“እነሆ! እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ”
በእምነታቸው ምሰሏቸው
“እነሆ! እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ”
ማርያም ወደ ቤቷ የመጣውን እንግዳ በመገረም ትኩር ብላ ተመለከተችው። እንግዳው ለማነጋገር የፈለገው አባቷን ወይም እናቷን ሳይሆን እሷን ነው። እንደ ናዝሬት ባለ ትንሽ ከተማ ውስጥ ፀጉረ ልውጥ የሆነ ሰው በቀላሉ ተለይቶ ስለሚታወቅ እንግዳው የናዝሬት ነዋሪ አለመሆኑን እርግጠኛ ነች። በተጨማሪም ማንኛውም ግለሰብ፣ እንግዳው ከሌሎች ለየት ያለ መሆኑን በቀላሉ ማወቅ አያዳግተውም። ሰላምታውም ቢሆን ያልተለመደ ዓይነት ነበር። እንዲህ አላት:- “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው።”—ሉቃስ 1:28
ማርያም በገሊላ በምትገኘው ናዝሬት ውስጥ የሚኖረው የኤሊ ልጅ ስትሆን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሷ መናገር የሚጀምረው በዚህ መንገድ ነው። ይህ በሕይወቷ ውስጥ ከባድ ውሳኔዎችን የምታደርግበት ወቅት ነበር። ማርያም ዮሴፍ ለሚባል በአናጢነት ሙያ ለሚተዳደር ሰው ታጭታ ነበር። ይህ ሰው ሀብታም ባይሆንም እንኳ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ነበረው። ማርያም የዮሴፍ ረዳት በመሆን ቀላል ሕይወት የመምራት እንዲሁም ከባለቤቷ ጋር ሆና ልጆች የማሳደግ እቅድ ነበራት። ይሁን እንጂ ከአምላክ የተሰጣትን ኃላፊነት ሊነግራት ከመጣው ከዚህ እንግዳ ጋር ድንገት ተገናኘች። ይህ ኃላፊነት በሕይወቷ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከትልባታል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ማርያም ብዙ የሚናገረው ነገር አለመኖሩ ያስገርምህ ይሆናል። ስለ ቤተሰቧም ሆነ ስለ ባሕርይዋ ብዙም የማይናገር ሲሆን ስለ መልኳም ቢሆን ምንም የሚገልጸው ነገር የለም። ያም ሆኖ የአምላክ ቃል የሚናገረው ነገር፣ ስለ ማንነቷ ተጨማሪ እውቀት እንድናገኝ እንደሚረዳን ጥርጥር የለውም።
ስለ ማርያም ትክክለኛውን ነገር ለማወቅ በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ስለ ማንነቷ ከሚነገሩት በርካታ ግምታዊ አመለካከቶች አሻግረን መመልከት ይኖርብናል። በመሆኑም አሁን የምንወያየው ማርያምን ስለሚወክሉ ሥዕሎችና ቅርጻ ቅርጾች አይደለም። በተጨማሪም “ወላዲተ አምላክ” እና “የሰማይ ንግሥት” እንደሚሉት ያሉ ስሞችን በመስጠት ይህችን ትሑት ሴት ከሚገባው በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ውስብስብ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንም ሆነ ቀኖናዎችን አንመለከትም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማርያም በሚነግረን ነገር ላይ ብቻ እናተኩራለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እምነቷና እሷን መምሰል ስለምንችልበት መንገድ በመጠቆም በዋጋ ሊተመን የማይችል ጥልቅ እውቀት ይሰጠናል።
አንድ መልአክ ማርያምን አነጋገራት
ማርያምን ሊጎበኛት የመጣው እንግዳ፣ ተራ ሰው ሳይሆን መልአኩ ገብርኤል ነው። መልአኩ፣ ማርያምን “እጅግ የተወደድሽ ሆይ” ብሎ ሲጠራት “በጣም ደንግጣ” የነበረ ሲሆን ያልተለመደ ሰላምታውም ግራ አጋብቷት ነበር። (ሉቃስ 1:29) ማርያም እጅግ የተወደደችው ወይም ሞገስን ያገኘችው በማን ዘንድ ነበር? ማርያም በሰዎች ዘንድ የተለየ ሞገስ አገኛለሁ ብላ እንደማትጠብቅ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ መልአኩ እየተናገረ ያለው በይሖዋ አምላክ ዘንድ ሞገስ ስለማግኘቷ ነበር። ማርያም በአምላክ ዘንድ ሞገስ ማግኘቷን ከፍ አድርጋ ትመለከተው ነበር። ያም ሆኖ ግን የአምላክን ሞገስ ማግኘት ይገባኛል የሚል የኩራት ስሜት አላደረባትም። በመሆኑም ከማርያም ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። እኛም የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ጥረት የምናደርግ ከሆነ የእሱን ሞገስ አግኝቻለሁ የሚል የኩራት መንፈስ ሊኖረን አይገባም። አምላክ ትዕቢተኞችን የሚቃወም ሲሆን ትሑታንን ግን ይወዳቸዋል እንዲሁም ይረዳቸዋል።—ያዕቆብ 4:6
መልአኩ፣ እጅግ ታላቅ መብት ማግኘቷን ስለሚያበስራት ማርያም እንዲህ ዓይነቱን ትሕትና ማሳየቷ በእርግጥም አስፈላጊ ነበር። ገብርኤል፣ የምትወልደው ልጅ እጅግ ታላቅ እንደሚሆን ለማርያም ሲነግራት እንዲህ ሉቃስ 1:32, 33) አምላክ፣ ለዳዊት ከዘሮቹ አንዱ ለዘላለም እንደሚነግሥ ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የገባለትን ቃል ማርያም እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም። (2 ሳሙኤል 7:12, 13) በመሆኑም የምትወልደው ልጅ የአምላክ ሕዝቦች ለዘመናት ሲጠባበቁት የነበረውን መሲሕ ነው!
አለ:- “አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” (በተጨማሪም መልአኩ፣ ልጇ ‘የልዑል ልጅ እንደሚባል’ ነገራት። አንዲት ሴት እንዴት የአምላክን ልጅ ልትወልድ ትችላለች? ደግሞስ ማርያም እንዴት ልጅ ልትወልድ ትችላለች? ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ የነበረ ቢሆንም ገና አልተጋቡም። በመሆኑም “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” በማለት መልአኩን በግልጽ ጠየቀችው። (ሉቃስ 1:34) እዚህ ላይ ማርያም ድንግል መሆኗን ለመናገር እንዳላፈረች ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ንጽሕናዋን ከፍ አድርጋ ተመልክታዋለች። በዛሬው ጊዜ በርካታ ወጣቶች ድንግልናቸውን ለማስወሰድ የሚቸኩሉ ከመሆናቸውም ሌላ እንደዚያ ባላደረጉት ላይ ያፌዛሉ። ዓለም በእርግጥም ተለውጧል፤ ይሖዋ ግን አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) በማርያም ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም አምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን በጥብቅ የሚከተሉ ሰዎችን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል።—ዕብራውያን 13:4
ማርያም የአምላክ ታማኝ አገልጋይ ብትሆንም ፍጹም አልነበረችም። ታዲያ፣ ፍጹም የሆነውን የአምላክን ልጅ እንዴት መውለድ ትችላለች? ገብርኤል እንዲህ አላት:- “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።” (ሉቃስ 1:35) ቅዱስ ሲባል “ንጹሕ” እና “የጠራ” ማለት ነው። ሰዎች ለልጆቻቸው ኃጢአትን እንደሚያስተላልፉ የታወቀ ነው። በዚህ ወቅት ግን ይሖዋ አንድ አስደናቂ ተአምር ሊፈጽም ነው። ይሖዋ በሰማይ የሚኖረውን የልጁን ሕይወት ወደ ማርያም ማሕጸን ያዛውራል። በዚህ ጊዜ ልጁን ከማንኛውም ኃጢአት ለመጠበቅ አምላክ ቅዱስ መንፈሱን በማርያም ላይ ‘እንዲጸልል’ ያደርጋል። ታዲያ ማርያም መልአኩ የነገራትን አመነች? ምን መልስ ትሰጥ ይሆን?
ማርያም ለገብርኤል የሰጠችው መልስ
የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ምሑራንን ጨምሮ ይህ ተአምር መፈጸሙን የሚጠራጠሩ ሰዎች፣ ‘ድንግል የሆነችው ማርያም ልጅ ወለደች’ የሚለውን ሐሳብ ማመን ይቸግራቸዋል። እነዚህ ሰዎች ከፍተኛ እውቀት ቢኖራቸውም ለመረዳት ቀላል የሆነውን ይህን ሐቅ ማስተዋል ተስኗቸዋል። ገብርኤል እንደተናገረው “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም።” (ሉቃስ 1:37) ማርያም ጠንካራ እምነት ስለነበራት ገብርኤል የነገራትን ሁሉ ሳትጠራጠር አምናለች። ይሁን እንጂ ያመነችው ምንም ማስረጃ ሳይኖራት አልነበረም። እንደ ማንኛውም ሰው እሷም ለእምነቷ መሠረት የሚሆን ማስረጃ ማግኘት አስፈልጓታል። ገብርኤልም ተጨማሪ ማስረጃ ሰጣት። አረጋዊት ስለነበረችው ስለ ዘመዷ ኤልሳቤጥ ነገራት። መካን የሆነችው ይህች ሴት በተአምር ጸንሳ ነበር!
ታዲያ አሁን ማርያም ምን ታደርግ ይሆን? ማርያም ትልቅ ኃላፊነት የተጣለባት ሲሆን አምላክ በገብርኤል በኩል የነገራትን ሁሉ እንደሚፈጽም ማስረጃ አግኝታለች። እንዲህ ያለውን ትልቅ መብት ስትቀበል የፍርሃት ስሜት አልተሰማትም ብለን ማሰብ አይኖርብንም። ይህን ኃላፊነት መወጣት ቀላል አልነበረም። በአንድ በኩል ለዮሴፍ ታጭታ ስለነበር ማርገዟን ሲያውቅ እሷን ለማግባት ፈቃደኛ የመሆኑ ጉዳይ ያሳስባታል። በሌላ በኩል ደግሞ
የተጣለባት ኃላፊነት ራሱ ከባድ ነው። ማርያም በማሕፀኗ የምትሸከመው ከፍጥረታት ሁሉ እጅግ ታላቅ የሆነውን የአምላክን ውድ ልጅ ነው! ይህን ልጅ፣ ራሱን ከጉዳት መከላከል ከማይችልበት ከሕፃንነቱ ጀምራ መንከባከብና ከዚህ ክፉ ዓለም መጠበቅ ነበረባት። ይህ በእርግጥም ከባድ ኃላፊነት ነው!መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጠንካራና ታማኝ የሆኑ ሰዎች አምላክ የሰጣቸውን አስቸጋሪ የሚመስል ተልእኮ ለመቀበል ያቅማሙበት ጊዜ እንደነበር ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ አንደበተ ርቱዕ እንዳልሆነ በመግለጽ የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ለማገልገል አሻፈረኝ ብሎ ነበር። (ዘፀአት 4:10) ኤርምያስም ቢሆን “ገና ሕፃን ልጅ ነኝ” በማለት አምላክ የሰጠውን ተልእኮ ለመቀበል ብቁ እንዳልሆነ ገልጿል። (ኤርምያስ 1:6) ዮናስ ደግሞ አምላክ እንዲያከናውን የሰጠውን ሥራ ላለመፈጸም ሸሽቷል! (ዮናስ 1:3) ማርያምስ ምን ታደርግ ይሆን?
ማርያም፣ ለገብርኤል “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” በማለት የሰጠችው መልስ ትሑትና ታዛዥ መሆኗን በግልጽ ያሳያል። (ሉቃስ 1:38) አንዲት ባሪያ ከአገልጋዮች ሁሉ ያነሰች ተደርጋ ትታይ የነበረ ሲሆን ጌታዋ መላው ሕይወቷን ይቆጣጠረው ነበር። ማርያም ይሖዋን የተመለከተችው እንዲህ ነበር። ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግላት፣ ለታማኝ አገልጋዮቹ ታማኝ እንደሚሆን እንዲሁም ይህንን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የምታደርገውን ጥረት እንደሚባርክላት ታውቅ ነበር።—መዝሙር 18:25
አንዳንድ ጊዜ አምላክ፣ ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ አስቸጋሪ ብሎም ፈጽሞ የማይቻል ተግባር እንድናከናውን ይጠይቀን ይሆናል። ይሁንና ማርያም እንዳደረገችው፣ በአምላክ በመታመን ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ለእሱ ማስገዛታችን ተገቢ መሆኑን የሚያሳዩ በቂ ምክንያቶች በአምላክ ቃል ውስጥ ሰፍረውልናል። (ምሳሌ 3:5, 6) ታዲያ እኛስ እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኞች ነን? ከሆንን አምላክ በእሱ ላይ ያለን እምነት ይበልጥ እንዲጠናከር የሚያደርጉ ማስረጃዎችን ይሰጠናል።
ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ሄደች
ገብርኤል፣ ስለ ኤልሳቤጥ የተናገረው ነገር ለማርያም ትልቅ ትርጉም ነበረው። ማርያም ያለችበትን ሁኔታ ከኤልሳቤጥ በተሻለ ማን ሊረዳ ይችላል? በመሆኑም ማርያም ወደ ተራራማው የይሁዳ ከተማ አቀናች፤ ይህ ጉዞ ምናልባት ሦስት ወይም አራት ቀናት ሊወስድ ይችላል። ማርያም፣ ወደ ኤልሳቤጥና ወደ ካህኑ ዘካርያስ ቤት ስትደርስ ይሖዋ እምነቷን የሚያጠናክር ተጨማሪ ማስረጃ ሰጣት። ኤልሳቤጥ ልክ የማርያምን ሰላምታ እንደሰማች በማሕፀኗ ውስጥ ያለው ጽንስ በደስታ ዘለለ። ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ማርያምን “የጌታዬ እናት” አለቻት። አምላክ፣ ማርያም የምትወልደው ልጅ ለኤልሳቤጥ ጌታዋ ማለትም መሲሕ እንደሚሆን ገልጦላት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ “ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!” በማለት ስላሳየችው ታዛዥነት ማርያምን አመስግናታለች። (ሉቃስ 1:39-45) አዎን፣ ይሖዋ ለማርያም የገባላት ቃል ሙሉ በሙሉ መፈጸሙ አይቀርም!
ቀጥላም ማርያም ተናገረች። ማርያም የተናገረችው ሐሳብ በሉቃስ 1:46-55 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። ይህ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው ከሚገኙት የማርያም ንግግሮች ሁሉ ረጅሙ ሲሆን ስለ እሷም ባሕርይ ብዙ ነገር ይጠቁመናል። ማርያም፣ የመሲሑ እናት እንድትሆን ለተሰጣት መብት ይሖዋን ለማወደስ የተጠቀመችባቸው ቃላት የአመስጋኝነትና የአድናቆት መንፈስ እንዳላት ያሳያሉ። ይሖዋ ትዕቢተኞችንና ኃያላንን እንደሚያዋርድ እንዲሁም እሱን ለማገልገል የሚጥሩትን የተናቁትንና ምስኪኖችን እንደሚረዳ የተናገረችው ሐሳብ የእምነቷን ጥንካሬ ያሳያል። ከዚህም በላይ ምን ያህል እውቀት እንደነበራት ይጠቁማል። እዚህ ላይ ማርያም ከ20 ጊዜ በላይ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሳ እንደተናገረች ይገመታል!
ማርያም በአምላክ ቃል ላይ በጥልቅ ታሰላስል እንደነበር ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ትሑት ስለነበረች የራሷን ሐሳብ ከመናገር ይልቅ ከቅዱሳን መጻሕፍት ለመጥቀስ መርጣለች። ልጇ ካደገ በኋላ በአንድ ወቅት “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው” ብሎ ተናግሮ ነበር። ይህም የማርያም ዓይነት መንፈስ እንዳለው ያሳያል። (ዮሐንስ 7:16) እኛም ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘እኔስ ለአምላክ ቃል እንዲህ ያለ አክብሮት አሳያለሁ? ወይስ የራሴን አመለካከትና ሐሳብ መናገር ይቀናኛል?’ ማርያም በዚህ ረገድ ያላት አቋም ግልጽ ነው።
ማርያም ኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር የቆየች ሲሆን በእነዚህ ጊዜያት እርስ በርስ እንደተበረታቱ ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 1:56) ማርያምና ኤልሳቤጥ ጥሩ ወዳጅነት ያለውን ጠቀሜታ እንድንገነዘብ ይረዱናል። እኛም አምላካችንን ይሖዋን ከልብ የሚወዱ ወዳጆችን ለማፍራት ጥረት የምናደርግ ከሆነ መንፈሳዊ እድገት እንደምናደርግና ይበልጥ ወደ እሱ እንደምንቀርብ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ምሳሌ 13:20) በመጨረሻም ማርያም ወደ ቤቷ የምትመለስበት ጊዜ ደረሰ። ዮሴፍ ያለችበትን ሁኔታ ሲያውቅ ምን ይል ይሆን?
ማርያምና ዮሴፍ
ማርያም እርግዝናዋ እስኪታወቅ ድረስ ለዮሴፍ ሳትነግረው መቆየት አልፈለገችም። ሁኔታውን ለዮሴፍ መንገሯ እንደማይቀር ግልጽ ነው። ይህን ከማድረጓ በፊት ግን ይህ ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ሁኔታውን ሲሰማ ምን ሊል እንደሚችል ሳታስብ አልቀረችም። ያም ሆኖ ጉዳዩን አንድም ሳታስቀር ነገረችው። ዮሴፍ ነገሩን ሲሰማ እጅግ እንደተረበሸ መገመት አያዳግትም። ይህ ሰው እጮኛው የምትነግረውን ነገር አምኖ ቢቀበል ደስ ባለው፤ ሆኖም የምትነግረው ነገር ከዚህ ቀደም ፈጽሞ ሆኖ የማያውቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በወቅቱ ዮሴፍ ምን አስቦ እንደነበር ባይናገርም ሊፈታት እንደወሰነ ይገልጻል። በዚያን ዘመን አንድ ወንድና ሴት ከተጫጩ እንደተጋቡ ተደርገው ይታዩ ነበር። ዮሴፍ ማርያምን በሕዝብ ፊት እንድትጋለጥ ወይም ቅጣት እንዲደርስባት ስላልፈለገ በስውር ሊተዋት ወሰነ። (ማቴዎስ 1:18, 19) ማርያም ይህ ደግ ሰው እጅግ መጨነቁን ስታይ አዝና መሆን አለበት። ያም ሆኖ ማርያም አላማረረችም።
ይሖዋ፣ ዮሴፍ የተሻለ ነው ብሎ ባሰበው መንገድ እንዲሄድ አልፈቀደለትም። በመሆኑም የአምላክ መልአክ በሕልም ተገልጦለት ማርያም የጸነሰችው በተአምር መሆኑን ነገረው። ዮሴፍ ይህን በመስማቱ እፎይታ አግኝቶ መሆን አለበት! በዚህ ወቅት ዮሴፍ፣ ማርያም እንዳደረገችው ይሖዋ የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ። ዮሴፍ፣ ማርያምን ያገባት ሲሆን የይሖዋን ልጅ እንዲንከባከብ የተሰጠውን ልዩ ኃላፊነት ለመወጣትም ራሱን አዘጋጀ።—ማቴዎስ 1:20-24
ያገቡም ሆኑ የማግባት ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ከ2,000 ዓመት በፊት ይኖሩ ከነበሩት ከእነዚህ ባልና ሚስት ጥሩ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ዮሴፍ፣ ባለቤቱ የእናትነት ኃላፊነቷን ለመወጣት የምታደርገውን ጥረት ሲመለከት የይሖዋ መልአክ የሰጠውን መመሪያ መታዘዙ እንዳስደሰተው ግልጽ ነው። ዮሴፍ ከባድ ውሳኔዎችን ሲያደርግ በይሖዋ መታመን ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝቧል። (መዝሙር 37:5፤ ምሳሌ 18:13) የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ጥንቃቄና ደግነት የተሞላባቸው እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም።
ማርያም፣ ዮሴፍን ለማግባት ፈቃደኛ መሆኗስ ምን ያስተምረናል? ዮሴፍ የነገረችውን ነገር መጀመሪያ ላይ ለማመን ተቸግሮ የነበረ ሊሆን ቢችልም ማርያም ወደፊት የቤተሰቡ ራስ የሚሆነው እሱ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በትዕግሥት መጠበቅን መርጣለች። ይህ ደግሞ ለእሷ ትልቅ ትምህርት ሰጥቷት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያን ሴቶችም ግሩም ትምህርት ይዟል። በተጨማሪም ይህ ሁኔታ ዮሴፍም ሆነ ማርያም ሐቀኛ መሆንና በግልጽ መነጋገር ትልቅ ጥቅም እንዳለው እንዲረዱ ሳያደርጋቸው አልቀረም።
እነዚህ ወጣት ባልና ሚስት ትዳራቸውን ከሁሉ በተሻለ መሠረት ላይ እንደገነቡ ግልጽ ነው። ይሖዋ አምላክን ከምንም ነገር በላይ ከመውደዳቸውም ሌላ ኃላፊነት የሚሰማቸውና አሳቢ ወላጆች በመሆን እሱን የማስደሰት ፍላጎት ነበራቸው። እርግጥ ነው፣ የተትረፈረፈ በረከት የሚያገኙ ሲሆን ከፊታቸው እጅግ ተፈታታኝ የሆኑ ሁኔታዎችም ይጠብቋቸዋል። ዮሴፍና ማርያም እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ ታላቅ የሆነውን ኢየሱስን የማሳደግ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለጥሩ ትዳር መሠረቱ አምላክን መውደድ ነው