መንፈስ ቅዱስ—ለሕይወትህ አስፈላጊ የሆነ ኃይል
መንፈስ ቅዱስ—ለሕይወትህ አስፈላጊ የሆነ ኃይል
“ከፊትህ አታርቀኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድ።” (መዝሙር 51:11) ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ያለውን ልባዊ ጸሎት ያቀረበው ከባድ ኃጢአት በሠራ ጊዜ ነበር።
ዳዊት በሕይወት ዘመኑ መንፈስ ቅዱስ ያለውን ኃይል በተደጋጋሚ መመልከት ችሏል። ይህ ኃይል፣ ዳዊት ገና ልጅ ሳለ አስፈሪ ወታደር የነበረውን ጎልያድን ድል እንዲያደርግ ብርታት ሰጥቶታል። (1 ሳሙኤል 17:45-50) ከዚህም በተጨማሪ እስካሁን ካሉት መዝሙራት ሁሉ የሚበልጡ እጅግ ግሩም የሆኑ መዝሙራትን እንዲጽፍ አስችሎታል። ዳዊት “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉ በአንደበቴ ላይ ነበረ” በማለት ተናግሯል።—2 ሳሙኤል 23:2
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መንፈስ ቅዱስ በዳዊት ሕይወት ላይ የተጫወተውን ሚና በተመለከተ ተናግሯል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ያዳምጡት ለነበሩ ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር ‘ይሖዋ ጌታዬን፦ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ብሏል።” (ማርቆስ 12:36፤ መዝሙር 110:1) ኢየሱስ፣ ዳዊት መዝሙሮቹን የጻፈው በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ዳዊትን የረዳው ይኸው መንፈስ እኛንስ ይረዳናል?
“ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል”
እርግጥ ነው፣ መዝሙር ጽፈህ አታውቅ ይሆናል። ይሁንና እንደ ግዙፉ ጎልያድ አስፈሪ የሆኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከፊትህ ተጋርጠውብህ ይሆናል። የኢሳቤልን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። * ባሏ ወጣት ሴት ወዶ ትቷት ሄደ። ከፍተኛ ዕዳ ጥሎባት የሄደ ከመሆኑም ሌላ ትንንሽ ሴቶች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ አያደርግላትም ነበር። ኢሳቤል እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “በዚህ ወቅት እንደተከዳሁና እንደ ቆሻሻ እንደተቆጠርኩ ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር። ያም ሆኖ ባለቤቴ ትቶኝ ከሄደ ጀምሮ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ደግፎ እንዳቆመኝ ይሰማኛል።”
ኢሳቤል ምንም ጥረት ሳታደርግ መንፈስ ቅዱስን አገኛለሁ ብላ ጠብቃ ነበር? በፍጹም፣ አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጣት በየዕለቱ ትለምነው ነበር። የወደፊቱን ጊዜ በማሰብ በፍርሃት እንዳትርድ እንዲሁም ለልጆቿ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግና ለራሷ የነበራትን ጥሩ ግምት መልሳ ማግኘት እንድትችል የአምላክ ኃይል እንደሚያስፈልጋት ታውቅ ነበር። ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ የተናገረውን ሐሳብ ተግባራዊ አድርጋለች፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።”—ማቴዎስ 7:7
ሮቤርቶ የነበረበት ሁኔታ ከኢሳቤል የተለየ ቢሆንም እሱም የአምላክ መንፈስ እንደሚያስፈልገው የተሰማው ጊዜ ነበር። ሮቤርቶ የትንባሆና የሀሺሽ ሱስ ነበረበት። ይህንን ሱስ ለማሸነፍ ሁለት ዓመት ቢታገልም በተደጋጋሚ ጊዜ አገርሽቶበት ነበር። ሮቤርቶ እንዲህ ብሏል፦ “ዕፅ መውሰዳችሁን ስታቆሙ በጭንቀት ትዋጣላችሁ። ሰውነታችሁ በየዕለቱ ዕፁን አምጣ አምጣ ይላችኋል።”
ሮቤርቶ በመቀጠል እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ይሁን እንጂ አምላክን በሚፈልገው መንገድ ማገልገል እንድችል አኗኗሬን ለመለወጥ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር። አእምሮዬን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ አዎንታዊ ሐሳቦች ለመሙላት ጥረት አደርግ ነበር። አምላክ አኗኗሬን ማስተካከል እንድችል ኃይል እንዲሰጠኝ በየቀኑ አጥብቄ እጸልይ ነበር። በራሴ ኃይል ሊሳካልኝ እንደማይችል አውቅ ነበር። ይሖዋ ጸሎቴን በምን መንገድ እንደመለሰልኝ መመልከት ችያለሁ፤ በተለይ ሱሱ አገርሽቶብኝ ተስፋ በምቆርጥበት ጊዜ ይህን ይበልጥ መገንዘብ ችያለሁ። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ኃይሌን እንደሚያድስልኝ አምናለሁ፤ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ባላገኝ ኖሮ መቼም ቢሆን ከሱሴ መላቀቅ አልችልም ነበር።”—ፊልጵስዩስ 4:6-8
“እንደ ንስር በክንፍ” መውጣት
ልክ እንደ ኢሳቤልና ሮቤርቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የመንፈስ ቅዱስን ኃይል በራሳቸው ሕይወት መመልከት ችለዋል። አንተም ፈቃደኛ ከሆንክ ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን ለመፍጠር የተጠቀመበትን ኃይል ይሰጥሃል። መንፈሱን እንዲሰጥህ አምላክን ከልብህ ብትለምነው መንፈስ ቅዱስን ለአንተ ለመስጠት ፈቃደኛ ከመሆኑም በላይ ጉጉትም አለው። ሆኖም ይህን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት ስለ አምላክ የሚናገረውን እውነት መማርና ፈቃዱን ለመፈጸም ልባዊ ፍላጎት ማሳደር ይኖርብናል።—ኢሳይያስ 55:6፤ ዕብራውያን 11:6
በመንፈስ ቅዱስ ስትሞላ አምላክን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማገልገልና በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ዓይነት ችግር ለመቋቋም የሚያስችልህን ብርታት ታገኛለህ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል፦ “[ይሖዋ] ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጕልበት ይጨምራል። . . . እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።”—ኢሳይያስ 40:28-31
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.6 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘አምላክ ኃይል እንዲሰጠኝ በየቀኑ አጥብቄ እጸልይ ነበር። በራሴ ኃይል ሊሳካልኝ እንደማይችል አውቅ ነበር። ይሖዋ ጸሎቴን በምን መንገድ እንደመለሰልኝ መመልከት ችያለሁ’
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በሥራ ላይ ያለው ቅዱስ መንፈስ
አምላክ ምድርንና ጽንፈ ዓለምን ለመፍጠር መንፈስ ቅዱስን ተጠቅሟል። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች። መንፈስህን ስትልክ፣ እነርሱ ይፈጠራሉ።”—መዝሙር 104:24, 30፤ ዘፍጥረት 1:2፤ ኢዮብ 33:4
መንፈስ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ መርቷቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም . . . ይጠቅማል” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ‘በአምላክ መንፈስ መሪነት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በአምላክ እስትንፋስ” የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው። የይሖዋ እስትንፋስ ወይም መንፈስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ‘የአምላክን ቃል’ ማስተላለፍ እንዲችሉ መርቷቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 2:13
መንፈስ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል እንዲተነብዩ አስችሏቸዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው ብሏል፦ “በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያለው ትንቢት ሁሉ ሰው ከራሱ ሐሳብ ያፈለቀው [አይደለም።] . . . ምክንያቱም መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ።”—2 ጴጥሮስ 1:20, 21፤ ኢዩኤል 2:28
መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስና ሌሎች የእምነት ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብኩና ተአምራት እንዲፈጽሙ ረድቷቸዋል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ምሥራች እንዳውጅ ቀብቶኛል፤ ለተማረኩት ነፃነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንድሰብክ፣ የተጨቆኑትን ነፃ እንዳወጣ።”—ሉቃስ 4:18፤ ማቴዎስ 12:28
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
መንፈስ ቅዱስ የሚረዳን በየትኞቹ መንገዶች ነው?
መንፈስ ቅዱስ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች እንድትቋቋምና ጎጂ ልማዶችን እንድታሸንፍ ኃይል ይሰጥሃል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13
መንፈስ ቅዱስ አምላካዊ ባሕርያትን እንድታዳብር ይረዳሃል። “የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው።”—ገላትያ 5:22, 23
መንፈስ ቅዱስ የሚያጋጥሙህን ችግሮች በጽናት እንድትቋቋም ኃይል ይሰጥሃል። “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ።”—ፊልጵስዩስ 4:13