ከፍተኛ ጥፋት አስከትለዋል። ለዚህ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች መካከል ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ስለ አካባቢ ጥበቃ ትክክለኛ ግንዛቤ ማጣታቸው፣ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ሕንፃዎችን መገንባታቸው፣ የተሳሳተ እቅድ ማውጣታቸውና የተሰጧቸውን ማስጠንቀቂያዎች ችላ ማለታቸው ይገኙበታል። በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የሚሠሩት ስህተትም ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ነው።
እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ አደጋ ተመልከት። በኢየሱስ ዘመን፣ ድንገት የተናደ ግንብ የ18 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ ነበር። (ሉቃስ 13:4) አደጋው ሊደርስ የቻለው፣ በሰዎች ስህተት ወይም ‘ጊዜና ያልተጠበቀ ክስተት’ ባመጣው ነገር አሊያም በሁለቱም ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይህ ሁኔታ የአምላክ የቅጣት ፍርድ እንዳልሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መክብብ 9:11 NW
አምላክ የተፈጥሮ ኃይሎችን በመጠቀም ጥፋት አምጥቶ ያውቃል? አዎን፣ ይሁንና ከተፈጥሮም ሆነ ከሰው ሠራሽ አደጋዎች በተቃራኒ እነዚህ ጥፋቶች ሰዎችን በጅምላ የሚጨርሱ አልነበሩም፤ ከዚህ ይልቅ በዓላማ የተደረጉ ከመሆኑም ሌላ የተከሰቱት በጣም ጥቂት በሆኑ አጋጣሚዎች ነበር። የእምነት አባት በሆነው በኖኅ ዘመን የተከሰተው ዓለም አቀፍ የውኃ ጥፋትና በሎጥ ዘመን የደረሰው የሰዶምና የገሞራ ከተሞች ጥፋት ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። (ዘፍጥረት 6:7-9, 13፤ 18:20-32፤ 19:24) ንስሐ ያልገቡ ክፉ ሰዎች በእነዚህ መለኮታዊ ፍርዶች ጠፍተዋል፤ በአምላክ ዓይን ጻድቃን የሆኑ ሰዎች ግን በሕይወት ተርፈዋል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ይሖዋ አምላክ ሁሉንም ዓይነት መከራዎች ለማስወገድና የተፈጥሮ አደጋዎች ከሚያስከትሉት ጉዳት እፎይታ እንድናገኝ ለማድረግ ችሎታው፣ ፍላጎቱም ሆነ አቅሙ አለው። መዝሙር 72:12 በአምላክ የተቀባውን ንጉሥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን አስመልክቶ “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል።