የአምላክ ኃይል በከዋክብት ላይ ይንጸባረቃል
የአምላክ ኃይል በከዋክብት ላይ ይንጸባረቃል
“ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።”—ኢሳይያስ 40:26
ፀሐያችን መካከለኛ መጠን ያላት ኮከብ ብትሆንም ከምድር 330,000 ጊዜ ትበልጣለች። በምድር አቅራቢያ የሚገኙት አብዛኞቹ ከዋክብት ከፀሐይ የሚያንሱ ናቸው። እንደ ቪ382 ሲግኒ ያሉ ሌሎች ከዋክብት ግን ፀሐያችንን ከ27 እጥፍ በላይ ይበልጧታል።
ፀሐያችን ምን ያህል ኃይል ታመነጫለች? እሳት ከሚነድበት አንድ አካባቢ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ብትሆንና ሙቀቱ ቢሰማህ፣ እሳቱ ምን ያህል ኃይለኛ እንደሆነ መገመት አያዳግትህም። ፀሐይ ከምድር በአማካይ 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቃ ትገኛለች። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ፀሐይዋ ልታቃጥለን ትችላለች! በጣም የሚገርመው ነገር ፀሐይ ከምታመነጨው ኃይል ውስጥ ወደ ምድር የሚደርሰው ከሁለት ቢሊዮን አንድ እጅ ያህሉ ብቻ ነው። እንደዛም ሆኖ ይህ ኃይል በምድር ያሉትን ፍጥረታት በሕይወት ለማቆየት በቂ ነው።
እንዲያውም የፀሐይ ኃይል እንደ ምድር ያሉ 31 ትሪሊዮን ፕላኔቶች ቢኖሩ በሁሉም ውስጥ ያሉትን ፍጥረታት በሕይወት ለማቆየት እንደሚያስችል የሳይንስ ሊቃውንት ይናገራሉ። ወይም በሌላ አነጋገር የፀሐይን ኃይል ለአንድ ሴኮንድ ብቻ ማጠራቀም ቢቻል ዩናይትድ ስቴትስ ይህን ኃይል “አሁን ባላት ፍጆታ ለ9,000,000 ዓመታት ያህል ልትጠቀምበት ትችላለች” በማለት የስፔስ ዌዘር ፕሬዲክሽን ሴንተር ድረ ገጽ ይናገራል።
የፀሐይ ኃይል የሚመነጨው አቶሞች እንዲሰባበሩ በማድረግ ከፍተኛ ኃይል እንዲፈጠር የሚያደርገው የኑክሌር ማብለያ ከሚገኝበት ከፀሐይዋ እምብርት ውስጥ ነው። ፀሐይ በጣም ግዙፍ ስትሆን ውስጠኛው ክፍሏ ደግሞ ጥቅጥቅ ያለ ነው፤ በመሆኑም በውስጠኛው ክፍል የሚፈጠረው ኃይል ወደ ላይኛው የፀሐይ ክፍል ለመድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ይፈጅበታል። ስፔስ ዌዘር ፕሬዲክሽን ሴንተር በድረ ገጹ ላይ እንደገለጸው “ፀሐይ አሁን ኃይል ማመንጨቷን ብታቆም በምድር ላይ ጉልህ ለውጥ ለመታየት 50,000,000 ዓመታት ሊወስድ ይችላል!”
እስቲ ይህንን ሐቅ ተመልከት:- ምሽት ላይ ቀና ብለህ ስትመለከት በጠራው ሰማይ ላይ እንደ ፀሐይ ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል የሚያመነጩ በሺዎች የሚቆጠሩ ከዋክብት ታያለህ። የሳይንስ ሊቃውንት ደግሞ በጽንፈ ዓለም ውስጥ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብት እንዳሉ ያምናሉ!
እነዚህ ሁሉ ከዋክብት እንዴት ተገኙ? ምክንያቱን መረዳት ባይችሉም አብዛኞቹ ተመራማሪዎች ጽንፈ ዓለም ከዛሬ 14 ቢሊዮን ዓመታት ገደማ በፊት በድንገት ወደ ሕልውና መምጣቱን ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:1) ከፍተኛ ኃይል የሚያመነጩ ከዋክብትን የፈጠረው አካል ‘ብርቱ ችሎታ ያለው’ ተብሎ መጠራቱ ምንም አያስደንቅም።—ኢሳይያስ 40:26
አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?
ይሖዋ አምላክ ፈቃዱን የሚያደርጉትን ለማበርታት ኃይሉን ይጠቀምበታል። ለአብነት ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎችን ስለ አምላክ ለማስተማር የተቻለውን ሁሉ ጥሯል። ጳውሎስ ከሰው የላቀ ኃይል አልነበረውም፤ ያም ሆኖ ከባድ ተቃውሞ እያለም እንኳ በርካታ መልካም ሥራዎችን ማከናወን ችሏል። እንዴት? ጳውሎስ ይህንን “እጅግ ታላቅ ኀይል” ያገኘው ከአምላክ እንደሆነ ተናግሯል።—2 ቆሮንቶስ 4:7-9
ማቴዎስ 24:3, 37-39፤ ሉቃስ 17:26-30
ይሖዋ አምላክ፣ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን ሆነ ብለው የሚጥሱ ሰዎችን ለማጥፋትም ኃይሉን ተጠቅሟል። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የሰዶምና የገሞራ ጥፋትን እንዲሁም በኖኅ ዘመን የተከሰተውን የጥፋት ውኃ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ይሖዋ የጥፋት ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ ኃይሉን የሚጠቀመው ክፉዎችን ለማጥፋት ብቻ እንደሆነ ጠቁሟል። በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ይሖዋ መሥፈርቶቹን ችላ የሚሉትን ለማጥፋት ኃይሉን በቅርቡ እንደሚጠቀምበት ትንቢት ተናግሯል።—አንተስ ምን ይሰማሃል?
በከዋክብት ላይ በሚንጸባረቀው የአምላክ ኃይል ላይ ስታሰላስል እንደ ንጉሥ ዳዊት ይሰማህ ይሆናል:- “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?”—መዝሙር 8:3, 4
ግዙፍ ከሆነው ጽንፈ ዓለም ጋር ራሳችንን በማወዳደር ምን ያህል ኢምንት መሆናችንን አምነን መቀበላችን በእርግጥም ትሑት መሆናችንን ያሳያል። ይህ ሲባል ግን አምላክ ኃያል መሆኑ ምንም ማድረግ እንደማንችል እንዲሰማን ሊያደርገን አይገባም። ይሖዋ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ የሚከተሉትን አበረታች ሐሳቦች እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል:- “[አምላክ] ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጕልበት ይጨምራል። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ። እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።”—ኢሳይያስ 40:29-31
አምላክ፣ ፈቃዱን ለመፈጸም የምትፈልግ ከሆነ ቅዱስ መንፈሱን እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ይሁንና ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ መጠየቅ ይኖርብሃል። (ሉቃስ 11:13) የአምላክ ኃይል ማንኛውንም ፈተና እንድትቋቋም የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጥሃል።—ፊልጵስዩስ 4:13
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የአምላክ ኃይል ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጥሃል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ ጀምሮ ከግራ ወደ ቀኝ:- ዊርልፑል ጋላክሲ፣ ፐልያዲስ የከዋክብት ክምችት፣ ኦሪዮን ኔቡላ፣ አንድሮሜዳ ጋላክሲ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፀሐይ ከምድር 330,000 ጊዜ ትበልጣለች
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ፐልያዲስ:- NASA, ESA and AURA/Caltech; ሌሎቹ:- National Optical Astronomy Observatories