በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዳግመኛ መወለድ መዳን የሚገኝበት መንገድ ነው?

ዳግመኛ መወለድ መዳን የሚገኝበት መንገድ ነው?

ዳግመኛ መወለድ​—መዳን የሚገኝበት መንገድ ነው?

“ዳግም ተወልደሃል?” ተብለህ ብትጠየቅ ምን መልስ ትሰጣለህ? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሕዝበ ክርስትና አማኞች “እንዴታ!” በማለት ይመልሳሉ። ዳግመኛ መወለድ የሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክትና መዳን የሚገኝበት ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች “አንድ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ . . . ክርስቲያን አይደለም” በማለት እንደጻፈው እንደ ሮበርት ስፕራውል ያሉ የሃይማኖት መሪዎችን አመለካከት ይጋራሉ።

አንተም፣ ዳግመኛ መወለድ መዳን የሚገኝበት መንገድ እንደሆነ ታምናለህ? እንዲህ ብለህ የምታምን ከሆነ ዘመዶችህና ወዳጆችህ ይህን መንገድ እንዲያውቁትና እንዲመላለሱበት ልትረዳቸው እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። እንዲህ ማድረግ እንዲችሉ ግን ዳግመኛ በተወለደና ባልተወለደ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ዳግመኛ መወለድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንዴት ልታስረዳቸው ትችላለህ?

ብዙዎች “ዳግመኛ መወለድ” የሚለው ሐሳብ አንድ ሰው አምላክንና ክርስቶስን ለማገልገል ቃል በመግባቱ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሙት መሆኑ ቀርቶ ሕያው መሆኑን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው ዳግመኛ የተወለደ ሰው የሚባለው “በተለይ ከአንድ ሃይማኖታዊ ክንውን በኋላ [መንፈስ መቀበል ሊሆን ይችላል] የእምነቱን ቃል ኪዳን እንደገና ያደሰ ወይም በአዲስ መልክ ያረጋገጠ ክርስቲያን” ነው።—ሚርያም-ዌብስተርስ ኮሊጂየት ዲክሽነሪ—11ኛ እትም

ይህ መዝገበ ቃላት የሰጠው ፍቺ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደማይስማማ ብታውቅ ትገረም ይሆን? ዳግመኛ ስለመወለድ የአምላክ ቃል የሚሰጠው ትክክለኛ ትምህርት ምን እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ? ስለዚህ ጉዳይ በጥልቀት ማጥናትህ እንደሚጠቅምህ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ዳግመኛ ስለመወለድ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘትህ ሕይወትህንም ሆነ ስለወደፊቱ ጊዜ ያለህን አመለካከት ይነካል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

“ዳግመኛ መወለድ” የሚለው ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው፣ ኢየሱስ ከአንድ የሃይማኖት መሪ ጋር በኢየሩሳሌም ያደረገውን አስገራሚ ውይይት በሚተርከው በ⁠ዮሐንስ 3:1-12 ላይ ብቻ ነው። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በገጽ 4 ላይ ባለው ሣጥን ላይ ማግኘት ትችላለህ። ጥቅሱን ትኩረት ሰጥተህ እንድታነበው እናበረታታሃለን።

በዚህ ዘገባ ላይ ኢየሱስ ‘እንደ አዲስ ከመወለድ’ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ነገሮችን ተናግሯል። * ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ለሚከተሉት አምስት አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ እንድናገኝ ይረዳናል፦

ዳግመኛ መወለድ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ዳግመኛ መወለድ በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ ነው?

ዓላማው ምንድን ነው?

አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው እንዴት ነው?

አንድ ሰው ዳግመኛ መወለዱ ከአምላክ ጋር ባለው ዝምድና ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?

እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች አንድ በአንድ እንመርምር።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ‘እንደ አዲስ መወለድ’ የሚለው ሐረግ በ⁠1 ጴጥሮስ 1:3, 23 ላይ የሚገኝ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ “ዳግመኛ መወለድ” የሚለውን ሐሳብ ለመግለጽ የሚጠቀምበት ሌላው ሐረግ ነው። ሁለቱም አገላለጾች የናኦ ከሚለው የግሪክኛ ግስ የተገኙ ናቸው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ”

“ከፈሪሳውያን ወገን፣ የአይሁድ ገዥ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው በማታ ወደ ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለው፦ ‘ረቢ፣ አንተ ከአምላክ ዘንድ የመጣህ አስተማሪ እንደሆንክ እናውቃለን፤ ምክንያቱም አምላክ ከእሱ ጋር ካልሆነ በቀር አንተ የምትፈጽማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች መፈጸም የሚችል አንድም ሰው የለም።’ ኢየሱስም መልሶ ‘እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ማንም ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የአምላክን መንግሥት ሊያይ አይችልም’ አለው። ኒቆዲሞስም ‘ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግም ወደ እናቱ ማህፀን ገብቶ ሊወለድ አይችልም፤ ይችላል እንዴ?’ አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ ‘እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ማንም ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ ደግሞ መንፈስ ነው። ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ ስላልኩህ አትገረም። ነፋስ ወደፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ሆኖም ከየት እንደሚመጣና ወዴት እንደሚሄድ አታውቅም። ከመንፈስ የተወለደም ሁሉ እንደዚሁ ነው።’ ኒቆዲሞስም መልሶ ‘እነዚህ ነገሮች እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ?’ አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ የእስራኤል አስተማሪ ሆነህ ሳለህ እነዚህን ነገሮች አታውቅም? እውነት እውነት እልሃለሁ፣ እኛ የምናውቀውን እንናገራለን፣ ያየነውንም እንመሠክራለን፤ እናንተ ግን እኛ የምንሰጠውን ምሥክርነት አትቀበሉም። ስለ ምድራዊ ነገሮች ነግሬያችሁ የማታምኑ ከሆነ ስለ ሰማያዊ ነገሮች ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?’”—ዮሐንስ 3:1-12