በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በይሖዋ ፊት አደገ’

‘በይሖዋ ፊት አደገ’

በእምነታቸው ምሰሏቸው

‘በይሖዋ ፊት አደገ’

ሳሙኤል ሕዝቡን በአንክሮ እየተመለከተ ነው። ሕዝቡ፣ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በነቢይነትና በፈራጅነት ሲያገለግል የኖረው ይህ ታማኝ ሰው ያደረገላቸውን ጥሪ በመቀበል በጌልገላ ከተማ ተሰብስበዋል። በዘመናችን አቆጣጠር መሠረት ወቅቱ ግንቦት ወይም ሰኔ ሲሆን የዝናቡ ወቅት ካቆመ ቆይቷል። በአካባቢው ባሉት ማሳዎች ላይ የሚታየው የስንዴ አዝመራ ለአጨዳ እንደደረሰ ያስታውቃል። በሕዝቡ መካከል ጸጥታ ሰፍኗል። ሳሙኤል የእነዚህን ሰዎች ልብ መንካት የሚችለው እንዴት ይሆን?

ሕዝቡ የሠሩት ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የገባቸው አይመስልም። ሰብዓዊ ንጉሥ ካልነገሠልን እያሉ ሳሙኤልን ሲወተዉቱት ቆይተዋል። እንዲህ ያለ ጥያቄ ሲያቀርቡ ለአምላካቸው ለይሖዋና የእሱ ነቢይ ሆኖ ለሚያገለግለው ሰው ከፍተኛ ንቀት ማሳየታቸው እንደሆነ አልተገነዘቡም። ሕዝቡ፣ ይሖዋ ንጉሣቸው እንዳይሆን የናቁት ያህል ነበር! ታዲያ ሳሙኤል ንስሐ እንዲገቡ ሊያነሳሳቸው የሚችለው እንዴት ይሆን?

ሳሙኤል ለሕዝቡ “ዕድሜዬ ገፍቶአል፤ ጠጕሬም ሸብቶአል” አላቸው። እንደ ጥጥ ነጭ የሆነው የሳሙኤል ፀጉር፣ ለሚናገረው ነገር ሕዝቡ ይበልጥ ክብደት እንዲሰጡት የሚያደርግ ነው። ነቢዩ ቀጥሎም “ከወጣትነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስመራችሁ ቈይቻለሁ” አላቸው። (1 ሳሙኤል 11:14, 15፤ 12:2) ሳሙኤል ቢያረጅም የወጣትነት ጊዜውን አልረሳውም። የልጅነት ሕይወቱ ትዝታ አሁንም ከአእምሮው አልተፋቀም። ገና ልጅ እያለ ያደረጋቸው ውሳኔዎች በሕይወቱ ሙሉ በአምላኩ በይሖዋ ላይ እምነት እንዲኖረውና ለእሱ ያደረ እንዲሆን ረድተውታል።

ሳሙኤል እምነት በሌላቸውና ታማኝነት በጎደላቸው ሰዎች መካከል ይኖር የነበረ ቢሆንም ምንጊዜም እምነቱን ለመገንባትና ይህን እምነቱን ላለማጣት ይጥር ነበር። በዛሬው ጊዜም የምንኖረው እምነተ ቢስና ምግባረ ብልሹ በሆነ ዓለም ውስጥ በመሆኑ በዚያን ዘመን እንደነበረው ሁሉ እምነትን መገንባት ተፈታታኝ ነው። ሳሙኤል ገና ከለጋ ዕድሜው ጀምሮ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

‘ብላቴናው በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር’

የሳሙኤል የልጅነት ሕይወት ለየት ያለ ነበር። ጡት ከጣለ ብዙም ሳይቆይ ምናልባትም በአራት ዓመቱ ገደማ በራማ ካለው ቤታቸው 30 ኪሎ ሜትር ርቆ በሴሎ በሚገኘው የይሖዋ ቅዱስ ማደሪያ ማገልገል ጀመረ። ሕልቃና እና ሐና የሚባሉት ወላጆቹ ልጃቸውን ለይሖዋ ሰጡት፤ ከዚህ በኋላ ሳሙኤል ሕይወቱን በሙሉ ናዝራዊ በመሆን ለአምላክ ልዩ አገልግሎት ያቀርባል። * የሳሙኤል ወላጆች ልጃቸውን እዚያ ትተውት መሄዳቸው እንደማይወዱት የሚያሳይ ነው?

በጭራሽ! ሕልቃና እና ሐና ልጃቸው በሴሎ ጥሩ እንክብካቤ እንደሚደረግለት ያውቁ ነበር። ሳሙኤል የሚሠራው ከሊቀ ካህናቱ ከዔሊ ጋር ስለነበር ዔሊ ሁኔታውን እንደሚከታተል ጥርጥር የለውም። እንዲሁም ከመገናኛው ድንኳን ጋር በተያያዘ የሚያገለግሉ በርካታ ሴቶች የነበሩ ሲሆን እነሱም በተደራጀ መንገድ ሥራቸውን ያካሂዱ እንደነበረ መረዳት ይቻላል።—ዘፀአት 38:8

ሐና እና ሕልቃናም ቢሆኑ ይሖዋን ለምነው ያገኙትን ተወዳጅ የበኩር ልጃቸውን ፈጽሞ አልረሱትም። ሐና፣ ወንድ ልጅ እንዲሰጣት አምላክን ለምናው የነበረ ሲሆን ልጅ ካገኘች ሕይወቱን ሙሉ ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርብ ለአምላክ እንደምትሰጠው ቃል ገብታ ነበር። ሐና በየዓመቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትሄድ ሳሙኤል በመገናኛው ድንኳን ሲያገለግል የሚለብሰው አዲስ መደረቢያ እየሠራች ታመጣለት ነበር። ብላቴናው ሳሙኤል ወላጆቹ እየመጡ ሲጠይቁት በጣም ይደሰት እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ወላጆቹ ልዩ በሆነው በዚያ ቦታ ይሖዋን ማገልገሉ ምን ያህል ትልቅ መብት እንደሆነ ሲያስተምሩት የሚያገኘው ፍቅራዊ ማበረታቻና መመሪያ እንደሚያጠናክረው ምንም ጥያቄ የለውም።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆችም ከሐና እና ከሕልቃና ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ በቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት ችላ ማለታቸው የተለመደ ነገር ነው። የሳሙኤል ወላጆች ግን መንፈሳዊ ነገሮችን ያስቀደሙ ሲሆን ይህም ልጃቸው ሲያድግ በሕይወቱ ውስጥ ለተከተለው አካሄድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።—ምሳሌ 22:6

ልጁ እያደገ ሲሄድና በሴሎ አካባቢ ያሉትን ኮረብቶች እየተዘዋወረ ሲቃኝ በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንችላለን። ከኮረብቶቹ ላይ ሆኖ ከተማዋንና በስተግርጌዋ የሚታየውን ሸለቆ በሚቃኝበት ጊዜ የይሖዋን የመገናኛ ድንኳን ሲመለከት ልቡ በደስታና በኩራት ሳይሞላ አይቀርም። ይህ የመገናኛ ድንኳን በእርግጥም ቅዱስ ቦታ ነበር። * በሙሴ አመራር ከ400 ዓመታት በፊት የተሠራው ይህ የመገናኛ ድንኳን በመላው ዓለም ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ የሚቀርብበት ብቸኛው ስፍራ ነበር።

ትንሹ ሳሙኤል የመገናኛውን ድንኳን እየወደደው ሄደ። ከጊዜ በኋላ ራሱ በጻፈው ዘገባ ላይ “ብላቴናው ሳሙኤል ግን ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር” የሚል ሐሳብ ሰፍሯል። (1 ሳሙኤል 2:18) ይህ ቀለል ባለ መንገድ የሚዘጋጅ እጅጌ የሌለው ቀሚስ ሳሙኤል በመገናኛው ድንኳን የካህናቱ ረዳት ሆኖ እንደሚሠራ የሚያሳውቅ ሳይሆን አይቀርም። ሳሙኤል የካህናት ወገን ባይሆንም እንኳ ወደ መገናኛው ድንኳን ግቢ የሚያስገቡትን በሮች ማለዳ ላይ መክፈትንና አረጋዊውን ዔሊን መንከባከብን የሚጨምሩ ሥራዎች ነበሩት። ሳሙኤል ያገኘውን መብት በጣም ይወደው የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ የልጅ አእምሮውን የሚረብሽ ነገር ያጋጥመው ጀመር። በይሖዋ ቤት ውስጥ በጣም መጥፎ የሆነ ነገር እየተፈጸመ ነበር።

ምግባረ ብልሹነት ቢኖርም ንጽሕናውን ጠብቋል

ሳሙኤል ዓይን ያወጣ ክፋትና ምግባረ ብልሹነት ሲፈጸም በለጋ ዕድሜው ተመልክቷል። ዔሊ፣ አፍኒንና ፊንሐስ የሚባሉ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት። የሳሙኤል ዘገባ “የዔሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር” በማለት ይናገራል። (1 ሳሙኤል 2:12) በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጹት ሁለት ሐሳቦች የማይነጣጠሉ ናቸው። አፍኒንና ፊንሐስ “ምናምንቴዎች” ወይም ቃል በቃል ሲተረጎም “የከንቱነት ልጆች” ነበሩ፤ ምክንያቱም ይሖዋን አይፈሩም ነበር። ይሖዋ ላስቀመጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶችና ብቃቶች ግድ አልነበራቸውም። ያን ሁሉ ኃጢአት ለመሥራት ያበቃቸውም ይኸው ነው።

የካህናትን ኃላፊነትና በአምላክ የማደሪያ ድንኳን ውስጥ መሥዋዕቶች የሚያቀርቡበትን መንገድ በተመለከተ የአምላክ ሕግ የሚሰጠው መመሪያ የማያሻማ ነበር። ይህ መሆኑም ተገቢ ነበር! ምክንያቱም በመገናኛው ድንኳን የሚቀርቡት መሥዋዕቶች፣ ሕዝቡ በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም እንዲኖራቸውና በረከቱንም ሆነ አመራሩን ለማግኘት ብቁ እንዲሆኑ አምላክ ኃጢአታቸውን ይቅር ለማለት ያደረገውን ዝግጅት የሚያመለክቱ ነበሩ። ይሁን እንጂ አፍኒንና ፊንሐስ አብረዋቸው የሚያገለግሉት ካህናት ሕዝቡ ለሚያቀርባቸው መሥዋዕቶች ከፍተኛ ንቀት እንዲያድርባቸው አድርገዋል። *

እንዲህ ያለው ከባድ ኃጢአት በገሃድ ይፈጸም የነበረ ሲሆን ሁኔታውን ለማስተካከል ምንም ዓይነት የእርምት እርምጃ አልተወሰደም፤ ብላቴናው ሳሙኤል ዓይኑን ማመን አቅቶት ሁኔታውን ሲመለከት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ሳሙኤል፣ ድሃና ችግረኛ የሆኑ እንዲሁም የተጨቆኑ ሰዎችን ጨምሮ መንፈሳዊ ማጽናኛና ማበረታቻ ብናገኝ ብለው ወደዚያ ቅዱስ ድንኳን ቢመጡም አዝነው፣ ተጎድተው ወይም ተሸማቀው የተመለሱ ምን ያህል ሰዎችን ተመልክቶ ይሆን? ከዚህም በተጨማሪ አፍኒንና ፊንሐስ፣ ይሖዋ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር የሰጠውን ሕግ በመናቅ በመገናኛው ድንኳን ከሚያገለግሉት አንዳንድ ሴቶች ጋር ዝሙት መፈጸማቸውን ሲያውቅ ሳሙኤል ምን ተሰምቶት ይሆን? (1 ሳሙኤል 2:22) ምናልባትም ዔሊ እርምጃ እንደሚወስድ ተስፋ አድርጎ ይሆናል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ችግር ለማስተካከል ከማንም የበለጠ ሥልጣን የነበረው ዔሊ ነው። ሊቀ ካህናት እንደመሆኑ መጠን በመገናኛው ድንኳን ለሚፈጸመው ነገር ተጠያቂ ነበር። አባት እንደመሆኑ መጠን ደግሞ ልጆቹን የማረም ግዴታ ነበረበት። ልጆቹ ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም ጭምር እየጎዱ ነበር። ይሁን እንጂ ዔሊ ሊቀ ካህናትም ሆነ አባት ከመሆኑ አንጻር በሁለቱም አቅጣጫ የተጣለበትን ኃላፊነት ሳይወጣ ቀርቷል። ለልጆቹ ለዘብ ያለ ተግሣጽ ከመስጠት ያለፈ ነገር አላደረገም። (1 ሳሙኤል 2:23-25) እነዚህ ልጆች ግን ጠንከር ያለ ተግሣጽ ያስፈልጋቸው ነበር። ለፈጸሙት ኃጢአት ሞት ይገባቸው ነበር!

ነገሮች በጣም ከመበላሸታቸው የተነሳ አንድ “የእግዚአብሔር ሰው” ለዔሊ ኃይለኛ የፍርድ መልእክት እንዲናገር ይሖዋ ልኮት ነበር። ይሖዋ ስሙ ባልተጠቀሰው በዚህ ነቢይ አማካኝነት ለዔሊ “ከእኔ ይልቅ ልጆችህን የምታከብራቸው ስለ ምንድን ነው?” አለው። አምላክ ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ የነበሩት የዔሊ ልጆች በአንድ ቀን እንደሚሞቱና የዔሊ ቤተሰብም ታላቅ መከራ እንደሚደርስባቸው ሌላው ቀርቶ በክህነት አገልግሎት ውስጥ የነበራቸውን የተከበረ ቦታ እንኳ እንደሚያጡ ትንቢት አስነገረ። ታዲያ ይህ ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ በዚያ ቤተሰብ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ አድርጎ ይሆን? ዘገባው ልባቸው ተነክቶ ለውጥ ስለማድረጋቸው የሚገልጸው ነገር የለም።—1 ሳሙኤል 2:27 እስከ 3:1

ይህ ሁሉ ምግባረ ብልሹነት በሳሙኤል ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን? መጥፎ ታሪኮችን በያዘው በዚህ ዘገባ ውስጥ ሳሙኤል ስላደረገው እድገት አለፍ አለፍ ብለው የሰፈሩት ሐሳቦች ብርሃን የሚፈነጥቁ ናቸው። በ⁠1 ሳሙኤል 2:18 ላይ እንደተገለጸው “ብላቴናው ሳሙኤል” በታማኝነት “በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል” እንደነበር አስታውስ። ሳሙኤል በዚያ ለጋ ዕድሜውም እንኳ ሕይወቱ ለአምላክ በሚያቀርበው አገልግሎት ላይ ያተኮረ ነበር። በዚሁ ምዕራፍ In በቁጥር 21 ላይ “ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ” የሚል ደስ የሚያሰኝ ሐሳብ እናገኛለን። ሳሙኤል እያደገ ሲሄድ በሰማይ ከሚገኘው አባቱ ጋር የነበረው ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ ሄደ። ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ የጠበቀ ዝምድና መመሥረት በየትኛውም ዓይነት ምግባረ ብልሹነት ላለመሸነፍ የሚረዳ አስተማማኝ መከላከያ ነው።

ሳሙኤል፣ ሊቀ ካህናቱም ሆነ ልጆቹ ኃጢአት የሚሠሩ ከሆነ እሱም የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል ሊያስብ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ሌሎች ምግባረ ብልሹ መሆናቸው ኃጢአት ለመሥራት በጭራሽ ሰበብ ሊሆን አይገባም። በዛሬው ጊዜ በርካታ ክርስቲያን ወጣቶች በዙሪያቸው ያሉ አንዳንድ ሰዎች ጥሩ ምሳሌ ባይሆኗቸውም እንኳ የሳሙኤልን አርዓያ በመከተል ‘በእግዚአብሔር ፊት ማደጋቸውን’ ቀጥለዋል።

እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ሳሙኤልን የጠቀመው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ብላቴናውም ሳሙኤል በአካልና በሞገስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እያደገ ሄደ” ይላል። (1 ሳሙኤል 2:26) ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ሳሙኤል በብዙዎች ዘንድ በተለይ በሕይወቱ ትልቅ ቦታ በሚሰጣቸው ሰዎች ዘንድ በጣም የሚወደድ ልጅ ነበር። ይህ ብላቴና የታማኝነት ጎዳና በመከተሉ ይሖዋም ወዶት ነበር። ሳሙኤል በሴሎ የሚፈጸመውን ክፋት ሁሉ ለማስተካከል አምላኩ ይሖዋ እርምጃ እንደሚወስድ ያውቅ እንደነበር ጥርጥር የለውም፤ ይሁን እንጂ ‘ይህን የሚያደርገው መቼ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ሳያሳስበው አልቀረም።

“ባሪያህ ይሰማልና ተናገር”

ሳሙኤል በአእምሮው ይመላለሱ ለነበሩት ጥያቄዎች አንድ ሌሊት መልስ አገኘ። ሊነጋ የተቃረበ ቢሆንም ገና ጎህ አልቀደደም፤ የድንኳኑም መብራት አልጠፋም ነበር። ኮሽታ በማይሰማበት በዚህ ጊዜ ሳሙኤል አንድ ድምፅ ሲጠራው ሰማ። ሳሙኤል ስሙን የጠራው በጣም ያረጀውና ዓይኖቹ ሊታወሩ የተቃረቡት ዔሊ መስሎት ነበር። ብላቴናው ከአልጋው በመነሳት ወደ አረጋዊው ሰው ‘እየሮጠ ሄደ።’ ይህ ልጅ ዔሊ ምን ፈልጎ እንደጠራው ለማወቅ ባዶ እግሩን እየተጣደፈ ሲሄድ በዓይነ ሕሊናህ ይታይሃል? ሳሙኤል ዔሊን በአክብሮትና በደግነት ይይዘው እንደነበረ ማወቁ ልብ ይነካል። ዔሊ ብዙ የበደለ ቢሆንም እንኳ አሁንም ይሖዋ የሾመው ሊቀ ካህናት ነበር።—1 ሳሙኤል 3:2-5

ሳሙኤል ዔሊን ቀሰቀሰውና “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለው። ዔሊ ግን እንዳልጠራው በመግለጽ ተመልሶ እንዲተኛ ነገረው። ሆኖም ይኸው ሁኔታ ከአንዴም ሁለቴ ተደገመ! በመጨረሻም ዔሊ ምን እየተከናወነ እንዳለ ተገነዘበ። በዚያ ዘመን ይሖዋ በራእይም ሆነ በነቢያት ተጠቅሞ ለሕዝቡ መልእክት ማስተላለፉ ብርቅ ነበር፤ ለነገሩ ይህ ምንም አያስገርምም! አሁን ግን ይሖዋ በዚህ ልጅ አማካኝነት ለሕዝቡ እንደገና መናገር እንደጀመረ ዔሊ ተገነዘበ። በመሆኑም ሳሙኤልን ወደ መኝታው ተመልሶ እንዲሄድና ይህን ድምፅ እንደገና ከሰማ ምን መልስ እንደሚሰጥ ነገረው። ሳሙኤልም የተባለውን አደረገ። ብዙም ሳይቆይ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” የሚል ጥሪ ሰማ። ብላቴናውም “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ።—1 ሳሙኤል 3:1, 5-10

በመጨረሻም ይሖዋ በሴሎ የሚሰማው አገልጋይ አገኘ። ሳሙኤል በሕይወቱ ሙሉ እንዲህ ማድረጉን ቀጥሏል። አንተስ እንዲህ ዓይነት ልማድ አለህ? ይሖዋን ለመስማት መለኮታዊ ድምፅ በሌሊት እንዲያናግረን መጠበቅ የለብንም። በዛሬው ጊዜ የአምላክን ድምፅ በምሳሌያዊ ሁኔታ ምንጊዜም መስማት እንችላለን። ድምፁ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። አምላክን ይበልጥ ባዳመጥነውና የሚነግረንን ተግባራዊ ባደረግን መጠን እምነታችንም በዚያው ልክ እያደገ ይሄዳል። ከሳሙኤል ጋር በተያያዘም የተፈጸመው ይኸው ነው።

በዚያ ሌሊት በሴሎ የተከናወነው ነገር በሳሙኤል ሕይወት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ብላቴና የአምላክ ነቢይና ቃል አቀባይ በመሆኑ ከይሖዋ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና መሥርቷል። መጀመሪያ ላይ ብላቴናው የይሖዋን መልእክት ለዔሊ መንገር አስፈርቶት ነበር፤ ምክንያቱም የሰማው ነገር በዚያ ቤተሰብ ላይ የተነገረው ትንቢት በቅርቡ ሊፈጸም መሆኑን የሚገልጽ የመጨረሻ የፍርድ መልእክት ነበር። ይሁን እንጂ ሳሙኤል እንደምንም ራሱን በማደፋፈር መልእክቱን የተናገረ ሲሆን ዔሊም መለኮታዊውን ፍርድ መቀበሉን በትሕትና ገለጸ። ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ የተናገረው በሙሉ ተፈጸመ። እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጦርነት የገጠሙ ሲሆን አፍኒንና ፊንሐስ በአንድ ቀን ተገደሉ። ዔሊም የይሖዋ ቅዱስ ታቦት እንደተማረከ ሲሰማ ሞተ።—1 ሳሙኤል 3:10-18፤ 4:1-18

ሳሙኤል ግን ታማኝ ነቢይ በመሆኑ ስሙ ይበልጥ እየገነነ ሄደ። ዘገባው “እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር [እንደነበር]” ከገለጸ በኋላ ሳሙኤል ከሚናገረው ትንቢት ውስጥ አንዱም መሬት ጠብ እንደማይል ይናገራል።—1 ሳሙኤል 3:19

“ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ”

ይህ ሲባል ታዲያ እስራኤላውያን የሳሙኤልን አመራር በመከተል ታማኝና ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያለው ሕዝብ ሆነው ነበር ማለት ነው? አይደለም። ነቢዩ ሳሙኤል በእስራኤል ላይ ይፈርድ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ሕዝቡ በዚህ ስላልረኩ ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲያስተዳድራቸው እንደሚፈልጉ ገለጹ። እነሱም እንደ ሌሎች ብሔራት መሆን ፈልገው ነበር። ነቢዩ የይሖዋን መመሪያ በመከተል የጠየቁትን ፈጸመላቸው። ይሁን እንጂ ሳሙኤል እስራኤላውያን የኃጢአታቸውን ክብደት እንዲገነዘቡ ማድረግ ነበረበት። ሕዝቡ የናቁት ሳሙኤልን ሳይሆን ይሖዋን ነበር! ስለዚህ ነቢዩ ሕዝቡን ወደ ጌልገላ ሰበሰባቸው።

ሳሙኤል ያሳሰበውን ጉዳይ ለእስራኤላውያን ሲናገር እስቲ እናዳምጥ። አረጋዊው ሳሙኤል ሕይወቱን ሙሉ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ እንደኖረ ለእስራኤላውያን አስታወሳቸው። ከዚያም “ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።” ነቢዩ ነጎድጓድና ዝናብ እንዲልክ ይሖዋን ለመነው።—1 ሳሙኤል 12:17, 18

በዚያ ወቅት ነጎድጓድና ዝናብ እንዴት ሊመጣ ይችላል? እንዲህ ያለ ነገር ጨርሶ ተሰምቶ አያውቅም! ሕዝቡ ዝናብ መምጣት ስለመቻሉ ቅንጣት ታህል ተጠራጥረው ወይም በሳሙኤል ላይ አሹፈው ከነበረ ይህ ስሜታቸው ብዙም አልዘለቀም። ሰማዩ በአንዴ ጠቆረ። ኃይለኛው ነፋስ በማሳዎቹ ላይ ያለውን ስንዴ መሬት ላይ ረፈረፈው። ጆሮ የሚያደነቁረው የነጎድጓዱ ድምፅ ያስገመግም ጀመር። ከዚያም የጠቆረው ሰማይ ዶፉን ለቀቀው። ታዲያ የተሰበሰቡት ሰዎች ምን ተሰማቸው? “ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩ።” የፈጸሙት ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አሁን ገና ገባቸው።—1 ሳሙኤል 12:18, 19

ዓመፀኛ የሆነውን የዚህን ሕዝብ ልብ መንካት የቻለው ሳሙኤል ሳይሆን ይሖዋ ነበር። ሳሙኤል ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ እርጅና ዘመኑ ድረስ በአምላኩ ታምኗል። እንዲህ በማድረጉም ይሖዋ ክሶታል። ይሖዋ ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። ሳሙኤልን በእምነቱ የሚመስሉትን ሰዎች አሁንም ይደግፋቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ናዝራዊነት የአልኮል መጠጥ አለመጠጣትንና ፀጉርን አለመቆረጥን ጨምሮ ከአንዳንድ ነገሮች መቆጠብን የሚያካትት ስእለት ነው። አብዛኞቹ ናዝራውያን እንዲህ ዓይነቱን ስእለት የሚሳሉት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ሲሆን እንደ ሳምሶን፣ ሳሙኤልና መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ጥቂት ሰዎች ግን ሕይወታቸውን በሙሉ ናዝራውያን ሆነው ኖረዋል።

^ አን.12 ይህ ቅዱስ ማደሪያ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሲሆን በእንጨት አውታር ላይ የተዘረጋ ትልቅ ድንኳን ነበር። ድንኳኑ የተሠራው ምርጥ በሆኑ ቁሳቁሶች ይኸውም በአቆስጣ ቆዳ፣ ውብ በሆነ መንገድ በተጠለፉ ጨርቆች እንዲሁም በብርና በወርቅ በተለበጡ ውድ እንጨቶች ነበር። ይህ ቅዱስ ድንኳን የሚገኘው አራት ማዕዘን ቅርጽ ባለው ግቢ ውስጥ ሲሆን በግቢው ውስጥ የሚያምር መሠዊያም አለ። ከጊዜ በኋላ በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ካህናት የሚጠቀሙባቸው ሌሎች ክፍሎችም ሳይጨመሩ አልቀሩም። ሳሙኤል የሚተኛው ከእነዚህ ክፍሎች በአንዱ ውስጥ ይመስላል።

^ አን.16 ካህናቱ የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች ይንቁ እንደነበር የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎችን ከዘገባው መመልከት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሕጉ ከመሥዋዕቱ ውስጥ የካህናቱ ድርሻ የትኛው እንደሆነ ለይቶ ይገልጽ ነበር። (ዘዳግም 18:3) ክፉዎቹ ካህናት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚከተሉት አሠራር ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነበር። ካህናቱ፣ ሥጋው እየተቀቀለ ሳለ አገልጋዮቻቸውን በመላክ ከድስቱ ውስጥ ማንኛውንም ምርጥ ሥጋ በሜንጦ አውጥተው እንዲያመጡላቸው ያደርጉ ነበር! ሌላው ደግሞ ሕዝቡ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያው ላይ እንዲቃጠልላቸው ሲያመጡ ክፉዎቹ ካህናት የመሥዋዕቱ ስብ ገና ለይሖዋ ከመቅረቡ በፊት አገልጋያቸው መሥዋዕት የሚያቀርበውን ሰው አስገድዶ ጥሬ ሥጋ እንዲያመጣላቸው ያደርጉ ነበር።—ዘሌዋውያን 3:3-5፤ 1 ሳሙኤል 2:13-17

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሳሙኤል ፍርሃት ቢሰማውም የይሖዋን የፍርድ መልእክት ለዔሊ በታማኝነት አስተላልፏል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሳሙኤል በእምነት የጸለየ ሲሆን ይሖዋም ነጎድጓድና ዝናብ በመላክ ምላሽ ሰጥቶታል