የሰው ልጆች ስላላቸው የወደፊት ተስፋ
ከኢየሱስ ምን እንማራለን?
የሰው ልጆች ስላላቸው የወደፊት ተስፋ
ኢየሱስ በሰማይ ስለሚገኝ ሕይወት ተናግሯል?
አዎን ተናግሯል! ኢየሱስ ራሱ ከሞት ተነስቶ ከአባቱ ጋር ለመኖር ወደ ሰማይ አርጓል። ይሁንና ሞቶ ከመነሳቱ በፊት ለአሥራ አንዱ ታማኝ ሐዋርያቱ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ። . . . የምሄደው ለእናንተ ቦታ ለማዘጋጀት ነው” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:2) ይህን መብት የሚያገኙት ግን ጥቂቶች ናቸው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “አንተ ትንሽ መንጋ፣ አባታችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ ስለፈቀደ አትፍሩ” ባላቸው ጊዜ ይህንን ሐቅ ግልጽ አድርጎታል።—ሉቃስ 12:32
‘የትንሹ መንጋ’ አባላት ወደ ሰማይ ሄደው ምን ያደርጋሉ?
አብ፣ ይህ ትንሽ ቡድን በሰማይ ባለው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር እንዲገዛ ፈቃዱ ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ለሐዋርያው ዮሐንስ ታማኝ የሆኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው እንደሚገዙ’ ገልጾለታል። (ራእይ 1:1፤ 5:9, 10) ይህ እንዴት ያለ የምሥራች ነው! የሰው ልጅ እጅግ ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ መልካም አስተዳደር ነው። በኢየሱስ የሚመራው ይህ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በዳግም ፍጥረት የሰው ልጅ፣ ክብር በተላበሰው ዙፋኑ ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ እኔን የተከተላችሁኝ እናንተም በአሥራ ሁለት ዙፋኖች ላይ [ትቀመጣላችሁ]።” (ማቴዎስ 19:28) ኢየሱስና ተከታዮቹ የሚገዙበት መንግሥት፣ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት በምድር ላይ የነበሩት ፍጹም ሁኔታዎች ‘ዳግም እንዲፈጠሩ’ ወይም እንደገና እንዲታደሱ ያደርጋል።
ኢየሱስ ለተቀረው የሰው ዘር ምን ተስፋ ሰጥቷል?
በሰማይ እንዲኖር ከተፈጠረው ከኢየሱስ በተቃራኒ የሰው ልጆች የተፈጠሩት በምድር ላይ እንዲኖሩ ነው። (መዝሙር 115:16) ኢየሱስ “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ” በማለት የተናገረው ለዚህ ነው። (ዮሐንስ 8:23) ኢየሱስ የሰው ልጆች በምድር ላይ ስለሚያገኙት ተስፋ ተናግሯል። በአንድ ወቅት “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:5) ኢየሱስ ይህን ሲናገር በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የሚከተለውን መዝሙር በተዘዋዋሪ መንገድ እየጠቀሰ ነበር፦ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:11, 29
በመሆኑም የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት ወደ ሰማይ የሚሄዱት ‘የትንሹ መንጋ’ አባላት ብቻ አይደሉም። ኢየሱስ በመላው ዓለም ለሚኖሩት ሌሎች ሰዎች ስለተዘረጋው ተስፋም ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16
አምላክ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ የሚያስወግደው እንዴት ነው?
ኢየሱስ “ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህ ዓለም ገዥ አሁን ወደ ውጭ ይጣላል” በማለት በተናገረበት ጊዜ ለመከራ መንስኤ ከሆኑት ሁለት ነገሮች እንደምንገላገል ገልጿል። (ዮሐንስ 12:31) አንደኛ፣ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የሚያደርጉ ክፉ ሰዎች የጥፋት ፍርድ ይፈረድባቸዋል። ሁለተኛ፣ ሰይጣን ወደ ውጭ የሚጣል ሲሆን ከዚያ ወዲህ የሰው ልጆችን ማሳሳት አይችልም።
ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ ለመማር ብሎም በእነሱ ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር ለማሳየት አጋጣሚ ሳያገኙ ስለሞቱ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ስለኖሩ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ኢየሱስ ከጎኑ ተሰቅሎ ለነበረው ወንጀለኛ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል። (ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ፣ ይህን ሰውም ሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችን ገነት በሆነችው ምድር ላይ ከሞት ሲያስነሳ ይህ ሰው ስለ አምላክ የመማር አጋጣሚ ያገኛል። ከዚያ በኋላ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ከሚያገኙት ገሮችና ጻድቃን መካከል ለመቆጠር ይበቃል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3ንና ምዕራፍ 7ን ተመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.13 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29