ከአምላክ የሚገኝ ሀብት
ከአምላክ የሚገኝ ሀብት
ለአምላክ ታማኝ ከሆንክ ሀብት በመስጠት ይባርክሃል? ምናልባት ይባርክህ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሚባርክህ አንተ የምትጠብቀውን ዓይነት ሀብት በመስጠት ላይሆን ይችላል። የኢየሱስ እናት የሆነችውን ማርያምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መልአኩ ገብርኤል በተገለጠላት ጊዜ በአምላክ ዘንድ ‘እጅግ የተወደደች’ እንደሆነችና የአምላክን ልጅ እንደምትወልድ ነግሯታል። (ሉቃስ 1:28, 30-32) ያም ሆኖ ማርያም ሀብታም አልነበረችም። ኢየሱስን ከወለደች በኋላ መሥዋዕት አድርጋ ያቀረበችው “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች” ነበር፤ በዚያን ጊዜ እንዲህ ያለ መሥዋዕት የሚያቀርቡት ድሆች ነበሩ።—ሉቃስ 2:24፤ ዘሌዋውያን 12:8
ማርያም ድሃ መሆኗ አምላክ እንዳልባረካት የሚያሳይ ነው? በፍጹም! ከዚህ በተቃራኒ ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በሄደች ጊዜ ‘ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋንም ከፍ አድርጋ “አንቺ [ማርያም] ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማህፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው!” አለቻት።’ (ሉቃስ 1:41, 42) ማርያም፣ የአምላክን ተወዳጅ ልጅ ወልዳ የማሳደግ መብት አግኝታለች።
ኢየሱስም ቢሆን ሀብታም አልነበረም። ኢየሱስ በድሃ ቤተሰብ ውስጥ ተወልዶ ማደግ ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ በኖረበት ዘመን ሁሉ ድሃ ነበር። የእሱ ደቀ መዝሙር ለመሆን ይፈልግ ለነበረ አንድ ሰው እንዲህ ብሎታል፦ “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም መስፈሪያ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም።” (ሉቃስ 9:57, 58) ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መጥቶ ያደረገው ነገር ደቀ መዛሙርቱ ከፍተኛ ሀብት እንዲኖራቸው አስችሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በእሱ ድህነት እናንተ ባለጸጋ ትሆኑ ዘንድ እሱ ባለጸጋ ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድሃ ሆኗል” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 8:9) ኢየሱስ በዚያን ዘመን ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ምን ዓይነት ሀብት ነበር? በዛሬው ጊዜስ?
ምን ዓይነት ሀብት?
ሀብታም ሰው በአምላክ ከመታመን ይልቅ በገንዘቡ ሊተማመን ስለሚችል ቁሳዊ ሀብት አብዛኛውን ጊዜ ለእምነት እንቅፋት ይሆናል። ኢየሱስ “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል!” በማለት ተናግሯል። (ማርቆስ ) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸው ቁሳዊ ሀብት አይደለም። 10:23
እንዲያውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ድሆች ነበሩ። ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ምጽዋት እየጠየቀ በነበረበት ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ ብሎታል፦ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፦ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነስና ተራመድ!”—የሐዋርያት ሥራ 3:6
በተጨማሪም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የተናገረው ሐሳብ አብዛኞቹ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ድሆች እንደነበሩ ይጠቁማል። እንዲህ ብሏል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ስሙ። አምላክ በእምነት ባለጸጋ እንዲሆኑና እሱን ለሚወዱ ቃል የገባውን መንግሥት እንዲወርሱ ከዓለም አንጻር ድሆች የሆኑትን አልመረጠም?” (ያዕቆብ 2:5) ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንዲሆኑ ከተጠሩት መካከል አብዛኞቹ “በሰብዓዊ አመለካከት ጥበበኞች” ወይም “ኃያላን” አሊያም “ከትልቅ ቤተሰብ የተወለዱ” እንዳልሆኑ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 1:26
ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸው ሀብት ቁሳዊ አይደለም ከተባለ ታዲያ የሰጣቸው ምን ዓይነት ሀብት ነው? ኢየሱስ ለሰምርኔስ ጉባኤ በላከው ደብዳቤ ላይ “መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፤ ይሁንና ሀብታም ነህ” ብሎት ነበር። (ራእይ 2:8, 9) በሰምርኔስ የሚገኙ ክርስቲያኖች ድሆች ቢሆኑም እንኳ ከብርና ከወርቅ እጅግ የላቀ ሀብት ነበራቸው። ሀብታም እንዲሆኑ ያደረጋቸው በአምላክ ላይ ያላቸው እምነትና ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸው ነው። እምነት “ሁሉም ሰው የሚኖረው ነገር ስላልሆነ” ውድ የሆነ ሀብት ነው። (2 ተሰሎንቄ 3:2) እምነት የሌላቸው ሰዎች በአምላክ ዓይን ድሆች ናቸው።—ራእይ 3:17, 18
እምነት የሚያስገኘው ሀብት
ታዲያ እምነት ውድ ሀብት ሊሆን የሚችለው በምን መንገዶች ነው? በአምላክ ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ‘ከደግነቱ፣ ከቻይነቱና ከትዕግሥቱ’ ተጠቃሚዎች ሮም 2:4) በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላላቸው ‘ለበደላቸው ይቅርታ ያገኛሉ።’ (ኤፌሶን 1:7) ከዚህም በላይ እነዚህ ግለሰቦች፣ እምነት ያላቸው ሰዎች ‘ከክርስቶስ ቃል’ የሚያገኙት ዓይነት ጥበብ ይኖራቸዋል። (ቆላስይስ 3:16) እነዚህ ሰዎች በእምነት ወደ አምላክ ሲጸልዩ ልባቸውንና አእምሯቸውን የሚጠብቅላቸውን እንዲሁም ደስታና እርካታ የሚያስገኝላቸውን ‘ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ ያገኛሉ።—ፊልጵስዩስ 4:7
ይሆናሉ። (ከእነዚህ ሁሉ ጥቅሞች ባሻገር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ በሰዎች ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ነው፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:16) አንድ ሰው ስለ አብና ስለ ወልድ ትክክለኛ እውቀት ሲቀስም ይህ የወደፊት ተስፋ ይበልጥ እውን ይሆንለታል። ምክንያቱም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።”—ዮሐንስ 17:3
የአምላክ በረከቶች በዋነኝነት የሚያስገኙት መንፈሳዊ ጥቅም ቢሆንም ስሜታዊና አካላዊ ጥቅምም ያስገኛሉ። እስቲ በብራዚል የሚኖረውን ዳሊድዮን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ዳሊድዮ ስለ አምላክ ዓላማ የሚናገረውን ትክክለኛ እውቀት ከመማሩ በፊት የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ ነበር። ይህ ደግሞ ከቤተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት አበላሽቶበት ነበር። በተጨማሪም ሁሌ ገንዘብ እንደተቸገረ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከጀመረ በኋላ ግን በሕይወቱ ውስጥ አስደናቂ ለውጥ አደረገ።
ዳሊድዮ ያገኘው አዲስ እውቀት ከጎጂ ልማዶች እንዲላቀቅ አስችሎታል። ከፍተኛ መንፈሳዊ እድገት ካደረገ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ከዚህ ቀደም ከቡና ቤት ወደ ቡና ቤት እሄድ ነበር፤ አሁን ግን የምሄደው ከቤት ወደ ቤት ነው።” በአሁኑ ጊዜ ዳሊድዮ የአምላክ ቃል የሙሉ ጊዜ አስተማሪ ሆኗል። ያደረገው ለውጥ ጤንነቱን ያሻሻለለት ከመሆኑም በላይ የተሻለ የገንዘብ አቅም እንዲኖረው አስችሎታል። ዳሊድዮ “በፊት በመጠጥ አጠፋ የነበረውን ገንዘብ አሁን የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ወይም የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ለመግዛት እጠቀምበታለሁ” ብሏል። ከዚህም በተጨማሪ እንደ እሱ መንፈሳዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር መቀራረቡ በርካታ እውነተኛ ጓደኞችን እንዲያፈራ አስችሎታል። ዳሊድዮ በአሁኑ ወቅት ስለ አምላክ ከመማሩ በፊት ይኖረኛል ብሎ አስቦት የማያውቀውን የአእምሮ ሰላምና እርካታ አግኝቷል።
በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት በማሳደሩ ምክንያት አርኪ ሕይወት መምራት የቻለው ሌላው ሰው ደግሞ ሬናቶ ነው። በአሁኑ ጊዜ በፊቱ ላይ የሚነበበውን ደስታ ለተመለከተ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ከፍተኛ በደል ተፈጽሞበታል ብሎ ማመን ይከብዳል። የሬናቶ እናት እሱን የጣለችው ገና አራስ እያለ ነበር። በቦርሳ ተደርጎ አግዳሚ ወንበር ሥር ተጥሎ በተገኘበት ወቅት ሰውነቱ ክፉኛ ተቦጫጭሮና በልዞ የነበረ ከመሆኑም በላይ እትብቱ እንኳ አልተቆረጠም ነበር። ሁለት ሴቶች በዚያ ሲያልፉ አግዳሚው ሥር ያለው ቦርሳ ሲንቀሳቀስ ተመለከቱ። መጀመሪያ ላይ አንድ ሰው የድመት ግልገል ረስቶ የሄደ መስሏቸው ነበር። ሴቶቹ ቦርሳው ውስጥ ያለው ነገር አራስ ልጅ መሆኑን ሲረዱ ሕክምና እንዲያገኝ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል በፍጥነት ይዘውት ሄዱ።
ከእነዚህ ሁለት ሴቶች አንዷ የይሖዋ ምሥክር ነበረች። ይህች ሴት ሪታ ለምትባል ለሌላ የይሖዋ ምሥክር ስለ ሕፃኑ ነገረቻት። ሪታ አንዲት ሴት ልጅ ብቻ ያለቻት ሲሆን በተደጋጋሚ ጊዜ ለመውለድ ብትሞክርም ሽሉ በማሕፀኗ ውስጥ እንዳለ ይሞትባት ነበር።
ሪታ ወንድ ልጅ እንዲኖራት በጣም ትፈልግ ስለነበር ሬናቶን ለማሳደግ ወሰነች።ሪታ፣ ሬናቶ ገና ልጅ እያለ ወላጅ እናቱ እሷ እንዳልሆነች ነገረችው። ያም ሆኖ ፍቅራዊ እንክብካቤ ታደርግለት የነበረ ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በልቡ ለመትከል ከፍተኛ ጥረት ታደርግ ነበር። እያደገ ሲሄድ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጉጉት ማሳየት ጀመረ። በተጨማሪም በሚገርም ሁኔታ ሕይወቱ በመትረፉ አመስጋኝ ነው። ሬናቶ መዝሙራዊው ዳዊት “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ባነበበ ቁጥር ዓይኖቹ እንባ ያቀራሉ።—መዝሙር 27:10
ሬናቶ፣ ይሖዋ ላደረገለት ነገር ሁሉ አድናቆት እንዳለው ለማሳየት በ2002 የተጠመቀ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነ። እስከ አሁን ድረስ ስለ ወላጅ እናቱና አባቱ የሚያውቀው ነገር የለም፤ ወደፊትም ቢሆን ላያውቅ ይችላል። ይሁን እንጂ ሬናቶ ካገኛቸው ስጦታዎች ሁሉ በጣም ውድ እንደሆነ የሚሰማው አፍቃሪና ተንከባካቢ አባት ስለሆነው ስለ ይሖዋ ማወቅና በእሱ ላይ እምነት ማሳደር መቻሉ ነው።
አንተም ከአምላክ ጋር አስደሳች የሆነ የቅርብ ወዳጅነት ለመመሥረት ትፈልግ ይሆናል፤ እንዲህ ያለው ወዳጅነት አርኪ ሕይወት እንድትመራ ያስችልሃል። ከይሖዋ አምላክና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲህ ያለ ዝምድና ለመመሥረት አጋጣሚ የተከፈተው ሀብታም ድሃ ሳይባል ለሁሉም ሰዎች ነው። ይህ ዝምድና ቁሳዊ ሀብት ላያስገኝ ቢችልም በዓለም ያለ ገንዘብ ሁሉ ቢሰበሰብ ሊገዛው የማይችለው ውስጣዊ ሰላምና እርካታ ያስገኝልናል። በምሳሌ 10:22 ላይ የሚገኙት “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” የሚሉት ቃላት በእርግጥም እውነተኛ ናቸው።
ይሖዋ አምላክ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች አሳቢነት እንደሚያሳይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።” (ኢሳይያስ 48:18) ይሖዋ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌና አስተሳሰብ ይዘው ወደ እሱ የሚቀርቡ ሰዎችን አብዝቶ እንደሚባርክም እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል፦ “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል።”—ምሳሌ 22:4
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በአምላክ ላይ እምነት ካለን ሰላም እርካታና ደስታ እናገኛለን
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ወላጆች በቁሳዊ ረገድ ድሆች የነበሩ ቢሆንም የአምላክ በረከት አልተለያቸውም