በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ የራሳችንን ምርጫ እንድናደርግ ይፈልጋል

ይሖዋ የራሳችንን ምርጫ እንድናደርግ ይፈልጋል

ወደ አምላክ ቅረብ

ይሖዋ የራሳችንን ምርጫ እንድናደርግ ይፈልጋል

ዘዳግም 30:11-20

“ለይሖዋ ታማኝ ሳልሆን እቀር ይሆን የሚል መሠረት የሌለው ፍርሃት ብዙ ጊዜ ያድርብኛል።” ይህን የተናገረችው አንዲት ክርስቲያን ስትሆን በልጅነቷ ያሳለፈቻቸው መጥፎ ገጠመኞች ‘ነገሮች አይሳኩልኝም’ የሚል ድምዳሜ ላይ እንድትደርስ አድርገዋታል። ታዲያ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ትክክል ነው? ሁኔታዎችን ለማስተካከል ምንም ዓይነት ምርጫ የለንም ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ አምላክ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ሕይወታችንን እንዴት እንደምንመራ የራሳችንን ምርጫ ማድረግ እንችላለን። ይሖዋ ትክክለኛ ምርጫ እንድናደርግ ይፈልጋል፤ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይነግረናል። እስቲ በ⁠ዘዳግም ምዕራፍ 30 ላይ የሚገኘውን ሙሴ የተናገረውን ሐሳብ እንመርምር።

አምላክ የሚፈልግብንን ነገር ማወቅና ያወቅነውን በተግባር ማዋል ከባድ ነው? * ሙሴ እንዲህ ብሏል፦ “በዛሬው ዕለት የምሰጥህ ትእዛዝ ይህን ያህል አስቸጋሪ ወይም ከአንተ የራቀች አይደለችም።” (ቁጥር 11) ይሖዋ ልናደርገው የማንችለውን ነገር እንድንፈጽም አይጠይቀንም። መሥፈርቶቹ ምክንያታዊና ልናሟላቸው የምንችላቸው ናቸው። በተጨማሪም እነዚህን መሥፈርቶች ማወቅ ከባድ አይደለም። አምላክ ከእኛ የሚፈልገውን ለማወቅ ‘ወደ ሰማይ መውጣት’ ወይም ‘ባሕር መሻገር’ አያስፈልገንም። (ቁጥር 12, 13) መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን በግልጽ ይነግረናል።—ሚክያስ 6:8

ይሁን እንጂ ይሖዋ እሱን እንድንታዘዘው አያስገድደንም። ሙሴ “ዛሬ ሕይወትንና በረከትን፣ ሞትንና ጥፋትን በፊትህ አኑሬአለሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ቁጥር 15) ከሕይወትና ከሞት እንዲሁም ከበረከትና ከጥፋት አንዱን የመምረጥ ነፃነት አለን። አምላክን ለማምለክና ለመታዘዝ በመምረጥ በረከቱን ማግኘት አሊያም እሱን ላለመታዘዝ በመምረጥ የሚያስከትለውን ውጤት መቀበል እንችላለን። ከሁለት አንዱን የመምረጡ ፋንታ የእኛ ነው።—ቁጥር 16-18ገላትያ 6:7, 8

ይሖዋ የፈለግነውን የሕይወት ጎዳና ብንመርጥ ግድ እንደማይሰጠው ሊሰማን ይገባል? በፍጹም! ሙሴ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ “ሕይወትን ምረጥ” ብሏል። (ቁጥር 19) ታዲያ ሕይወትን መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው? ‘አምላክን በመውደድ፣ ቃሉን በማዳመጥና ከእርሱ ጋር በመጣበቅ’ እንደሆነ ሙሴ ገልጿል። (ቁጥር 20) ይሖዋን የምንወድ ከሆነ ታዛዦች በመሆን እሱን ለማዳመጥ ፈቃደኞች እንሆናለን፤ እንዲሁም የመጣው ቢመጣ ከእሱ ጋር በታማኝነት እንጣበቃለን። እንዲህ ያለውን ጎዳና በመከተል ሕይወትን መምረጥ እንችላለን። ይህን ጎዳና ከተከተልን በዛሬው ጊዜ ሕይወታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መምራት እንችላለን፤ እንዲሁም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖረናል።—2 ጴጥሮስ 3:11-13፤ 1 ዮሐንስ 5:3

ሙሴ የተናገረው ሐሳብ አንድ እውነት ያረጋግጥልናል። በዚህ ክፉ ዓለም፣ ያሳለፍካቸው ገጠመኞች ምንም ይሁኑ ምን ሁኔታዎችን ለማስተካከል ምንም ዓይነት ምርጫ የለህም ወይም ነገሮች አይሳኩልህም ማለት አይደለም። ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት በመስጠት አክብሮሃል። አዎ፣ ይሖዋን ለመውደድና ለማዳመጥ እንዲሁም ለእሱ እስከመጨረሻው ታማኝ ለመሆን መምረጥ ትችላለህ። እንዲህ ያለ ምርጫ የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ ጥረትህን ይባርከዋል።

በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችው ሴት ይህንን እውነት ማለትም ይሖዋን ለመውደድና እሱን ለማገልገል የመምረጥ ነፃነት ያለን መሆኑን ማወቋ እንድትጽናና አድርጓታል። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን እወደዋለሁ። ሆኖም በጣም አስፈላጊው ነገር ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር መሆኑን የምዘነጋበት ወቅት አለ፤ ሐቁ ግን ለይሖዋ ፍቅር ካለኝ ለእሱ ታማኝ መሆን የምችል መሆኑ ነው።” አንተም በይሖዋ እርዳታ ለእሱ ታማኝ መሆን ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በጥቅምት 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ወደ አምላክ ቅረብ—ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።