በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብዙዎች ፍርሃት ምንድን ነው?

የብዙዎች ፍርሃት ምንድን ነው?

የብዙዎች ፍርሃት ምንድን ነው?

“ወደ ጥፋት እያመራን መሆኑን ለመገንዘብ ሃይማኖተኛ መሆን አያስፈልግህም።”—ስቴፈን ኦሊሪ፣ የሳውዘርን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር *

ከላይ በቀረበው ሐሳብ ትስማማለህ? እነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ሰዎች መጪውን ጊዜ እንዲፈሩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹን ይገልጻሉ። ተከታታይ ርዕሶቹ ሕይወት ከምድር ገጽ ጨርሶ እንደማይጠፋ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምን እንደሆነም ያብራራሉ። እነዚህ ርዕሶች የያዟቸውን መረጃዎች ስታነብ ስጋት ሊያድርብህ ቢችልም ብሩሕ አመለካከት ለመያዝ የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ።

የኑክሌር ጦርነት ስጋት ገና አልረገበም። በ2007 ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተሰኘው መጽሔት “የመጀመሪያዎቹ አቶሚክ ቦምቦች በሂሮሺማና ናጋሳኪ ላይ ከተጣሉበት ጊዜ ወዲህ ዓለም የአሁኑን ያህል እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ምርጫዎች ተደቅነውበት አያውቁም” በማለት አስጠንቅቋል። ጉዳዩ ይህን ያህል አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ከላይ የተጠቀሰው ቡለቲን በዚያ ዓመት ይኸውም በ2007 ወደ 27,000 ገደማ የኑክሌር መሣሪያዎች እንደነበሩና ከእነዚህ መካከል 2,000 ያህሉ “በተፈለገው ጊዜ በደቂቃዎች ውስጥ ሊተኮሱ እንደሚችሉ” ዘግቧል። ከእነዚያ መሣሪያዎች ውስጥ ጥቂቶቹ እንኳን ቢፈነዱ ከፍተኛ ጥፋት ይከተላል!

ከዚያን ጊዜ ወዲህ የኑክሌር ጦርነት ስጋት ቀንሷል? ዋነኛ የኑክሌር ባለቤት የሆኑት አምስቱ አገሮች ማለትም ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ዩናይትድ ስቴትስ “አንድም፣ ከኑክሌር መሣሪያዎች ጋር በተያያዘ አዲስ ዓይነት አሠራሮችን ተግባራዊ እያደረጉ ናቸው፤ አሊያም እንዲህ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው አሳውቀዋል” በማለት የኤስ አይ ፒ አር አይ 2009 የዓመት መጽሐፍ ይናገራል። * * ይሁን እንጂ ይህ የዓመት መጽሐፍ የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት የሆኑት እነዚህ አገሮች ብቻ አለመሆናቸውን ይገልጻል። ሕንድ፣ ፓኪስታንና እስራኤል እያንዳንዳቸው ከ60 እስከ 80 የሚደርሱ የኑክሌር ቦምቦች እንዳሏቸው ተመራማሪዎች ይገምታሉ። እንዲሁም የሳይንስ ሊቃውንቱ በመላው ዓለም፣ ሊተኮሱ ዝግጁ የሆኑ በጠቅላላው 8,392 የኑክሌር መሣሪያዎች እንዳሉ ተናግረዋል!

የአየር ንብረት ለውጥ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል። ከላይ የተጠቀሰው ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ “የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኑክሌር የጦር መሣሪያዎች የሚያስከትሉትን ያህል የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል” በማለት ይናገራል። ቀደም ሲል በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ያገለግሉ እንደነበሩት ፕሮፌሰር ስቴፈን ሀውኪንግ እና በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የትሪኒቲ ኮሌጅ ኃላፊ እንደሆኑት እንደ ሰር ማርቲን ሬስ ያሉ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው የሳይንስ ሊቃውንትም ከላይ በተጠቀሱት ማስጠንቀቂያዎች ይስማማሉ። ኃላፊነት የጎደለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የሰው ልጅ በአካባቢው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ሊቀለበስ በማይችል መልኩ ሊለውጠው ወይም ሥልጣኔ እንዲያከትም ሊያደርግ እንደሚችል ይሰማቸዋል።

ስለ ጥፋት የሚናገሩት ትንበያዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስጨንቀዋቸዋል። ታዋቂ በሆነ አንድ የኢንተርኔት ድረ ገጽ ላይ “የዓለም መጨረሻ” (“end of the world”) የሚለውን ሐረግ እና “2012” የሚለውን ዓመተ ምህረት ጽፈህ መረጃ ለማግኘት ብትፈልግ በዚያ ዓመት የዓለም መጨረሻ እንደሚሆን የሚገልጹ ግምታዊ ትንበያዎችን የያዙ በመቶ የሚቆጠሩ ገጾች ታገኛለህ። ሰዎች እንዲህ ሊሉ የቻሉት ከምን ተነስተው ነው? “ረጅሙ አቆጣጠር” የተሰኘ የማያ ሕዝቦች ጥንታዊ የዘመን አቆጣጠር በ2012 እንደሚያበቃ በስሌት ተደርሶበታል። ብዙዎች ይህ ስሌት፣ ሥልጣኔ ሊያከትም መሆኑን የሚጠቁም ሳይሆን አይቀርም ብለው ፈርተዋል።

ሃይማኖተኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግዑዟ ምድር እንደምትጠፋ ያስተምራል ብለው ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች፣ እምነታቸውን ጠብቀው የኖሩ ሁሉ ወደ ሰማይ እንደሚወሰዱና ቀሪው የሰው ዘር ግን ምስቅልቅሏ በሚወጣው ምድር ላይ እየተሠቃየ እንደሚኖር አሊያም ወደ ሲኦል እንደሚጣል ያስባሉ።

በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ሙሉ በሙሉ እንደምትበላሽ ወይም እንደምትጠፋ ይናገራል? ሐዋርያው ዮሐንስ “በመንፈስ የተነገረን ቃል ሁሉ አትመኑ፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ የተነገሩት ቃላት ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ” በማለት አሳስቧል። (1 ዮሐንስ 4:1) ሌሎች የሚሉትን እንዲሁ ከመቀበል ይልቅ አንተ ራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም መጨረሻ ምን እንደሚል ለምን አታነብም? መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ሐሳብ ስታውቅ ትገረም ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2ኤም ኤስ ኤን ቢ ሲ ድረ ገጽ ላይ በጥቅምት 19, 2005 ከወጣው “አደጋዎች ስለጥፋት ቀን የሚናገሩ ትንቢቶች እንዲበዙ አድርገዋል” ከሚል ርዕስ የተወሰደ።

^ አን.5 ኤስ አይ ፒ አር አይ የሚለው ምህጻረ ቃል የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋምን ያመለክታል።

^ አን.5ኤስ አይ ፒ አር አይ የ2009 የዓመት መጽሐፍ ላይ የቀረበው ዘገባ የተጻፈው በኤስ አይ ፒ አር አይ የጦር መሣሪያዎች ቁጥጥርና ቅነሳ ፕሮግራም የኑክሌር መሣሪያዎች ፕሮጀክት አንጋፋ ተመራማሪና ዋና ኃላፊ በሆኑት ሻነን ካይል እና በዚሁ ተቋም ውስጥ ተመራማሪ በሆኑት ቪታሊ ፌድቼንኮ እንዲሁም የአሜሪካውያን የሳይንስ ሊቃውንት ፌዴሬሽን የኑክሌር መረጃ ፕሮጀክት ዳይሬክተር በሆኑት ሀንስ ክሪሰንሰን ነው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Mushroom cloud: U.S. National Archives photo; hurricane photos: WHO/League of Red Cross and U.S. National Archives photo