በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፋት እንደሚወገድ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል!

ክፋት እንደሚወገድ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል!

ክፋት እንደሚወገድ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል!

አምላክ፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃሉን የሰጠን ሲሆን ቃሉም ሰዎች መጥፎ ነገር የሚፈጽሙበትን ምክንያት ይገልጽልናል። በተጨማሪም አምላክ ነፃ ምርጫና ራሳችንን የመግዛት ችሎታ ስለሰጠን መጥፎ ድርጊቶችን ላለመፈጸም መምረጥ እንችላለን። (ዘዳግም 30:15, 16, 19) ይህ ዓይነት ችሎታ ስላለን በውስጣችን ሊኖር የሚችል ማንኛውንም መጥፎ ዝንባሌ ለይተን ማወቅና አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ መውሰድ እንችላለን። በዚህ መንገድ ከመጥፎ ድርጊቶች መታቀባችን ለእኛም ሆነ በዙሪያችን ላሉት ሰዎች ደስታ ያስገኛል።—መዝሙር 1:1

ይሁን እንጂ እኛ በግለሰብ ደረጃ መጥፎ ድርጊቶችን ከመፈጸም ለመታቀብ የቱንም ያህል ጥረት ብናደርግ ዓለማችን ሌሎች ሰዎች በሚፈጽሟቸው ክፉ ድርጊቶች መታመሷ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ” በማለት ያስጠነቅቃል። አክሎም ይህ ዘመን “ለመቋቋም የሚያስቸግር” እንዲሆን የሚያደርገው ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆች የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ፣ ኃይሉን ግን ይክዳሉ፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

ከላይ በተጠቀሰው ትንቢት ላይ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” የሚለውን አገላለጽ ልብ ብለህ ይሆናል። ይህ ምን ማለት ይመስልሃል? አብዛኞቹ ሰዎች “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” የሚለው አገላለጽ ወደ ፍጻሜው የሚመጣ ነገር መኖሩን የሚጠቁም እንደሆነ ይገነዘባሉ። ወደ ፍጻሜው የሚመጣው ነገር ምን ሊሆን ይችላል? አምላክ በቃሉ ውስጥ የሰጠንን ተስፋዎች ልብ በል።

ክፉዎች ከምድር ገጽ ይወገዳሉ።

“ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”መዝሙር 37:10, 11

“እግዚአብሔር የሚወዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ክፉዎችን ሁሉ ግን ያጠፋል።”መዝሙር 145:20

ጭቆና ጨርሶ ይወገዳል።

“ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል።”መዝሙር 72:12, 14

“ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት [ያገኛል]።” —ሮም 8:21

የሰዎች ቁሳዊ ፍላጎት ይሟላል።

“እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም።”ሚክያስ 4:4

“ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ፣ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይረዝማል፤ እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።” ኢሳይያስ 65:21, 22

ፍትሕ ይሰፍናል።

“አምላክ . . . ቀንና ሌሊት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ ፍትሕ እንዲያገኙ አያደርግም? እላችኋለሁ፣ በፍጥነት ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል።”ሉቃስ 18:7, 8

“እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኞቹንም አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል።” መዝሙር 37:28

በራስ ወዳድነት ፈንታ ጽድቅ ይሰፍናል።

“የዓለም ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ።”ኢሳይያስ 26:9

“አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።”2 ጴጥሮስ 3:13

አሁንም እንኳ ሰዎች እየተለወጡ ነው

እንደነዚህ ያሉት ተስፋዎች ሁላችንንም እንደሚያስደስቱን ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ምን ማረጋገጫ አለ? እንደ እውነቱ ከሆነ አምላክ የሰጠን ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ የሚያሳይ ማስረጃ በአሁኑ ጊዜም ማግኘት ይቻላል። ይህ ማስረጃ ምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ራስ ወዳድነትን፣ የሥነ ምግባር ብልግናን ወይም የኃይለኝነትን ባሕርይ አስወግደው ሐቀኛ፣ ሰላማዊና ደግ መሆን መቻላቸው አምላክ የሰጠን ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ማስረጃ ይሆነናል። በዛሬው ጊዜ ቁጥራቸው ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች በታሪክ ዘመናት በሙሉ ለታየው ከፍተኛ ጥላቻ፣ ዓመፅና ደም መፋሰስ ምክንያት በሆኑት የዘር፣ የጎሣ፣ የብሔር፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልዩነቶች የማይበገር ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት መሥርተዋል። * በዛሬው ጊዜ እንደዚህ ያሉ ለውጦች እየተከናወኑ መሆናቸው አምላክ የገባቸው ተስፋዎች መጠነ ሰፊ ፍጻሜ እንደሚያገኙ ለማመን የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ይሆነናል።

ይሁንና እንዲህ ዓይነቶቹን ለውጦች የሚያመጣው ምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ነቢዩ ኢሳይያስ በጻፈው ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ላይ እናገኛለን። ነቢዩ እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር፦

“ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል፤ ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ ጥጃ፣ የአንበሳ ደቦልና የሰባ ከብት በአንድነት ይሰማራሉ፤ ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል። . . . አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። ጡት የሚጠባ ሕፃን በአደገኛ እባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፤ ጡት የጣለም ሕፃን እጁን በእፉኝት ጕድጓድ ይከትታል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጕዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”—ኢሳይያስ 11:6-9

ይህ ትንቢት የሚናገረው እንስሳት ከሰዎች ጋር ተስማምተው የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ብቻ ነው? አይደለም፤ ትንቢቱ ከዚህ ያለፈ ትርጉም አለው። የጥቅሱ የመጨረሻ ክፍል ለዚህ ለውጥ ምክንያት የሚሆነውን ነገር ሲገልጽ “ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች” እንደሚል ልብ በል። አምላክን ማወቅ የእንስሳትን ባሕርይ ሊለውጥ ይችላል? የማይመስል ነገር ነው። ይሁን እንጂ አምላክን ማወቅ ሰዎችን ሊለውጥ የሚችል ሲሆን ደግሞም ይለውጣቸዋል! ይህ ትንቢት፣ የአራዊት ዓይነት ባሕርይ የነበራቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በመማራቸውና የተማሩትን ተግባራዊ በማድረጋቸው ይህን ባሕርያቸውን አስወግደው የክርስቶስን ዓይነት ባሕርይ እንደሚያዳብሩ ይገልጻል።

ለምሳሌ የፔድሮን * ሁኔታ እንመልከት። ፔድሮ የአንድ የአሸባሪዎች ድርጅት አባል በነበረበት ወቅት ፍትሕ እንዲሰፍን ለማድረግ እየታገለ እንደሆነ ያምን ነበር። ሥልጠና ከተሰጠው በኋላ አንድን የፖሊሶች ሰፈር በፈንጂ እንዲደመስስ ታዝዞ ነበር። ይህን ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንዳለ ተይዞ ታሰረ። ፔድሮ በእስር ቤት ዓመት ከስድስት ወር ያሳለፈ ሲሆን በዚያም የዓመፅ ተግባሩን አላቋረጠም። እሱ በእስር ቤት ሳለ ባለቤቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር። ፔድሮም ሲፈታ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረ ሲሆን ስለ ይሖዋ አምላክ የተማረው ነገር በአስተሳሰቡና ለሕይወት ባለው አመለካከት ላይ ታላቅ ለውጥ እንዲያደርግ አነሳሳው። “አሸባሪ ሆኜ በቆየሁባቸው ዓመታት የአንድም ሰው ሕይወት ባለማጥፋቴ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ” ይላል ፔድሮ። “አሁን ስለ እውነተኛ ሰላምና ፍትሕ የሚናገረውን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ለማድረስ የአምላክ መንፈስ ሰይፍ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ እጠቀማለሁ።” ሌላው ቀርቶ ፔድሮ በአንድ ወቅት ሊደመስሰው ወደነበረው ሰፈር በመሄድ ሰላም ስለሚሰፍንበትና ዓመፅ ስለማይኖርበት ዓለም የሚገልጸውን መልእክት ለማካፈል ጥረት አድርጓል።

የአምላክ ቃል በሰዎች ላይ የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ፣ ክፋት እንደሚወገድ አምላክ በሰጠው ማረጋገጫ ላይ እምነት ለማሳደር ምክንያት ይሆነናል። አዎን፣ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ስለሚያደርጉ መጥፎ ነገር መፈጸማቸው ጨርሶ የሚቀርበት ጊዜ ይመጣል። የክፋት ድርጊቶች ምንጭ የሆነውንና ከበስተጀርባ ሆኖ ዓለምን ወደፈለገው አቅጣጫ እየጠመዘዘ ያለውን ሰይጣን ዲያብሎስን ይሖዋ በቅርቡ ያስወግደዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:19) ይሁንና በቅርቡ ክፉው ሰይጣን ይወገዳል። እንዲሁም ክፉ መንገዳቸውን ለመተው አሻፈረን የሚሉ ሰዎች ይወገዳሉ። እንደዚህ ባለው አስደሳች ጊዜ መኖር እንዴት የሚያስደስት ይሆን!

ታዲያ አንድ ሰው እንዲህ ባለው ጊዜ ለመኖር ምን ማድረግ አለበት? በዛሬው ጊዜ በሰዎች ላይ ለውጥ እያመጣ ያለውና በቅርቡ ደግሞ በመላው ዓለም እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርገው ‘እግዚአብሔርን ማወቅ’ እንደሆነ አስታውስ። እንደ ፔድሮ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት የምትቀስምና የተማርከውን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ አንተም ‘ጽድቅ በሚሰፍንበት’ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ ታገኛለህ። (2 ጴጥሮስ 3:13) እንግዲያው በተከፈተልህ አጋጣሚ ተጠቅመህ ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት እንድትቀስም እናበረታታሃለን፤ ምክንያቱም ይህን እውቀት መቅሰም የዘላለም ሕይወት ያስገኝልሃል።—ዮሐንስ 17:3

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.21 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የይሖዋ ምሥክሮች—እነማን ናቸው? ምን ብለው ያምናሉ? (እንግሊዝኛ) የተሰኘውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር ተመልከት።

^ አን.25 ስሙ ተለውጧል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንተም ‘ጽድቅ በሚሰፍንበት’ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ ታገኛለህ።—2 ጴጥሮስ 3:13