ከሁሉ የላቀው የአምላክ ፍቅር ማረጋገጫ
ወደ አምላክ ቅረብ
ከሁሉ የላቀው የአምላክ ፍቅር ማረጋገጫ
አብርሃም አምላክን የሚወድ ሰው ነበር። ይህ ታማኝ የእምነት አባት በስተርጅናው የወለደውን ልጁን ይስሐቅንም ይወደዋል። ይሁንና ይስሐቅ የ25 ዓመት ገደማ ልጅ ሳለ አብርሃም ከተፈጥሮ ስሜቱ ጋር የሚጋጭ ፈተና አጋጠመው፤ ይኸውም አምላክ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ጠየቀው። ይሁን እንጂ ታሪኩ በይስሐቅ ሞት አልተደመደመም። ወሳኝ የሆነው ሰዓት በደረሰ ጊዜ አምላክ መልአክ በመላክ ጣልቃ ገባ። በዘፍጥረት 22:1-18 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አምላክ ለእኛ ያለውን ታላቅ ፍቅር በትንሹ የሚያሳይ ትንቢታዊ ጥላ ነበር።
ዘፍጥረት 22:1 “እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው” ይላል። አብርሃም የእምነት ሰው ነበር፤ ሆኖም ከዚህ በፊት አጋጥሞት በማያውቅ ሁኔታ እምነቱ ሊፈተን ነው። አምላክ “የምትወደውን አንዱን ልጅህን፣ ይስሐቅን ይዘህ . . . እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው። (ቁጥር 2) አምላክ አገልጋዮቹ ከአቅማቸው በላይ እንዲፈተኑ እንደማይፈቅድ አስታውስ። በመሆኑም ይህ ፈተና አምላክ በአብርሃም ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳለው ያሳያል።—1 ቆሮንቶስ 10:13
አብርሃም የታዘዘውን ለማድረግ ምንም ጊዜ አላጠፋም። ታሪኩ እንዲህ ይላል፦ “በማግስቱ ጠዋት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይስሐቅን ይዞ፣ ለመሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጕዞውን ጀመረ።” (ቁጥር 3) አብርሃም የቀረበለትን ፈተና በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማንም እንዳልተናገረ ግልጽ ነው።
ከዚህ በኋላ የሦስት ቀን ጉዞ አደረጉ፤ በዚህ ወቅት አብርሃም በጉዳዩ ላይ በሚገባ ለማሰላሰል ጊዜ አግኝቷል። ሆኖም አብርሃም የነበረው ቁርጥ አቋም አልተዳከመም። የተናገራቸው ቃላት ምን ያህል እምነት እንደነበረው ያሳያሉ። አምላክ የመረጠውን ተራራ በርቀት ሲመለከት አገልጋዮቹን “እናንተ . . . እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው። ይስሐቅ መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበው በግ የት እንደሆነ በጠየቀ ጊዜ አብርሃም “[በጉን] እግዚአብሔር ራሱ ያዘጋጃል” አለው። (ቁጥር 5, 8) አብርሃም ከልጁ ጋር ተመልሶ እንደሚመጣ ተስፋ አድርጎ ነበር። ለምን? ምክንያቱም “አምላክ [ይስሐቅን] ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር።”—ዕብራውያን 11:19
በተራራው ላይ አብርሃም ‘ልጁን ለማረድ ቢላዋውን ሲያነሳ’ አንድ መልአክ እጁን ገታው። ከዚያም አምላክ በልጁ ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርበው ቀንዶቹ በቍጥቋጦ መካከል የተጠላለፉ አንድ በግ አዘጋጀለት። (ቁጥር 10-13) በአምላክ ዓይን ሲታይ ይስሐቅ ቃል በቃል መሥዋዕት ሆኖ የቀረበ ያህል ነበር። (ዕብራውያን 11:17) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር “[አብርሃም] ያሳየው ፈቃደኝነት በአምላክ ዘንድ ድርጊቱን የፈጸመ ያህል ተደርጎ ተቆጥሮለታል” በማለት ገልጸዋል።
ይሖዋ በአብርሃም ላይ እምነት መጣሉ ትክክል እንደነበር ተረጋግጧል። እንዲሁም አብርሃም በይሖዋ ላይ እምነት ማሳደሩ ወሮታ አስገኝቶለታል፤ ምክንያቱም አምላክ ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ያጠናከረ ከመሆኑም ሌላ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘሩ እንደሚባረኩ በመግለጽ ከእሱ ጋር ተጨማሪ ቃል ኪዳን ገብቷል።—ቁጥር 15-18
ይሖዋ፣ አብርሃምን ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ከማቅረብ ያስጣለው ቢሆንም እሱ ግን የራሱን ልጅ መሥዋዕት አድርጎ ከማቅረብ ወደኋላ አላለም። አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ያሳየው ፈቃደኝነት አምላክ አንድያ ልጁ የሆነውን ኢየሱስን ለእኛ ኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበትን ሁኔታ ለማሳየት ጥላ ሆኖ አገልግሏል። (ዮሐንስ 3:16) ክርስቶስ መሥዋዕት ሆኖ መቅረቡ ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ከሁሉ የላቀ ማረጋገጫ ነው። አምላክ ለእኛ ሲል እንዲህ ዓይነት መሥዋዕት ከከፈለ እኛም ‘አምላክን ለማስደሰት ስል ምን ዓይነት መሥዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።