ስህተት ለማግኘት ያደረግኩት ጥረት እውነትን እንዳውቅ አስቻለኝ
ስህተት ለማግኘት ያደረግኩት ጥረት እውነትን እንዳውቅ አስቻለኝ
ሩዶልፍ ስቱዋርት ማርሻል እንደተናገረው
አንድ የካቶሊክ ቄስ “የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚጠቀሙ ከእነሱ ጋር አንነጋገርም” አለኝ። ወደ ቄሱ የሄድኩት የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት ስህተት መሆኑን ለባለቤቴ እንዲያሳያት ለመጠየቅ ስለነበር የሰጠው መልስ አስገረመኝ። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት ስህተት እንደሆነ ለባለቤቴ ለማስረዳት ስል ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ወሰንኩ።
በዚህ ወቅት የ43 ዓመት ጎልማሳ የነበርኩ ሲሆን የማሳመን ችሎታዬንና የሥነ መለኮት እውቀቴን ተጠቅሜ የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት ስህተት መሆኑን ለማረጋገጥ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ኮሌጅ ድረስ ትምህርቴን የተከታተልኩት በካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው። በ1969 በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ያገኘሁ ሲሆን በተጓዳኝ ይሰጡ የነበሩትን የፍልስፍናና የሥነ መለኮት ትምህርቶችም ተከታትያለሁ። ሆኖም በካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በቆየሁባቸው ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስን ጨርሶ ተምሬ አላውቅም።
የኮሌጅ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ እንደ እኔው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ከሆነችው ከፓትሪሺያ መክጊን ጋር ተጋባን። ከጊዜ በኋላ ሁለታችንም ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያችንን አገኘን። በ1977 ስቱዋርትን የወለድን ሲሆን በኋላም በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ሳክረሜንቶ ከተማ መኖር ጀመርን። ቀጣዮቹን 23 ዓመታት በካሊፎርኒያ ግዛት ሕግ የማርቀቅ ሥራ በሚከናወንበት ሌጅስሌቲቭ አናሊስትስ ኦፊስ በተባለ ተቋም ውስጥ ሠርቻለሁ። ሥራዬ ለትምህርት የሚመደበው በጀት በግዛቲቱ ኢኮኖሚ ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ማጥናት ነበር። ጠንክሬ እሠራ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ኑሮ ነበረኝ። የልጅ አባት መሆኔም አስደስቶኛል። ውዷ ባለቤቴ በታማኝነት ትደግፈኝ የነበረ ሲሆን እኔም እደግፋት ነበር።
በ25 ሳንቲም የተገኘ መልስ
ስቱዋርት የሁለት ዓመት ልጅ ሳለ ፓትሪሺያ ከይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ አግኝታ ከእነሱ ጋር ማጥናት ጀመረች። ከሦስት ዓመት በኋላ ተጠመቀች። የይሖዋ ምሥክሮች ከበዓላትና ደም ከመውሰድ ጋር በተያያዘ ጠባብ አመለካከት እንዳላቸው ይሰማኝ ነበር። ሆኖም ስለ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች የሚሰጡትን ማስረጃ አሳማኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የሚገርመው እኔ በምኖርበት ግዛት ከትምህርት ጋር በተያያዘ ሕግ የማውጣት ኃላፊነት ያላቸውን ሰዎች ካቀፈ ኮሚቴ ጋር በ1987 በተደረገ አንድ ልዩ ስብሰባ ላይ ሐሳብ እንድሰጥ በተጠየቅኩበት ወቅት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያለኝን ይህን ስሜት በግልጽ መናገር የምችልበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር።
የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ግዛቶች ጋር ተወዳድሮ የፌዴራሉ መንግሥት ያቀረበውን የስድስት ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ለማሸነፍ የገንዘብ ድጋፍ አስፈልጎት ነበር። ፕሮጀክቱ የተነደፈው ለምርምር የሚረዳ በጣም ግዙፍ የሆነ አንድ መሣሪያ ለመገንባት ታስቦ ነበር። ይህ ፕሮጀክት ለግዛቲቱ ኢኮኖሚ እምብዛም ፋይዳ እንደማይኖረው በመግለጽ ፕሮጀክቱን ለማሸነፍ ገንዘብ ማውጣት አስፈላጊ እንዳልሆነ ሐሳብ አቀረብኩ። ዩኒቨርሲቲው ደግሞ ሁለት የፊዚክስ
የኖቤል ተሸላሚዎች በስብሰባው ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ አደረገ። ሁለቱም፣ ፕሮጀክቱ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም አስመልክተው ማብራሪያ ሰጡ። አንደኛው ከአጽናፈ ዓለም አመጣጥ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ሊያስገኝ እንደሚችል ተናገረ። ሌላኛው ደግሞ በምድር ላይ ሕይወት እንዴት እንደጀመረ ለመረዳት የሚያስችል የእውቀት ብርሃን እንደሚፈነጥቅ ገለጸ።በዚህ ጊዜ የኮሚቴው ሊቀ መንበር ወደ እኔ ዞር አለና፦
“ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ብናወጣ የሚበዛ ይመስልሃል?” በማለት ጠየቀኝ።
“እነዚህ ጥያቄዎች አንገብጋቢ መሆናቸው ምንም አያጠራጥርም” በማለት መለስኩ። “ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ አንድ መጽሔት ቅዳሜ ጠዋት ቤት ድረስ መጥተው ሰጥተውኝ ነበር። መጽሔቱን የወሰድኩት 25 ሳንቲም መዋጮ በማድረግ ነው። በ25 ሳንቲም የተገኘው መልስ የስድስት ቢሊዮን ዶላሩ ፕሮጀክት ሊያስገኝ ከሚችለው መልስ ያንሳል ብዬ አላስብም።”
የኖቤል ተሸላሚዎቹን ጨምሮ እዚያ የነበሩት ሰዎች በሙሉ ከት ብለው ሳቁ። ኮሚቴው ፕሮጀክቱን ለማሸነፍ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ቢፈቅድም የእኔን ሐሳብ የተቃወመ ሰው አልነበረም።
ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ በቤት ውስጥ ካለው ለውጥ ጋር በተያያዘ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ተሰማኝ። መጽሐፍ ቅዱስንና የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ለስድስት ዓመታት ያህል ከፓትሪሺያ ጋር ብንወያይም ፓትሪሺያ በስብከቱ ሥራ የበለጠ ሰዓት ለማሳለፍ መፈለጓ አሳዘነኝ። ይህን ማድረግ በዩኒቨርሲቲ በመሥራት የምታሳልፈውን ሰዓት መቀነስ ይጠይቅባታል። ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላት ሴት እንዴት እንዲህ ያለ እርምጃ ትወስዳለች የሚለው ነገር ቢያሳዝነኝም ሐሳቧን ለማስቀየር ልናገረውም ሆነ ላደርገው የምችለው አንድም ነገር ያለ አይመስልም ነበር።
ከእኔ የተሻለ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያለው ሰው የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚጋጭ በቀላሉ ለባለቤቴ ሊያስረዳት እንደሚችል ስለተሰማኝ እንዲህ ያለ ሰው ለማግኘት ሞከርኩ። ከትምህርቶቻቸው መካከል አንዱ እንኳ የተሳሳተ እንደሆነ ማረጋገጥ ከተቻለ ሌሎቹን ትምህርቶች እንድትጠራጠር ያደርጋታል የሚል ስሜት አደረብኝ። የባለቤቴን ሐሳብ ለማስለወጥ የሚያስፈልገው ይሄ ብቻ ነው። በመሆኑም እኔና ፓትሪሺያ ቀደም ሲል እንሄድበት በነበረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያገለግል ቄስ ስለ ሁኔታው አማከርኩት። ውይይታችን የተደመደመው በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ በተገለጸው መንገድ ነበር። ቄሱ ከባለቤቴ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲነግረኝ፣ ትንሽ ጊዜ ሊወስድብኝ ቢችልም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት ምን ስህተቶች እንዳሉበት እኔው ራሴ አውቄ ለፓትሪሺያ ማስረዳት እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።
ስህተት ለማግኘት ያደረግኩት ጥረት
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የአምላክን ቃል ሳጠና ይበልጥ የማረከኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ባቢሎን አወዳደቅ የጻፈውን ዝርዝር ሐሳብ አነበብኩ። ሁኔታው ከመፈጸሙ ከ200 ዓመታት ገደማ በፊት የተነገረው ይህ ትንቢት ባቢሎንን ድል የሚያደርጋት ቂሮስ መሆኑን በስም ጠቅሶ የሚናገር ሲሆን ከተማዋን ለመያዝ የኤፍራጥስን ወንዝ እንዴት አቅጣጫ እንደሚያስቀይርም ኢሳይያስ 44:27 እስከ 45:4) ከዓመታት በፊት በትምህርት ቤት ስለ ወታደራዊ የጦር ስልት በተማርንበት ወቅት ስለ ባቢሎን አወዳደቅ አጥንተን ነበር። ነቢዩ ዳንኤል ስለ ኃያሉ የግሪክ ንጉሥ እንዲሁም እሱ ከሞተ በኋላ በኃይል ከእሱ ያነሱ አራት መንግሥታት እንደሚነሱ፣ ትንቢቱ ከመፈጸሙ ከ200 ዓመታት በፊት አስቀድሞ በዝርዝር እንደተናገረ ተማርኩ። (ዳንኤል 8:21, 22) በዚህ ጊዜ ትምህርት ቤት ሳለሁ ስለ ታላቁ እስክንድር የተማርኩት ትዝ አለኝ። በማመሳከሪያ ጽሑፎች ላይ ምርምር ሳደርግ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተጻፉት በእርግጥም ትንቢቶቹ ከመፈጸማቸው በፊት መሆኑን ማረጋገጥ ቻልኩ።
ይገልጻል። (ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን በቀጠልኩ መጠን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ይበልጥ ተገነዘብኩ፤ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ለዓመታት ያጠናሁ ቢሆንም እንዲህ ያለ እውቀት አላገኘሁም ነበር። ታዲያ ይህ እውቀት ምን እንዳደርግ አነሳሳኝ? ሕይወቴን ለይሖዋ ወስኜ የእሱ ምሥክር ለመሆን አሰብኩ። (ኢሳይያስ 43:10) ከቄሱ ጋር ውይይት ካደረግን ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ1991 ተጠመቅኩ። ልጃችንም በቀጣዩ ዓመት ተጠመቀ።
ትኩረት የምንሰጠው ነገር ሲለወጥ የቤተሰባችን ግብም ተለወጠ። ከተጠመቅኩ በኋላ ካደረግኳቸው ነገሮች መካከል አንዱ ባለቤቴ ከአምስት ዓመት በኋላ 50 ዓመት ሲሞላት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪነቷን እንድታቆም አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ነበር። ባለቤቴ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ ይበልጥ ለመርዳት ስላሰበች አቅኚ ለመሆን ፈለገች። ይህም በወቅቱ በዓመት ውስጥ 1,000 ሰዓት ማለትም በወር 83 ሰዓት ያህል በስብከቱ ሥራ መካፈል ይጠይቅባት ነበር። በ1994 በሥራ የምታሳልፈውን ሰዓት በመቀነስ አቅኚ ሆነች። ለራሴ ካወጣኋቸው ግቦች መካከል ደግሞ የመስበክ ችሎታዬን ማሻሻል፣ በምችለው ሁሉ ጉባኤያችንን መርዳት እንዲሁም በአካባቢያችን ለሚካሄደው የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ በፈቃደኝነት የሒሳብ ሥራ መሥራት ይገኙበታል።
በሥራ ቦታ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የመወያየት አጋጣሚ ያገኘሁበት ጊዜ ነበር። ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ሙያ ያላት አንዲት ሴት በአንድ ወቅት መሥሪያ ቤታችን ውስጥ ተቀጥራ መሥራት ጀመረች። ይህቺ ሴት የይሖዋ ምሥክር የነበረች ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥርጣሬ ስላደረባት እምነቷ ተዳክሞ ነበር። መንፈሳዊነቷ እንዲጠናከር መርዳት በመቻሌ ደስ ብሎኛል። ይህቺ ሴት ከጊዜ በኋላ ወዳደገችበት ከተማ የተመለሰች ሲሆን በአቅኚነት ማገልገል ጀምራለች።
ከትምህርት ጋር በተያያዘ ሕግ የማውጣት ኃላፊነት ያላቸውን ሰዎች ያቀፈው ኮሚቴ፣ የፌዴራሉ መንግሥት የነደፈው ፕሮጀክት ምን ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ለማዳመጥ በ1995 ባደረገው አንድ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር። የኮሚቴው ሊቀ መንበር ፕሮጀክቱ ምን ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ የፌዴራሉን መንግሥት ተወካይ ጠየቀው። ተወካዩ ፕሮጀክቱ ለቴክሳስ ግዛት እንደተሰጠና በሦስት ምክንያቶች የተነሳ እስከ አሁን ድረስ እንዳልተጠናቀቀ ገለጸ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ፕሮጀክቱን ለማካሄድ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ገና ሥራው ሳይጀመር ከስድስት ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር አድጓል። በሁለተኛ ደረጃ፣ የፌዴራሉ መንግሥት ገንዘቡን ለሌላ ዓላማ በተለይ ደግሞ በ1991 ከኢራቅ ጋር ተደርጎ ለነበረው ጦርነት ለማዋል ፈልጎ ነበር። በሦስተኛ ደረጃ፣ ፕሮጀክቱን የነደፈው አካል ሕይወትን አስመልክቶ ለተነሱት ጥያቄዎች መልሱን ከይሖዋ ምሥክሮች በ25 ሳንቲም ማግኘት እንደሚቻል ተገንዝቧል! ያን ጊዜ የሰጠሁትን ሐሳብ ብዙ ሰዎች መስማታቸውና ከኮሚቴው ጋር ባደረግነው ሌላ ስብሰባ ላይ በድጋሚ መነሳቱ አስገረመኝ።
በስብሰባው ላይ የነበሩት ሰዎች በሙሉ ሲስቁ አንዳንድ የኮሚቴው አባላት ወደ እኔ ተመለከቱ። “መጽሔቶቹን ማንበብ የምትፈልጉ ከሆነ አሁን መልሶቹን በነፃ ማግኘት ትችላላችሁ” በማለት ከመጽሔቶቹ ጋር በተያያዘ የተደረገውን ማሻሻያ ለተሰብሳቢዎቹ ነገርኳቸው።
እርካታና ትርጉም ያለው ሕይወት
ባለቤቴ ጡረታ ከወጣች በኋላ ለእኔ ደግሞ የአምስት ዓመት እቅድ አወጣን። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች በማስተማር ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ ስለፈለግኩ በሳምንት ውስጥ የተወሰነ ሰዓት ብቻ መሥራት የምችልበትን ሥራ ለማግኘት መሥሪያ ቤቴ ሳያውቅ አንዳንድ ድርጅቶችን መጠየቅ ጀመርኩ። ምንም ሳላስበው መሥሪያ ቤቴ የተወሰነ ሰዓት ብቻ እንድሠራ ግብዣ አቀረበልኝ። በመሆኑም በ1998 እኔም አቅኚ ሆንኩ።
አንድ ቀን ጠዋት ከባለቤቴ ጋር ወደ ስብከት ለመሄድ እየተዘጋጀን ሳለ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ከሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ስልክ ተደወለልኝ። የደወለልኝ ወንድም በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ለየት ያለ ችሎታ ያላቸው ወንድሞችንና እህቶችን እየፈለጉ እንደሆነ ገልጾልኝ ብሩክሊን ውስጥ በሚካሄድ አንድ ፕሮጀክት ላይ መሥራት እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። ምንም ሳላመነታ ፈቃደኛ መሆኔን ገለጽኩለት። በዚህም የተነሳ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል በዋናው
መሥሪያ ቤት መሥራት ችለናል። ይህን ፕሮጀክት ለመጨረስ ስል በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ከነበረኝ ሥራ አስቀድሜ ጡረታ ወጣሁ። ከዚያ በኋላ ፌርፊልድ፣ ካሊፎርኒያ በተካሄደው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታ ላይ በፈቃደኝነት ተካፍለናል። በሳክረሜንቶ የነበረውን ቤታችንን ሸጥንና ፓሎ አልቶ ውስጥ በሚገኝ አነስተኛ አፓርታማ ውስጥ መኖር ጀመርን። ቀደም ብዬ ጡረታ መውጣቴ ተጨማሪ በረከቶችን እንዳገኝ አስችሎኛል። ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ካናዳ፣ ብሪታንያ እና ጀርመን በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሥር በተካሄዱ ፕሮጀክቶች ላይ ተካፍለናል።እኛን እንደረዱን የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ እኔና ባለቤቴም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ እያጣጣምን ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ከይሖዋ ያገኘሁት ትምህርት ከፍተኛ ትምህርት በመከታተል ካገኘሁት እውቀት በእጅጉ ይበልጣል። በዚህ ምድር ላይ ከሚሰጥ ከየትኛውም ትምህርት በተለየ መለኮታዊ ትምህርት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስስና ጥልቀት ያለው ነው። ይሖዋ የሰዎችን አእምሮ ሊለውጥና ልባቸውን ሊነካ በሚችል መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር እንዲችሉ ምሥክሮቹን አሠልጥኗቸዋል። መማሬን እንድቀጥል የሚያነሳሳኝም ይህ ነው። እኔና ባለቤቴ በአሁኑ ጊዜ በሕይወታችን ደስተኞች ስለሆንን እንዲሁም በእውቀታችን ተጠቅመን የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ ይሖዋ አምላክን የማገልገል ልዩ መብት ስላገኘን አመስጋኞች ነን።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የአምላክን ቃል ሳጠና ይበልጥ የማረከኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ነበር
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከፓትሪሺያ ጋር በሠርጋችን ቀን
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኔና ፓትሪሺያ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች እንዲማሩ በመርዳቱ ሥራ ስንካፈል