በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዳግመኛ መወለድ ዓላማው ምንድን ነው?

ዳግመኛ መወለድ ዓላማው ምንድን ነው?

ዳግመኛ መወለድ​—ዓላማው ምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች፣ ዘላለማዊ መዳን ለማግኘት ዳግመኛ መወለድ አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ራሱ አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለድበት ዓላማ ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ማንም ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የአምላክን መንግሥት ሊያይ አይችልም።” (ዮሐንስ 3:3) በመሆኑም፣ አንድ ሰው ዳግመኛ መወለድ የሚያስፈልገው መዳን ለማግኘት ሳይሆን ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት ነው። ይሁንና አንዳንዶች ‘ወደ አምላክ መንግሥት መግባትም ሆነ መዳን ማግኘት ተመሳሳይ ነገር አይደሉም እንዴ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ተመሳሳይ አይደሉም። ልዩነታቸውን ለመገንዘብ በመጀመሪያ ‘የአምላክ መንግሥት’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።

መንግሥት ሲባል እውን የሆነ መስተዳድር ማለት ነው፤ ስለዚህ ‘የአምላክ መንግሥት’ ሲባል ‘የአምላክ መስተዳድር’ ማለት ነው። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነና ከእሱ ጋር አብረው የሚገዙ ሰዎች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ዳንኤል 7:1, 13, 14፤ ማቴዎስ 26:63, 64) ከዚህም በተጨማሪ ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙት ሰዎች “ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ” የተውጣጡ እንደሆኑና “በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው [እንደሚገዙ]” ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 5:9, 10፤ 20:6) የአምላክ ቃል፣ ነገሥታት ሆነው የሚገዙት ‘ከምድር የተዋጁ’ ሰዎች 144,000 እንደሆኑና “ትንሽ መንጋ” ተብለው እንደሚጠሩ ይገልጻል።—ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 14:1, 3

የአምላክ መንግሥት መቀመጫ የት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክን መንግሥት” በሌላ ቦታ ላይ “መንግሥተ ሰማያት” ብሎ የሚጠራው መሆኑ ኢየሱስና አብረውት የሚነግሡት ሰዎች የሚገዙት ከሰማይ እንደሆነ ያሳያል። (ሉቃስ 8:10፤ ማቴዎስ 13:11) ስለዚህ የአምላክ መንግሥት፣ በኢየሱስ ክርስቶስና ከሰው ልጆች በተመረጡት ተባባሪ ገዢዎች የተዋቀረ በሰማይ ያለ መስተዳድር ነው።

ታዲያ ኢየሱስ፣ አንድ ሰው ‘ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት’ ዳግመኛ መወለድ እንዳለበት ሲናገር ምን ማለቱ ነው? አንድ ሰው በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት ዳግመኛ መወለድ እንደሚያስፈልገው መግለጹ ነው። በቀላል አነጋገር፣ ዳግመኛ የመወለድ ዓላማ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በሰማይ ነገሥታት እንዲሆኑ ማዘጋጀት ነው።

ዳግመኛ መወለድ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንዲሁም በአምላክ ምርጫ ላይ የተመካ መሆኑን ተመልክተናል፤ ከዚህም በላይ ዓላማው የተወሰኑ ሰዎችን በሰማይ ነገሥታት እንዲሆኑ ማዘጋጀት መሆኑን አይተናል። ሆኖም አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው እንዴት ነው?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዳግመኛ የመወለድ ዓላማ፣ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በሰማይ ነገሥታት እንዲሆኑ ማዘጋጀት ነው

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ መንግሥት፣ በኢየሱስ ክርስቶስና ከሰው ልጆች በተመረጡት ተባባሪ ገዢዎች የተዋቀረ መስተዳድር ነው