አባት ለሌላቸው ልጆች አባት
ወደ አምላክ ቅረብ
አባት ለሌላቸው ልጆች አባት
“በተቀደሰ መኖሪያው ያለ አምላክ፣ አባት ለሌላቸው ልጆች አባት ነው።” (መዝሙር 68:5 የ1980 ትርጉም) በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ ስለ ይሖዋ አምላክ ልብ የሚነካ ትምህርት ይሰጠናል፤ ይሖዋ እርዳታ ለሚያሻቸው ሰዎች ያስባል። አምላክ ከወላጆቻቸው አንዱን በሞት ላጡ ልጆች እንደሚያስብላቸው ለእስራኤላውያን ከተሰጠው ሕግ በግልጽ መመልከት ይቻላል። ‘አባትና እናት ስለሌለው ልጅ’ * በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበትን በዘፀአት 22:22-24 ላይ ያለውን ሐሳብ እስቲ እንመርምር።
አምላክ “አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ” በማለት አስጠንቅቋል። (ቁጥር 22) ይህ ጥቅስ ሰዎች ወላጆች ለሌሏቸው ልጆች ሰብዓዊነት እንዲያሳዩ የሚጠይቅ ሐሳብ ሳይሆን መለኮታዊ ትእዛዝ ነበር። አባቱን ያጣ ልጅ ከጥቃት የሚጠብቀውና የሚንከባከበው ሰው ስለሌለ ሌሎች ግፍ ሊፈጽሙበት ይችላሉ። ማንም ሰው እንዲህ ባለው ልጅ ላይ በማንኛውም መንገድ “ግፍ” እንዳይፈጽም ሕጉ ይከለክላል። “ግፍ አትዋሉ” የሚለው ሐረግ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ “አታስጨንቁ” እና “አታጉላሉ” ተብሏል። አባት በሌለው ልጅ ላይ በደል መፈጸም በአምላክ ዘንድ በቀላሉ የሚታይ ነገር አልነበረም። አምላክ ይህን ጉዳይ ምን ያህል አክብዶ ይመለከተዋል?
ሕጉ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ።” (ቁጥር 23) የጥንቱ የዕብራይስጥ ቅጂ፣ ቁጥር 22 ላይ “ግፍ አትዋሉ” በማለት በብዙ ቁጥር የሚናገር ሲሆን ቁጥር 23 ላይ ግን “ግፍ ብትውልባቸው” በማለት በነጠላ ቁጥር ተጠቅሟል። ይህም እስራኤላውያን በግለሰብም ሆነ በብሔር ደረጃ ይህንን መለኮታዊ ሕግ የማክበር ኃላፊነት እንደነበረባቸው ያሳያል። እስራኤላውያን አባት የሌላቸውን ልጆች እንዴት እንደሚይዙ ይሖዋ ይመለከት ነበር። እነዚህን ልጆች ይሰማቸው ነበር፤ ለእርዳታ ለሚያሰሙት ጩኸት ምላሽ ለመስጠት ምንጊዜም ዝግጁ ነበር።—መዝሙር 10:14 የ1980 ትርጉም፤ ምሳሌ 23:10, 11
አንድ ሰው አባት የሌለውን ልጅ ቢበድለውና ልጁ ወደ አምላክ ቢጮህስ? አምላክ ምን ይሰማዋል? ይሖዋ “ቍጣዬ ይነሣል፤ በሰይፍም እገድላችኋለሁ” ብሏል። (ቁጥር 24) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ይህ ሐሳብ “ቃል በቃል ሲቀመጥ ‘አፍንጫዬ ይግላል’ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህም በጣም መበሳጨትን የሚያመለክት ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።” ይሖዋ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ፍርድ የመስጠቱን ኃላፊነት በእስራኤል ለነበሩ ሰብዓዊ ዳኞች እንዳልተወው ልብ በል። ራሱን መከላከል በማይችል ልጅ ላይ በደል በሚፈጽም በማንኛውም ሰው ላይ አምላክ ራሱ ይፈርድበታል።—ዘዳግም 10:17, 18
ይሖዋ ዛሬም አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) አንዱንም ይሁን ሁለቱን ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች ከልቡ ይራራል። (ያዕቆብ 1:27) ምንም በማያውቁ ልጆች ላይ ግፍ ወይም ጥቃት ሲፈጸም፣ አባት ለሌላቸው ልጆች አባት የሆነው ይሖዋ የጽድቅ ቁጣ ይቆጣል። ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ልጆችን የሚበድሉ ሰዎች ከይሖዋ “ጽኑ ቍጣ” አያመልጡም። (ሶፎንያስ 2:2) እንደነዚህ ያሉ ክፉ ሰዎች “በሕያው አምላክ እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር” መሆኑን ይማራሉ።—ዕብራውያን 10:31
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.1 ‘አባት የሌለው ልጅ’ የሚለው አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች በአምላክ ቃል ውስጥ 40 ጊዜ ያህል ይገኛል። እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል ወንዶች ልጆችን የሚያመለክት ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለሴት ልጆች እንደማይሠራ አድርገን ማሰብ የለብንም። የሙሴ ሕግ አባት የሌላቸውን ሴት ልጆችም መብት ያስጠብቅ ነበር።—ዘኍልቍ 27:1-8