ሰዎች መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ ግራ የሚጋቡት ለምንድን ነው?
ሰዎች መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ ግራ የሚጋቡት ለምንድን ነው?
መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው? ይህ ጥያቄ ቀላል ቢመስልም መልሱን ለማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት አሥራ ስድስተኛ በአውስትራሊያ ተሰብስበው ለነበሩ ሰዎች እንዲህ ብለው ነበር፦ “ስለ መንፈስ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ከአቅማችን በላይ ነው ማለት ይቻላል።”
‘መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ በርካታ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ከሚሰነዘሩት አስተያየቶች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
• በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ውስጥ የሚኖር እውን አካል።
• አምላክ በምድር ላይ የሚገኝበት መንገድ።
• የሥላሴ ሦስተኛው አካል።
ሰዎች እንዲህ ያሉ ግራ የሚያጋቡ ሐሳቦችን የሚሰነዝሩት ለምንድን ነው? አንዳንድ የሃይማኖት ምሑራን፣ መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ ጋር እኩል የሆነ የራሱ አካል አለው ብለው ካስተማሩበት ከአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ግራ እንደተጋቡ ናቸው። ይሁንና ቅዱሳን መጻሕፍትም ሆኑ የጥንቶቹ የክርስቶስ ተከታዮች እንዲህ ያለ ነገር አላስተማሩም። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ብሏል፦ “ብሉይ ኪዳን የአምላክን መንፈስ አካል እንዳለው አድርጎ አይገልጸውም፤ . . . የአምላክ መንፈስ የአምላክ ኃይል ነው።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ጥቅሶች የአምላክን መንፈስ የሚገልጹት የተወሰነ አካል እንደሆነ ሳይሆን ረቂቅ ነገር እንደሆነ አድርገው ነው። መንፈስና የአምላክ ኃይል ተመሳሳይ እንደሆኑ ተደርጎ መገለጹ ይህንን ያስረዳል።”
ሰዎች፣ ኃይልን አካል እንደሆነ አድርገው ማሰብ የሚከብዳቸው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። በመሆኑም በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው አብዛኞቹ ሰዎች፣ መንፈስ ቅዱስ አካል ወይም “ሕልውና” እንዳለው አድርገው አይቀበሉም። ትክክል የሆነው የእነዚህ ሰዎች አመለካከት ነው? ወይስ “መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የተለየ ራሱን የቻለ አካል ነው” የሚል ግትር አመለካከት ያላቸውን የሃይማኖት ምሑራን ትምህርት ማመን ይኖርብናል?
አስተማማኝ መልስ ለማግኘት ስለ መንፈስ ቅዱስ በጥልቀት የሚያብራራውንና የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ቅዱስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እርሱ እውነትን ለማስተማር፥ የተሳሳቱትን ለመገሠጽ . . . ይጠቅማል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16 የ1980 ትርጉም
ስለ መንፈስ ቅዱስ እውነታውን ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? እውነቱን ማወቅህ ከአምላክ እርዳታ ለማግኘት የሚያስችልህን መንገድ ሊከፍትልህ ስለሚችል ነው። አንዳንድ ጊዜ በራስህ ኃይል መጽናት እንደማትችል ሆኖ ይሰማሃል? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶላቸዋል፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ . . . እናንተ . . . ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!”—ሉቃስ 11:9, 13
በሚቀጥሉት ርዕሰ ትምህርቶች ላይ መንፈስ ቅዱስ ምን እንደሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን ማብራሪያ እንመለከታለን። እንዲሁም ይህ ኃይል በሕይወታችን ውስጥ ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ቅዱሳን መጻሕፍት መንፈስ ቅዱስ ምን እንደሆነ ይነግሩናል