ዕብራይስጥ እና ግሪክኛ መማር ያስፈልግሃል?
ዕብራይስጥ እና ግሪክኛ መማር ያስፈልግሃል?
አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መጀመሪያ የተጻፈው በሁለት ቋንቋዎች ይኸውም በዕብራይስጥና በግሪክኛ ነበር። * ጸሐፊዎቹ በእነዚህ ቋንቋዎች ተጠቅመው መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መሪነት ነው። (2 ሳሙኤል 23:2) በመሆኑም ያሰፈሩት መልእክት “በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ” ነው ሊባል ይችላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡት አብዛኞቹ ሰዎች የዕብራይስጥን ወይም የግሪክኛን ቋንቋ አይችሉም። በመሆኑም ወደ ራሳቸው ቋንቋ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም ይኖርባቸዋል። አንተም እንዲህ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሶች የተተረጎሙት በመንፈስ መሪነት ባለመሆኑ እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል፦ ‘የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበብኩ መልእክቱን ሙሉ በሙሉ መረዳት እችላለሁ? ወይስ ዕብራይስጥና ግሪክኛ መማር ይኖርብኛል?’
ልብ ሊባሉ የሚገቡ ነጥቦች
ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ልብ ልትላቸው የሚገቡ የተለያዩ ነጥቦች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የጥንቱን የዕብራይስጥ ወይም የግሪክኛ ቋንቋ ማወቅ በራሱ አንድን ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የመረዳት ተአምራዊ ችሎታ እንዲኖረው ያደርገዋል ማለት አይደለም። ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት አይሁዳውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እናንተ በቅዱሳን መጻሕፍት የዘላለም ሕይወት የምታገኙ ስለሚመስላችሁ እነሱን ትመረምራላችሁ፤ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሠክሩ ናቸው። ሆኖም ሕይወት እንድታገኙ ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም።” (ዮሐንስ 5:39, 40) እነዚህ ሰዎች ችግራቸው ምን ነበር? ዕብራይስጥን መረዳት ተስኗቸው ነበር? አልነበረም፣ ቋንቋውን ጠንቅቀው ያውቁት ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ “እናንተ የአምላክ ፍቅር በውስጣችሁ እንደሌለ በሚገባ አውቃለሁ” ብሏቸው ነበር።—ዮሐንስ 5:42
በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ የቆሮንቶስ ከተማ ይኖሩ የነበሩትን ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አይሁዳውያን ተአምራዊ ምልክቶች ማየት ይፈልጋሉ፤ ግሪካውያን ደግሞ ጥበብን ይሻሉ፤ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁዳውያን መሰናክል ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው።” (1 ቆሮንቶስ 1:22, 23) በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መልእክት ለመቀበል ቁልፉ ዕብራይስጥ ወይም ግሪክኛ መናገር መቻል አልነበረም።
ሁለተኛ፣ በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ዘመናዊውን ዕብራይስጥ ወይም ግሪክኛ መናገር ቢችሉም እነዚህ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸው የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቋንቋዎች በጣም የተለዩ ናቸው። በዛሬው ጊዜ ግሪክኛ ተናጋሪ በሐዋርያት ሥራ 7:20 ላይ “ውብ” እንዲሁም በዕብራውያን 11:23 ላይ “መልከ መልካም” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በዘመናችን ባለው ግሪክኛ “የሚያስቅ” የሚል ፍቺ አለው። በተጨማሪም በቋንቋው የሰዋስው ሕግም ሆነ ዓረፍተ ነገሮች በሚዋቀሩበት መንገድ ላይ ብዙ ለውጥ ተደርጓል።
የሆኑ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን ግሪክኛ በትክክል መረዳት ያስቸግራቸዋል። ይህ የሆነው በቀድሞዎቹ ቃላት ምትክ አዳዲስ ቃላት በመጨመራቸው እንዲሁም በጥንቱ ግሪክኛ ውስጥ የነበሩ በርካታ ቃላት ትርጉማቸው በመቀየሩ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ዘመናዊውን የዕብራይስጥ ወይም የግሪክኛ ቋንቋ መማርህ መጽሐፍ ቅዱስን መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ይበልጥ በትክክል እንድትረዳ ያስችልሃል ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ወቅት ሰዎች እነዚህን ቋንቋዎች እንዴት ይጠቀሙባቸው እንደነበር ለመረዳት መዝገበ ቃላቶችንና የሰዋስው መጻሕፍትን መመልከት ያስፈልግሃል።
ሦስተኛው ነጥብ ደግሞ አዲስ ቋንቋ መማር በጣም አስቸጋሪ ሊሆን መቻሉ ነው። በሌላ ቋንቋ የተወሰኑ ሐረጎችን መማር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ መጀመሪያ ላይ ቀላል ሊሆን ቢችልም ቃላት የሚኖራቸውን በቀላሉ የማይታይ የትርጉም ልዩነት እንዲሁም የሚያስተላልፉትን የተለያየ መልእክት ለመረዳት ለዓመታት ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ይጠይቅብህ ይሆናል። ይህን በምታደርግበት ጊዜ ‘ቁንጽል እውቀት አደገኛ ነው’ የሚለውን የቆየ አባባል እውነተኝነት በሕይወትህ ትመለከት ይሆናል። እንዴት?
የቃሉ ትርጉም ምንድን ነው?
የአንተን ቋንቋ የሚማር ሰው የአንድን ቃል ትርጉም ጠይቆህ ያውቃል? ከሆነ መልስ መስጠት ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን ተገንዝበህ ይሆናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንድ ቃል የተለያየ ትርጉም ሊኖረው ስለሚችል ነው። ግለሰቡ፣ ቃሉን በዓረፍተ ነገር ውስጥ አስገብቶ ምሳሌ እንዲሰጥህ ጠይቀኸው ይሆናል። ቃሉ እንዴት እንደተሠራበት ካላወቅህ የትኛውን ፍቺ መናገር እንዳለብህ መወሰን ያስቸግርህ ይሆናል። ለአብነት ያህል፣ “ተኮሰ” የሚለው የአማርኛ ቃል ምን ትርጉም እንዳለው ተጠየቅህ እንበል። ይህ ቃል በተለያየ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ሲገባ የተለያየ ፍቺ ሊኖረው ይችላል። አቃጠለ ወይም ለበለበ፣ ፀጉርን አስዋበ ወይም በካውያ ልብስን ዳመጠ የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። በሌላ አገባቡ ደግሞ በመሣሪያ ጥይትን ወይም ሮኬትን አስፈነጠረ አሊያም የግንብ ድንጋዮችን መገጣጠሚያ በሲሚንቶ እየመረገ ዳመጠ የሚል ትርጉም አለው። ቃሉ፣ የሰውነት ሙቀት መጨመርን ወይም ብረት አግሎ ገላን መጥበስን ለማመልከት ሊሠራበት ይችላል። “ተኮሰ” የሚለው ቃል በዘይቤያዊ አነጋገር መቆጣትንም ሊያመለክት ይችላል። ከእነዚህ ሁሉ ትክክለኛው ትርጉም የትኛው ነው?
መዝገበ ቃላት አንድ ቃል ሊኖሩት የሚችሉትን ትርጉሞች በሙሉ ይሰጥህ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንድ መዝገበ ቃላት ብዙ ጊዜ ከሚሠራበት የቃሉ ትርጉም ጀምረው ቃሉ ያሉትን ፍቺዎች በሙሉ በቅደም ተከተል ይዘረዝራሉ። የምትፈልገው ፍቺ የትኛው እንደሆነ ለይተህ ለማወቅ የሚያስችልህ፣ ቃሉ በዓረፍተ ነገር ውስጥ የገባበት መንገድ ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት ስለ ሕክምና የተወሰነ እውቀት አለህ እንበል፤ በአንተ ላይ የሚታዩት የሕመም ምልክቶች መንስኤያቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈለግህ። ይህን ለማድረግ የሕክምና መዝገበ ቃላት መጠቀም ትችላለህ። መዝገበ ቃላቱን በመመልከት በአንተ ላይ የሚታዩት የሕመም ምልክቶች 90 በመቶ የሚጠቁሙት አንድ ዓይነት በሽታ እንዳለብህ መሆኑን ትገነዘብ ይሆናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ምልክቶች 10 በመቶ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ በሽታ እንዳለብህ የሚጠቁሙ መሆናቸውን ከመዝገበ ቃላቱ ትረዳ ይሆናል። በሽታህ ምን እንደሆነ በትክክል ለማወቅ እንድትችል ስለ ሕክምና የበለጠ ማወቅ ይኖርብሃል። በተመሳሳይም አንድ ቃል 90 በመቶ የሚያመለክተው አንድን ፍቺ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና በምታነበው አስፈላጊ ጽሑፍ ላይ የገባው የቃሉ ሌላ ትርጉም ከሆነ ቃሉ 90 በመቶ የሚያመለክተውን ፍቺ ማወቅህ ምንም ፋይዳ የለውም። የቃሉን ትርጉም ለመረዳት በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ የገባበትን መንገድ ማወቅ ያስፈልግሃል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ቃላት ከማጥናት ጋር በተያያዘም እነዚህ ቃላት በዓረፍተ ነገር ውስጥ እንዴት እንደተሠራባቸው ማወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኛውን ጊዜ “መንፈስ” ተብለው የሚተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት እንደየአገባባቸው የተለያየ ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ “ነፋስ” ተብለው ቢተረጎሙ ትክክል ሊሆን ይችላል። (ዘፀአት 10:13፤ ዮሐንስ 3:8) በሌላ ቦታ ደግሞ በሁሉም ሕያዋን ፍጥረታት ይኸውም በሰዎችም ሆነ በእንስሳት ውስጥ የሚገኘውን ሕይወትን የሚያቆይ ኃይል ያመለክታሉ። (ዘፍጥረት 7:22፤ መዝሙር 104:29፤ ) በዓይን የማይታዩት በሰማይ የሚገኙ ፍጥረታትም መናፍስት ተብለዋል። ( ያዕቆብ 2:261 ነገሥት 22:21, 22፤ ማቴዎስ 8:16) በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል ደግሞ የእሱ ቅዱስ መንፈስ ይባላል። (ዘፍጥረት 1:2፤ ማቴዎስ 12:28) ይኸው ቃል አንድ ግለሰብ አንድን ዓይነት ዝንባሌ፣ ባሕርይ ወይም ስሜት እንዲያንጸባርቅ ያደረገውን ኃይል እንዲሁም በአንድ የሰዎች ቡድን ላይ ጎልቶ የሚታይን ዝንባሌ ለማመልከትም ይሠራበታል።—ኢያሱ 2:11 NW፤ ገላትያ 6:18
አንድ የዕብራይስጥ ወይም የግሪክኛ መዝገበ ቃላት እነዚህን የተለያዩ ትርጉሞች ሊዘረዝር ቢችልም የምትፈልገውን ፍቺ ለማወቅ የሚረዳህ ቃሉ በዓረፍተ ነገር ውስጥ የገባበት መንገድ ነው። * የምታነበው መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራይስጥና በግሪክኛ የተጻፈም ይሁን በአንተ ቋንቋ የተተረጎመ፣ አንድን ቃል ለመረዳት ቃሉ እንዴት እንደተሠራበት ማወቅ ያስፈልግሃል።
የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶችን መጠቀም ስህተት ነው?
አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን ዕብራይስጥ ወይም ግሪክኛ አሊያም ሁለቱንም ቋንቋዎች ለመማር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። እነዚህ ሰዎች መልእክቱን ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማይችሉ ቢገነዘቡም መጽሐፍ ቅዱስን መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ማንበብ መቻላቸው ያስደስታቸዋል፤ ያደረጉት ጥረት ሁሉ የሚክስ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች መረዳት ባትችል ተስፋ ቆርጠህ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መፈለግህን ልታቆም ይገባል? በፍጹም! እንዲህ የምንልባቸውን ምክንያቶች እንመልከት።
በመጀመሪያ፣ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶችን መጠቀም ስህተት አይደለም። እንዲያውም በተለምዶ አዲስ ኪዳን የሚባሉትን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የጻፉት ሰዎች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲጠቅሱ አብዛኛው ጊዜ የተጠቀሙት ወደ ግሪክኛ ከተተረጎመው ቅጂ ነበር። * (መዝሙር 40:6፤ ዕብራውያን 10:5, 6) እነዚህ ሰዎች ዕብራይስጥ መናገር እንዲሁም በዕብራይስጥ ከተጻፉት ከመጀመሪያዎቹ ቅዱሳን መጻሕፍት መጥቀስ ቢችሉም መልእክቱ የተጻፈላቸው ሰዎች በቀላሉ ሊያገኙት በሚችሉት ትርጉም መጠቀምን ይበልጥ አመቺ ሆኖ እንዳገኙት ግልጽ ነው።—ዘፍጥረት 12:3፤ ገላትያ 3:8
ሁለተኛ፣ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች መረዳት ቢችልም ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ የሚያነበው በትርጉም እንጂ መጀመሪያ በተናገረበት ቋንቋ አይደለም። ይህ የሆነበት ምክንያት የወንጌል ጸሐፊዎች፣ ኢየሱስ በወቅቱ በነበረው የዕብራይስጥ ቋንቋ የተናገረውን ሐሳብ የጻፉት በግሪክኛ በመሆኑ ነው። * የጥንቶቹ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የጻፏቸውን መጻሕፍት እነሱ በተጠቀሙበት ቋንቋ ማንበብ መቻል የተለየ ጥበብ ያስገኛል ብሎ የሚያስብ ሰው ካለ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ የምናገኘው በትርጉም ብቻ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ያለው አመለካከት ምን አንድምታ እንዳለው ማጤን ይኖርበታል። ከሁሉ የሚበልጠው የይሖዋ አገልጋይ የተናገረው ሐሳብ በጽሑፍ የተላለፈው እሱ በተጠቀመበት ቋንቋ ሳይሆን በወቅቱ አብዛኛው ሕዝብ በሚገባው ቋንቋ ተተርጉሞ ነው፤ ይሖዋ የአገልጋዩን ሐሳብ ሰዎች በመንፈስ ተመርተው በዚህ መልክ እንዲጽፉት ማድረጉ መጽሐፍ ቅዱስን የምናነብበት ቋንቋ ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ ይጠቁማል። ዋናው ቁም ነገር በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በምናነብበት ጊዜ መልእክቱን በሚገባን ቋንቋ ማንበባችንና ለተግባር መነሳሳታችን ነው።
ሦስተኛ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው “ምሥራች” ‘ከብሔር፣ ከነገድ፣ ከቋንቋና ከሕዝብ ሁሉ’ ለተውጣጡ ትሑት ሰዎች መሰበክ ይኖርበታል። (ራእይ 14:6፤ ሉቃስ 10:21፤ 1 ቆሮንቶስ 1:27-29) በዚህ መሠረት፣ በዛሬው ጊዜ የሚገኙት አብዛኞቹ ሰዎች ሌላ ቋንቋ መማር ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው ቋንቋ ከተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ዓላማ መማር ችለዋል። በብዙ ቋንቋዎች የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ፤ ይህ ደግሞ አንባቢዎች የፈለጉትን እንዲመርጡ አጋጣሚውን ይሰጣቸዋል። *
ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን እውነት በትክክል መረዳትህን እንዴት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ? የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ጥቅስ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ግምት ውስጥ በማስገባት መጽሐፍ ቅዱስን በርዕሰ ጉዳይ ከፋፍሎ ማጥናት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መልእክት ለመረዳት እንደሚያስችል ተገንዝበዋል። ለአብነት ያህል፣ አንድን ርዕስ ከመረጡ በኋላ (ለምሳሌ “ጋብቻ”) ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥቅሶች ይመለከታሉ። በዚህ መንገድ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመረዳት በሌላኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ሐሳቡ እንዴት እንደተብራራ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉንም ሰው በግለሰብ ደረጃ በነፃ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራሉ፤ አንተስ ለምን በዚህ ዝግጅት አትጠቀምም? የሰዎች ቋንቋ ምንም ይሁን ምን፣ የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 2:4፤ ራእይ 7:9
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.2 የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተጻፉት መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈበት ዕብራይስጥ ጋር በጣም በሚቀራረበው በአረማይክ ቋንቋ ነበር። ዕዝራ 4:8 እስከ 6:18ን እንዲሁም ዕዝራ 7:12-26ን፤ ኤርምያስ 10:11ን እና ዳንኤል 2:4ለ እስከ 7:28ን እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል።
^ አን.14 እዚህ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባው ነጥብ አንዳንድ መዝገበ ቃላትና የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የአንድን ቃል ቀጥተኛ ፍቺ ከማስቀመጥ ይልቅ ቃሉ በአንድ መጽሐፍ ቅዱስ (ለምሳሌ ኪንግ ጄምስ ቨርሽን በተባለው ትርጉም ውስጥ) እንዴት እንደተተረጎመ የሚዘረዝሩ መሆኑ ነው።
^ አን.17 ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ በነበሩበት ዘመን ሁሉም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በግሪክኛ ተተርጉመው ነበር። ይህ ትርጉም ሰብዓ ሊቃናት የሚባል ሲሆን ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን በስፋት ይጠቀሙበት ነበር። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙትና ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ ከተወሰዱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቅሶች አብዛኞቹ ከሰብዓ ሊቃናት ትርጉም የተወሰዱ ናቸው።
^ አን.18 ሐዋርያው ማቴዎስ ወንጌሉን መጀመሪያ ላይ የጻፈው በዕብራይስጥ እንደሆነ ይታመናል። ይህ እውነት ቢሆንም እንኳ እስከ ዘመናችን ድረስ ሳይጠፋ የቆየው፣ ከመጀመሪያው መጽሐፍ ወደ ግሪክኛ የተተረጎመው ቅጂ ሲሆን ተርጓሚውም ማቴዎስ ራሱ ሳይሆን አይቀርም።
^ አን.19 ስለተለያዩ የትርጉም ዓይነቶችና ትክክለኛ ትርጉም መምረጥ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በዚህ መጽሔት የግንቦት 1, 2008 እትም ላይ የወጣውን “ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም
ኢየሱስና ሐዋርያቱ በነበሩበት ዘመን የኖሩ ግሪክኛ ተናጋሪ አይሁዳውያን የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉምን በስፋት ይጠቀሙ ነበር። የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ተብለው የሚጠሩት ወደ ግሪክኛ የተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ናቸው። የሰብዓ ሊቃናት ትርጉምን አስገራሚ የሚያደርገው ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ ሌላ ቋንቋ ለመተርጎም በተደረገው ጥረት እስከ ዛሬ ከሚታወቁት የመጀመሪያው መሆኑ ብቻ ሳይሆን መጽሐፉን ለመተርጎም በርካታ ሰዎች መሳተፋቸውና ረጅም ጊዜ መፍጀቱ ነው። በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተወሰኑ ተርጓሚዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን ሰብዓ ሊቃናትን ማዘጋጀት የጀመረ ሲሆን የትርጉም ሥራው የተጠናቀቀው ከመቶ ዓመት በኋላ በሌሎች ተርጓሚዎች ነበር።
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ማለትም ክርስቶስ መሆኑን ለማስረዳት በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ጥሩ አድርገው ለመጠቀም ፈጣኖች ነበሩ። እነዚህ ክርስቲያኖች በሰብዓ ሊቃናት በጣም ይጠቀሙ ስለነበር አንዳንዶች መጽሐፉን “የክርስቲያኖች” ትርጉም እንደሆነ አድርገው መመልከት ጀምረው ነበር። ይህ ደግሞ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በአይሁዳውያን ዘንድ የነበረውን ተወዳጅነት እያጣ እንዲሄድና በግሪክኛ በርካታ አዳዲስ ትርጉሞች እንዲዘጋጁ ምክንያት ሆኗል። ከእነዚህ ትርጉሞች መካከል አንዱ በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ይኖር በነበረው ወደ አይሁድ እምነት በተለወጠው በአክዌላ የተዘጋጀው ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ይህ ትርጉም “እጅግ አስገራሚ ገጽታ” እንዳለው ገልጸዋል። በጥንቶቹ የዕብራይስጥ ፊደላት የተቀመጠው ይሖዋ የሚለው መለኮታዊ ስም በአክዌላ የግሪክኛ ትርጉም ውስጥ በብዛት ይገኛል።
[የሥዕል ምንጭ]
Israel Antiquities Authority
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዋናው ቁም ነገር በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በምናነብበት ጊዜ መልእክቱን በሚገባን ቋንቋ ማንበባችንና ለተግባር መነሳሳታችን ነው