በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ልጅሽን ውሰጂ”

“ልጅሽን ውሰጂ”

ወደ አምላክ ቅረብ

“ልጅሽን ውሰጂ”

2 ነገሥት 4:8-37

የልጅ ሞት ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው መሪር ሐዘኖች መካከል አንዱ ነው። ይሖዋ አምላክ በሞት ያጣናቸውን ሰዎች ዳግመኛ ሕያው ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው። በጥንት ጊዜ ይኖሩ ለነበሩ ጥቂት ሰዎች ሙታንን የማስነሳት ኃይል ሰጥቷቸው የነበረ መሆኑ ለዚህ ማረጋገጫ ይሆነናል። ይህን ከሚያሳዩት ታሪኮች አንዱ በ2 ነገሥት 4:8-37 ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ሲሆን ዘገባው ነቢዩ ኤልሳዕ አንድን ትንሽ ልጅ ከሞት እንዳስነሳ ይገልጻል።

ታሪኩ የተፈጸመው በሱነም ከተማ ነው። አንዲት መካን ሴትና ባሏ፣ ለኤልሳዕ ዘወትር ምግብና ማረፊያ በማቅረብ ደግነት ያሳዩት ነበር። የሚደረግለትን ደግነት ያደንቅ የነበረው ይህ ነቢይ አንድ ቀን ሴትየዋን “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ” አላት። ይመጣል ብላ ያላሰበችው ቀን በመጨረሻ ሲደርስ ኤልሳዕ ባላት መሠረት ወንድ ልጅ ለመታቀፍ በቃች። የሚያሳዝነው ግን ደስታዋ ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልጁ በእርሻ ቦታ ሳለ ከባድ ራስ ምታት አመመውና ወደ ቤት ተወሰደ፤ እዚያም “በእናቱ ጭን ላይ” እንዳለ ሞተ። (ቁጥር 16, 19, 20) በሐዘን የተቆራመደችው እናቱ ሬሳውን ይዛ ወደ ላይ በመውጣት ነቢዩ አዘውትሮ በሚተኛበት አልጋ ላይ አስተኛችው።

ወዲያውኑም ለባሏ ነግራ ኤልሳዕን ለማግኘት 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ወደሚገኘው ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደች። ባገኘችው ጊዜም ለማልቀስ፣ ለመጮህ ወይም ሐዘኗን ለመግለጽ ያደረገችው ነገር አልነበረም። ምናልባት ወደዚህ የመጣችው ከኤልሳዕ በፊት የነበረው ነቢዩ ኤልያስ የአንዲትን መበለት ልጅ ከሞት እንዳስነሳ ስለሰማች ይሆን? (1 ነገሥት 17:17-23) ሱነማዪቱ ሴት ኤልሳዕም የእሷን ልጅ ወደ ሕይወት መመለስ እንደሚችል እምነት አድሮባት ይሆን? ሁኔታው ምንም ሆነ ምን ኤልሳዕ ከእሷ ጋር ካልሄደ ወደ ቤት እንደማትመለስ ነገረችው።

ወደ ሱነም ከተመለሱ በኋላ ኤልሳዕ ብዙ ጊዜ ያርፍበት ወደነበረው ክፍል ብቻውን ሲገባ የሞተው ልጅ “በዐልጋው ላይ ተጋድሞ” ተመለከተ። (ቁጥር 32) ነቢዩ በጸሎት ወደ ይሖዋ የቀረበ ሲሆን ጸሎቱ የጋለ ስሜት የተንጸባረቀበት ምልጃ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ከዚያም ኤልሳዕ የትንሹን ልጅ ሰውነት ሲይዝ “የልጁ ሰውነት መሞቅ ጀመረ።” መሥራቱን አቁሞ የነበረው የልጁ ልብ እንደገና መምታት ጀመረ! ኤልሳዕ እናቱን ከጠራት በኋላ “ልጅሽን ውሰጂ” አላት፤ በዚህ ጊዜ እናቱ ሐዘኗን በመርሳት ከደስታዋ ብዛት የምትሆነው ጠፍቷት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።—ቁጥር 34, 36

የሱነማዪቱ ልጅ ከሞት እንደተነሳ የሚናገረው ይህ ታሪክ ተስፋ የሚፈነጥቅ ከመሆኑም ሌላ በእጅጉ ያጽናናል። ይሖዋ ልጆቻቸውን በሞት ያጡ ወላጆች የደረሰባቸውን ሐዘን ይረዳል። ከዚህም በላይ የሞቱትን መልሶ ሕያው ለማድረግ ይናፍቃል። (ኢዮብ 14:14, 15) ኤልሳዕም ሆነ በጥንት ጊዜ የነበሩ ሌሎች የፈጸሟቸው ትንሣኤዎች፣ ይሖዋ እሱ በሚያመጣው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ መጠነ ሰፊ በሆነ መንገድ የሚያከናውነውን ትንሣኤ ከወዲሁ የሚያመላክቱ ናሙናዎች ናቸው። *

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚናገረው ተስፋ የምንወደውን ሰው በሞት በማጣታችን የሚሰማንን ሐዘን አያስቀርልንም። ብቸኛ ልጁን በሞት ያጣ አንድ ታማኝ ክርስቲያን “የደረሰብኝ ሐዘን ሙሉ በሙሉ የሚወገደው ልጄ ዳግመኛ እቅፌ ውስጥ ሲገባ ብቻ ነው” በማለት ተናግሯል። በሞት ካጣሃቸው የምትወዳቸው ሰዎች ጋር ዳግመኛ የምትገናኝበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። ከእነሱ ጋር ዳግመኛ የምትገናኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ማሰብህ ብቻ እንኳ ሐዘንህን ሊያቀልልህ ይችላል። እንዲህ የመሰለውን ግሩም ተስፋ ስለሰጠን አምላክ ይበልጥ ለማወቅ አትጓጓም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 መጽሐፍ ቅዱስ ትንሣኤን አስመልክቶ ስለሚሰጠው ተስፋ የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7⁠ን ተመልከት።