ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት በ30 ጥሬ ብር የተዋዋለው ለምንድን ነው?
የአስቆሮቱ ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ ኢየሱስን አሳልፎ ቢሰጣቸው ምን ያህል እንደሚከፍሉት ሲጠይቃቸው “ሠላሳ ጥሬ ብር” ቈጥረው ሰጡት። (ማቴዎስ 26:14, 15) ይህ የገንዘብ መጠን ካህናቱ ለኢየሱስ ከፍተኛ ጥላቻና ንቀት እንደነበራቸው ያሳያል።
ካህናቱ ለይሁዳ ሊሰጡት የተስማሙት ገንዘብ በጊዜው አይሁዳውያን ለመገበያያነት ይጠቀሙበት የነበረውን የብር ሰቅል ሳይሆን አይቀርም። በ30 ሰቅል ምን ነገሮችን መግዛት ይቻል ነበር? የሙሴ ሕግ፣ ይህ የገንዘብ መጠን አንድ ባሪያ የሚሸጥበት ዋጋ እንደሆነ ይናገራል። ከዚህም በተጨማሪ ሠላሳ ሰቅል አነስተኛ መሬት ሊገዛ ይችል ነበር።—ዘፀአት 21:32፤ ማቴዎስ 27:6, 7
ነቢዩ ዘካርያስ፣ የአምላክ ሕዝቦች እረኛ በመሆን ላከናወነው ተግባር ዋጋ እንዲከፍሉት ታማኝ ያልሆኑትን እስራኤላውያንን በጠየቃቸው ጊዜ “ሠላሳ ብር” መዝነውለት ነበር። ይህ ሁኔታ፣ የአምላክን ነቢይ ለማዋረድና ከአንድ ባሪያ አስበልጠው እንደማይመለከቱት ለማሳየት ሆን ብለው የፈጸሙት ተግባር ነው። በመሆኑም ይሖዋ “ሊከፍሉኝ የተስማሙበትን ጥሩ ዋጋ ‘በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው’” በማለት ዘካርያስን አዘዘው። (ዘካርያስ 11:12, 13) ዘካርያስ የተሰጠውን ትእዛዝ አክብሮ የፈጸመው ተግባር ይሁዳ፣ ይሖዋ የእስራኤል እረኛ አድርጎ የሾመውን ኢየሱስን አሳልፎ በመስጠት ያገኘውን ጥሬ ብር ምን እንዳደረገው የሚገልጸውን ታሪክ ያስታውሰናል።—ማቴዎስ 27:5
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው “የፍቺ ወረቀት” ምንድን ነው?
የሙሴ ሕግ እንደሚከተለው ይላል:- “አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ፣ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፣ የፍቺ ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት።” (ዘዳግም 24:1) የዚህ ሰነድ ዓላማ ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ወረቀት ላይ ምን ይጻፍ እንደነበር የሚነግረን ነገር የለም። ይሁንና ሰነዱ የተፈታችውን ሴት መብትና ፍላጎት የሚያስከብር እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
ከ1951-1952 ባሉት ጊዜያት በይሁዳ ምድረ በዳ ውስጥ ከሚገኘው ዋዲ ሙራባት ከሚባለው ደረቅ ወንዝ በስተ ሰሜን ባሉ ዋሻዎች ውስጥ በርከት ያሉ ጥንታዊ ቅርሶች ተገኝተዋል። ከተገኙት በርካታ ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል በ71 ወይም በ72 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጻፈ የሚገመት በአረማይክ ቋንቋ የተዘጋጀ የፍቺ ወረቀት ይገኝበታል። ይህ የፍቺ ወረቀት አይሁዳውያን በሮማውያን ላይ ባመጹበት በስድስተኛው ዓመት ማርሄሽቫን በተባለው ወር በመጀመሪያው ቀን ምን እንደተከሰተ ይገልጻል። በማሳዳ የሚኖረው የናክሳን ልጅ ዮሴፍ፣ የሃናብላታ ተወላጅ የሆነችውን የዮናታንን ልጅ ሚርያምን እንደፈታት ይገልጻል። ሚርያም የወደደችውን አይሁዳዊ የማግባት ነፃነት እንዳላትም ይናገራል። ዮሴፍ፣ በተጋቡበት ወቅት ሚርያም ይዛ የመጣችውን ጥሎሽ እንደመለሰላትና ለጠፋውም ንብረት አራት እጥፍ ካሣ እንደከፈላት ይገልጻል። በፍቺው ወረቀት ላይ የዮሴፍና የሦስት ምሥክሮች ማለትም የማልካ ልጅ ኤሊኢዘር፣ የማልካ ልጅ ዮሴፍና የሃናና ልጅ ኤልኤዘር ፊርማ ይገኛል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዋዲ ሙራባት የሚገኙት ዋሻዎች
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ71 ወይም በ72 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጻፈ የሚገመት የፍቺ ወረቀት
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Caves: Todd Bolen/Bible Places.com; certificate: Clara Amit, Courtesy of the Israel Antiquities Authority