በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር “ትኩሳት” ይዟታል—መድኃኒት ይገኝላት ይሆን?

ምድር “ትኩሳት” ይዟታል—መድኃኒት ይገኝላት ይሆን?

ምድር “ትኩሳት” ይዟታል—መድኃኒት ይገኝላት ይሆን?

የምድር ሙቀት እየጨመረ እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ ነው። ከአርክቲክ በስተ ደቡብ በአላስካ ክልል የምትገኘው የኒውቶክ መንደር ለዚህ ምሳሌ ትሆናለች። ኒውቶክ የተቆረቆረችበት ፐርማፍሮስት በመባል የሚታወቀው በበረዶ የተሸፈነ የምድር ንጣፍ እየቀለጠ ነው። በዚህ አካባቢ የሚኖረው ፍራንክ “[ከእንግዲህ ወዲህ] በፐርማፍሮስት መኖር አልፈልግም፤ ምክንያቱም በጣም ጨቅይቷል” ሲል በምሬት ተናግሯል። ጠረፋማ አካባቢ የሚገኘው ይህ መንደር በአሥር ዓመት ውስጥ ተጠርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ።

ኢንተርገቨርመንታል ፓነል ኦን ክላይሜት ቼንጅ (IPCC) የተባለው ድርጅት “የከባቢ አየር ሙቀት መጨመሩ አሌ የማይባል ሐቅ ነው” ብሏል። የምድር ሙቀት መጨመሩ ይህ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል። የሳይንስ ሊቃውንት የአየር ንብረት ለውጥ ብለው የሚጠሩት ይህ ሁኔታ ድርቅ፣ ኃይለኛ ዝናብ፣ የሙቀት መጠን መጨመር እንዲሁም በመላው ምድር የሚከሰት አውሎ ነፋስን ጨምሮ መጥፎ የአየር ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ታዲያ የምድራችን የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው? መድኃኒት ይገኝላት ይሆን?

የምድርን በሽታ መመርመር

ሆስፒታል የገባ አንድ ሕመምተኛ እንደሚደረግለት ሁሉ የሳይንስ ሊቃውንትም በምድር ላይ የሚታየውን የአየር ንብረት ለውጥ በቅርበት ይከታተላሉ። የአየር ትንበያ ጣቢያዎች የዝናቡን መጠን ይመዘግባሉ፤ ሳተላይቶች የግግር በረዶዎችን መቅለጥ ይከታተላሉ፤ በውቅያኖስ ላይ ያሉ የአየር ንብረትን የሚመዘግቡ መሣሪያዎች በውቅያኖስ ውስጥ ያለውን ሙቀት ይመዘግባሉ፤ አውሮፕላኖች ላይ የሚገጠሙ መሣሪያዎች የከባቢ አየር ጋዞችን መጠን ይለካሉ። በዚህ መንገድ ከተለያዩ ቦታዎች የተሰበሰቡት መረጃዎች በዓይነቱ ልዩ ወደሆነ ኮምፒውተር ውስጥ ይገባሉ። ከዚያም የምድርን አየር ንብረት የሚያሳይ ሞዴል ከተዘጋጀ በኋላ በሂደት ላይ እንዳለ አድርጎ በማሠራት ከአሥር ሌላው ቀርቶ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ምን ሊከሰት እንደሚችል ይተነብያል።

ታዲያ የምርመራው ውጤት ምን ያሳያል? አንዳንዶች ከባቢው አየር፣ ሙቀት እንዲጨምር በሚያደርጉ ጋዞች ተጨናንቋል የሚል እምነት አላቸው። በ2006 ብቻ በዓለም ላይ ወደ ከባቢ አየር የተለቀቀው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን “አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነት በመጨመር 32 ቢሊዮን ቶን መድረሱን” ታይም መጽሔት ዘግቧል። ግሪን ሃውስ የሚባለው ከመስታወት የተሠራ ቤት ሙቀት አፍኖ እንደሚይዝ ሁሉ እንዲህ ያሉት ጋዞችም የምድር ሙቀት ወደ ጠፈር እንዳይገባ አምቀው ስለሚይዙ ለምድር ሙቀት መጨመር አስተዋጽኦ አድርገዋል። ታዲያ ይህ ምን ያስከትል ይሆን? ኢንተርገቨርመንታል ፓነል ኦን ክላይሜት ቼንጅ እንዳለው ከሆነ፣ ወደ ከባቢው አየር የሚለቀቁት ጋዞች በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከቀጠሉ “በምድር የአየር ንብረት ላይ በርካታ ለውጦች ማስከተላቸው” አይቀርም። ይህም አሁን ካለው ሁኔታ በእጅጉ የከፋ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ብዙዎች፣ ለዚህ መፍትሔው ወደ ከባቢ አየር በሚለቀቀው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሆነ ይስማማሉ። ይሁን እንጂ ጋዞቹ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁበት መጠን ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል ቢደረግ እንኳ የኮምፒውተር መረጃዎች እንደሚያሳዩት “የሙቀት መጠን መጨመርና [በዚህም ሳቢያ የሚከሰተው] የባሕር ጠለል ከፍታ መጨመር ለብዙ መቶ ዓመታት ይቀጥላል።”

መፍትሔ ከየት ማግኘት ይቻላል?

የአየር ሁኔታ ትንበያ በጣም የተወሳሰበ ሳይንስ መሆኑ እሙን ነው። “ለምሳሌ ያህል፣ የምድር ሙቀት ሲጨምር ደመናዎች ምን ይሆናሉ? የምድር ሙቀት እንዲጨምር አስተዋጽኦ የሚያደርጉትና ሙቀትን በውስጣቸው ይዘው ከፍ ብለው የሚንሳፈፉት ደመናዎች የፀሐይ ብርሃንን ከሚጋርዱ ጥቅጥቅ ካሉ የደመና ዓይነቶች ይልቅ በብዛት ይከሰቱ ይሆን?” በማለት ኧርዝ ኦብዘርቫቶሪ የተባለ በኢንተርኔት የሚሠራጭ አንድ ጽሑፍ ይጠይቃል። አክሎም “በአሁኑ ሰዓት የሳይንስ ሊቃውንት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የላቸውም” በማለት ይናገራል።

በሌላ በኩል መጽሐፍ ቅዱስ ‘በላይ ያሉትን ደመናትን’ ጨምሮ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ” ይሖዋ አምላክ መሆኑን ያረጋግጥልናል። (ዘፍጥረት 14:19፤ ምሳሌ 8:28) ይሖዋ ‘በደመናት ውስጥ ጥበቡን’ እንዳኖረ ገልጿል። አዎን፣ ይሖዋ የሳይንስ ሊቃውንት መረዳት የማይችሉትን ነገር በሚገባ ያውቃል።—ኢዮብ 38:38

ከዛሬ 2,700 ዓመታት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተመዘገበው፣ አምላክ የምድርን ከባቢ አየር በተመለከተ ‘ዝናም ወርዶ ምድርን ሳያርስ ወደ ላይ እንደማይመለስ’ መናገሩን ልብ በል። (ኢሳይያስ 55:10) ይህ የውኃ ዑደት ምን እንደሚመስል በአጭሩ ይገልጻል። እርጥበት አዘል ደመናዎች ወደ ዝናብነት በመቀየር ‘ምድርን ያርሳሉ።’ የፀሐይ ሙቀት ውኃውን ወደ ተን እንዲቀየር በማድረግ ‘ወደላይ እንዲመለስ’ ማለትም ወደ ከባቢ አየር እንዲገባ ያደርገዋል፤ በዚህ መንገድ ዑደቱ ይቀጥላል። የይሖዋ ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሌሎች ጽሑፎች ከመጻፋቸው ከብዙ ዘመናት በፊት የምድርን አየር ንብረት በተመለከተ አስገራሚ የሆነ ዝርዝር ሐሳብ አስፍሯል። ይህ፣ ፈጣሪ ባለው ችሎታ ላይ ያለህን እምነት አያጠናክርልህም? ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ለተያያዙ ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት የምድራችንን አሠራር ጠንቅቆ ወደሚያውቀው እንዲሁም ‘የነፋስ ፈጣሪ’ እና ‘የዝናብ አባት’ ወደሆነው አምላክ መዞራችን ምክንያታዊ አይሆንም?—አሞጽ 4:13፤ ኢዮብ 38:28

ምድር የተፈጠረችው በዓላማ ነው

የምድራችን የወደፊት ዕጣን በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም በአንድ ነገር ግን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ይኸውም ምድራችን ከሌሎች ፕላኔቶች ሁሉ ልዩ ነች። ከሌሎች ፕላኔቶች በተለየ መልኩ በምድር ላይ የተለያዩ አስደናቂ ሕያዋን ፍጥረታት ይኖራሉ። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የሳይንስ ሊቃውንት የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባሉ። ከእነዚህም መካከል ውኃ እንደልብ መኖሩን፣ ምድር ከፀሐይ በትክክለኛው ርቀት ላይ መገኘቷን እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የኦክስጂን መጠንን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ጋዞች በተመጣጠነ ሁኔታ መገኘታቸውን ይጠቅሳሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ እነዚህ ነገሮች የሚናገር መሆኑን ስታውቅ ሳትገረም አትቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ ዘፍጥረት 1:10 አምላክ በአንድነት የተሰበሰበውን ‘ውሃ ባሕር ብሎ እንደጠራው’ የሚገልጽ ሲሆን ይህም በምድር ላይ ውኃ እንደልብ የሚገኝ መሆኑን ያሳያል። ዘፍጥረት 1:3 ላይ “እግዚአብሔር ‘ብርሃን ይሁን’ አለ፤ ብርሃንም ሆነ” ይላል። ፕላኔታችን ከፀሐይ በትክክለኛው ርቀት ላይ የምትገኝ መሆኗ፣ በላይዋ ላይ ያለው አብዛኛው ውኃ ወደ በረዶነት እንዳይቀየር አስተዋጽኦ አድርጓል። በሌላ በኩል ምድር ወደ ፀሐይ ብትቀርብ ኖሮ በላይዋ ላይ ያለው ውኃ ሁሉ ተኖ ያልቅ ነበር።

ዘፍጥረት 1:6 ደግሞ አምላክ “ጠፈር” ወይም ከባቢ አየር እንደፈጠረ ይናገራል። በመቀጠል በቁጥር 11 እና 12 ላይ አምላክ በምድር ላይ ሣር፣ ተክሎችና ዛፎች እንዲበቅሉ እንዳደረገ ይገልጻል። እነዚህ ነገሮች በምድር ላይ ኦክሲጅን መኖሩን የሚጠቁሙ ሲሆኑ ይህም ሰዎችም ሆኑ እንስሳት በምድር ላይ በሕይወት ለመኖር አስችሏቸዋል።

ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? አምላክ ምድርን ውኃ እንደልብ እንዲኖራት፣ ከፀሐይ በትክክለኛው ርቀት ላይ እንድትገኝ እንዲሁም አስፈላጊ ጋዞች በተመጣጠነ ሁኔታ እንዲኖሩባት አድርጎ ሲፈጥራት ዓላማ እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ‘ምድርን የሰው መኖሪያ እንጂ ባዶ እንድትሆን እንዳልፈጠራት’ ይናገራል። (ኢሳይያስ 45:18) መዝሙር 115:16 ላይ “ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ይላል። አዎን፣ ምድር የተፈጠረችው የሰው መኖሪያ እንድትሆን ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ከፈጠረ በኋላ ውብ በሆነው በኤድን ገነት እንዳስቀመጣቸው ይነግረናል። ምድርን ‘ማልማትና መንከባከብ’ ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 2:15) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” ብሏቸዋል። (ዘፍጥረት 1:28) ከፊታቸው እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ተዘርግቶላቸው እንደነበር አስብ! መላዋ ምድር እስክትሸፈን ድረስ ገነትን ማስፋትና በእሷ ላይ ለዘላለም መኖር ይችሉ ነበር። እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነበር!

የሚያሳዝነው ግን፣ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አምላክን ከመታዘዝ ይልቅ ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር መረጡ፤ ይህ ደግሞ የሰው ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ እየተከተሉ ያሉት ጎዳና ነው። (ዘፍጥረት 3:1-6) ይህ ምን ውጤት አስከተለ? ሰዎች ምድርን ከማልማትና ከመንከባከብ ይልቅ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ‘ምድርን እያጠፏት’ ይገኛሉ። (ራእይ 11:18) አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እንዳልተለወጠ ማወቃችን ግን ያጽናናናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ [አጸናት]” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝሙር 104:5) በተጨማሪም ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:5) ታዲያ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

ከፊታችን ብሩህ ተስፋ ይጠብቀናል

አንድ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት “የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ችግር ነው” ብለዋል። ታዲያ ዓለም አቀፋዊ የሆነ መፍትሔ ያስፈልጋል ቢባል አትስማማም? ኢየሱስ ክርስቶስ መፍትሔው የአምላክ መንግሥት መሆኑን ጠቁሟል። ተከታዮቹን “መንግሥትህ ትምጣ” በማለት እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) በሰማይ የተቋቋመውና መላውን ምድር የሚያስተዳድረው ይህ መንግሥት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት በቅርቡ “[በአሁኑ ጊዜ ያሉትን] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል።” (ዳንኤል 2:44) በተጨማሪም ‘ምድርን የሚያጠፏትን ያጠፋል።’ (ራእይ 11:18) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ምድርን የሚያበላሹና የተፈጥሮ ሀብትን ያላግባብ የሚጠቀሙ ሁሉ ይጠፋሉ።

ይሁንና የተበላሸችው ምድራችን ምን ትሆናለች? ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ እንደ ነፋስና ማዕበል ያሉ የተፈጥሮ ኃይሎችን የመቆጣጠር ሥልጣን እንዳለው ማሳየቱ ትኩረት የሚስብ ነው። ጥቂት ቃላትን በመናገር ብቻ ኃይለኛ ማዕበልን ጸጥ አሰኝቷል። (ማርቆስ 4:35-41) “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” በመሆን በሰማይ ላይ እየገዛ ያለው ኢየሱስ ምድርንም ሆነ የተፈጥሮ ኃይሎችን በላቀ ሁኔታ ይቆጣጠራል። (ራእይ 17:14) እንዲያውም ኢየሱስ አገዛዙን “አዲስ ዓለም” በማለት ገልጾታል። (ማቴዎስ 19:28) ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ሐረግ “ሁሉም ነገር የሚታደስበት ጊዜ” በማለት አስቀምጦታል። (ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) ኢየሱስ ምድርን በማደስ ከኤድን ገነት ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ እንዲኖር ያደርጋል። ገነት መልሶ ይቋቋማል። (ሉቃስ 23:43) ምድር በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ከያዛት “ትኩሳት” ትፈወሳለች።

በአሁኑ ጊዜም እንኳ የአምላክ መንግሥት ከሚያስገኘው በረከት ተጠቃሚ መሆን ትችላለህ። እንዴት? ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለምሥራቹ ምላሽ እየሰጡ ሲሆን ሕይወታቸውም ተለውጧል። አደገኛ ሱሶችን ማሸነፍ ችለዋል። የቤተሰብ ሕይወታቸው ተሻሽሏል። የዘር ጥላቻ በፍቅር ተተክቷል። በእርግጥም የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ አገዛዝ ሊፈጽመው ያልቻለውን ነገር በማከናወን ላይ ነው። የአምላክ መንግሥት፣ ከ235 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች አንድነት ባለው በእውነተኛ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ኅብረት ውስጥ እንዲታቀፉ አድርጓል! አዎን፣ የአምላክ መንግሥት ተገዥዎች ገነት በምትሆነው በዚህች ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር እየተዘጋጁ ነው።

ምድር ብሩህ የወደፊት ተስፋ አላት። አንተም እንዲህ ያለ ተስፋ እንዲኖርህ ምኞታችን ነው!

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሌሎች ጽሑፎች ከመጻፋቸው ከብዙ ዘመናት በፊት የውኃ ዑደትን በተመለከተ ገልጿል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ “ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም፣ ‘ጸጥ፣ ረጭ በል!’ አለው። ነፋሱም ጸጥ፣ ርጭ አለ፤ ፍጹምም ጸጥታ ሆነ”

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገነት ስትቋቋም ምድር ከያዛት “ትኩሳት” ትፈወሳለች

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Godo-Foto