ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ኢየሱስን ይቃወሙት የነበሩት ጸሐፍት እነማን ናቸው?
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ከጸሐፍት ጋር የተገናኘው በኢየሩሳሌም ብቻ ሳይሆን በትናንሽ ከተማዎችና መንደሮች ጭምር ነበር። ከኢየሩሳሌም ሌላው ቀርቶ ከፓለስቲና ምድር ውጪ ባሉ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚገኙት ጸሐፍት፣ የበታች ባለሥልጣናትና ሕግን ጠንቅቀው የተማሩ ምናልባትም ጽሑፍ የመገልበጥ ሥራ የሚያከናውኑ ወይም ባሉበት አካባቢ ዳኞች ሆነው የሚያገለግሉ ሳይሆኑ አይቀሩም።—ማርቆስ 2:6፤ 9:14፤ ሉቃስ 5:17-21
በኢየሩሳሌም ውስጥ የሚኖሩት ጸሐፍት ከአይሁድ መንግሥት ጋር ተቀራርበው ይሠሩ ነበር። (ማቴዎስ 16:21) ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እነዚህ ጸሐፍት የነበራቸውን የሥራ ድርሻ በተመለከተ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የፍርድ ነክ ጉዳዮችንም ሆነ የአይሁድን ልማድና ሕግ በማስፈጸም እንዲሁም በሳንሄድሪን ዕለት ዕለት የሚካሄዱትን ሥራዎች በማከናወን ረገድ ካህናቱን ይረዱ የነበሩ ይመስላል።” ታዋቂ የሕጉ አስተማሪዎች እንደመሆናቸው መጠን ከእነዚህ ጸሐፍት መካከል አንዳንዶቹ የሳንሄድሪን ወይም የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አባላት ነበሩ። በተጨማሪም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ጋር ያገለግሉ ነበር።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጸሐፍት አብዛኛውን ጊዜ የተገለጹት የኢየሱስን ትምህርት የሚቃወሙ ሰዎች ተደርገው ነው። ይሁንና አንዳንዶቹ አልተቃወሙትም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ከጸሐፍት አንዱ ኢየሱስን “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” ብሎት ነበር። ኢየሱስ ከጸሐፍት ወገን ለሆነ ለሌላ ሰው “አንተ ከአምላክ መንግሥት የራቅህ አይደለህም” ብሎታል።—ማቴዎስ 8:19፤ ማርቆስ 12:28-34
አንድ ሰው የተቀባ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?
በጥንት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ በአንድ ግለሰብ ራስ ላይ ዘይት ማፍሰስ የአክብሮት ወይም የእንግዳ ተቀባይነት መግለጫ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ ዓላማ የሚጠቀሙት በሽቶ የተቀመመ የወይራ ዘይት ነበር። በተጨማሪም በዘመኑ የነበሩት ዕብራውያን፣ አንድ ሰው በሚሾምበት ወቅት በራሱ ላይ ዘይት በማፍሰስ ይቀቡት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አሮን ሊቀ ካህናት ሆኖ እንዲያገለግል በተሾመበት ወቅት በዘይት ተቀብቷል። (ዘሌዋውያን 8:12) መጽሐፍ ቅዱስ ንጉሥ ዳዊትን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ . . . ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ።”—1 ሳሙኤል 16:13
አንድን ሰው ለመሾም መቀባትን ለማመልከት የገባው የዕብራይስጥ ቃል ማሻክ የሚል ሲሆን መሲሕ የሚል ትርጉም ያለው ማሺያክ የሚለው ቃል የተገኘውም ከዚሁ ቃል ነው። ክሪስቶስ ወይም ክርስቶስ የሚለው ቃል የተገኘው ማሻክ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ካለው ክሪዮ ከሚለው የግሪክኛ ቃል ነው። በመሆኑም አሮንም ሆነ ዳዊት መሲሕ ማለትም የተቀባ ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። ሙሴም ቢሆን አምላክ ወኪሉ ሆኖ እንዲያገለግል ስለሾመው ቅቡዕ ወይም ክርስቶስ ተብሎ ተጠርቷል።—ዕብራውያን 11:24-26
የናዝሬቱን ኢየሱስ ለከፍተኛ ሥልጣን የሾመው አምላክ ነው። ኢየሱስ የተቀባው በዘይት ሳይሆን በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው። (ማቴዎስ 3:16) ኢየሱስ በይሖዋ የተመረጠ ቅቡዕ እንደመሆኑ መጠን መሲሕ ወይም ክርስቶስ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።—ሉቃስ 4:18