“መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል”
ወደ አምላክ ቅረብ
“መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል”
በታሪክ ዘመናት ሁሉ በርካታ ሰብዓዊ መንግሥታት ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ተደርገዋል። አንዳንዶች በምርጫ ተሸንፈው ሌሎች ደግሞ በኃይል ተገደው ከሥልጣናቸው ወርደዋል። በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስስ ምን ማለት ይቻላል? አምላክ የሾመው ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ወቅት እንቅፋት የሚሆንበት ነገር ይኖር ይሆን? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ይሖዋ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ማግኘት እንችላለን፤ ይህ ሐሳብ በ2 ሳሙኤል ምዕራፍ 7 ላይ ይገኛል።
በምዕራፉ መጀመሪያ ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ዳዊት ተራ ሰብዓዊ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እሱ ውብ በሆነ ቤተ መንግሥት ውስጥ እየኖረ የአምላክ ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ መቀመጡ በጣም አሳዝኖት ነበር። * ዳዊት ለይሖዋ ተገቢ የሆነ ቤት ወይም ቤተ መቅደስ ለመሥራት እንደሚፈልግ ገለጸ። (ቁጥር 2) ቤቱን የሚሠራው ግን ዳዊት አይደለም። ቤተ መቅደሱን የሚሠራው የዳዊት ልጅ እንደሚሆን ይሖዋ በነቢዩ ናታን አማካኝነት ለዳዊት ነገረው።—ቁጥር 4, 5, 12, 13
ዳዊት ለአምላክ ቤት ለመሥራት ከልቡ ተነሳስቶ ያቀረበው ጥያቄ ይሖዋን አስደሰተው። አምላክ፣ ዳዊት የዚህን ያህል ለእሱ ያደረ መሆኑን በማየትና አስቀድሞ ያስነገረውን ትንቢት ግምት ውስጥ በማስገባት በዳዊት የንግሥና መስመር የሚመጣ ሰው እንደሚያስነሳና ይህ ሰው ለዘላለም እንደሚነግሥ ቃል ገባለት። ነቢዩ ናታን አምላክ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል።” (ቁጥር 16) ታዲያ በዚህ ቃል ኪዳን መሠረት የዳዊት ዙፋን ወራሽ የሚሆነውና ለዘላለም የሚገዛው ማን ነው?—መዝሙር 89:20, 29, 34-36
የናዝሬቱ ኢየሱስ ከዳዊት የዘር ሐረግ የመጣ ነበር። አንድ መልአክ ስለ ኢየሱስ መወለድ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ መንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:32, 33) በዚህ መንገድ ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባው ቃል ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜውን አገኘ። ኢየሱስ የሚገዛው በሰዎች ተመርጦ ሳይሆን አምላክ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በመሆኑ ለዘላለም የመግዛት መብት አለው። አምላክ የሚሰጠው ተስፋ ደግሞ ምንጊዜም ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እናስታውስ።—ኢሳይያስ 55:10, 11
ከ2 ሳሙኤል ምዕራፍ 7 ሁለት ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ገዥ እንዳይሆን የሚያግደው ምንም ነገር የለም። በመሆኑም ገዥ የሆነበትን ዓላማ እንደሚፈጽም ይኸውም የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲሆን እንደሚያደርግ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማቴዎስ 6:9, 10
ሁለተኛ፣ ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ልብ የሚነካ ትምህርት ያስተምረናል። ይሖዋ፣ የዳዊትን ውስጣዊ ፍላጎት እንደተመለከተና እንዳደነቀው አስታውስ። ይሖዋ ለእሱ አምልኮ ያለንን ቅንዓት እንደሚመለከተውና እንደሚያደንቀው ማወቁ የሚያጽናና ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደ ጤና ማጣት ወይም የዕድሜ መግፋት ያሉ ከአቅማችን በላይ የሆኑ ሁኔታዎች በአምላክ አገልግሎት የምንመኘውን ያህል እንዳንካፈል ያግዱን ይሆናል። ከሆነ ይሖዋ ልባችን ለእሱ አምልኮ ባለን ቅንዓት የተሞላ መሆኑን እንደሚመለከት ማወቁ በራሱ ሊያጽናናን ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 የቃል ኪዳኑ ታቦት ይሖዋ በሰጠው መመሪያና ፕላን መሠረት የተሠራ የሣጥን ቅርጽ ያለው ቅዱስ ዕቃ ነበር። ታቦቱ ይሖዋ በጥንቷ እስራኤል መኖሩን ያመለክት ነበር።—ዘፀአት 25:22