“አናጺው”
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሕይወት
“አናጺው”
“ይህ የአናጺው ልጅ አይደለም?”—ማቴዎስ 13:55
ኢየሱስ “የአናጺው ልጅ” ብቻ ሳይሆን “አናጺው” በመባልም ይታወቅ ነበር። (ማርቆስ 6:3) ይህን ሙያ የተማረው ከአሳዳጊ አባቱ ከዮሴፍ መሆን አለበት።
ኢየሱስ በአናጺነት ሲሠራ ምን ዓይነት ችሎታ ማዳበርና የየትኞቹን መሣሪያዎች አጠቃቀም ማወቅ አስፈልጎት ነበር? ለናዝሬት ነዋሪዎች የትኞቹን ምርቶች አቅርቦ እንዲሁም ምን ዓይነት አገልግሎት ሰጥቶ ይሆን? ደግሞስ የእንጨት ሥራ ባለሙያ ለመሆን በልጅነቱ ያገኘው ሥልጠና በኋለኛው ሕይወቱ የጠቀመው እንዴት ነው?
የቤተሰብ ሙያ። ከታች ያለው ሥዕል አንድ አባት ለታላቅ ልጁ መሰርሰሪያ መሣሪያውን እንዴት በዘዴና በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚችል ሲያስተምረው ያሳያል። ታናሽየውም አባቱ የሚናገረውን በትኩረት እያዳመጠ ከመሆኑም በላይ ሥራው እንዴት እንደሚከናወን እየተከታተለ ነው።
ወንዶች ልጆች ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለውን መደበኛ የሙያ ሥልጠና የሚጀምሩት ከ12 እስከ 15 ዓመት ባለው ዕድሜ ነበር። አብዛኛውን ጊዜም ሙያውን የሚማሩት ከአባታቸው ነበር። ሥልጠናው ብዙ ዓመታት የሚፈጅ ሲሆን ወንዶች ልጆችም በሙያቸው የተካኑ አናጺዎች ለመሆን የሚያስፈልጋቸውን ችሎታ ለማዳበር ከፈለጉ ብርቱ ጥረት ማድረግ ነበረባቸው። ዮሴፍ ከኢየሱስ ጋር በመሥራት፣ በመጨዋወትና
ሙያውን ለእሱ በማስተላለፍ አስደሳች ጊዜያት አሳልፎ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ዮሴፍ፣ ኢየሱስ ሙያውን እንደተካነው ሲመለከት ታላቅ ኩራት ተሰምቶት መሆን አለበት!እውቀት፣ ጥንካሬና ክህሎት ያስፈልግ ነበር። አንድ አናጺ የሚሠራበትን እንጨት ባሕርይ ማወቅ ያስፈልገው ነበር። እንደ ሸውሸዌ፣ የሊባኖስ ዛፍ፣ ሾላና ወይራ ካሉት በአካባቢው ከሚበቅሉ ዛፎች መካከል መምረጥ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሚኖር አናጺ ዛሬ እንዳሉት ያሉ በሚፈልገው መጠን ተጠርቦ የተዘጋጀ ጣውላ መርጦ መግዛት የሚችልባቸው የእንጨት መሰንጠቂያ ቤቶች ወይም የሕንፃ መሣሪያ አቅራቢ ድርጅቶች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ ወደ ጫካ በመሄድ ተስማሚ የሆኑ ዛፎችን መርጦ መቁረጥ ከዚያም እነዚህን ከባድ ግንዶች ወደሚሠራበት ቦታ ማጓጓዝ ነበረበት።
አንድ አናጺ ቆርጦ ባመጣው እንጨት ምን ምን ነገሮችን ይሠራ ነበር? ቤቶችን በመሥራት ከቤት ውጪ ብዙ ሰዓት ያሳልፍ ይሆናል። ለጣሪያ የሚሆኑ ወራጅ እንጨቶችን እየቆረጠ ያዘጋጅ እንዲሁም ወደ ፎቅ የሚያስወጡ ደረጃዎች፣ መዝጊያዎችና መስኮቶች ይሠራ ነበር።
አናጺ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችንም ይሠራ ነበር። በዚህ ገጽ ላይ የሚገኘው ሥዕላዊ መግለጫ እንደሚያሳየው አናጺው ከሚሠራቸው የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች መካከል መሳቢያና መደርደሪያ እንዲሁም መዝጊያ ያላቸው ዕቃ ማስቀመጫዎች (1)፣ በርጩማዎች (2)፣ ወንበሮች (3)፣ የተለያየ ቅርጽና መጠን ያላቸው ጠረጴዛዎች (4) እንዲሁም የሕፃናት አልጋዎች ይገኙበታል። አንዳንዶቹን ዕቃዎች ለማስጌጥ በሚያምርና በረቀቀ መንገድ የተቀረጹ እንጨቶችን ይለጥፍባቸው ይሆናል። ዕቃዎቹ እንዳይበላሹ ለማድረግና ለማስዋብ ደግሞ ሰም፣ ቫርኒሽ ወይም ዘይት ይቀባቸው ይሆናል።
በተጨማሪም አንድ አናጺ የአካባቢው ገበሬዎች የሚጠቀሙባቸው የግብርና መሣሪያዎችን ይኸውም ጠንካራ ከሆኑ እንጨቶች የሚሠሩ ቀንበሮችን (5) እንዲሁም መንሾችን፣ መቧጠጫዎችንና ላይዳዎችን (6) ይሠራ ነበር። አናጺው በሚሠራው ማረሻ (7) ጫፍ ላይ የሚገጠመው ሹል ብረት ድንጋያማ በሆኑ ቦታዎች አፈሩን እየሰነጠቀ ትልም ማውጣት እንዲችል ማረሻው ጠንካራ ተደርጎ መሠራት ነበረበት። አናጺው የእንጨት ጋሪዎችንና (8) ሠረገላዎችን የሚሠራ ሲሆን ከእንጨት የተሠሩ ጎማዎች ይገጥምላቸው ነበር፤ ጎማዎቹ መሃላቸው ድፍን ሊሆን አሊያም ራጂ ሊኖረው ይችላል። አናጺው የሠራቸውን የቤት ዕቃዎች፣ መሣሪያዎችና ተሽከርካሪዎች መጠገንና ማደስም የሥራው ክፍል ነበር።
ኢየሱስ አናጺ ሆኖ መሥራቱ በመልኩና ቁመናው ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ እንደሚሆን በዓይነ ሕሊናህ መሳል ትችላለህ? የመካከለኛው ምሥራቅ ፀሐይ ቆዳውን አጥቁሮት፣ ለዓመታት ባከናወነው የጉልበት ሥራ የተነሳ ጡንቻዎቹ ፈርጥመው እንዲሁም ሸካራ የሆኑ እንጨቶችን በመሸከም ብዛት ብሎም መጥረቢያዎችን፣ መዶሻዎችንና መጋዞችን በመጠቀም የተነሳ እጆቹ መጅ አውጥተው ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ምሳሌዎች ለማግኘት አስችሎታል። ኢየሱስ ቀላል በሆኑና ሕዝቡ በሚያውቃቸው ነገሮች ተጠቅሞ ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን በማስተማር ረገድ የተካነ ነበር። አናጺ በመሆን ያሳለፈው ሕይወት ለአንዳንዶቹ ምሳሌዎቹ መሠረት ሆኖት ይሆን? ይህ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት። ኢየሱስ በአንድ ወቅት ለሚያዳምጡት ሕዝብ “ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ትተህ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ?” ብሏቸው ነበር። ግንድ ምን ያህል ግዙፍ ሊሆን እንደሚችል አንድ አናጺ ያውቃል። (ማቴዎስ 7:3) በሌላ ጊዜም ኢየሱስ ለተሰበሰቡት ሰዎች “ዕርፍ ጨብጦ በኋላው ያሉትን ነገሮች የሚመለከት ሰው ለአምላክ መንግሥት የሚገባ አይደለም” በማለት ተናግሯል። እሱ ራሱ ብዙ ዕርፎችን ሳይሠራ አልቀረም። (ሉቃስ 9:62) ኢየሱስ ካቀረባቸው ደግነት የተንጸባረቀባቸው ግብዣዎች አንዱ አናጺ ከሚሠራው መሣሪያ ጋር የተያያዘ ነበር። ኢየሱስ “ቀንበሬን ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ” ብሎ ነበር። አክሎም “ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነው” ብሏል። (ማቴዎስ 11:29, 30) የማይከረክር ከዚህ ይልቅ “ልዝብ” ወይም ምቹ የሆነ ቀንበር እንዴት መሥራት እንደሚቻል ኢየሱስ ያውቅ እንደነበረ ጥርጥር የለውም።
የኢየሱስ ተቃዋሚዎች “የአናጺው ልጅ” ብለው የጠሩት እሱን ለማቃለል ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትም ሆኑ በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች አናጺ የነበረው የዚያ ትሑት ሰው ተከታይ መሆንን እንደ ክብር ይቆጥሩታል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
የአናጺው ዕቃዎች
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሚኖር እንደ ኢየሱስ ያለ አናጺ እዚህ ላይ የሚታዩትን መሣሪያዎች እንዴት እንደሚጠቀምባቸው ማወቅ ያስፈልገው ነበር። መጋዙ (1) የእንጨት እጀታ ያለው ሲሆን ከብረት የተሠራ ምላጭ ይገጠምለታል፤ የመጋዙ ጥርሶች የተሠሩበት መንገድ ለየት ያለ በመሆኑ አናጺው እንጨቱን የሚቆርጠው መጋዙን ወደ ራሱ ሲስበው ነው። ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ማዕዘን ለመጠበቅ ስኳድራ (2) እንዲሁም የሚሠራቸው ነገሮች ቀጥ ያሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ቱንቢ (3) ይጠቀማል። ከዚህም በተጨማሪ ከአናጺው ዕቃዎች መካከል ውኃ ልክ መጠበቂያ (4)፣ ለመለኪያ የሚያገለግል ዘንግ (5)፣ እንጨትን እየፋቁ ለማስተካከል የሚያገለግል ስል የብረት ምላጭ የተገጠመለት መላጊያ (6)፣ እንዲሁም ዛፎችን ለመቁረጥ የሚጠቀምበት (7) መጥረቢያ ይገኙበታል።
አናጺው መፍተያ መሣሪያ ለመሥራት ቅርጽ ማውጫ (8) እና ጎጅ መሮ (9) ይጠቀማል። በአናጺው ሣጥን ክዳን ላይ የእንጨት መዶሻ (10) የሚታይ ሲሆን ይህም መሮዎችን ለመምታት ወይም ሁለት እንጨቶችን ለማያያዝ የሚያገለግሉ ቀጠን ያሉ እንጨቶችን መትቶ ለማስገባት ያገለግላል። በተጨማሪም ሣጥኑ ላይ አነስተኛ የእጅ መጋዝ (11)፣ እንጨት ለመፋቅ የሚያገለግል ቢላ መሰል መሣሪያ (12) እና ጥቂት ምስማሮች (13) ይታያሉ። ከሣጥኑ ፊት የብረት መዶሻ (14) እና እንጨት ለመጥረብ የሚያገለግል ፋስ (15) ይገኛሉ። በሣጥኑ ክዳን ላይ ቢላ (16) እንዲሁም የተለያየ መጠን ያላቸው መሮዎች (17) ይታያሉ። መሰርሰሪያ መሣሪያው (18) ደግሞ ሣጥኑን ተደግፎ ተቀምጧል።