በጥንት ጊዜ ከሜድትራንያን ባሻገር የተደረጉ ጉዞዎች
በጥንት ጊዜ ከሜድትራንያን ባሻገር የተደረጉ ጉዞዎች
በዛሬው ጊዜ ሰዎች አውሮፕላን ስለሚጠቀሙ ከአንዱ አህጉር ወደ ሌላው አህጉር መሄድ ቀላል ነው። ይሁንና በጥንት ጊዜም ሰዎች ረጅም ጉዞ ያደርጉ እንደነበረ ታውቃለህ?
ክርስቶስ ከመወለዱ ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ንጉሥ ሰለሞን ከእስራኤል ርቀው ከሚገኙ ቦታዎች የሚፈልጋቸውን ዕቃዎች ለማስመጣት ብዙ መርከቦችን ሠርቶ ከጢሮስ ንጉሥ መርከቦች ጋር ልኮ ነበር። (1 ነገሥት 9:26-28፤ 10:22) በዘጠነኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ዮናስ ወደ ተርሴስ * ለመሄድ እስራኤል ውስጥ በሜድትራንያን ባሕር ላይ በሚገኘው በኢዮጴ ወደብ መርከብ ተሳፍሮ ነበር። (ዮናስ 1:3) በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ሐዋርያው ጳውሎስ በእስራኤል ከነበረችው ከቂሳርያ ተነስቶ በጣሊያን፣ በኔፕልስ ባሕረ ሰላጤ ወደምትገኘው ወደ ፑቲዮሉስ (በአሁኗ ፖትዞሊ) ተጉዞ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 27:1፤ 28:13
ታሪክ ጸሐፊዎች በጳውሎስ ዘመን ነጋዴዎች ብዙውን ጊዜ በመርከብ ከሜድትራንያን አካባቢ ተነስተው በቀይ ባሕር በኩል ወደ ሕንድ ይሄዱ እንደነበረና ከሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ አንዳንዶች እስከ ቻይና ድረስ ይጓዙ እንደነበረ ይናገራሉ። * ይሁንና በጥንት ጊዜ ከሜድትራንያን ባሻገር ወደ ምዕራብ ስለተደረጉ ጉዞዎችስ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? በጥንት ጊዜ የነበሩት መርከበኞች በዚያ አቅጣጫ ምን ያህል ርቀው ተጉዘዋል?
የጥንቶቹ ፊንቄያውያን ያደረጉት ጉዞ
ጳውሎስ ከኖረበት ዘመን በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የባሕር ላይ ጉዞ ያደርጉ የነበሩ ሰዎች ከምዕራቡ ዓለም ጋር የንግድ ግንኙነት ያደርጉ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ሊባኖስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ፊንቄያውያን በ1200 ዓ.ዓ. እስከ አትላንቲክ ድረስ እንደተጓዙ ይታመናል። በ1100 ዓ.ዓ. አካባቢ ጌደርን ቆረቆሩ፤ በአሁኑ ጊዜ ካዲዝ የምትባለው ይህች የስፔን የወደብ ከተማ ከጂብራልተር የባሕር ወሽመጥ ከፍ ብላ ትገኛለች። በዚያ ከነበሩት ዕቃዎች መካከል ከአካባቢው ተቆፍሮ ይወጣ የነበረው የብር ማዕድንና የአትላንቲክ ነጋዴዎች ያስመጡት የነበረው የቆርቆሮ ማዕድን ይገኙበታል።
ሄሮዶተስ የተባለው ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ እንደዘገበው በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ይኖር የነበረው ኒካዑ የተባለው የግብፁ ፈርዖን በቀይ ባሕር ላይ በፊንቄያውያን መርከበኞች የሚመሩ በርካታ መርከቦችን አሰባስቦ ነበር። ዓላማውም አፍሪካን ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ለመዞር ነበር።
በዚያን ጊዜ ፊንቄያውያን የአፍሪካን የባሕር ዳርቻዎች ለብዙ ዘመናት ሲያስሱ ቆይተው ነበር። ያም ሆኖ የአትላንቲክን ውቅያኖስ ዳር ይዘው ወደ ደቡብ አቅጣጫ ይጓዙ የነበሩ መርከበኞች ከፊት ለፊታቸው በሚመጣ ከባድ ነፋስና ፈረሰኛ ውኃ የተነሳ በጣም ርቀው መጓዝ ያዳግታቸው ነበር። ሄሮዶተስ እንደጻፈው ከሆነ ፊንቄያውያን አዲስ ጉዞ በመጀመር ከቀይ ባሕር ተነስተው የምሥራቅ አፍሪካን ዳርቻ ጥግ ጥጉን በመያዝ በስተ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ አመሩ። በዓመቱ አጋማሽ አካባቢ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደው ዘር ዘርተው ምርቱ እስከሚሰበሰብበት ጊዜ ድረስ ከቆዩ በኋላ ጉዟቸውን እንደገና ቀጠሉ። በሦስተኛው ዓመት መላውን አህጉር ዞረው በሜድትራንያን በኩል ወደ ግብፅ እንደተመለሱ ሄሮዶተስ ተናግሯል።
ሄሮዶተስ፣ ፊንቄያውያን የአፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ ደርሰው ሽቅብ ሲታጠፉ ፀሐይን በስተ ቀኛቸው በኩል እንዳዩ የተናገሩትን ጨምሮ እሱ ሊያምነው ያልቻለ በርካታ ነገሮችን እንደነገሩት በመግለጽ ዘገባውን ደምድሟል። በእርግጥም በጥንት ጊዜ ይኖር ለነበረ ለአንድ ግሪካዊ ሰው ይህን ማመን አዳጋች ነበር። ከምድር ወገብ በስተ ሰሜን ለኖረ ሰው ዕድሜውን በሙሉ ፀሐይን ሲያይ የኖረው በስተ ደቡብ በኩል ነው። በመሆኑም ይህ ሰው ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሲጓዝ ፀሐይዋ በስተ ግራው ትሆናለች። ይሁንና ከምድር ወገብ በስተ ደቡብ በሚገኘው ኬፕ ኦቭ ጉድ ሆፕ ፀሐይዋ በእኩለ ቀን ላይ በስተ ሰሜን ስለምትሆን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ለሚጓዝ ሰው ፀሐይዋ በስተ ቀኙ ትሆናለች።
የሄሮዶተስ ዘገባ በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ታሪክ ጸሐፊዎችን ሲያወዛግብ ቆይቷል። በዚያ ዘመን መርከበኞች አፍሪካን ዞረዋል የሚለው ሐሳብ ለብዙዎች የማይታመን ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ ፈርዖን ኒካዑ እንዲህ ያለ ጉዞ እንዲደረግ ትእዛዝ ሰጥቶ እንደነበረና በዘመኑ ከነበረው ጥሩ ችሎታና እውቀት አንጻርም እንዲህ ያለውን ጉዞ ማድረግ የሚቻል እንደነበረ ምሑራን ያምናሉ። ታሪክ ጸሐፊው ላየነል ካሰን እንደሚከተለው ብለው ነበር፦ “እንዲህ ዓይነቱን ጉዞ ማድረግ እንደሚቻል ምንም ጥርጥር የለውም። ፊንቄያውያን መርከበኞች፣ ሄሮዶተስ በገለጸው ጊዜና ሁኔታ መሠረት ጉዞ ማድረግ የማይችሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም።” የሄሮዶተስ ዘገባ ምን ያህል እውነትነት እንዳለው በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ ሰዎች በዚያ ዘመን ወደማይታወቁ አካባቢዎች የባሕር ጉዞ ለማድረግ ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጉ እንደነበረ ፍንጭ ይሰጠናል።
ፒቲየስ ወደ ሰሜን ያደረገው ጉዞ
በጥንት ዘመን በሜድትራንያን አካባቢ ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ተጉዘው እስከ አትላንቲክ የዘለቁት ፊንቄያውያን ብቻ አልነበሩም። የግሪክ መርከበኞች በሜድትራንያን ዙሪያ ከቆረቆሯቸው መንደሮች መካከል ማሳሊያ (በአሁኑ ጊዜ ማርሴይል የምትባለው የፈረንሳይ ከተማ) ትገኝበታለች። በባሕርና በየብስ ላይ በሚካሄደው ንግድ ከተማዋ በልጽጋ ነበር። ነጋዴዎች ከማሳሊያ የሜድትራንያንን ወይን፣ ዘይትና የነሐስ ዕቃ ወደ ሰሜን ይልኩ የነበረ ሲሆን ከሰሜን ደግሞ ያልተጣራ ብረትና አምበር ያስመጡ ነበር። የማሳሊያ ነዋሪዎች እነዚህ ዕቃዎች ከየት እንደሚገኙ ለማወቅ ይፈልጉ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። በመሆኑም በ320 ዓ.ዓ. አካባቢ ፒቲየስ የተባለ የማሳሊያ ሰው በስተ ሰሜን ርቀው የሚገኙትን እነዚህን ቦታዎች ለማየት ጉዞ ጀመረ።
ፒቲየስ ከጉዞው ሲመለስ ጉዞውን በሚመለከት ኦን ዚ
ኦሽን የሚል መጽሐፍ ጻፈ። ምንም እንኳ በግሪክኛ የጻፈው የመጀመሪያው መጽሐፍ ባይኖርም ቢያንስ 18 የሚያህሉ የጥንት ጸሐፊዎች ከእሱ መጽሐፍ ላይ ጠቅሰው ጽፈዋል። ከፒቲየስ መጽሐፍ ላይ የተወሰዱት እነዚህ ሐሳቦች፣ ፒቲየስ በጉዞው ወቅት ስለተመለከተው ባሕር፣ ሞገድ፣ መልክዓ ምድርና ሕዝብ በጥንቃቄ ማስፈሩን ያሳያሉ። በተጨማሪም የአንድን ዘንግ ጥላ ርዝመት ተጠቅሞ በአንድ በሚታወቅ ዕለት እኩለ ቀን ላይ ፀሐይዋ ምን ያህል አንግል እንደምትፈጥር ለማስላት ችሎ ነበር፤ ከዚህ በመነሳት በስተ ሰሜን አቅጣጫ እስከ የት ድረስ እንደተጓዘ መገመት ችሎ ነበር።ፒቲየስ ይህን ጉዞ ለማድረግ የፈለገው ሳይንሳዊ ምርምር ለማድረግ ነበር። ይሁን እንጂ የተጓዘበት ዋነኛ ዓላማ ይህ ብቻ ነው ብሎ ማመን ያዳግታል። ምሑራን እንደሚገምቱት ከሆነ ፒቲየስ አምበርና ቆርቆሮ ወደሚገኝባቸው ወደ እነዚህ ሩቅ የባሕር ዳርቻዎች የተጓዘው በማሳሊያ የነበሩ ነጋዴዎች ወደ እነዚህ ቦታዎች የሚወስደውን የባሕር መንገድ እንዲያጣራላቸው ልከውትና የገንዘብ ድጋፍ አድርገውለት ስለነበር ነው። ታዲያ ፒቲየስ የተጓዘው ወዴት ነበር?
ወደ ብሪትኒ፣ ብሪታንያና ከዚያ ባሻገር
ፒቲየስ አይቤሪያን ከዞረ በኋላ በጎል የባሕር ዳርቻ ወደ ላይ ተጉዞ ወደ ብሪትኒ በማቅናት እዚያ ከመርከብ የወረደ ይመስላል። ይህ ሊታወቅ የቻለው ከለካቸው የፀሐይ አንግሎች መካከል በየብስ ላይ ሆኖ እንደለካው የሚገመተው አንደኛው አንግል በሰሜን ብሪትኒ ከሚገኝ ቦታ ጋር በትክክል ስለሚመሳሰል ነው። *
የብሪትኒ ሕዝቦች ከብሪታንያ ጋር የንግድ ግንኙነት የሚያደርጉ የተዋጣላቸው የመርከብ ሠሪዎችና መርከበኞች ነበሩ። በብሪታንያ ደቡባዊ ምዕራብ ጫፍ ላይ የምትገኘው ኮርንዎል፣ ነሐስ ለመሥራት የሚያገለግለው የቆርቆሮ ማዕድን በብዛት የነበረባት ስትሆን ፒቲየስም ጉዞውን የቀጠለው ወደዚያ ነበር። በሪፖርቱ ላይ ስለ ብሪታንያ የቆዳ ስፋትና ቅርጿ ከሞላ ጎደል ሦስት ማዕዘን እንደሚመስል መጥቀሱ በዚህ ደሴት ዙሪያ ተጉዞ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።
ፒቲየስ የሄደበትን መንገድ በትክክል ማወቅ ባይቻልም በብሪታንያና በአየርላንድ መካከል ተጉዞ አይስል ኦቭ ማን በተባለ ቦታ ከመርከብ እንደወረደ መገመት ይቻላል፤ እንዲህ ሊባል የሚችለው ለሁለተኛ ጊዜ ለክቶ ያገኘው የፀሐይ አንግል ከዚህ ቦታ የኬንትሮስ መስመር ጋር ስለሚመሳሰል ነው። ፀሐይ የምትፈጥረውን አንግል ለሦስተኛ ጊዜ የለካው በስኮትላንድ ምዕራባዊ ዳርቻ ማዶ በሚገኘው በአውተር ሄበርዲዝ ውስጥ በሉዊስ ዊዝ ሃሪስ ሳይሆን አይቀርም። ትልቁ ፕሊኒ የፒቲየስን ሪፖርት ጠቅሶ በጻፈው ዘገባ ላይ በኦርክኒ ደሴቶች 40 የሚያህሉ ደሴቶች እንዳሉ ስለገለጸ ፒቲየስ ከአውተር ሄበርዲዝ በኋላ ከስኮትላንድ በስተ ሰሜን ወደሚገኙት ኦርክኒይ ደሴቶች ተጉዞ ሊሆን ይችላል።
ፒቲየስ ከብሪታንያ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ስድስት ቀን ከተጓዘ በኋላ ቱሌ በማለት የጠራውን ምድር እንዳገኘ ጽፏል። አያሌ ጥንታዊ ደራሲዎች ፒቲየስ በእኩለ ሌሊት ፀሐይ የሚወጣበት ምድር በማለት ስለ ቱሌ የሰጠውን ገለጻ ጠቅሰው ጽፈዋል። ከዚያ ተነስቶ አንድ ቀን ሲጓዝ ባሕሩ “ግግር በረዶ” የሆነበት ቦታ እንደደረሰ ጽፏል። ፒቲየስ የገለጸው ቱሌ በትክክል የሚገኘው የት እንደሆነ ብዙዎችን ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ ሲሆን አንዳንዶች በፌሮ ደሴቶች፣ ሌሎች በኖርዌይ አንዳንዶች ደግሞ በአይስላንድ ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ቱሌ የሚገኘው የትም ይሁን የት የጥንት ጸሐፊዎች ይህ ቦታ “በስተ ሰሜን በኩል በስም ከሚታወቁት ስፍራዎች ሁሉ ርቆ የሚገኝ” እንደሆነ ያምኑ ነበር።
ምናልባት ፒቲየስ ወደ ብሪታንያ ሲመለስ በአብዛኛው በሄደበት መንገድ እንደተመለሰና በመጨረሻም ይህን ደሴት በመዞር ጉዞውን እንዳጠናቀቀ ይገመታል። ወደ ሜድትራንያን ከመመለሱ በፊት በሰሜናዊ አውሮፓ ባሕር ዳርቻ ላይ ተጨማሪ አሰሳ አድርጎ ይሁን አይሁን አይታወቅም። ያም ሆነ ይህ ትልቁ ፕሊኒ ፒቲየስን አምበር የሚያመርቱ አካባቢዎችን ያጠና ሊቅ እንደሆነ አድርጎ ጠቅሶታል። የዚህ ውድ ማዕድን ጥንታዊ ምንጮች የአሁኗ ዴንማርክ ክፍል የሆነው ጀትላንድና የባልቲክ ባሕር ደቡባዊ ዳርቻ ናቸው። እርግጥ ነው፣ ፒቲየስ ስለ እነዚህ አካባቢዎች ያወቀው በምሥራቅ ብሪታንያ ወደሚገኙ ወደቦች በሄደበት ጊዜ ከሰማው ነገር ሊሆን ቢችልም እስከሚታወቀው ድረስ ወደ እነዚያ አካባቢዎች እንደሄደ የተናገረው ነገር የለም።
ከፒቲየስ ቀጥሎ ወደ ብሪታንያ መሄዱን እንደጻፈ የሚነገርለት ሌላው የሜድትራንያን ተጓዥ በ55 ዓ.ዓ. ወደዚህች ደሴት ደቡባዊ ክፍል መጥቶ የነበረው ጁሊየስ ቄሳር ነው። በ6 ዓ.ም. ሌሎች ሮማውያን ዘማቾችም እስከ ሰሜናዊ ጀትላንድ ድረስ ተጉዘው ነበር።
አድማሶችን ማስፋት
ፊንቄያውያንና ግሪካውያን ያደረጉት ጉዞ ሰዎች ስለ ጂኦግራፊ ያላቸው የእውቀት አድማስ በሜድትራንያን ብቻ ሳይወሰን እስከ አትላንቲክ ብሎም እስከ አፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ አልፎ ተርፎም እስከ አርክቲክ ሰሜናዊ ክፍል ድረስ እንዲሰፋ አድርጓል። በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም ለአሰሳ፣ ለንግድ፣ የእውቀት አድማስን ለማስፋት ብሎም እጅግ ሩቅ ወደሆኑ ቦታዎች ጉዞ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ነበር፤ ይህ ደግሞ የሰዎች አስተሳሰብና እውቀት እንዲሰፋ አድርጓል።
ጥንት ስለተደረጉት አሰሳዎች የተጻፉና አሁን ድረስ በእጃችን የሚገኙት የታሪክ መዛግብት መንፈሰ ጠንካራ መርከበኞች ካደረጓቸው ስኬታማ ጉዞዎች ውስጥ የዘገቡት ጥቂቱን ብቻ ነው። በጥንት ጊዜ ከነበሩት መርከበኞች መካከል ስለሄዱባቸው ቦታዎች ሳይጽፉ ወደ መነሻቸው የተመለሱ ምን ያህል ይሆኑ? ከትውልድ ስፍራቸው ተነስተው ወደ ሩቅ አገር በመጓዝ ሳይመለሱ የቀሩ መርከበኞችስ ስንት ይሆኑ? እነዚህ እስካሁን መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች ናቸው። ይሁን እንጂ በጥንት ጊዜ ክርስትና ስለተስፋፋበት መንገድ ልናውቀው የምንችለው ነገር አለ።— ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 ይህ ስም ብዙውን ጊዜ የግሪክና የሮም ጸሐፊዎች ታርቴሰስ ብለው ይጠሩት ከነበረው በደቡባዊ ስፔን ከሚገኝ አንድ አካባቢ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ይገመታል።
^ አን.4 ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ስለተደረጉ ጉዞዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥር 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን “ሚስዮናውያን በስተ ምሥራቅ የት ድረስ ተጉዘው ሊሆን ይችላል?” የሚል ርዕስ ተመልከት።
^ አን.16 በዘመናዊ አጠራር በስተ ሰሜን በ48° በ42’ ኬንትሮስ ላይ ይገኛል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ምሥራቹ ‘በፍጥረት ሁሉ መካከል ተሰብኳል’
ከ60-61 ዓ.ም. አካባቢ ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል ተሰብኳል” በማለት ጽፎ ነበር። (ቆላስይስ 1:23) ታዲያ እንዲህ ሲል ክርስቲያኖች በሕንድ፣ በሩቅ ምሥራቅ፣ በአፍሪካ፣ በስፔን፣ በጎል፣ በብሪታንያ፣ በባልቲክ እንዲሁም አሳሹ ፒቲየስ ቱሌ ብሎ በጠራት አገር ሰብከዋል ማለቱ ነበር? ይህ የማይሆን ነገር ቢመስልም አይሆንም ብለን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም።
ይሁን እንጂ ምሥራቹ በስፋት ተሠራጭቶ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ክርስትናን የተቀበሉ አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች አዲሱን እምነታቸውን ቢያንስ ቢያንስ እስከ ጳርቴና፣ ኤላም፣ ሜዶን፣ ሜሶጶጣሚያ፣ ዓረብ አገር፣ ትንሿ እስያ፣ በቀሬናም በኩል ባሉት የሊቢያ ወረዳዎችና ሮም ድረስ ይዘው ሄደዋል፤ ይህ ደግሞ ጳውሎስ የጻፈላቸው ሰዎች የሚያውቁትን ዓለም ያካትት ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 2:5-11
[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
መርከበኞች በአፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ ዞረው ወደ ምዕራብ ሲሄዱ ፀሐይን በስተ ቀኛቸው እንዳዩዋት መናገራቸውን ሄሮዶተስ ዘግቧል
[ካርታ]
አፍሪካ
ሜድትራንያን ባሕር
ሕንድ ውቅያኖስ
አትላንቲክ ውቅያኖስ
[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የግሪካዊው መርከበኛ የፒቲየስ ረጅም የባሕር ጉዞ
[ካርታ]
አየርላንድ
አይስላንድ
ኖርዌይ
ሰሜን ባሕር
ብሪታንያ
ብሪትኒ
አይቤሪያን ባሕረ ገብ መሬት
የአፍሪካ ሰሜናዊ ጠረፍ
ሜድትራንያን ባሕር
ማርሴይል